“የኢትዮጵያ ማንሰራራት ማሳያ በሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ ሁሉም እንዲሳተፍ ጥሪዬን አቀርባለሁ” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡የኢትዮጵያ ማንሰራራት ማሳያ በሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ችግኝ በመትከል እንዲሳተፍ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከተማ የወንዞች ተፋሰስ መነሻ በሆነው በጉለሌ ወረዳ 6 የዘንድሮውን የአረጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ ትናንት አስጀምረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ለችግኞች የሚመች ቦታ በመምረጥ መከወን የሚገባ ሲሆን ሁሉም በመትከል ኢትዮጵያን እንዲያለብስ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ማንሰራራት ማሳያ በሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍልና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ እንዲሳተፍ ጥሪዬን አቀርባለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር “በመትከል ማንሰራራት” የሚል መሪ ቃል የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ እጅግ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን ያስገኘ ሥራ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህ ዓመት ከሚተከለው ችግኝ ጋር 47 ነጥብ 5 ቢሊዮን ገደማ እንደርሳለን። ይህም በሚቀጥለው ዓመት ከምንተክለው ጋር ሲደመር 54 ቢሊዮን ልንደርስ ያስችለናል ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞች አርዓያ በመሆን አፍሪካዊ ባሕል እንደሚሆን ገልጸው፤ በዚህ መርሐ ግብር ያመናችሁ፣ የተሳተፋችሁ እጆቻችሁ ጭቃ የነካ፣ የተከላችሁ፣ የተንከባከባችሁ ኢትዮጵያውያን፣ በኢትዮጵያ የምትገኙ ዲፕሎማቶች፣ ይህንን ሕልም የደገፋችሁ የየትኛው ሀገር ዜጎች በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ፥ እንኳን ደስ ያለን ልላችሁ እወዳለሁ ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በሚቀጥለው ዓመት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ የምታገኘውን ውጤት ሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞች በአርዓያነት በመከተል አፍሪካ መጋቢ፣ አፍሪካ ሰጪ፣ አፍሪካ ፈር ቀዳጅ አኅጉር መሆኗን በማሳየት አፍሪካዊ ባህል ይሆናል ብለዋል።

“እንጀምራለን እንጨርሳለን፤ እንጀምራለን እናስተምራለን፤ እንጀምራለን እናንሰራራለን፤ ይህ ኢትዮጵያዊነት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ላለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት የሚመግበንን፣ የእናት ምትክ የሆነንን ተፈጥሮን አክብረን፣ አብረን መኖር ባለመቻላችን ኢትዮጵያ ከሌሎች ጠባቂ ሆና ቆይታለች ብለዋል፡፡

በተያዘው እቅድ መሠረት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ካሳካን በኋላ ኢትዮጵያ በምግብ ሙሉ በሙሉ ራሷን የቻለች ሀገር መሆኗን ለዓለም እናበስራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ በወንዝ ዳር ልማት ሥራዎች ተራራዎቹ በኮንሶ እጆች ሽሩባ መሠራታቸውን ገል ጸው፤ ይህን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ጌትነት ምሕረቴ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You