ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች፡፡ የለውጡ ማጠንጠኛ ዋነኛ መሰረት ደግሞ የመደመር እሳቤ ነው፡፡ ይህ የመደመር እሳቤ ደግሞ በሀገሪቱ ቀደም ሲል የነበሩ መልካም የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እድሎችን ጠብቆ ማስፋት፤ ባለፉት ዘመናት የተሰሩ ስህተቶችን ማረምና የመጪውን ትውልድ ፍላጎትና ጥቅም ማስከበር ላይ ያተኮሩ ሶስት ዋነኛ ሀገራዊ ዓላማዎች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
እነዚህ የመደመር ዕሳቤዎች ከተሳኩ ደግሞ የኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት ይጠበቃል፤ የህዝቦችዋ ክብር ከፍ ይላል፤ ሀገራዊ ብልጽግናም ይረጋገጣል፡፡ ስለሆነም 2012 ዓ.ም እነዚህ አጓጊ ሀገራዊ ርዕዮች እንዲሳኩ መሰረት የሚጣልበት ዓመት እንደሚሆን የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በቅርቡ በተካሄደው የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ2012 በጀት ዓመት የጋራ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
ይህ የመደመር ዕሳቤ ዘወትር እንደሚደረገው መንግስታት በተቀየሩ ቁጥር አፍርሶ እንደገና ከዜሮ ከመጀመር አባዜ የሚያላቅቀን መስመር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ የተገነባች ወይም በየዘመናቱ የሚመጡ መሪዎች እያፈረሱ የሚገነቧት ሀገር አይደለችም፡፡ በሺ ዓመታት ሂደት ውስጥ ያከማቸናቸውና ለዛሬና ለነገ የሚጠቅሙን መነሻ ሀብቶች ያሉን ህዝቦች ነን፡፡
እነዚህን የጋራ ሀብቶች እንደሌሉ ቆጥሮ ከዜሮ መጀመሩ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ስለሆነም ባለን ላይ እየደመርን የጎደለንን በአዲስ መልክ እየፈለግን ሀገራችንን ከብልጽግና ማማ ላይ ማድረስ የሁላችንም ግዴታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዘንድሮ የምንጀምረው ለነገ የማናሳደርው የቤት ስራችን ነው፡፡
በሌላ በኩል ያለ ፍንባቸው የታሪክ ምዕራፎች መልካም ጸጋዎች እንዳሉት ሁሉ በርካታ ስህተቶችም አሉት። የእኩልነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መጓደል፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የመ ሳሰሉት የታሪካችን አካል የነበሩና ቶሎ ልናርማቸው የሚ ገቡን ጉድለቶቻችን ናቸው። እዚህ የታሪክ ጉድለ ቶቻችንን ከመሸፋፈን ይልቅ የእኛው አካላት እንደነበሩ አምነን ዛሬም ሆነ ነገ እንዳይደገሙ አበክሮ መስራቱ ላይ መጠንከር ይገባናል፡፡ ይሄኛውም ዘንድሮ የምንጀምረው ለነገ የማናሳድረው የሁላችንም የቤት ስራ ነው።
መልካም ስራዎቻችንን ይዘን ያጋጠሙንን ችግሮች አርመን የምንጓዝበት ዋነኛ ዓላማም ለመጪው ትውልድ የበለጸገችና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለማውረስ ነው፡፡ ስለሆነም ወጣቱን ትውልድ በልማቱም ሆነ በዴሞክራሲው መስክ ማሳተፍ ሀገርን ለመረከብ ዝግጁ የሆነ ወጣትን ለመፍጠር ያስችላል።
ይህም ዘንድሮ የምንጀምረውና ለነገ የማንተወው የቤት ስራችን ነው። ይህንን የቤት ስራችንን በአግባቡ ለመወጣትም የትላንቱን ሰንቀን የነገውን አቅደን ወደፊት እንራመድ፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 8/2012