የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ወትሮም ቢሆን የርስ በርስ ጦርነትና ግጭት አያጣውም። በቀጣናው በሚገኙ ሀገራት በየጊዜው ጎሣን፣ ድንበርንና፣ ፖለቲካንና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን መሠረት አድርገው በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ሠላማዊ ዜጎች ለሠላም እጦት፣ ለስደት፣ መፈናቀል፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ሲጋለጡ ይስተዋላል። ይህ ሁኔታም ከመለዘብ ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል።
በቀጣናው ሠላምና መረጋጋት ለማምጣት ብርቱ ጥረት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም ጥረቶቹ ሁሉ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጡ አልቻሉም። ለእስካሁኑ ጥረት ፍሬ አልባ መሆን የቀጣናው ሀገራት መንግሥታት ሠላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት አናሳ መሆን፣ በሠላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የሲቪል ማኅበራት፣ የተገፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎችም አለመካተትና በጥናት ላይ የተመረኮዙ የሠላምና መረጋጋት ሥራዎችን አለመከናወንና ሌሎችም በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ይሁንና በቀጣናው አሁን ላይ የሚታየውን የሠላም እጦትና አለመረጋጋት በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት እገዛ ሊያደርግ የሚችል /African Strategic Plan For Peace and Security/ የተሰኘ ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል። ይህ ስትራቴጂ እ.ኤ.አ ከ2024 እስከ 2033 የሚቆይ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ይተገበራል። ስትራቴጂውም Bread for the World (BftW) እና The American Friends Service Committee (AFSC) በተሰኙ ዓለም አቀፍ የልማትና ግብረሠናይ ድርጅቶች እንደተዘጋጀ ታውቋል።
ወይዘሪት ሳምራዊት ወርቁ በአሜሪካን ፍሬንድስ ሰርቪስ ኮሚቴ ስር በሚገኘውና ተቀማጭነቱን በአዲስ አበባ ባደረገው ሰላማ ኸብ ፕሮግራም ቢሮ ፕሮጀክት ፎካል ፖይንት ሆነው ያገለግላሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ስትራቴጂው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለአስርት ዓመታት በተለያየ ምክንያት በተፈጠሩ ግጭቶችና ጦርነቶች ጉዳት እንደደረሰበት ይታወቃል። ይህ ግጭትና ጦርነት አንዴ ጋብ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዳግም ሲያገረሽ ቆይቷል። ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘም ከፍተኛ ጉዳት ሲያስተናግድና የአካባቢውም ማኅበረሰብ የጉዳቱ ሰለባ ሲሆን ይታያል።
ከዚህ አኳያ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ውስጥ ያሉ የሚመለከታቸው አካላት ባለፉት ዓመታት ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም ጥረቱ ግን በቂ አይደለም። ምክንያቱም አሁንም ቢሆን በቀጣናው ግጭቶችና የእርስ በርስ ጦርነቶች እየቀጠሉ በመምጣታቸው ነው። ከዚህ በመነሳት ነው ሁለቱ አጋር ድርጅቶች የአፍሪካ ቀንድን እያስጨነቁ ባሉ ጉዳዮች ላይ አስተዋፅዖ ያበረክታል ተብሎ የሚጠበቀውን ይህን ስትራቴጂ በመረጃ ላይ ተንተርሰው ያዘጋጁት።
ይህ ስትራቴጂ አምስት መሠረታዊ ምሶሶዎች ያሉት ሲሆን እነዚህም በጥናት ላይ የተመሠረተ ሙግት ማድረግ፣ አካቶነት፣ የሽግግር ፍትሕና ፈውስ፣ አስተዳደርና የአየር ንብረትና የአካባቢ ጥበቃ ፍትሕ ናቸው። በነዚህ ምሶሶዎች ላይ መሠረቱን ያደረገው ስትራቴጂው ይህ ተዓማኒነት ላለውና ተፅዕኖ ፈጣሪ ቅስቀሳ ቅድሚያ በመስጠት ብሎም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የግጭት መከላከል እና አፈታትን ለመደገፍ ያለመ ነው።
ወይዘሪት ሳምራዊት እንደሚናገሩት፣ በዚህ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች በተለያየ መልኩ የብዙ ችግሮች ገፈት ቀማሽ ሆነው ቆይተዋል። አንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች ደግሞ የከፋ ጉዳት አስተናግደዋል። ከዚህ አንፃር ስትራቴጂው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ ክብራቸውን መልሰው እንዲያገኙ ዕድል የሚሰጥና አካታች ሂደት ላይ ያተኮረ ነው። በዚህም ስትራቴጂው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሠላም ግንባታና መረጋጋት ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ዕድል ይሰጣቸዋል። በተለይ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ሌሎች የተገፉ የማኅረሰብ ክፍሎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መሪዎችና የሃይማኖት መሪዎች በስትራቴጂው ትግበራ ይበልጥ የሚሳተፉ ይሆናል።
በአሜሪካን ፍሬንድስ ሰርቪስ ኮሚቴ ስር በሚገኘውና ተቀማጭነቱን በአዲስ አበባ ባደረገው ሰላማ ኸብ ፕሮግራም ቢሮ ዳይሬክተር ሚስተር ሞሰስ ቻሲህ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፣ በዚህ ስትራቴጂ ትግበራ ሂደት በሁለተኛው የስትራቴጂው ምሶሶ ውስጥ አካል ጉዳተኞች እንዲሳተፉ ተካተዋል። የአካል ጉዳተኞች ባላቸው ጉዳት ምክንያት ሁኔታዎችና መሠረተልማቶች ለእነርሱ በምን መልኩ አመቺና ተደራሽ መሆን እንዳለባቸውና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች ይካሄዳሉ። ስለዚህ አካል ጉዳተኞች በዚህ ስትራቴጂ ትግበራ ሂደት በውይይቶቹ ላይ በመሳተፍ እየገጠሟቸው ያሉ ችግሮች ያወራሉ፤ ለችግሮቹ መፍትሔ እንዲገኝም ጥያቄያቸውን ያቀርባሉ።
ሁኔታው መዋቅር የመፍጠር ከሆነ ደግሞ አካል ጉዳተኞች በስትራቴጂው ትግበራ ሂደት ተሳትፈው መዋቅር የመገንባት እውቀት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል። በሚፈጠረው መዋቅር ውስጥም አካል ጉዳተኞች በሁለንተናዊ መልኩ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ግጭት በበዛበት በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ አካል ጉዳተኝነት ምንም ነገር ከማድረግ እንደማያግድ ማየት ተችሏል። የአካል ጉዳተኝነት ጉዳይ የፖለቲካ አጀንዳ እንዲሆን የመንግሥት አመራሮችንና ሌሎችን ባለድርሻ አካላት ማሳመን ያስፈልጋል። ለዚህ ስትራቴጂው ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል።
በዚህ አጋጣሚ ከአካል ጉዳተኝነት ጋር በተያያዘ ለማኅበረሰብ ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር፣ ተሳትፎን ማሳደግ ይገባል። ስለዚህ በስትራቴጂው ትግበራ ሂደት አካል ጉዳተኞች እንዲሳተፉ ይፈለጋል። ሚናቸውንም መጫወት ይጠበቅባቸዋል። አካል ጉዳተኞች በርካታ እምቅ ችሎታ ያላቸው እንደመሆኑ በስትራቴጂው ትግበራ ሂደት በተለይ በአካል ጉዳተኝነት ረገድ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት የራሳቸውን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ ይጠበቃል።
በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሠላምና መረጋጋትን ለማምጣት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው የታመነበት /African strategic plan for Peace and security/ ስትራቴጂ ‹‹The Africa WE Want›› በሚል መሪ ቃል ዛሬ በሂልተን ሆቴል የኢትዮጵያ የመንግሥት ተወካዮችና፣ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም