መንግሥትነት፡- ከታላቅነቱ ክብደቱ፤ከክብደቱ ታላቅነቱ
የሰዎች ሁለንተናዊ ማንነት የሚቀረጸው በወላጆ ቻቸው መሆኑን ለማረጋገጥ እኔ ጥሩ ማሳያ ነኝ። ከፈጣሪዬ ጀምሮ የአስተማሪዎቼ፣ የጓደኞቼና የአደኩበት ማህበረሰብ ድርሻ እንዳለ ሆኖ አሁን ያለው የእኔ ማንነት ሙሉ በሙሉ የወላጆቼ ነጸብራቅ መሆኑን አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ። ይህንንም በራሴ ላይ ባደረኩት ጥልቅ ጥናት አረጋግጫለሁ። ጥናቴ ትክክል እንደሆነ ማረጋገጫ ከሆኑኝ በርካታ ምክያንቶች ደግሞ አንደኛው ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ “መንግሥትና እግዚአብሔር አንድ ናቸው” የሚለው አባባል ነው።
ከልጅነቴ ጀምሮ ቤት ውስጥ እየሰማሁ ያደኩት ይህ አባባል አሁን ላይ ለእኔ አባባል ብቻ አይደለም። በሰው ልጅ ሁለንተናዊ ህይወት ውስጥ ወሳኝ ሚና ካላቸው ጥቂት ቋሚ እሳቤዎች መካከል በባህሪው “ርኩስም፣ ቅዱስም” በመሆኑ በውስብስብነቱና በአይጨበጤነቱ ስለሚታወቀው የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ ያለኝ አመለካከት የተቃኘበት መሰረታዊ መርሔ ነው። ፖለቲካዊ እሳቤዎችን የምበይንበትና የማነብርበት ከቤተ-ሰቦቼ የወረስኩት ቤተ-ሃሳቤ ነው። ፖለቲካን በተመለከተ የምመራበት መሪ ፍልስፍናዬ ነው።
ልብ ብሎ ለመረመረው ሰው “መንግሥትና እግዚአብሔር አንድ ናቸው” የሚለው አባባል ከአባባልነት በላይ ትልቅ ምስጢርን ያዘለ ዕፁብ ድንቅ የሚያስብል አስተሳሰብን የተሸከመ ፍሬ ከናፍር ነው። ለምን ቢባል በዚህ አባባል ውስጠ “አንድ ናቸው” የሚለው ተለዋጭ ዘይቤ የሁለት ታላላቅ አካላትን ማንነት ማሳየት ነው ዋነኛ ዓላማው- የመንግሥትንና የእግዚአብሔርን የግብር ተነጻጻሪነት! ታዲያ እዚህ ጋር “መንግሥትና እግዚአብሔር የሚመሳሰሉበት(አንድ የሚሆኑበት) ማለትም የግብር ተመሳስሏቸው በምንድን ነው?” የሚለውን ጥያቄ ስንመልስ ነው የምስጢሩ ምስጢር የሚገለጽልን።
እግዚአብሔር የዓለሙን ፍጥረት ከፈጠረ በኋላ ዝም ብሎ ውጡ- ህግ ለቅቆ አልተወውም፡፡ የፈጠረውን ፍጥረት ሁሉ፣ ህይወት ያለውንም ህይወት የሌለውንም፣ የሚታየውንም የማይታየውንም፣ ሰማይንም ምድርንም የሚያስተዳድርበት ህግና ሥርዓት አበጅቶለታል። ዳር ድንበር፣ ወሰንና መዳረሻ፣ ቅርጽና መጠን፣ ልኬት ህልቆ መሳፍርት በሌለው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለውን ፍጥረት ሁሉንም እንደየፍጥርጥሩ በሥርዓቱና በአግባቡ ይመራል፣ ያስተዳድራል።
ይህም ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ለሚመራውና ለሚያስተዳድረው ፍጥረት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ አንዳችም ሳያስቀር አሟልቶ ያቀርባል። ቀንና ሌሊትን፣ ፀሐይና ጨረቃን፣ ክረምትና በጋን እያፈራረቀ ፍጡራኖቹን ይመግባል። ይህንንም የሚያደርገው ሳይጠየቅ ነው። ምክንያቱም ሰማይና ምድርን መምራትና ማስተዳደር ታላቅ ስልጣን ብቻ ሳይሆን ኃላፊነቱም በመሆኑ ነው።
መንግሥት ደህንነታቸውን እንዲጠብቅላቸው፣ የጋራ ፍላጎታቸውንና ማህበራዊ ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቅላቸው ሰዎች በይፋ ዕውቅና ሰጥተው የበላይ መሪ እና አስተዳዳሪ አድርገው የሚያቋቁሙት ተቋም ነው። ይሁን እንጅ መንግሥትን ከሌሎች መሰል የህዝብ የወል ተቋማት የሚለየው እንደ እግዚአብሔር ሁሉ ከባዱንና ትልቁን “የመምራትና የማስተዳደር ስልጣን” የተሸከመ መሆኑ ነው። ከፊት ለመሆን መመረጥ፣ ለመምራት ከህዝብ ፈቃድ ማግኘት ደግሞ ከሌላው የበለጠ “ውድ” መሆን ነው። ይህም የተለየ መብትን ያጎናጽፋል።
በዚህ መንገድ የተገኘው መብት ለራስ (ለመሪው) ከሚያስገኘው የተለየ ጥቅም በአሻገር መንግሥትን መንግሥት ያስባለውን በሰዎች ላይ ለማዘዝና ለመወሰን የሚያስችለውን ልዩ ኃይል ያጎናጽፋል። ይህ ነው እንግዲህ ልክ እንደ እግዚአብሔር በበላይነትና በታላቅነት ፍጡራንን፤ ከፍጡርም ታላቁን ሰውን ለመምራትና ለማስተዳደር የሚያስችለውን “ስልጣን” የሚባለውን ታላቅ እግዚአብሔራዊ ባህሪይ መንግሥት ተብሎ ለተሰየመው አካል የሚፈጥርለት። ሆኖም መንግሥትን እንደ እግዚአብሔር ታላቅ ያደረገው ይህ ስልጣን የሚባለው ልዩ መብት ለባለ መብቱ(መንግሥት ተብሎ ለሚጠራው አካል) የሚፈጥርለትን ታላቅ ኃይል ያህል በዚያው ልክ ከባድና ታላቅ ተጠያቂነትን(ኃላፊነትንም)
ይጠራል። ምክንያቱም ሁሉንም ከፊት ሆኖ በበላይነትና በአዛዥነት መምራትና ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን ልክ እንደ እግዚአብሔር ሁሉ ያለ ማንም ጎትጓችነትና ጠያቂነት የሚመሩትን አካላት ደህንነትና ጥቅም በአግባቡ አስጠብቆ መገኘት ግድ ስለሚል። በሌላ አባባል ከታላቁ ስልጣን ጀርባ ከባድ ተጠያቂነት መኖሩንም አውቆ ኃለፊነትን በአግባቡ መወጣትን ይጠይቃል። እናም ህዝብን የመምራትና የማስተዳደር ስልጣንና ኃላፊነት ወይም የመንግሥት ተግባር ምን ያህል ከባድ መሆኑን ለመግለጽ “መንግሥትና እግዚአብሔር አንድ ናቸው” ከሚለው የእኛው ኢትዮጵያዊ አባባል በላይ የተሻለ ማሳያ ሊኖር እንደማይችል የሚያስረግጥ ነው። ዐረፍተ ነገሩ ከአባባልነትም በላይ ግሩም ድንቅ የሆነ ምስጢር በውስጡ አምቆ የያዘ ጥልቅ ፍልስፍና ነው የተባለበት ምክንያትም ይኸው ነው።
በአግባቡ ያልሆነ ፍቅርም ያጠፋል
የእስራኤልን ህዝብ ከአራት መቶ ዓመታት የፈርኦን ባርነት ነፃ ያወጣውና ቀይ ባህርን ብቻ ሳይሆን ሌሎች እልህ አስጨራሽ ፈተናዎችን ተሻግሮ ህዝቡን ለተስፋይቱ ምድር ያበቃው ነብዩ ሙሴ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የአመራር ጥበብ የነበረው ታላቅ መሪ መሆኑን ዓለም ሁሉ በአንድ ቃል የሚመሰክረው ሐቅ ነው። ዛሬም ድረስ የመሪነት ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰደው ታላቁ መሪ ሙሴ ታዲያ ህዝቦቹን ይመራ የነበረው “ዐይን ያጠፋ ዐይኑ ይጥፋ፤ ጥርስ የሰበረ ጥርሱ ይሰበር” በሚል መተዳደሪያ ህግ ላይ ተመስርቶ ነበር። ይሁን እንጂ ያ ዓለም ሁሉ የሚያደንቀው የመሪዎች ተምሳሌት የሆነው የምድራችን ታላቅ መሪ ህዝቡን ለመምራት ይጠቀምበት የነበረው የአመራር ዘይቤ ጨከን ያለ የአጸፋ ቅጣት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው በግርምት ግራ መጋባታችን አይቀሬ ነው።
“የገደለን መግደል፣ ያጠፋንም ማጥፋትስ በቀልን እንጅ ፍትህን ሊያመጣ ይችላልን?” “ደግሞስ ምንም ቢሆን የሰውን ዓይን ማጥፋት ሰብዓዊነት የሌለው አረመኔያዊ ተግባር አይደለምን?፣ እናም “የተበዳይን ዓይን አጠፋ ብሎ የወንጀለኛን ዓይን የሚያጠፋ፤ ጥፋትን በጥፋት እየመለሰ በጥፋት ላይ ጥፋት የሚጨምር እንዲህ ዓይነቱ ቂል ነው እንዴ ታዲያ ታላቅ መሪ የሚባለው?” በሚል የሙሴን ታላቅነት አፈር ድሜ ልናበላው፤ የሙሴን የአመራር ዘይቤም “ስህተት” ራሳችንም “ትክክል” “ልክ” አድርገን ልንወስድ እንችላለን።
ነገር ግን የሙሴም ስህተት፣ የእኛም ልክነት “ትክክል” የሚሆነው ዛሬ ላይ ነው። ምክንያቱም አንድን ነገር ትክክል ወይም ስህተት የሚያስብለው ቀዳሚው መለኪያ “ጊዜ” በመሆኑ ነው። ይሁን እንጂ አንድን ነገር ትክክል ወይም ስህተት ለማለት ሌሎች ሁለት ዋና ዋና መለኪያዎች አሉ። እነኝህም “ሁኔታ” እና “ቦታ” ናቸው። አድራጊው የሚፈፅማቸው ተግባራት ሁሉ ትክክለኝነታቸው የሚለካው “ሙሴ የእስራኤልን ህዝብ ይመራ የነበረው መቼ፣ የት እና በምን ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነበር?” በሚለው መሰረታዊ የተገቢነት ጥያቄ አማካኝነት ነው።
ከዚህ አኳያ ሙሴ ህዝቦቹን ሲመራ የነበረበት ወቅት በሰው ልጅ ንቃተ ህሊናና በምልዓተ ዓለሙ መካከል ውስን መስተጋብር የነበረበት፣ የሰው ልጅ ህይወት ከተፈጥሮ ተፅዕኖዎች ብዙም ያልተላቀቀበትና ህይወት እንደዛሬው በቴክኖሎጂ ታግዛ ቀለል ያላለችበት፣ መብት፣ ግዴታ፣ ነፃነት፣ እኩልነት…በአዕምሮ ሳይሆን በአካላዊ ትግል አሸናፊ በሆኑ ጥቂቶች የኃይል መዳፍ ሥር የነበረችበት ዘመን ነው። እናም ህዝቡ የሚፈራው አካላዊ ቅጣትን ነበር፣ የሙሴ ህግም ተገቢነት ያለው በመሆኑ ትክክል ነበረ።
የሚመራው የእስራኤል ህዝብ የነበረበት ሁኔታም ለአራት መቶ ዓመታት በዘለቀ ባርነትና ጭቆና ውስጥ ነበር። በዚህም ህዝቡ ለዘመናት ባርነቱን አምኖና ጭቆናን አሜን ብሎ ተቀብሎ የኖረ በሥነ ልቦናም የእትብቱ መቀበሪያ ከሆነችውና ለአያት ቅድመ አያት ርስት ሆና ከተሰጠችው ማርና ወተት ከምታፈልቀው የተስፋይቱ ምድር እስራኤል ይለቅ ለገዥዎቹ ግብፃውያን እጅጉን የቀረበ ነበር። ለዚህም ነው ከሰማይ የወረደ መና እና ሥጋ እየቀረበለት “የለመድነው የግብፅ ሽንኩርት ይሻለን ነበር” እያሉ አብዝተው ሙሴን ይቃወሙት የነበረው። ታዲያ “ወርቅ ስታነጥፍለት ፋንድያ ነው” የሚል የባርነት ሥነ ልቦና የተጠናወተን ህዝብ ሙሴ መምራት የነበረበት በ“ዴሞክራሲ” ወይስ በዚያው በባርነቱ በለመደው “ዱሎክራሲ?” እናም ሙሴ ያደረገው ተገቢ ነበረ፣ ስለሆነም ትክክል ነበረ።
ሙሴ ህዝቡን ይመራበት የነበረው ቦታም ያው በረሃ ነበረ፤ ምንም የሌለበት ምድረ በዳ። ሰው ውሃ ጠማኝ ብሎ ሊያምጽብህ ይችላል፣ ምግብ አጣሁ ብሎ ሊያምፅብህ ይችላል… እንደ ሙሴ ሁሉም የተሰጠህ ሰው ሆነህ በታዓምር ደረቅ መሬት ላይ ውሃ እያፈለቅህ ብታጠጣው፣ ከሰማይ መና እያወረድክ ብትመግበው እንኳን “እንደ ሽንኩርት ታርሶ የበቀለ ካላበላሃኝ” ብሎ ሊያምጽብህ ይችላል። እናም ብዙ ፍላጎቶቹ ተሟልተውለት በሚኖርበት ቦታ እንኳን በቃኝ ብሎ የማያውቀውን የሰውን ልጅ ምንም ነገር በሌለበት በረሃ ለመምራት እንደ ሙሴ ዓይነት “ታዛዥና ቀጭ” መሪ መሆን ተገቢነት ያለው የአመራር ዘይቤ ነበረ። ማለትም ሙሴ ህዝቦቹ ከባርነት ለማውጣት እየተቃወሙትና እየወቀሱት፣ እየሰደቡትም በታላቅ ትህትናና እና በታዛዥነት ሁሉን እሽ እያለ በዴሞክራሲያዊ ዘይቤ ወደ ነፃነት መርቷቸዋል፤ ይህን ያደረገበት ምክንያትም ሁሉንም ነገር ታግሶና ችሎ ህዝቡን ለነፃነት ማብቃት ተገቢ ስለነበረ ነው።
ነገር ግን ይህን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍሎ ከፈርኦን ግፍና ጭቆና ካላቀቃቸው፣ ከባርነትም ነፃ ካወጣቸው በኋላ ፍጹም አግባብነት በሌለው መንገድ ከፈጣሪያቸው ህግና ሥርዓት ወጥተው፣ እርስ በእርስ ተከፋፍለው ጣኦት እያመለኩ ቅዱሱን ዓላማቸውን ስተው ወደ ጥፋት ጎዳና ገብተው “እምቢ አንሰማህም” ባሉት ጊዜ በምድራዊ ብቻ ሳይሆን በእባብ እንዲነደፉ በማድረግ መለኮታዊ ቅጣትም ቀጥቷቸዋል። ይህም ቅጣት በተገቢው ጊዜ የተደረገ በመሆኑ ትክክል ነበረ። ምክንያቱም እስራኤላውያን ማርና ወተት በምታፈሰው ከነዓን ይደርሱና የአባቶቻቸውን ርስትም ይወርሱ ዘንድ በውዴታ የማይችሉ ከሆነ በግዴታም ማድረግ ጥቅም እንጅ ጉዳት ስላልነበረው። ለዚህም ነው ተገቢነት የልክነትም እናት ናት መባሏ። እናም ሙሴ ልክም ታላቅም ነበረ በተገቢው ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ አግባብነት ያለውን ነገር አድርጓልና ሙሴ በእርግጥም ታላቅ ነበረ።
ሁሉም ነገር ትክክል ወይም ልክ የሚሆነው ጊዜን፣ ቦታንና ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ ሲሆንና ሲተገበር ነውና።እናም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና መንግሥታቸው የፍቅር፣ የመደመርና የይቅርታ መርህም አሁን ላይ በአገሪቱ ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እስካልተጣጣመ ድረስ ትክክል ሊሆን አይችልምና እንደ ሙሴ ለወቅቱና በአገሪቱ ውስጥ ለተፈጠረው ሁኔታ ተገቢነት ያለውን ሁሉ ሊያደርጉ ይገባል እንጂ ዝም ብለው ፍቅር ፍቅር በማለት ብቻ ትክክለኛ መሆን አይቻልም!!! በተገቢው መንገድ ካልሆነ ፍቅር ራሱ ስህተት፣ ማፍቀርም ልክ አይሆኑምና! በድህረ ለውጡ ዘመነ ኢህአዴግ አንድ ለእናቱ ተቃዋሚ የፓርላማ አባል የነበሩት፣ዕውቁ ፖለቲከኛና ፀሐፊ ግርማ ሰይፉ ሰሞኑን ፍትህ መጽሔት ላይ እንዳሉት ህግና ሥርዓትን በማስከበር እንጂ አገር በፍቅር አትቆምምና!
ከአውሬም ከሰይጣንም የሚያንስ ስብዕና
በነገራችን ላይ ከሰውነት ባህሪ የወጣ ጨካኝ ድርጊቶችን ሲፈጽም “ምን ዓይነት አውሬ ነው” እየተባለ ከእንስሳት ወይም ከአውሬ ጋር ሲወዳደር ይገርመኛል! አውሬው እኮ “የጭካኔ” ድርጊቱን የሚፈፅመው ተፈጥሯዊ ባህሪው ስለሆነ ነው ይህም ስህተት አይደለም፣ በቃ ሥራውን ነው የሠራው። ሰው ግን በፍፁም እንዲህ ዓይነት ጨካኝ ድርጊቶችን እንዲፈፅም የሚያደርግ አረመኔያዊ ባህሪይን ይዞ አልተፈጠረም! ሰው እንዲህ ዓይነት ክፉ ባህርያትን ያበቀለው ከራሱ ነው። ስለሆነም በተፈጥሮው መልካም ሆኖ የተፈጠረው ሰው በራሱ የሚያመነጨውን ክፋትና ጭካኔ በተፈጥሮ ከመጣው የአውሬ ጭካኔ ጋር ማነጻጸር ፍጹም ስህተት ነው።
ክፉና አረመኔ ሰው “አውሬ” ተብሎ ሊሰደብ አይገባም፤ ከተፈጥሮው የሌለውን ክፋትና አረመኔነት ፈልጎ ያመጣው ሰው “አውሬ” ተብሎ ሲጠራ እየተወደሰ ነውና ምናልባትም “አቡሃ ለሃሰት” ከተባለው የክፋትና የሐሰት አባት ከሆነው ከሰይጣን ሊሆን ይችላል የወረሰው። የጥንቱ ሳጥናኤል የአሁኑ ሰይጣን የእግዚአብሔር መልአክነትን ከአለቅነት ጋር አጣምሮ ለመልካም ዓላማ ተፈጥሮ ሳለ በሐሰት ታብዮ ከራሱ ልብ ክፋትን አብቅሎ፤ በራሱ ምርጫ የክፋትና የጥፋት ሁሉ ምንጭ ሆኗልና! እግዚአብሔር ስለረገመው ነው እንዲህ የሆነው ሊባል ይችላል።
ሆኖም ግን ሰይጣን የተረገመው በራሱ ፍላጎት በፈጠረው ክፋት እንጂ እግዚአብሔርማ ማንንም ሊረግም አይፈጥርም፤ እግዚአብሔርማ መልካም አድርጎ፣ መልዓክ አድርጎ፣ አለቃ አድርጎ ፈጥሮት ነበር እኮ! አልጠግብ ባይነቱ (ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ያለው ትልቅ ስልጣን ለእርሱ ተሰጥቶት ሳለ “የለም ይሄ አይበቃኝም እኔ ራሴ እግዚአብሔር መሆን አለብኝ” የሚለው የአልጠግብ ባይነት ፍላጎቱ)፤ ትዕቢቱ(ፍጡር መሆኑን ረስቶ ፈጣሪ ነኝ ማለቱ ሳያንሰው ከአንዴም ሁለት ሦስቴ በደሉንና ጥፋቱን ይቅር ሲባል ከክፋቱ አለመመለሱና ይቅርታንና ምህረትን ንቆ በክፉ ሥራው መቀጠሉ) አዋርዶታል። ራሱ የፈጠረው መጥፎ ሃሳብ ርግማን ሆኖታል። ሰውም ጨካኝና ክፉ የሚሆነው ክፋትና ጭካኔ ከእግዚአብሔር ያገኘው ተፈጥሯዊ ባሀርይው ሆኖ ሳይሆን ልክ እንደ ሳጥናኤል ክፋትንና ሐሰትን ከገዛ ከልቡ በሚያመነጭበት ወቅት ነው።
እንጂ በተፈጥሮውማ ሰው በፍጹም ክፉ ሊሆን አይችልም! ምክንያቱም ሰው ከሳጥናኤልም በላይ ለሆነ ታላቅ መልካም ዓላማ “የእግዚአብሔር መላዕክ” ሳይሆን “የእግዚአብሔር አምሳል” ሆኖ ነውና የተፈጠረው! እናም ለዚህ ታላቅ ዓላማ ተፈጥሮ ከራስ በሚመነጭ ክፉ ሃሳብ እንደ ሰይጣን በትዕቢትና በአልጠግብ ባይነት በጥፋት ላይ ጥፋት በበደል ላይ በደል መጨመር ከሳይጣንም በላይ ለክፉ ውድቀትና ውርደት ይዳርጋል! ስለሆነም በእግዚአብሔር አምሳል ከተፈጠረው ሰው የሚወጣው ክፋት በዚህም ምክንያት የሚፈጸመው ጥፋትና በደል ከሰይጣን ክፋትም ይገዝፋል! ቢያንስ ሰይጣን ክፉ የሆነውና በደል የፈጸመው “ለምን በአምሳልህ አልፈጠርከኝም” በሚል በእግዚአብሔር አኩርፎና ተቀይሞ ሊሆን ይችላል! ሰው ግን በምን ያመካኛል-በእግዚአብሔር አምሳል ከመፈጠር በላይ ምንም የለምና! እናም በገዛ ፈቃዱ ክፉና አረመኔ የሆነ ሰው “ሰይጣን” ብሎ መስደብ ትክክል አይደለም፣ በበደል ላይ በደልን የሚፈጽምና ይቅርታና ምህረት የማይገባው ክፉና አረመኔ ሰው ከአውሬም ከሰይጣንም የሚያንስ ወራዳ ፍጥረት ነውና!
ይህን ሃሳብ ሃገርን ከጥፋት ለማዳን
አሁን ላይ በእኛም ሃገር ለብዙ ሺ ዘመናት አብሮ በኖረ ወንድማማች ህዝብ መካከል በክፋት ፈላስፎች የተፈበረከ ሐሰተኛ የጥፋት ታሪክን የሚያስተምሩ፣ ጥላቻን የሚሰብኩ፣ ወንድም ወንድሙን እንዲያፈናቅል፣ እንዲገድል አመራር የሚሰጡ ከአውሬም ከሰይጣንም የሚብሱ የክፋት፣ የጭካኔና የጥፋት ስብዕና የተላበሱ ታህተ-ሰብዕ ሰዎች በመብዛታቸው ወቅትና ሁኔታውን የሚዋጅ የአመራር ዘይቤ ሊኖረን ይገባል።
የሚገርመው ነገር ሰዎቹ የክፋታቸውና የርኩሰታቸው መብዛት አይደለም ይሔን እንድል ያደረገኝ። ከእነርሱ አልፈው ይህንኑ የክፋትና የጥፋት አስተሳሰባቸውን ምንም በማያውቀው(የማያውቀው ክፋትን ብቻ ነው) በየዋሁ ህዝብ ውስጥ ለማስረጽና “አንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ማህበረሰብ” ለመገንባት የሚፈልጉ፣ ይህንን ጉዳይ ህልማቸውን ለማሳካትም ማንኛውንም ዓይነት ወንጀልና ርኩሰት በሰው ላይ የሚፈጽሙ፤ ይኸው አስተሳሰባቸውም “በመቃብራቸው ላይ ካልሆነ በቀር” እንዲቀየርባቸው የማይፈልጉ፤ በክፉ ሥራቸው የሚፎክሩ፣ ራሳቸውን ብቻ ፍጹም ትክክለኛ አድርገው የሚቆጥሩ፣ ርዝራዥ ትህትና ያልፈጠረባቸው፣ ሰውን በጣም የሚንቁ፣ ትዕቢተኞችና ምግባረ ብልሹ መሆናቸው ነው! ፍቅርና ይቅርታ ስታደርግላቸው የሚገድሉህ፣ ስትስማቸው የሚነክሱህ እነዚህ የጥፋት ልጆች፤ ራበን ሲሉት እጅግ የሚጣፍጠውንና የመላዕክት ምግብ የሆነውን የሰማይ መና አውርዶ ቢያቀርብላቸው በባርነት ዘመን ይበሉት የነበረውን ጥሬ ሽንኩርት ካልሆነ ብለው እንደሚቃወሙት የሙሴ ዘመን እስራኤላውያን ናቸው።
እናም ምንም ቢደረግላቸው ፍቅር አይገባቸውምና ለእነርሱ ባህርይ የሚሆን ተገቢነት ያለው አካሄድ ተግባራዊ ካልተደረገ “ሙት ይዞ ይሞታል” እንደሚባለው የጥፋት አበጋዞች ሃገርንም ይዘው እንዳይጠፉ ያለኝን ስጋት ሃገርን የመጠበቅ ኃላፊነት ለተሰጠው አካል ጊዜው ሳይመሽ መግለጽ እፈልጋለሁ። በዚህም የሃገር ጉዳይ እንደሚያሳስበው እንደ አንድ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ማድረግ የሚገባኝን በማድረጌ እውነተኛ ደስታ የተሰማኝ መሆኑን ሃገሬን እና አምላኳን እማኝ አድርጌ እገልጽላችኋለሁ።
ኢትዮጵያዬ እወድሻለሁ!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
ይበል ካሳ