በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተፃፈው “መደመር” የተሰኘው መፅሃፍ ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለምረቃ ይበቃል ።
የመፅሃፉ ምረቃም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ አዲስ አበባን ጨምሮ በ20 ከተሞች በዛሬው ዕለት ይከናወናል። በዋናነትም በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ አሶሳ፣ ጅግጅጋ፣ ሰመራ እና ሀረር ከተሞች ይመረቃል።
ይህ መፅሃፍ በተለያዩ በአማርኛ፤ኦሮሚኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን፥ 1 ሚሊየን ቅጂዎችም ታትመዋል።የመፅሃፉ ዋጋ 300 ብር ሲሆን፥ ገቢውም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት ይውላል ነው የተባለው።
ከሀገር ውስጥ ምረቃ በኋላም በውጭ ሀገራት በአሜሪካ እና ኬንያ በተለይም በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ሚኒሶታ እና ናይሮቢ የምረቃ ስነ ስርዓቱ የሚከናወን ይሆናል።‹‹መደመር› የተሰኘው ይህ መጽሐፍ የትናንት፣ የዛሬንና የነገን የኢትዮጵያ ጉዳዮች በወጉ መመልከት እና የተሻለ መስራት የሚያስችሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የዳሰሰ ስለመሆኑም ተነግሯል።
ይህ መጽሐፍ የመደመር እሳቤን በአራት መሠረታዊ ጉዳዮች አካቶ የያዘ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ክፍል መደመርን ከሰዋዊ ባህሪና ፍላጎት አንጻር የሚመለከት ነው። ሁለተኛው ጉዳይ መደመርን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ አንጻር የሚመለከት ሲሆን፤ ሦስተኛው ክፍል መደመርን ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አኳያ እንዲሁም አራተኛው ክፍል መደመርን ከኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አንጻር የሚያብራራ ነው። በዚህም መደመር ከእነዚህ አራት ነገሮች አንጻር ትናንትን የተመለከተ፣ ዛሬን ያሳየና ስለነገ የመፍትሄ አቅጣጫና የጉዞ አማራጭ ያስቀመጠ ነው።
መደመር ከሰዋዊ ባህሪና ፍላጎት አንጻር ሲታይ፤ የሰውን ልጅ ፍላጎትና ምኞት ከቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ፍላጎቶቹ አኳያ ተመልክቶ እነዚህ ፍላጎቶች እንዴት ተጣጥመው መሄድ እንዳለባቸው፤ ባህሪዎቹም መጥፎ ወይም መልካምነታቸው ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ አመላክቷል። በመሆኑም የመደመር እሳቤ ትናንት የነበረውን በመሰብሰብ፣ ዛሬ ያለውን በማከማቸትና ለነገ በማካበት ስሌት የተቃኘ ነው።
በተለይም እስካሁን ያሉ መልካም የፖለቲካና ኢኮኖሚ ድሎችን ማስቀጠል፣ የተሰሩ ስህተቶችን ማረምና ማከም፣ እንዲሁም የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት ማሳካት ቀዳሚ መርሁ ነው። ይህ ደግሞ የብቸኝነት ጉድለትን ሞልቶና ያለን አገራዊ ወረት ደምሮ ወደ ምሉዕነት በማምጣት፤ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር፣ የዜጎችን ክብር ማስጠበቅ እና ብልጽግናን ማምጣት ግቡ አድርጓል።
መደመር ከፖለቲካዊ ገጽታው አኳያ ደግሞ፣ ያሉና የነበሩ አገራዊና ዓለማቀፋዊ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞችንና ፍልስፍናዎችን የቃኘ ሲሆን፤ ብልጽግና የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካም ሆነ በማህበራዊ መስኩ የሚመጣ ለውጥ ጭምር እንደሆነ ያስቀምጣል።
በተለይ ጭቆና (ሰው ወለድ/ ቀጥተኛ እና መዋቅራዊ ጭቆና) ትልቁ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስብራት እንደሆነ ስለሚያምን፤ ጠንካራ ተቋማትንና አቅም ያለው አመራር መፍጠር፣ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር፣ ያልተማከለ ሪፎርም እና ዴሞክራሲያዊ ባህል መገንባት የቀጣይ ሥራዎች ጉዞ አካል ስለመሆናቸው ያስቀምጣል።
በኢኮኖሚው መስክም ቢሆን፤ በእስካሁን ጉዞው ኢኮኖሚው ያስገኘውን ወረት እና ቁልፍ ሳንካዎች በመለየት ጤናማ በሆነ ትብብርና ፉክክር ላይ ተመስርቶ መራመድ አስፈላጊ መሆኑን ያስቀምጣል።
በተለይም የሚታዩ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግር እና የማህበራዊ ኢኮኖሚ መዛባትን መፍታት በሚያስችል መልኩ ከሥራ እድል ፈጠራና ዋጋ ንረት ጋር የተያያዙ ውዝፍ ሥራዎችን ይዞ የሚሰራበትን አቅጣጫ ያስቀምጣል። የመጨረሻ ግቡም ሁሉን አቀፍ ብልጽግና አድርጎ የመዳረሻ መስመሮቹንም አመላክቷል።
ከውጭ ግንኙነት አኳያም የእስካሁኑን ጉዞ በመዳሰስ የቀጣይ የትብብርና ግንኙነት አቅጣጫ መሰረቶችን አስቀምጧል። በዚህም የመደመር እሳቤ እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ ጤናማ ፉክክርና ትብብር ላይ ተመስርቶ የሚጓዝ ይሆናል። ለዚህም፣ ያሉ አገራዊ ወረቶችን ማጉላት፣ መግባባትና ትብብርን ማስቀደም፣ ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም፣ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ መስጠት፣ ብሔራዊ እና የዜጎች ክብርን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሰራ ይሆናል። በጥቅሉ የመደመር የውጭ ግንኙነት ገጽታ ሙሉ እይታን፣ መሰናኘትን፣ ግንባታን፣ ሚዛንን፣ ተባብሮ መኖርን እና ሥርዓት መፍጠርን እንደ አምድ ይዞ የሚከወን ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 8/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር