የዘንድሮ ሀገር አቀፍ ምርጫ ሊካሄድ ወራት ቀርተውታል። የምርጫው ድምጽ መስጫ ወር ግንቦት ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ ቢደረግ ግፋ ቢል ከሁለት ወራት በኋላ የዕጩዎች እና የመራጮች ምዝገባ ሊካሄድ እንደሚችል ይገመታል። የፓርቲዎች ዝግጅት ግን ስለመኖሩ የሚታይ ነገር የለም።
ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ ለማካሄድ ቁርጠኝነቱን ደጋግሞ ከመግለጽ ባሻገር ለምርጫው እየተዘጋጀ ነው ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ የለም። ከምርጫው በፊት ወደአንድ ውሁድ ፓርቲ እንደሚመጣ በገባው ቃል መሠረት በአሁኑ ሰዓት ስለውህደት አብዝቶ እየተጨነቀ ያለበት ወቅት ነው። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም በመደመር ለመተካት ጉዞ የጀመረበት ወቅት ነው። በሌላ በኩል የኢህአዴግ ነባር መስራች የሆነው ህወሓት በግንባሩ ጠቅላላ ጉባዔ አጽድቆ የወጣውን ሀሳብ እንደአዲስ አንስቶ ውህደት በመቃብሬ ላይ ነው ከማለት አልፎ የውህደት ሀሳብ ሀገር ያፈርሳል እስከማለት የዘለቀ የልዩነት ሀሳብን ወደማቀንቀን የተሸጋገረበት ወቅትም ነው።
ይህ የገዥው ፓርቲ የውህደት ሀሳብ ያልተዋጠላቸው፣ ለአንዳንዶቹም የህልውና ስጋት የሆነባቸው አክራሪ የብሔር ሀይሎች ግጭቶችን በየቦታው ከመጫር አልፈው ወደዋና ከተማችን አዲስ አበባ ለማዛመት ያለ የሌለ አቅማቸውን ተጠቅመው እየሰሩ ያሉበት ወቅትም ነው። የሩቁን ትተን ሰሞኑን አንዳንድ ወጣቶች የራሳቸውን አደረጃጀት ፈጥረው በየካ አባዶ አካባቢ የጸጥታ ሀይሉን ስራ ተክተው ፍተሻ ሲያካሂዱ ተስተውለዋል። በወረዳ 19 (ሳሪስ አካባቢ) ኢዜማ የተባለ ፓርቲ ስብሰባ አውከው በሀይል ለመበተን እስከመንቀሳቀስ ደርሰዋል። ስለደረሰ ጉዳት በዝርዝር ባይታወቅም ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ግጭት ፈጥረዋል።
በአጠቃላይ አመረጋጋቱና የሠላም መደፍረስ ችግሮች ይነስም ይብዛም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮች መሆናቸው ብቻውን የመጪው ምርጫ ትልቅ ተግዳሮት አድርጎ መውሰድ ይቻላል።
በቅርቡ ሰባት ያህል የሚደርሱ የኦሮሞ ፓርቲዎች አብሮ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ማድረጋቸው በብዙ ወገኖች ዘንድ በአዎንታ የተወሰደ እርምጃ እንደነበር እናስታውሳለን። ሆኖም ይህ አብሮ የመስራት ስምምነት የዘውግ አደረጃጀትን ወደጎን ትቶ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት በውህደት ላይ ለሚገኘው ኢህአዴግ ምን ትርጉም እንደሚኖረውና የፓርቲዎቹ ቀጣይ ስምምነት ምን ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም። ይህ መሆኑም ስምምነቱ በቀጣዩ ምርጫ ላይ የሚኖረው አንደምታ ከወዲሁ ለመገመት አስቸጋሪ አድርጎታል።
በሌላ በኩል አንዳንድ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች በአመራር ችግር፣ በስያሜ ይገባኛል ሙግት ውስጣቸው እየታመሰ ነው። አንጋፋው ኦነግ እስካሁን በስያሜ ይገባናል ባዮች ውዝግብ ጋር ተያይዞ ስሙን በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ መዝገብ ላይ ማስፈር አልቻለም።
በተጨማሪም የተቀናቃኝ ኃይሉ ካምፕ ኩርፊያ ላይ መሆኑ ይሰማል። በሀገሪቱ ይንቀሳቀሳሉ ተብለው ከሚገመቱ ቁጥራቸው 130 በላይ የሚደርሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ወደ71 የሚጠጉት አዲሱን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ «ጥቅማችንን አላስጠበቀም» በሚል አኩርፈው በያዝነው ወር የረሀብ አድማ ጠርተዋል። የዚህም ጹሑፍም ዋንኛ ትኩረት ይኽው ርዕሰ ጉዳይ ይሆናል።
አድማ ለምን?
አዲስ የጸደቀውን የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ የተቃወሙ 71 ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች በያዝነው ጥቅምት ወር መጨረሻ በአዲስአበባ አራት ኪሎ የድል ሐውልት አደባባይ ላይ የረሀብ አድማ ለማድረግ ቀጠሮ መያዛቸው ተሰምቷል።
«አዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ የህልውናችን አደጋ ሆኗል» የሚሉት ይህንኑ እነዚሁ ፓርቲዎች የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባሳለፍነው መስከረም ወር መጨረሻ ሲከፈት በተቃወሙት አጀንዳ ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚወያይ ከሆነ አድማውን ለመተው አንድ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠውም ነበር። ሆኖም በሕግ አውጪው ፓርላማ በኩል ይህ ማስጠንቀቂያ አዘል ጥያቄ መልስ አለማግኘቱ ቅሬታ አቅራቢዎቹን ክፋኛ ያበሳጨ መስሏል።
የፓርቲዎቹ ቅሬታ መነሻ ሆነው የተሻሻለው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ነው። በዚህ አዋጅ ላይ ያቀረብናቸው የማሻሻያ ሀሳቦች ሆን ተብለው እንዳይካተቱ ተደርገዋል ከሚል ጀምሮ ለሀገር አቀፍ ፓርቲ 10 ሺ የድጋፍ ፊርማ እንዲሰባሰብ፣ ለክልላዊ ፓርቲ 4 ሺ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የሚለው በብርቱ ነቅፈውታል። የጀርመን ድምጽ በቅርብ ፓርቲዎቹ የሰጡትን መግለጫ መነሻ አድርጎ እንደዘገበው በአዲሱ አዋጅ እንደገና ተመዝገቡ መባላቸው ሕልውናቸውን ሊያሳጣ እንደሚችል ፓርቲዎቹ ስጋታቸውን ስለመግለጻቸው ዘግቧል። ከ20 ዓመታት በላይ ሲንገላቱ የነበሩ ፓርቲዎች በአዲሱ አዋጅ መሰረት እንደገና እንዲመዘገቡ ይጠበቃል ያሉት አንድ ፓርቲ አመራር አባል አዋጁ የፓርቲዎችን ሕልውና ያሳጣል በሚል ሞግተዋል።
አዋጁን የማጽደቅ ሒደት ምን ይመስላል
“የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር ረቂቅ አዋጅ” በሚል ስያሜ አዋጅ ቁጥር 1262/2011 ሆኖ በሙሉ ድምፅ የጸደቀው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ነበረ።
አዋጁ በአገሪቱ በየደረጃው የሚደረጉ ምርጫዎች ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆኑ ያስችላል ሲሉ ለምክር ቤቱ የገለጹት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ የሺመቤት ነጋሽ ናቸው። አዋጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን የተለያየ ሐሳብና አመለካከት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ለመራጩ ሕዝብ በተሻለ ደረጃ እንዲያሳውቁ ያስችላል ብለዋል።
መራጩ ሕዝብም በመረጃ ላይ በመመሥረት በነፃነት ወኪሎቹን የሚመርጥበት የምርጫ ሥርዓት ለመዘርጋት ታስቦ መቅረቡን፣ ተሳታፊ ፓርቲዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሚኖራቸውን መብትና ግዴታ በግልጽ የሚያሳይ የምርጫ ሥነ ምግባር እንዲከተሉ የሚያደርግ እንደሆነም ነው የተብራራው።
አዋጁ በዋናነት የምርጫ ሥርዓት፣ የምርጫ አፈጻጸም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሠራረትና አስተዳደር፣ የምርጫ ሥነ ምግባር፣ በምርጫ ሒደት የሚነሱ ክርክሮች የሚዳኙበትንና የሚፈቱበትን የአሠራር ሥርዓት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀናጁበትና እንደአዲስ የሚዋሀዱበትን ዝርዝር የያዘ፣ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት መሆኑ ተብራርቷል።
በተጨማሪም ከዚህ በፊት በስፋት ይስተዋሉ የነበሩ በርካታ ክፍተቶችን በመሙላት፣ በምርጫው ሒደትና ውጤት ላይ የበለጠ ተዓማኒነትን ለመፍጠር የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል። ቋሚ ኮሚቴው አዋጁን ባቀረበበት ወቅት የአዋጁ ስያሜን ጨምሮ በአዋጁ 149 በሚሆኑ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምሥረታ ጀምሮ እስከ መሥራች አባላት ቁጥርድረስ አዳዲስ አሠራሮችን እንዳካተተም ተገልጿል።
በአዲሱ አዋጁ በዋናነት መነጋገሪያና መወዛገቢያ ከሆኑት ድንጋጌዎች ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ ለመመዝገብ የሚያስፈልገው የአባላት ፊርማና የመንግሥት ሠራተኞች በምርጫ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ የተቀመጠላቸው መስፈርት ይገኙበታል። አዋጁ በረቂቅ ደረጃ ሲቀርብ አስቀምጧቸው ከነበሩ ድንጋጌዎች ውስጥ ያከራከረው፣ የመንግሥት ተቀጣሪ ሠራተኞች ለምርጫ ዕጩ ሆነው ለመቅረብ ሲፈልጉ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ ሥራቸውን ያቆማሉ የሚለው ነበር።
ነገር ግን ከፓርላማ አባላት በተደረገ ግፊት ይህ የረቂቁ ድንጋጌ እንዲስተካከል ተደርጎ ነው አዋጁ የፀደቀው። ሐሳቡ በግልም ሆነ በተቃዋሚና በገዥው ፓርቲ በኩል በዕጩነት የሚቀርቡ ተመራጮች የምርጫ ምዝገባ ተጀምሮ ምርጫው እስከሚካሄድበት ዕለት፣ ከመንግሥት ሥራቸው ተነስተው ያለ ደመወዝ እንዲቆዩ የሚያስገድድ ነበር።
ነገር ግን ጉዳዩ የፓርላማ አባላቱንም ሆነ ሌሎች የመንግሥት ሹሞች እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ለምርጫው ሲባል ሥራቸውን ይለቃሉ የሚል መንፈስ ስለነበረው ነው በኋላ ማስተካከያ የተደረገለት። ረቂቅ ድንጋጌው የተካተተበት ዋና ዓላማም ዕጩዎች በመንግሥት ሀብት የምርጫ እንቅስቃሴያቸውን እንዳያስፈጽሙ የሚል ነበር። በእርግጥ የረቂቁ ድንጋጌ በቀጥታ ቢያልፍ ኖሮ የገዥው ፓርቲ ተወካይ ዕጩዎች ነበሩ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት የሚሉ አሉ። ምክንያቱም ደግሞ በመንግሥት ሥራ ውስጥ የገዥው ፓርቲ አባላት ብዛት አላቸው የሚሉ ባለሙያዎች አሉ። ይህ ድንጋጌ አሁን በፀደቀው አዋጅ መሠረት፣ ‹‹የመንግሥት ሠራተኛ›› የሚለውን ለአዲስ ትርጓሜ አስቀምጦታል።
በአዲሱ ትርጓሜ መሠረት የመንግሥት ሠራተኛ ማለት በፌዴራል ወይም ለክልል መንግሥት በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሠራ ሲሆን ሚኒስትሮችን፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችን፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ደረጃና ከዚያ በላይ የሆኑ ተሿሚዎችን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና በየደረጃው ያሉ የክልል ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን ያካትታል።
በቀዳሚው ረቂቅ ትርጓሜ፣ ‹‹የመንግሥት ሠራተኛ . . .›› ይለቃል የሚለውን ከፍተኛ ባለሥልጣን ቢባል ‹‹ያለ ድምፅ ይሠራል›› በሚል ተክቶታል። ይህ ማሻሻያ ደግሞ ለአንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች የተለየ ዕይታ ሰጥቷቸዋል። አንድ የሕግ ባለሙያ እንዳስረዱት፤ ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ በምርጫ ወቅት እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ ያሳያል ብለዋል። ይህንንም ሲያብራሩ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ኢሕአዴግ ከአሥር በላይ የሚሆኑ የራሱን የምክር ቤት አባላት ነው የሚያወዳድረው። እነዚህን አባላት የትምህርት ደረጃ ከማስትሬት በላይ እንዲሆኑ በማገዝ እነሱኑ ነው የሚያወዳድረው። በዚህም መሠረት በዚህ ምርጫም በአብዛኛው እነዚሁኑ አባላት እንደሚያወዳድር ይጠበቃል ብለዋል።
ስለዚህ እነዚህን የምክር ቤት አባላት ያለ ደመወዝ በመጪው ምርጫ ሊያወዳድር የሚችል ሲሆን፤ በራሱ ላይ ብዙም ጫና እንደማይኖርበት ገልጸዋል። ይህ ማለት ደግሞ ኢሕአዴግ ለስድስት ወራት ደመወዝ ባይከፈለው ዕጩ የሚሆን አባል ስለማያጣ፣ በሌላ በኩል ኢሕአዴግ ለፓርላማ ወንበር ለሚወዳደሩ 547 አባላቱ ደመወዝ አይከፍልም ማለት ነው ይላሉ።
ይህ ድንጋጌ በአንፃሩ በተቃዋሚዎች ላይ ጫና መፍጠሩ እንደማይቀር ይናገራሉ። እንዲያውም የማድከሚያ መንገድ ሊሆን እንደሚችልም ባለሙያው ይገምታሉ። ከዚህ አንፃር አዲሱ አዋጅ ለኢሕአዴግ ሊጠቅም እንደሚችልም ባለሙያው ይገምታሉ። ለዚህ ደግሞ ማጠናከሪያ ተጨማሪ ሐሳብ ከአዋጁ ድንጋጌዎች የተገለጹትን በመጥቀስ አስረድተዋል። ለአብነት በማንኛውም ዕጩ ተወዳዳሪ በዕጩነት ለመመዝገብ ከሚወዳደርበት የምርጫ አካባቢ በበፊቱ ሕግ መሠረት እንዲያሰባስብ የተቀመጠው የድጋፍ ፊርማ ቁጥር፣ ለተቃዋሚዎች ከባድ እንደሚሆን ይገልጻሉ።
ኢሕአዴግ ግን ቢያንስ እስከ ስምንት ሚሊዮን የሚደርሱ አባላት ስላሉት፣ ከመራጮች ፊርማ ለማሰባሰብ ችግር የለበትም። ከእነዚህ ጉዳዮች አንፃር ነው አዲሱ አዋጅ ለኢሕአዴግ ያደላል የሚል መከራከሪያ የሚነሳው።
የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የፓርቲዎች ተቃውሞ አስመልክተው እንዲህ ይላሉ። «ብዙ ፓርቲዎች እንደገና ስለተከለሰው የሕጉ ክፍል አይናገሩም። ሁሉም አቤቱታቸው በፓርቲዎች ምዝገባ ጉዳይ ነው። ሕጉ ውስጥ የተቀየረውንና የተሻሻለውን ነገር ማየት አይፈልጉም:: 10 ሺህ ፊርማ የሚለውን ብቻ ነው የሚያነሱት። እኛ ይሄንን በጣም ዝቅተኛ መስፈርት ነው ብለን ነው የምናምነው። በሌላ በኩል፤ በርካታ የቀረቡ የማሻሻያ ሀሳቦች በሕጉ ተካተዋል። ይሄን ግን ፓርቲዎቹ አይጠቅሱም። ሁሉም የጋራ ም/ቤቱ አባል ፓርቲዎች ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። በርካታ ሀሳቦቻቸውም ተቀባይነት አግኝቶ በሕጉ ተካቷል። እነሱ የሚያነሱት ግን አንድ ሁለት ጉዳዮችን ነው።»
«ሕጉ በጥድፊያ ነው የፀደቀው የሚል ቅሬታም ይደመጣል?» በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም
«ሂደቱ ስምንት ወር ነው የፈጀው። ጥናት ተደርጎ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ተካሂዶ፣ የመጀመሪያው ረቂቅ ፓርላማ ገብቶ፣ እነሱም ለሁለት ጊዜያት በተገኙበት ውይይት ተደርጐ፣ በድጋሚ ግብአቶች ተጨምሮበትና ማሻሻያዎች ታክሎበት ነው የፀደቀው። እንደውም ረጅም ጊዜ የወሰደ ሂደት ነው። ይሄን ሕግ ተከትሎ ገና 40 ያህል መመሪያዎች እንደሚወጡ ፍንጭ ሰጥተዋል።
እንደማሳረጊያ
እንግዲህ አሉ ከሚባሉት 130 በላይ ፓርቲዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በዚህ የምርጫ ዓመት ከጸደቀ ገና የወራት ዕድሜ ያለው አዋጅ እንዲሻሻል ከፍተኛ ግፊት ለማድረግ እየጣሩ ነው። በሌላ በኩል የ2012 ቱ ምርጫ ጊዜ እየገሰገሰ መጥቶ በቀጥታ ወደሒደቱ ለመግባት ከሶስት ወራት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል።
ገዥው ፓርቲም ውስጣዊ ቀውሱን ፈትቶ፣ የውህደት ሀሳቡን አሳክቶ ፊቱን ሙሉ በሙሉ ወደምርጫ ሥራ የሚያዞርበት ቁመና ላይ አለመሆኑ የሚታይ ነው። የሠላምና መረጋጋት ተገማች አለመሆን ድምር ውጤቶች በቀጣዩ ምርጫ አፈጻጸም እንዲሁም ተአማኒነት ላይ የራሳቸው የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳርፉ እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ከእውነታው አያርቅም።
(ማጣቀሻዎች፡- የምርጫ ቦርድ ድረገጽ፣ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ፣ ሪፖርተር፣ አዲስ አድማስ፣ ጀርመን ድምጽ…)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012