የሥልጣኔ አሀዱ፣ የአልበገርነት፣ የጀግንነትና ነጻነት ተምሳሌትና የአፍሪካ ፈርጥ የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ እንደ አበባ በፈኩና ህብርን በተላበሱ ልጆችዋ ታፍራ፣ ተከብራና መመኪያቸው ሆና ዘመናትን አሳልፋለች። በልዩነት ያሸበረቁት ልጆቿ የባህል፣ የሃይማኖትና የቋንቋ ወዘተ ልዩነት ሳይገድባቸው ተዋደውና ተፋቅረው ብዙ ሺህ ዓመታትን ኖረዋል፤ እየኖሩም ነው።
አገራችን በሁሉም መልክ የታደለች ስለመሆኗ ምስክር አያሻም። ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ቅርሶቿ፣ የከርሰ ምድርና የገጸምድር የውሃ ሀብቷ፣ ለሰብልና ለእንስሳት እርባታ ምቹ የሆነው አየሯና መሬቷ፣ በአብዛኛው ወጣት የሆነውና ለሥራ የሚተጋ የሰው ኃይሏ፣ ተዝቆ የማያልቅ የተፈጥሮ ማዕድኗ ወዘተ አገራችን የተባረከችና የተቀደሰች ብሎም ያለምንም ማጋነን ከራሷ አልፋ ለዓለም የምትተርፍ አገር ስለመሆኗ የሚመሰክሩ ህያዋን ምስክሮች ናቸው።
ኢትዮጵያዊነት በሚባል የአንድነት ገመድ የተጋመዱት ብሄር ብሄረሰቦቿ በአንድነት በመቆም ደማቅ እና የጋራ ታሪኮችን መጻፋቸውም የታሪክ ድርሳናት መዝግበው ያስቀመጡት ደማቅ ታሪካችን ነው። አድዋ፣ ዶጋሊ፣ መተማ፣ ባድመ እና ዛላንበሳ ኢትዮጵያውያን ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ ደማቸውን አፍስሰውና መተኪያ የሌላትን ህይወታቸውን ሰውተው የምንኮራባትን አገር ያስረከቡባቸው የታሪክ አውዶች ናቸው።
እኛ ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም የዚህን ያህል የምንኮራባቸውን ወርቃማ ድሎች ያሉንን ያህል አንገት የሚያስደፉ ጭቆናዎችና በደሎችም በህዝባችን ላይ ተጭነው ለዘመናት የመከራን ዳገት ስንገፋ መኖራችን አሌ የማይባል ሀቅ ነው። እገሌ ከእገሌ ሳይባል መላ ህዝባችን የፊውዳሎችና አምባገነኖች አንገፍጋፊ በደልና ጭቆና ተሸክሞ በድህነትና እጅግ በሚያሳዝን ህይወት ሲገፋ መኖሩም የአደባባይ ሀቅ ነው።
በጭቁን ህዝቦች የጋራ ትግል አምባገነናዊው ሥርዓት ተወግዶ በአገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓት ከሰፈነ በኋላ በሀገራችን በብዙ መስክ መሻሻሎች ቢታዩም የህዝቦች ጥያቄ ግን በሚፈለገው ደረጃ ሳይመለስ ቆይቷል። በስመ ፌዴራሊዝም ይታዩ የነበሩ ዓይን ያወጡ ጣልቃ ገብነቶች፣ እጅግ አነገፍጋፊ ሙስናና ኢፍትሃዊነት ህዝቦችን አንገሽግሾ አሁን የመጣውን የለውጥ ኃይል ወልዷል።
የለውጥ አመራሩ ፈር ቀዳጅና የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድም እስካሁን የተከማቹ ችግሮችን ለመቅረፍና ለመጪው ትውልድ የተሻለች አገር ለማውረስ የሚያስችለውን መደመር የተባለ ፍልስፍና አዘል መጽሐፍ በትናንትናው ዕለት ለአገርና ለህዝብ አበርክተዋል። የመደመር እሳቤ መነሻ ዓላማ ለአገር በቅል ችግር አገር በቀል መፍትሄ እንዲሆን ማለት ነው። በሌላ አነጋገር መደመር የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ እንደማለት ነው።
የመደመር ፍልስፍና በአገራችን ኢትዮጵያ ያሉ መልካም የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ጠብቆ ማስፋት እንዲሁም የተሰሩ ስህተቶችን ማከም፣ ማረምና እርምጃ መውሰድ በጣም አስፈላጊ ነገሮች መሆናቸውን የሚያትት ሲሆን ህብረ ብሄራዊ አንድነት፣ የዜጎች ክብርና ብልጽግና የመደመር ግቦች እንደሆኑም ያስቀምጣል። የሚፈጠረው አገራዊ አንድነትም የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት፣ ባህልና ቋንቋ እንደጸጋ የሚውስድ እንጂ የሚደፈጥጥ እንዳልሆነ ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል።
ከዚህም በላይ ዜጎች በአገራቸውም ሆነ በውጭ አገር ክብራቸው ተጠብቆ መኖር እንደሚገባቸው አጽንኦት ይሰጣል። የመቆራቆዝና የመነቋቆር ምንጩ ድህነት ነው ብሎ በማመንም ይሄ የሚወገደው ብልጽግናን በማስፈን እንደሆነ ያመላክታል። ዋልታ ረገጥነት፣ አቅላይነት፣ ጊዜ ታካኪነት፣ ሙያን መናቅና እንቢተኝነት የመደመር ተግዳሮቶች መሆናቸውንም ይገልጻል።
የኢትዮጵያ ትልቁ የፖለቲካ ስብራት ጭቆና ነው ብሎ የሚያስቀምጠው ፍልስፍናው መፍትሄው ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት መሆኑንም ያስቀምጣል። ለፖለቲካ ሳይሆን ለአመራር ብቃት ትኩረት የሚሰጠው ይህ እሳቤ ብቃትና ውክልናን አመጣጥኖ መምራት ተገቢ መሆኑንም ያሰምርበታል።
እንደከዚህ ቀደሙ ከአንድ ቦታ በሚመነጭ ሳይሆን ተቋማት ባህሪያቸውን ያማከለ ሪፎርም ማድረግ እንዳለባቸውም ይመክራል። ከኢኮኖሚ ዕይታም አንጻር መደመር ዛሬ ላይ ያለንን መሰብሰብ ትናንት ከነበረው በጎ ሥራ በማከማቸትና በማካበት ሥርዓት ማስያዝ በሚሉ ቁልፍ መርሆዎች ይመራል። በዚህም ያለፉትን ጊዜያት ድሎች ጠብቆ ማስፋት፣ ስህተቶችን ያለምህረት ነቅሶ ማረም፣ የመጻኢውን ትውልድ ዕድል ስኬታማና ብሩህ ማድረግን እንደ መርህ የሚወስድ ነው።
በአጠቃላይ መደመር ከአገር ልጅ አዕምሮ የፈለቀ፣ አገራዊ ችግሮችን በሚገባ የዳሰሰ ያለፉትን ጥንካሬዎችና ድክመቶች ያመዛዘነ መድረስ የሚገባውን ርቀት አሻግሮ የተመለከተ ከምንም ነገር ቅድሚያ ለዜጎች ክብር የሚሰጥ በአጠቃላይ አገራችንን ከያዛት ቆፈን ማላቀቅን ያለመ መጽሐፍ ነውና ማንበብ ሃሳብ መጨመርና መተግበር ከህዝባችን የሚጠበቅ ቁልፍ ጉዳይ ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012