እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
“አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት አለመደብንም”
ይህ አባባል የኢትዮጵያን የንግድ እንቅስቃሴ በተገቢው መልኩ የሚያሳይ ይመስላል። እርግጥ ነው በአገራችን በተለያዩ ማህበረሰቦች ዘንድ አብሮ መብላትን ብቻ ሳይሆን በደስታም ሆነ በኀዘን አብሮ መሆንን እንዲሁም በእርሻና በሌሎችም እንቅስቃሴዎች ተባብሮ መሥራትን የሚያ ጎለብቱ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች መኖራቸው አሌ የሚባል አይደለም።
ከኢኮኖሚና ከንግድ እንቅስቃሴ አንጻር ካየነው ግን አብሮ የመብላትን ያህል አብሮ መሥራት አልዳበረም። ንግድና ኢንቨስትመንት ጎልብቷል ከሚባልባቸው አገሮች በተቃራኒው ሀብትን፣ ሙያን፣ ዕውቀትንና ልምድን በማዋጣት በጋራ የንግድ ሥራ ከማከናወን ይልቅ በተናጠል መሥራትን የሚመርጥ ማህብረሰብ ነው አብዛኛው የአገራችን ሕዝብ። ከንግድ ድርጅት አስተሳሰብ ይልቅ የጉሊት፣ የኪዮስክ ወይም የሱቅ በደረቴ አስተሳሰብ የንግድ ሥርዓቱ ዓይነተኛ መገለጫ ነው።
አብዛኛው ዜጋ የግሉን ሱቅ፣ የግሉን ሆቴል፣ የግሉን ፋብሪካ ወዘተ አቋቁሞ ነው መሥራት የሚፈልገው፤ የሚሠራውም። በተለምዶ የአፍሪካ ትልቁ ገበያ እየተባለ በሚጠራው መርካቶ እጅግ ሰፊ የሆነው የንግድ ሥራ የሚከናወነው በተናጠል ነው። በመላ አገሪቱ በሚገኙ ከተሞችና የኢንዱስትሪ ሥራ በሚከናወንባቸው አካባቢዎችም ቢሆን አብዛኞቹ ንግዶች በግለሰብ ደረጃ ነው የሚሠሩት።
እርግጥ ነው በአገሪቱ ከነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ሥርዓት ማቆጥቆጥ ጋር ተያይዞ ከጊዜ ወደጊዜ በተለይም ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማህበራት ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ይገኛል። ይሁንና እንዲህ ዓይነት የንግድ ድርጅቶች በአብዛኛው የህጉን የአባላት ቁጥር ለማሟላት በሚል ብቻ በድርጅቱ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የንብረት፣ የገንዘብም ሆነ የጊዜ አስተዋጽኦ በማያደርጉ የቤተሰብ አባላት የሚቋቋሙና በአንድ ግለሰብ ከፍተኛ ባለድርሻነትና ብቸኛ አንቀሳቃሽነት የሚመሩ በመሆናቸው የጋራነታቸው ለስም ካልሆነ በስተቀር ከግል ንግድ ሥራ ተለይተው የሚታዩ አይደሉም።
በተጨማሪም ከአገሪቱ የህዝብ ቁጥር ከፍተኛነት እና ኢኮኖሚውም ሰፊ መሰረት እየያዘ ከመምጣቱ ጋር ሲነጻጸር እንዲህ ዓይነት የንግድ ድርጅቶችም ሆኑ ሌሎች በሽርክና የሚከናወኑ የጋራ ንግድ ሥራዎች ያሉበት ደረጃ ዝቅተኛ ስለመሆኑም ጥናቶች ያሳያሉ። የጋራ ንግድ ሥራ ዓይነተኛ መገለጫና ከንግድ ድርጅቶች ሁሉ በሕጋዊ አቋም፣ በአደረጃጀት፣ በአመራር፣ በሀብትና በአባላት ብዛት ከፍተኛው እርከን ላይ በተቀመጠው በአክሲዮን ማህበር (Share Company) መልክ የተቋቋሙት ማህበራት ደግሞ ቁጥራቸው እጅግ አነስተኛ መሆኑን ነው ከንግድ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች የሚያሳዩት።
የንግድ ድርጅት አቋቁሞ የጋራ ንግድ ሥራ የመሥራት ልማድ ላለመዳበሩ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። የካፒታል እጥረት፣ ቢሮክራሲ የበዛበት የንግድ ምዝገባና አስተዳደር ስርዓት እንዲሁም የህግ ክፍተቶች በምክንያትነት ይነሳሉ። በተጨማሪም “የጋራ ነገር ወንጋራ (ወልጋዳ) ነው” የሚል ብሂል ካዳበረ ማህበረሰብ የተገኘ ሰው በጋራ መሥራት ጭቅጭቅ፣ አለመግባባትና ባስ ሲልም እዳን ይጎትታል (ሪስክ አለው) በሚል ምክንያት የራሱን ወረት (መንቀሳቀሻ ገንዘብ) ይዞ በግሉ መነገድን ምርጫው ማድረጉም አይቀርም።
ከሁሉም በላይ በበርካታ ልሂቃን እይታ “ከሽፈውብናል” በሚል በቁጭት እንደሚ ገለጹት የዘመናዊ የፖሊቲካ ሽግግራችን፣ የትምህርት፣ የዘመናዊ ትውልድ እና ግብረገብነት ግንባታ እንዲሁም ሌሎችም ጉዳዮቻችን ሁሉ ዕቃን በዕቃ ከመለወጥና ጥቂት ሸቀጥ በጉሊት ዘርግቶ በችርቻሮ ከመገበያየት ወደ ዘመናዊና ድርጅት መስርቶ በስፋት ንግድን ወደማከናወን የሚደረገው የንግድ ሽግግር እውን ላለመሆኑ ዓይነተኛው ምክንያት የተሳሳተ የፖለቲካ መስመር ይዘው ያስጓዙን መንግሥታትና በማህበረሰብ ደረጃ የባህርይ ለውጥ አለመምጣቱ ስለመሆኑ መናገር ይቻላል።
ከአገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ሳይነሳ ሊታለፍ የሚገባው ጉዳይ የመንግሥት ፈርጣማ ነጋዴነት ነው። ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግን ግንባር ፈጥረው የመሰረቱት አራቱም የፖለቲካ ድርጅቶች በባለቤትነት የተቆጣጠሯቸው የንግድ ድርጅቶችም ቱባዎቹ ነጋዴዎች ናቸው። የፓርቲዎቹን ለጊዜው አንንካውና በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ግዙፍ የንግድ ኩባንያዎች በመንግሥት እጅ ነው የሚገኙት።
ይህም አብሮ ያለመሥራት አባዜ በማህበረሰቡ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በመንግሥትም በኩል እንዳለ አጉልቶ ያሳያል። የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ሥርዓቱም ሆነ የንግድ እንቅስቃሴው የመዘመን ጉዞ የተንቀራፈፈበት ዋና ምክንያትም ይኸው ነው – መንግሥት የግሉን ዘርፍ አላስጠጋም ብሎ በብቸኝነት ቁልፍ ንግዶችን ለብቻው መያዙ። ለዚህ ይመስላል በብቸኝነት ይዟቸው የቆዩ ወሳኝ ድርጅቶቹን ሳይቀር ድርሻውን ለግሉ ዘርፍም በማካፈል የጋራ ንግድ ሥራን ወደሌላ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንቅስቃሴ የጀመረው።
የንግድ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ህግ
ስለ ሽርክና ስምምነት ከመመልከታችን አስቀድሞ የንግድ ድርጅቶችን ማየቱ ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም በመሰረቱ የሽርክና ስምምነት የሚባለው ነገር የሚያስፈልገው የንግድ ድርጅቶችን ለመመስረት ስለሆነ። በኢትዮጵያ ንግድን አብሮ መሥራት ዛሬም ድረስ ባይዳብርም በ1952 ዓ.ም ተደንግጎ እስከአሁንም በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ግን ከነውስንነቶቹ የንግድ ድርጅት መስርቶ አብሮ የመሥራት እንቅስቃሴን በስፋት ደንግጎ እናገኘዋለን።
ሕጉ የንግድ ማህበርን (ድርጅትን) ሲተረጉም ማንኛውም በሽርክና ስምምነት መሰረት የሚቋቋም ማህበር የንግድ ድርጅት (ማህበር) ይሰኛል ሲል ይገልጸዋል። ከዚህ የምንረዳው የትኛውንም ዓይነት የንግድ ማህበር እውን ለማድረግ በቅድሚያ የሽርክና ስምምነት አስፈላጊ መሆኑን ነው። ባለንበት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ዘመን ከባድ፣ አትራፊና ሰፋፊ ንግድና ኢንቨስትመንቶችን በግል ለማከናወን ስለማይቻል ግለሰቦች ሰብሰብ ብለው የሽርክና ስምምነት በማድረግ የንግድ ድርጅቶችን ያቋቋማሉ።
በንግድ ሕጋችን ውስጥ በሁለተኛው መጽሐፍ ከአንቀጽ 210 እስከ 560 ድረስ ያሉት ሰፊ ድንጋጌዎች ስለ ንግድ ድርጅቶች አመሰራረት፣ አነጋገድ፣ አደረጃጀት፣ ሂሳብ አያያዝ፣ የአባላትና የድርጅቶቹ ሕጋዊ ሰውነት ተጠያቂነት፣ የድርጅቶች መቀላለቀልና መፍረስ ጉዳዮችን የተመለከቱ ናቸው።
በንግድ ሕጉ የንግድ ድርጅቶች በአጠቃላይ የሽርክና ማህበራት እና ኩባንያዎች ተብለው በሁለት ይከፈላሉ። የሽርክና ማህበራት በኩባንያ (በኮርፖሬሽን) ደረጃ ሊቋቋሙ የማይችሉ በንጽጽር አነስተኛ ድርጅቶች ናቸው። ዓይነተኛ መገለጫቸው ደግሞ ዋነኛ መዋጮዎቹ ግለሰቦቹ (አባላቱ) ራሳቸው መሆናቸው ነው። ይህ ማለት የሽርክና ማህበራት ምንም እንኳን ግለሰቦች ገንዘባቸውን፣ ሙያቸውን እና ሀብታቸውን አዋጥተው የሚመሰርቷቸው ቢሆኑም ግለሰቦቹ በሽርክና ማህበራቱ ሕልውና ላይ እጃቸው ረዥም ነው።
ከሸሪኮቹ የአንዱ ችሎታ ማጣት (ሕፃንነት፣ እብደት፣ በሕግ ወይም በፍርድ የተጣለ ክልከላ)፤ ሞት፣ በግል ሥራቸው መክሰር ወይም በመካከላቸው የሚፈጠር አለመግባባት የማህበሩን መፍረስ ያስከትላል። ማንኛውም አባልም በራሱ ፈቃድ በፈለገው ጊዜ በማህበሩ ውስጥ ያለውን ድርሻ ለውጭ ሰው (ሦስተኛ ወገን) ማስተላለፍ አይችልም።
ከዚህም በላይ አባላቱ አንዳቸው ለሌላኛው ወኪሎች ናቸው። ማህበሩ ከሦስተኛ ወገኖች ለሚጠየቀው ማናቸውም ዕዳ የአንድነትና የነጠላ ዋሶች ያለባቸውን ዓይነት ኃላፊነት አለባቸው። ኃላፊነታቸው ያልተወሰነ በመሆኑ ዕዳ ጠያቂው ድርጅቱ ቢፈርስ ወይም ዕዳውን መክፈል ቢሳነው እንኳ አባላቱን ሲፈልግ በተናጠል ሲያሰኘውም በጋራ ጠይቆ ገንዘቡን ከግል ንብረታቸው ላይ የማስመለስ ህጋዊ መብት አለው።
ከእነዚህ ህጋዊ ባህርያት እንደምንረዳው የሽርክና ማህበራት በሚቀራረቡና በሚተማመኑ ወዳጅ ሸሪኮች አማካኝነት የሚመሰረቱ ናቸው። ከዚህም ሌላ ለአጭር ጊዜ እና ለተወሰነ የንግድ (የኢንቨስትመንት) ሥራ ጠቃሚዎችና ለአመራርም ቀላል ናቸው።
በአገራችን ሕግ የሽርክና ማህበራት የሚባሉት ተራ የሽርክና ማህበር፣ የእሽሙር ማህበር፣ የሕብረት ሽርክና ማህበርና ሁለት ዓይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማህበር ናቸው። ከእሽሙር ማህበር በስተቀር ታዲያ ሁሉም የሽርክና ማህበራት ህጋዊ ሰውነት ያላቸው (በራሳቸው መክሰስ መከሰስ፤ የንብረት ባለቤት መሆን ወዘተ የሚችሉ) ናቸው።
እነዚህ የሽርክና ማህበራት ዓይነቶች ከአመሰራረታቸው፣ ከማህበርተኞቹ መብትና ግዴታ፤ ከማህበራቱ ሥራ አመራር፣ በማህበራቱ እና በሦስተኛ ወገኖች እንዲሁም በአባላቱና በሦስተኛ ወገኖች መካከል ሊኖር ከሚገባው ግንኙነት እንዲሁም ከማህበራቱ የማፍረሻ ምክንያቶችና ከመፍረሳቸው ውጤቶች አንጻር የተለያየ የህግ አንድምታ አላቸው።
ከሽርክና ማህበራት ሌላ ሕጋዊ እውቅና የተሰጣቸው የንግድ ድርጅቶች ኩባንያዎች ናቸው። ኩባንያዎች ሁለት ዓይነት ናቸው – የአክስዮን ማህበር እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር። ኩባንያዎች ሰፋፊና የረዥም ጊዜ ንግዶችን ለማከናወን ጠቃሚ ናቸው። የማህበራቱ ካፒታል በአክስዮን (በሼር) የተከፋፈለና አባላቱም እንደየመዋጯቸው ልክ የአክስዮን ድርሻ ያላቸው ባለአክስዮን ማህበርተኞች መሆናቸው የኩባንያዎች ልዩ ባህርይ ነው። ኩባንያዎችን የአባላቱ መክሰር፣ ሞት ወይም አለመግባባት አያፈርሳቸውም። የአባላቱ ኃላፊነት የተወሰነ በመሆኑ ለሦስተኛ ወገኖች ያለባቸው ተጠያቂነት በኩባንያው ውስጥ ባላቸው አክስዮን ልክ ነው። (እያንዳንዱን የሽርክና ማህበርና ኩባንያዎች የተመለከቱ ዝርዝር ሕጋዊ ጉዳዮችን በሌሎች ጊዜያት የምንዳስስ ይሆናል)
የሽርክና ስምምነት
የንግድ ማህበር ማለት ማንኛውም በሽርክና ስምምነት መሰረት የሚቋቋም ማህበር ነው ብለናል። የሽርክና ስምምነት ማለት ደግሞ ከንግድ ሕጉ አንቀጽ 211 ድንጋጌ ላይ ሰፍሮ እንደምናነበው ሁለት ወይም ብዙ ሰዎች መዋጮ አዋጥተው በአንድነትና በሕብረት የኢኮኖሚ ተግባር ያለው ሥራ ለመሥራትና ከሚገኘው ትርፍም ሆነ ከሚመጣው ዕዳ ተካፋይ ለመሆን የሚስማሙበት ውል ነው።
ከድንጋጌው የምንረዳው ቀዳሚው ጭብጥ የሽርክና ስምምነት በመሰረቱ ውል መሆኑን ነው። ውል ከሆነ ደግሞ በሕግ ፊት ዋጋ የሚያወጣ እንዲሆን በፍትሐብሔር ህጋችን የተደነገጉትን አራት መለኪያዎች ማሟላት አለበት። እነዚህም የተዋዋዮች የመዋዋል ችሎታ፤ ፈቃዳቸው ጉድለት በሌለበት አኳኋን የተገለጸ መሆኑ፤ የተዋዋሉበት ፍሬ ጉዳይ በሕግና በመልካም ስነ ምግባር ቅቡልነት ያገኘ መሆኑ እንዲሁም ሕግ በሚጠይቅ ጊዜ የውሉ አቀራረጽ በህግ በተቀመጠው ሥርዓት (ፎርም) መሰረት የተደረገ መሆን አለበት የሚሉ ናቸው።
የንግድ ሕጉ ከእሽሙር ማህበር በስተቀር ማንኛውም የንግድ ማህበር የሚቋቋምበት ውል በጽሑፍ ካልተደረገ በስተቀር አይጸናም ስለሚል የሽርክና ስምምነት በጽሑፍ መደረግ ይኖርበታል ማለት ነው። ተራ የሽርክና ማህበርን እና ሁለት ዓይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማህበርን ለመመስረት ስምምነቱ በጽሑፍ ይደረግ እንጂ የስምምነቱ ዓይነትና ቅርጽ ለሽርከኞቹ ምርጫ የተተወ ነው። የሕብረት ሽርክና ማህበር ደግሞ በህጉ በተገለጸው መልኩ በመመስረቻ ጽሑፍ ነው የሚመሰረተው። የአክስዮን ማህበርና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርም በመመስረቻ ጽሑፍና በመተዳደሪያ ደንብ የሚመሰረቱ ሲሆን ስምምነቱ ሊይዝ የሚገባውንም ፍሬ ነገር ሕጉ ዘርዝሮ አስቀምጧል።
ሌላው የሽርክና ስምምነት መሰረታዊ ጉዳይ “ሁለት ወይም ብዙ ሰዎች” የሚለው አገላለጽ ነው። የተፈጥሮ ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው ድርጅት ሁሉ ሁለትና ከሁለት በላይ በመሆን የንግድ ማህበር መመስረት ይችላሉ። ከአክስዮን ማህበር በስተቀር ሁሉም የንግድ ድርጅቶች በትንሹ በሁለት ሰዎች ሊመሰረቱ ይችላሉ። የአክስዮን ማህበር ለመመስረት ግን በትንሹ አምስት ሰዎች ያስፈልጋሉ። አከራካሪ ቢሆንም አንዳንድ የበለጸጉት አገራት ሕጎች አንድ ሰው ብቻውን ኩባንያ እንዲመሰረት የሚፈቅዱ ሲሆን፤ እየተሻሻለ ያለው የእኛው የንግድ ሕግም ይህንኑ የሚፈቅድ ሆኖ ተቀርጿል። የመጨረሻውን የአባላት ቁጥር ስንመለከት ደግሞ ኃላፊነቱ ከተወሰነ የግል ማህበር በስተቀር ለሌሎቹ የንግድ ድርጅቶች ሕጉ ገደብ አላስቀመጠም። ኃላፊነቱ የተሰወነ የግል ማህበር አባላት ግን ከሃምሳ መብለጥ የለባቸውም።
የመዋጮ ጉዳይ ሌላው የሽርክና ስምምነት ፍሬ ነገር ነው። መዋጮው በካሽ፣ በዓይነት ወይም በአገልግሎት ወይም በሥራ ችሎታ (Skill) ሊሆን ይችላል። በሕግ ጥበቃ የተደረገለት የአዕምሮ ንብረትንም (ኮፒ ራይት፣ ፓተንት፣ የንግድ ምልክት) ማዋጣት ይቻላል።
ሰዎች የሽርክና ስምምነት አድርገው የንግድ ማህበር የሚመሰረትቱት በሕጉ አገላለጽ “የኢኮኖሚ ተግባር ያለው ሥራ ለማከናወን” ነው። ይህ አገላለጽ መሰረተ-ሰፊ ሲሆን፤ ማንኛውንም ትርፍ የሚያስገኙ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 5 ስር የተዘረዘሩትንና ሌሎችንም የንግድ ተግባራት ሁሉ ያጠቃልላል።
በንግድ ማህበራት ሥራ ላይ በተለይም ከሽርክና ስምምነቱ ጋር በተያያዘ ዋነኛው የሙግት መነሻ የትርፍና ኪሳራ ጉዳይ ነው። የሽርክና ስምምነት ሁሉም የማህበሩ አባላት ከሚገኘው ትርፍም ሆነ ከሚመጣው ዕዳ ተካፋይ ለመሆን የተስማሙ መሆናቸውን በግልጽ ማሳየት አለበት። ይሁንና በርካቶች ከሕግ የግንዛቤ እጥረት መነሻ ትርፍን በአንዱ እጅ ላይ፣ ዕዳን ደግሞ በሌላኛው ትከሻ ላይ የሚጭኑ ስምምነቶችን ሲያደርጉ ይስተዋላል።
ሕጉ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው ትርፉን ሁሉ ለአንደኛው ማህበርተኛ ብቻ የሚሰጥ ስምምነት ፈራሽ ነው። እንዲሁም የአንዱን ወይም የብዙዎቹን አባላት በማህበሩ ላይ ከሚመጣው ኪሳራ እንዳይነካው የሚያደርግ ስምምነትም ፍርስ ነው። ያም ሆኖ ተራ የሽርክና ማህበር በሆነ ጊዜ ግን በሥራ ችሎታው ብቻ ሸሪክ የሆነ ሰው የትርፍ ተካፋይ እንዲሆን፤ ኪሳራ ግን እንዳይነካው አድርጎ መዋዋል ሕጉ እንደሚፈቅድ ልብ ይሏል።
በመርህ ደረጃ የሽርክና ስምምነት ሁሉንም አባላት (ያገቡት የመዋጮ ዓይነትና ዋጋው ከግምት ሳይገባ) እኩል የትርፉ ፍሬ ተቋዳሽ እና የኪሳራው ወይም የዕዳው ተጋሪ የሚያደረግ መሆን አለበት። ትርፍና ኪሳራው እንደመዋጯቸው ዓይነትና ዋጋ እንዲሁ የተለያየ ሊሆን ይችላል የሚል ስምምነት እንዳያደርጉ ግን ሸሪኮቹን የሚከለክላቸው ሕግ የለም።
ከትርፍና ኪሳራ ጋር ተያይዞ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ በህብረት ሽርክና ማህበር ውስጥ አንድ ማህበርተኛ የሌሎች ሸሪኮቹን ፈቃድ ሳይጠይቅ የድርሻውን መብቶችና ጥቅሞች (ትርፍን ጨምሮ) ሌላ ሦስተኛ ወገን (ለምሳሌ አበዳሪው) እንዲጠቀምባቸው አሳልፎ የመስጠት መብት ያለው መሆኑ ነው። ይህ ግን ለሦስተኛው ወገን የማህበርተኛነት መብት እንደማይሰጠው ልብ ይሏል።
በደህና እንሰንብት!አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
(ከገብረክርስቶስ)