ጨረቃ በመሬትና በፀሐይ መካከል በምታልፍበት ጊዜ ጥላዋን በመሬት ላይ በመጣል የምትፈጥረው የፀሐይ ብርሃን መሸፈን ወይንም ግርዶሽ በሳይንሳዊ መታወቂያው ኤክሊፕስ ተብሎ ይታወቃል። በፖለቲካዊው ተጓዳኝ ትርጉሙ ደግሞ ይሄው ኤክሊፕስ የሚለው ቃል የሚሰጠው ፍቺ በአንድ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ የሚፈጸሙ ከፍተኛ ሤራዎች፣ ወንጀሎችና ጥፋቶች የዚያን መንግሥት መልካም ስም ወይንም ክብር ለማጉደፍ ጥላ የሚያጠሉበት ከሆነ መንግሥታዊ ግርዶሹ በዚሁ በኤክሊፕስ ይመሰላል፤ (the scandal caused an eclipse of the government reputation) እንዲሉ።
ወቅታዊ የሀገሬን ሁኔታ ልብ ብሎ ላስተዋለ ሰው በበርካታ ጉዳዮቻችን ላይ ያልተገቡ ክስተቶች ግርዶሽ እየፈጠሩብን ነገራችን ሁሉ በግማሽ ጎኑ ፀሐያማ ገጽታው ሲያይል ግማሹ ደግሞ በግርዶሽ እየተጋረደ ለጠብ፣ ለክርክር፣ ለአመፅ፣ ለእብሪት፣ ዳርጎን ሲያደናቁረንና ሲያናቁረን እያስተዋልን ነው። ከሀገራዊ የሪፎርሙ ትግበራ ጋር ተያይዞ አዳዲስ እና ተስፋ ፈንጣቂ “ብሩህ” ውጤቶች የመመዝገባቸውን ያህል በአንጻሩ ደግሞ በስኬቶቹና በተስፋዎቹ መካከል የሚስተዋሉት ኤክሊፕሶች በነጋ በጠባ ግራ እያጋቡንና እያቆሰሉን ፈተና ሆነውብናል።
በጸሐፊው እምነት ሀገራዊው ኤክሊፕስ ያስከተለብን ጉዳት በግማሽ ልጩ፣ በግማሽ ጎፈሬ ቢመሰል ተገቢ ይመስለኛል። በጎፈሬውም ውስጥ ሆነ በልጩው ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ውስጥ እየተብላላ የሚያሳክከን ፎረፎር ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥዝጣዜው እየጨመረ ስለሆነ በጊዜና በአጭሩ መቀጨት ካልቻለ ጦሱ ለልጅ ልጅ መተላለፉ አይቀርም። የዚህን መሰሉ ችግራችን ዋነኛ መነሾዎች የሀገራዊ ዓላማዎችና ዒላማዎች ፈር መሳት ይመስለኛል።
ዓላማ (purpose) መዳረሻ ግብ ነው። የታቀደውን መልካም ግብ ከስኬት ለማድረስ ደግሞ በወታደራዊ ቋንቋ አገላለጽ የደምም ሆነ የላብ ዋጋ ለመክፈል ቁርጠኝነት መጠየቁ ግድ ነው። ዓላማ እስከ ሞትም ቢሆን ያስጨክናል። ዓላማዬ “የምኖርለትም የምሞትበትም መርሄ ነው” የሚባለውም ስለዚሁ ነው። ወደ አንድ የታቀደ ግብ ለመድረስ መረማመጃ መንገዶቹ ቀይ ምንጣፍ የተነጠፈላቸውና ቄጤማ የተጎዘጎዘላቸው ላይሆኑ ይቻላሉ። ይህን መሰሉ የዓላማ ስኬትና ትሩፋት በቅዠት ዓለም ካልሆነ በስተቀር “የኤክሊፕስ ግርዶሽ” በሚበዛባቸው እኛን መሰል ሀገራት ዕውን ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።
ዓላማን ከግብ ለማድረስ የቆንጥር መሰናክሎችን ማለፍ፣ ሸረኞች የቀጠሩትን ቅጥር በአሸናፊነት መዝለል፣ ያልተጠበቁ ተግዳሮቶችን በጥበብ መቋቋም፣ እልህ አስጨራሽ ፈተናዎችንም ጉዳት ሳያደርሱ ማለፍ ግድ ይሏል። ዓላማ ከታቀደለት ግብ እንዳይደርስ ፈሩን የሚስት ከሆነ በጉዞ መካከል የሚፈጠሩት ያልተጠበቁ ኤክሊፕሶች መዘዛቸው የከፋ ውጤት ማስከተሉ አይቀርም። መዘዙ አንድን ትውልድ ብቻ አጎሳቁሎ የሚያልፍ ሳይሆን በተከታታይ ትውልዶችም ሊቀጥል ይችላል።
የዒላማ (target) ተኩስም ሆነ ጨዋታ በተነጻጽሮ የሚሰጠንን ትርጉም ልብ ብለን ብናስተውል ብዙ ግንዛቤዎችን ሊያመላክተን ይችላል። እንደ ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል አገላለጽ ቀደም ባሉት ዘመናት አንድ ተኳሽ፤ “ዐይኑን የሚያጠራው፣ የብረቱን (የመሣሪያውን) ጠባይ የሚረዳውና የሚያውቀው በዒላማ ተኩስ ሲፈትነው ነው። የጥይቱን አካሄድ ተመልክቶ ብረቱ እግር፣ ራስ ወይንም ጎን እንደሚሄድ መመርመር አለበት። አነጣጥረው በመተኮስ ዒላማቸውን የሚመቱ ብርቱዎች ልዩ ክብር ይጎናጸፋሉ። በኑሯቸውም ላይ ከፍ ያለ ማዕረግና ዋጋ ይሰጣቸዋል።” በአንጻሩ ፈሩን የሳተ ዒላማ “ፉርሽ” ተብሎ ብቻ የሚታለፍ ሳይሆን መሳቂያና መሳለቂያ በመሆን አነጣጣሪውን ለፀፀትና ለአንገት መድፋት ምክንያት ሊሆኑት ይችላሉ።
በዘመናዊ የዒላማ ጨዋታም ቢሆን አሸናፊም ሆነ ተደናቂ የሚሆን ግለሰብ አነጣጥሮና አልሞ በክቧ መሃል ለመሃል በምትገኘው ነጥብ ላይ ቀስቱን ካላሳረፈ በስተቀር ውጤት አምጥቶ ላይጨበጨብለት ይችላል። የሀገሬን ጉዳይ በኤክሊፕስ ለመመሰል የተገደድኩትም ነጋ ጠባ ዓላማቸውንና ዒላማቸውን የሳቱ ጉዳዮቻችን ሊፈጥሩ የሚችሉት የጦስ ጠባሳ ጉዳይ ሰላምና እንቅልፍ ነስቶ ስለሚያባንነኝ ነው።
በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ እንደምናነበው የጥንታዊያኑ እስራኤላውያን ካህናት ዕጣ ወድቆባቸው ወደ መቅደሱ ውስጠኛው ክፍል ገብተው የሕዝባቸውን ኃጢአት በጅምላ የሚያስተሰርዩት የአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ስም የተጻፈበትን አሸንክታብ በደረታቸው ላይ አጥልቀው ነበር። “አንድ ካህን ለነገዶቹ ሁሉ ተቀዳሚ ወኪል ነው” እየተባለ በአይሁዳውያን ዘንድ መታመኑም ስለዚሁ ነው።
በሀገሬ ውስጥ የሕዝብ ወኪል ነን የሚሉ ወገኖች በምርጫም ሆነ በእርግጫ “የሥልጣን መቅደስ” ውስጥ ገብተው መንበሩ ላይ ከተፈናጠጡ በኋላ የሚመሩትን ሕዝብ ልባቸው ላይ ቀርጸው በሆደ ሰፊነትና በአመራር ጥበብ ከማስተዳደር ይልቅ ራሳቸው የጠብና የመከራ መንስዔ ሲሆኑ እያስተዋልን ነው። እንወክለዋለን ከሚሉት የሕዝበ ሠራዊት ጥቅም ይልቅ ራሳቸውን አግዝፈውና አተልቀው “ከእኔና የእኔ ከሆነው በላይ ላሳር” ቀረርቶ ሲያሰሙ ማድመጥና ማስተዋል የተለመደ ወቅታዊ ትዕይንት ነው። ንቀት፣ ዕብሪት፣ ማንአለብኝነትና ትምክህት መለያቸው የሆኑት እነዚህ የሀገራዊ ኤክሊፕሶች መገለጫ ዜጎች ቁጥር ዕለት በዕለት ብዛታቸው እየተበራከተ በመሄድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለደረሰ በእንጭጩ ተቀጭተው ዓላማቸውና ዒላማቸው ካልከሸፈ በስተቀር ሊያደርሱ የሚችሉት ጥፋት በቀላሉ የሚገመት ላይሆን ይቻላል።
በሀገራችን ዘርፈ ብዙ ሕይወት ውስጥ ግርዶሽ ፈጣሪ የሆኑት እነዚህ ኤክሊፕሶች መልካቸውን እየለዋወጡ ሊበራከቱ የቻሉት በዋነኛነት በፖለቲካ ሲስተሙ ውስጥ በተሰነቀሩ በበርካታ “የአውቆ አበድ” ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ሰበብ እንደሆነ ሕዝቡ ከተረዳ ሰነባብቷል። ጭር ሲል የማይወዱት እነዚህ እረፍት አልባዎች ቅዠታቸውና ጉጉታቸው “ሥልጣንና ክብር” ፍለጋ ብቻ መሆኑን ከተረዳንም ቆይተናል።
እንደ ጅብ ጥላ በአንድ ጀንበር አቆጥቁጠው የሚያድሩት እነዚህ “የድል አጥቢያ አርበኞች” እና ከዕድሜ ሳይማሩ የጃጁት “የአባቶቻቸው ልጆች፤ የአያቶቻቸው ቅደመ አያቶች” ቢባሉ ስያሜው የማይበዛባቸው ፀረ ሕዝብ ግለሰቦችና ስብስቦች በሀገሪቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በፈበረኳቸው ታሪኮች እስከዛሬ ካደረሱት ጉዳት ሳናገግም ወደፊትም ያደርሳሉ ተብሎ የሚጠረጠው ጥፋት በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ በግዴታ ከምንታጠነው የሤራ ጭሳቸው የዓላማቸውንና የዒላማቸውን አስነጣሽነት በሚገባ እየተረዳን ነው።
እነዚህ የሀገር ክብርና የሕዝብ ታላቅነት ደንታ የማይሰጣቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ሊያፈርሱት የሚታገሉት ሕዝባዊ ሉዓላዊነት ህሊናቸው ተጋርዶባቸው እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሸመነባቸው ዕሴቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ታሪኮችና ትርክቶች የተወሳሰቡት፣ የተጋመዱትና የተዛነቁት አጥልለው ወይንም አንጥረው ሊለዩት በማይችሉት የደም ትስስርና ጀግኖች አባቶቻችን በታሪካችን ውስጥ እየከፈሉ ባቆሙልን የተከሰከሰ የአጥንት አእማድ መሆኑን በተረዱ ነበር። ለወደፊቱም ቢሆን እውነቱን እስኪረዱት ድረስ ጊዜ ይሰጣቸው የሚባሉ ዓይነቶች ሳይሆኑ የማኅበረሰብ አረሞች ስለሆኑ የሚበጀው ሕዝቡ ራሱ “እንቱፍ” ብሎ ንቆና አስንቆ እንዲያጋልጣቸው ሕዝባዊ መድረኮች ሳይዘገዩ መመቻቸት ያለባቸው ይመስለናል።
በማያውቁት ሕዝብ ስም እየማሉና ሕዝቡ የማይኖረውን የቅንጦት ኑሮ ለራሳቸው እየኖሩ የጥፋት ሰይፋቸውን የሚስሉበት እሳት እንዲግለበለብ ወላፈኑን በወናፍ ሚዲያዎቻቸውና በየስብሰባው ማጋጋላቸው የዕለት ተግባራቸው መሆኑን ራሳቸውን በራሳቸው ሲያጋልጡ ደጋግመን አድምጠናል። የክፋት ተልዕኳቸውን ዓላማና ዒላማ በአደባባይ የሚያውጁት “የመንግሥት ሽርክና” ያላቸው በሚያስመስል ድፍረትና እብሪት መሆኑን ስናስተውልም ነገረ ሥራው ይደበላለቅብናል። አንዳንዴ የፖለቲካ ኤክሊፕሱ ችግር ይሄና ይህ ነው ብሎ ለማመልከት እንኳ እየተቸገርን መሆኑ የውስብስብነቱን መጠን የሚያለመለክት ነው። የሀገሪቱን መፃኢ ዕድል የሚያጨልሙት ኤክሊፕሶች መደበላለቅም ችግሩ ከውስጥም ከውጭም እንደሆነ ይጠቁመናል።
“ለኪሳራ የጣፈው ቢነግድ አይተርፈው” እያልን የምንተርትለት የሀገሬ ሕዝብ በሸንጋዮች እየተቄለ፣ የክፉ ሴራዎች ተጠቂ እየሆነ እስከ መቼ እንደሚዘልቅ ለመተንበይ አስቸጋሪ እየሆነ የመጣ ይመስለናል። “ነውራቸው ክብራቸው፣ ሆዳቸው አምላካቸው” በሆኑ የእፉኝት ምላስ በተካኑ ግለሰቦችና ቡድኖች እስከ መቼ እየተነደፍን እንደምንኖር ለጊዜው መልሱ እርቆብናል። አርነት የምንወጣበትን ቀን ስናስብም ቀኑ ይረዝምብናል፣ ተስፋችንም ሲቀዘቅዝ ይታወቀናል።
ከሕዝባቸው የተፋቱ የሕዝብ መሪዎች ነን ባዮች “የባዕድነት ድፍረታቸውን” እንኳ ማወቅ እየተሳናቸው ኤክሊፕሳዊ ጥፋታቸውን በነጋ በጠባ ሲፈጽሙ ሃይ ባይ ማጣታችን ጥያቄያችንን እንዲከብድ አድርጎታል። ዓላማቸው ተጣሞ፣ ዒላማቸው ፈሩን ስቶ ነገሮች ሲመሰቃቀሉ እንኳ ሰብዓዊ ህሊናቸውን ከማዳመጥ ይልቅ እንስሳዊ ባህርያቸውን አጉልተው በማውጣት እልቂት ሲደግሱ ጥቂትም ቢሆን አይሰቀጥጣቸውም።
ሕዝቤ እያሉ ሕዝብ የሚነድፉ፣ ትርክት ፈጥረው ነባር ታሪክ የሚንዱ፣ ስለ ዕድገት እየተብከነከኑ የተገነባ የሚያፈርሱ “የቀበሮ ባህታውያንን” እምቢታችንን አጠናክረን በመሞገቱ ብንገፋበት ለእነርሱም ከጥፋት መታደጊያ ለእኛም ፈውሳችንን የሚያቀርብ ይመስለናል።
ሮማዊው ቄሳር ኔሮ (ከ54 – 68 ዓ.ም) የሮም ከተማን አብዛኛውን ክፍል እሳት ለኩሶ ያወደመው እብሪትና ትዕቢት ልቡን ስለደፈነው ብቻ ሳይሆን ከጡንቻው አቅም ጋር ማንም ሊስተካከል እንደማይችል ለማሳየት ጭምር እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ይተርኩልናል። ይህን መሰሉ አረመኔያዊ ድርጊት አልበቃ ብሎትም ብዙ ንፁሃን ዜጎችን በአደባባይ ሲገድልና ለአውሬዎች ሳይቀር አሳልፎ እየሰጣቸው በትዕይንቱ ይደሰት እንደነበር ታሪካዊ መረጃዎች ያረጋግጡልናል።
በሀገሬ ሰማይ ላይ ኤክሊፕስ የሚፈጥሩ የዘመናችን ኔሮዎችም ሕዝቡ በሰላም ውሎ እንዳይገባ፣ የከተሞች የፀጥታ አየር እንዲታወክና እንዲናጋ የሚለኩሱት እሳት ለጊዜው ነበልባሉ ባይታይም ውሎ አድሮ ግን የሚያደርሰው ውድመት በቀላሉ ታይቶ “በይህም ያልፋል ተስፋ” ብቻ የሚታለፍ ሊሆን በፍጹም አይገባም።
የሀገራችንን የለውጥ ተስፋ፣ ዓላማውንና ዒላማውን የሚፈታተኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መንስኤያቸውና መፍትሔው በሕዝብ ምክክር ጥርት ብሎ ስለሚወጣበት ብልሃት ባለ ራዕዮች ሳይዘናጉ ሊያስቡበት ይገባል የማጠቃለያ አስተያየታችን ነው። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012