ግናው አትሌት አበበ ቢቂላ በ 41 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ከ46 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 15 ቀን 1966 ዓ.ም ነበር።
ሻምበል አበበ ቢቂላ ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በደብረብርሃን ከተማ ደነባ ልዩ ስሙ ጃቶ በተባለ ስፍራ ከአባቱ አቶ ደምሴ እና ከእናቱ ከወይዘሮ ውድነሽ ነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም. ተወለደ::
አበበ የአባቱ ስም ቢቂላ ተደርጎ እንዲጠራ የተደረገው አበበ ክቡር ዘበኛ ሲቀጠር እናቱ ከአበበ አባት በፊት ካገቡት ከመጀመሪያ ባላቸው ከአቶ ቢቂላ የወለዱት ወንድሙ ኮሎኔል ክንፈ ቢቂላ ክቡር ዘበኛ ሲያስቀጥረው “ወንድሜ ነው” ብሎ ሲያስመዘግበው ነው። ይህን ልጁ ጽጌ አበበ እ.ኤ.አ. በ1996 በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፋ “Triumph and tragedy: A history of Abebe Bikila and his marathon career” በሚል ርዕስ ባሳተመችው መጽሐፍ ውስጥ ገልጻለች።
በ 17 ዓመት ዕድሜው አዲስ አበባ መጥቶ በውትድርና ተቀጥሮ ለንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ክቡር ዘበኛ ከተቀጠረ በኋላ ለውትድርና ስራው የሚያደርገው እንቅስቃሴ ወደ ስፖርት አለም እንዳመጣው ይነገራል።
በጦር ካምፕ ውስጥ አበበ የሚያደርጋቸውን ልምምዶች እና ውድድሮች በንቃት ይከታተሉ የነበሩት ሲውዲናዊው አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን የአበበን ችሎታ በመገንዘባቸው ከሌሎቹ አትሌቶች ጋር ተቀላቅሎ ልምምድ እንዲሰራ አደረጉት። በኋላም የ1948ቱ የሜልቦርን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉት አትሌቶች አለባበስና አገራቸውን ወክለው መሮጣቸው በፈጠረበት መነሳሳት በሀገር ውስጥ የሚደረጉ ውድድሮች ላይ መካፈል ጀመረ::
አበበ ቢቂላ ለመጀመሪያ ጊዜ በማራቶን ያሸነፈው በሀምሌ ወር 1960 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በተደረገ ውድድር ሲሆን፤ ርቀቱን ለማጠናቀቅ የወሰደበት ጊዜ 2ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ 23 ሰከንድ ነበር። በነሀሴ ወር ሁለተኛ ውድድሩን ሲያደርግ የመጀመሪያ ሰዓቱን ከማሻሻሉም በተጨማሪ ከአለም በከፍታዋ ሶስተኛ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሮጦ በእንደዚህ አይነት ሰአት ማራቶንን ከጨረሰ በሌላ አለም በሚደረጉ ውድድሮች ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበት ነበር።
ይሁን እንጂ አበበ በ1960ው ኦሎምፒክ ለመሳተፍ ወደሮም ከመሄዱ በፊት ከአገር ውጪ ምንም አይነት ውድድር ባለማድረጉ ለኦሎምፒኩ የመጀመሪያ ተመራጭ አልነበረም። የመጀመሪያ ተመራጩ ዋሚ ቢራቱ በመታመሙ አበበ ቡድኑን በመቀላቀል ወደ ሮም አቀና።
የኦሎምፒኩ የማራቶን ውድድር ከመጀመሩ ሁለት ሰአታት ቀደም ብሎ በውድድሩ ለአትሌቶች ጫማዎችን ሲያቀርብ የነበረው አዲዳስ ለአበበ እግር ይበቃል ብሎ ያቀረባቸው ጫማዎች አልሆን አሉት። ኢትዮጵያ ውስጥ በልምምድ ወቅት በአብዛኛው ያለጫማ ይሮጥ የነበረው አበበም በባዶ እግሩ ለመሮጥ ሃሳብ አቅርቦ አሰልጣኙ ተስማምተው ወደ ውድድሩ ገባ።
ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት አሰልጣኙ ኦኒ ኒስከን የአበበ ተፎካካሪ 26 ቁጥር የተጻፈበት መለያ የሚለብሰው ሞሮኳዊው ራህዲ ሊሆን እንደሚችል በመገንዘባቸው አበበን 26 ቁጥር የለበሰው አትሌት ላይ ትኩረትህን አድርግ ብለው መክረውት ነበር። በአጋጣሚ ራህዲ 10 ሺህ ሜትር ሲሮጥ የለበሰውን 185 ቁጥር የተጻፈበት ማሊያውን በመልበሱ አበበ ውድድሩ እየተጋመሰ ሲሄድ 26 ቁጥር የለበሰ ሯጭ ፍልጋ ቢያማትርም ሊመለከተው አልቻለም። ራህዲ 185 ቁጥር ማሊያውን ለብሶ አብሮት በመሪነት እየሮጠ ነበር።
ማራቶኑ ሊጠናቀቅ ሶስት ኪሎ ሜትሮች ያህል እስኪቀሩት ድረስ አበበና ራህዲ ጎን ለጎን አብረው ሲሮጡ ቆይተው አበበ ፍጥነቱን በመጨመር ራህዲን በ200 ሜትሮች ያህል ቀድሞት ውድድሩን በሁለት ሰዓት ፣ ከአሥራ አምስት ደቂቃ፣ ከአሥራ ስድስት ነጥብ ሁለት ሴኮንድ (2:15:16.2) በማጠናቀቅ የዓለም ክብረ ወሰንን ሰብሮ የወርቅ ሜዳሊያ አገኘ። ራህዲ ሁለተኛ፣ ባሪ ማጊ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን አገኙ። ሌሎቹ ሯጮች ሲያለከልኩና ጥቂቶቹም ራሳቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ሲውድቁ፤ በባዶ እግሩ ማራቶኑን የሮጠው አበበ ስታዲየሙ ውስጥ ሲያሟሙቅና ሰውነቱን ሲያፍታታ የተመለከቱት በስታዲየሙ የተገኙ ተመልካቾችና አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እጃቸውን በአፋቸው ለመጫን ተገደዋል።
በውድድሩ ማግሥት የኢጣሊያ ጋዜጦች ‹‹ኢትዮጵያን ለመውረር የኢጣሊያ አገር ወታደር ሁሉ አስፈልጎ ነበር፤ ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው›› የሚል ጽሁፍ ይዘው ወጡ። ከዚህ ታላቅ ድል በኋላ አበበ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በተደረገለት የጀግና አቀባበል “እንዴት ይረሱታል የአበበን ዝና መሐንዲስ ይመስል ሲቀይስ ጐዳና’’ ተብሎ ተዘፍኖለታል።ኢትዮጵያዊው አትሌት አበበ ቢቂላ በኦሎምፒክ ታሪክ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ አትሌት ነው። በማራቶን ደግሞ የመጀመሪያው ወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ ጥቁር አትሌት ነው። ይህም ብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ በር ከፍቷል።
አበበ በድል ጎዳና መገስገሱን ቀጥሎበት በ1964ቱ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ውድድሩ ከመጀመሩ 40 ቀናት ቀደም ብሎ የትርፍ አንጀት ይዞት ሆስፒታል ገብቶ የቀዶ ጥገና ከተደረገለት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሳያገግም ሮጦ 78 ሯጮች በተሳተፉበት የማራቶን ውድድር አንደኛ በመውጣት ርቀቱን 2ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11ነጥብ 2 ሰከንድ በሆነ ጊዜ አጠናቆ የአለምን ክብረወሰን በመስበር በሁለት ተከታታይ ኦሎምፒኮች ማራቶንን አከታትሎ በማሸነፍ አለምን አስገርሟል።
ጋዜጠኞች ከውድድሩ በኋላ ድካም የሚባል ነገር ይሰማው እንደሆነ ሲጠይቁት “አስር ኪሎ ሜትር ጨምር ካላችሁኝ እጨምራለሁ” ብሎ እንደመለሰ ይነገራል። አበበ ከቶኪዮው ድል በኋላ ወደሀገሩ ሲገባ የሙሉ መቶ አለቃነት ማዕረግ ሲሰጠው ቮልስ ዋገን መኪናም ተሸልሟል።
በ1968ቱ የሜክሲኮ ኦሎምፒክ አበበ የተሳተፈ ቢሆንም ባጋጠመው ህመም ምክንያት 15ኛው ኪሎ ሜትር ላይ አቋርጦ ለመውጣት ተገደደ። በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ማራቶን ያላትን ክብር እንድታስጠብቅ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበት ማሞ ወልዴ በአበበ አቋርጦ መውጣት ሳይረበሽ አንደኛ ወጥቶ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።
መጋቢት 15 ቀን 1961 ዓ.ም ከአዲስ አበባ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አበበ የመኪና አደጋ አጋጠመው። አደጋው ከባድ በመሆኑ ለህክምና ወደ እንግሊዝ ተልኮ ለስምንት ወራት ያህል ሲታከም ቢቆይም ሊድን ባለመቻሉ ዳግም በወርቃማ እግሮቹ መቆም አልቻለም። በጊዜው የአለም ጋዜጠኞች “እንዳንተ ያለ ታላቅ ሯጭ በዊልቸር ተደግፎ መኖርን እንዴት ይቀበላል?’’ የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡለት አበበ “ማራቶንን በኦሎምፒክ ያሸነፍኩት በእግዚአብሄር ፈቃድ ነበር። ይህ አደጋም የደረሰብኝ በእግዚአብሄር ፈቃድ ነው። ማራቶንን ሳሸንፍ በታላቅ ደስታ እንዳሳለፍኩ ሁሉ ይሄንንም አደጋ በጸጋ ተቀብዬ እኖራለሁ” ሲል መለሰ። በአንድ ወቅትም ለዋሚ ቢራቱ ያለውን ፍቅር ፣ ክብርና አድናቆት ሲገልጽ “እኔ የዓለም አንደኛ የኢትዮጵያ ግን ሁለተኛ ሯጭ ነኝ” ብሏል።
አበበ ጥቅምት 15 ቀን 1966 ዓ.ም በ41 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ሲለይ ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴን ጨምሮ ከ75 ሺህ በላይ ህዝብ ተገኝቶ በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን የቀብር ስነ ስርአቱ ተፈጽሟል። አበበ ከወይዘሮ የውብዳር ወልደ ጊዮርጊስ ጋር ትዳር መስርቶ አራት ልጆችን አፍርተዋል።
በስሙ በርካታ መታሰቢያዎች ተሰይመውለታል። አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኝ ስታዲየም በስሙ ተሰይሟል። በጣሊያን ከሮም ከተማ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዋ ላዲስፖሊን ከተማ የእግረኞች ድልድይና መንገድ በስሙ “ፖንቴ አበበ ቢቂላ” ተብሎ እንዲጠራ ተደርጓል። የሴኔጋል መዲና ዳካር የመጀመሪያውን የአፍሪካ አትሌቲክስ ውድድር ምክንያት በማድረግ ወደ “ዴምባ ዲዮፕ” ስታዲየም የሚያስገባውን መንገድ የአበበ ቢቂላ መንገድ ብላ ሰይማዋለች።
ቪብራም የተባለ የአሜሪካ የጫማ ድርጅት ከአመታት በፊት አበበን ለመዘከር ፋይቭ ፊንገርስ ቢቂላ (Five Fingers Bikila) የተባለ ጫማ ገበያ ላይ አውሏል። በ2004 ዓ.ም በእውቅ የሲኒማ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች የተሰራ አትሌቱ ወይም በእንግሊዘኛ መጠሪያው “The Athlete” የተሰኘው ማንነቱንና የስፖርት ህይወቱን የሚዳስስ ፊልም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለእይታ ቀርቧል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
የትናየት ፈሩ