ሰው በመጠጥ ብቻ አይሰክርም። ብዙ አይነት ስካር አለ። ለምሳሌ ደስታ፣ ንዴትና የበቀል ስሜት ከልክ ሲያልፉ ያሰክራሉ። ሁሉም አይነት ስካር ወደ ውስጥ ባስገባነው ነገር ልክ ይገለፃል። ታዲያ የትኛውም አይነት ስካር ማስተዋልን ያስጥላል። እዚህም እዚያም ያስረግጣል።
ስካርን በሚበይን መግቢያ ለመግባት የመረጥኩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማት በማግኘታቸው በንዴት የጦፉ አላዋቂዎች የሰከረ ሀሳባቸውን በየሚዲያው ሲረጩ ተመልክቼ ነው።
ኒዮስቶ የተባሉት የኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴ ጸሐፊ ከኦስሎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልክ ደውለው “የዚህን ዓመት የኖቤል የሰላም ሽልማት በማሸነፍዎ እንኳን ደስ አለዎት ማለት እፈልጋለሁ” አሏቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም “በጣም ነው የማመሰግነው ዜናውን ስሰማ እጅግ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ይህ ለአፍሪካ፣ ለኢትዮጵያ የተሰጠ ሽልማት ነው። በአህጉራችን የሰላም ግንባታውን ለማስቀጠል የተቀሩት የአፍሪካ መሪዎች ይህን ሽልማት በአዎንታዊ መልኩ እንደሚወስዱት ተስፋ አደርጋለሁ። በጣም ደስ ብሎኛል አመሰግናለሁ።” አሉ።
ይህን ክስተት ተከትሎ አያሌ የዓለም የዜና አውታሮች ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ አገራትና ታዋቂ ግለሰቦች በሽልማቱ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ። ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ድክመቶች በመዘርዘርና ሽልማቱን ግላዊ በማድረግ እንደማይገባቸው በመናገር ተጠመዱ።
የአትላንታው አድማስ ሬዲዬ ጋዜጠኛ ቴድሮስ ዳኜ ‹‹ሚስቱን በመደብደብ የሚታወቅ ሳይንቲስት ነገ የኤድስ ቫይረስን በአንድ ቀን የሚያጠፋ መድኃኒት ሰርቶ የኖቤል ሽልማት ሊያገኝ ይችላል። ሽልማቱ ለመድኃኒቱ እንጂ ለድብደባው አይደለም። ባገኘው የምርምር ውጤትና ሽልማት አወድሰነው ፣ ሚስቱን በመደብደቡ ግን እንቃወመው ›› የሚል ሀሳብ ሰንዝሮ ነበር ።
ጥሩ ያልሆነን ነገር ስንተች ሰሚ የምናገኘው ፣ ጥሩ የሆነውን ስንደግፍ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከ20 በላይ ዓለምአቀፍ ሽልማቶችን አግኝተዋል። እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሸለሙት ተሳስተው ከሆነ ሰውዬው በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በመሸወዳቸው ሌላ ሽልማት ይገባቸዋል።
ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ተደማጭነት እንዲጨምር ያደርጋል። እስካሁን ከሆነውና እየሆነ ካለው በላይ ለአገሪቱ ቀጣይ ጉዞ የሚኖረው አስተዋጽኦ ያመዝናል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ሰው የተሸላሚውን ምላሽ አስመልክተው ለቪኦኤ ሲናገሩ “ሽልማቱን እንደ እዳና ለህዝብ ፣ ለአገርና ለዓለም ሰላምና አንድነት ብዙ ነገር ለመስራት እንደተከፈለ ቀብድ ነው የቆጠሩት” ማለታቸው ይህን ያስረዳል።
አንዳንዶችም ሽልማቱ የተበረከተው ለአገራቸውና ለህዝባቸው ጭምር መሆኑን በመዘንጋት ሊያቃልሉት ሞክረዋል። አንዳንድ አገራዊ ሚዲያዎች ኢትዮጵያዊ መሪ በዓለም መድረክ ታላቅ የሆነውን የኖቤል የሰላም ሽልማትን ማሸነፉን ለመዘገብ ተጠይፈዋል። ለነገሩ እነዚህ ሚዲያዎች የተቋቋሙበት ዓላማ እንዲህ እንዳሁኑ ዓለም ያደነቀውንና ፀሐይ የሞቀውን ነገር ለመዘገብ ሳይሆን ‹‹የተደበቀን›› ና ያልተፈጠረን ነገር አጉልቶ ለህዝብ ለማቅረብ ነው። ብዙ ልፋትንና በጀትን የሚጠይቅ ፤ የዚያኑ ያህልም ረብጣ ዶላር የሚያሳቅፍ የዘመኑ ሥራ ይህ ነው። የተፈጠረን ክስተት ምንጭ ጠቅሶ መዘገብማ የአማተሮች ተግባር ነው።
ታዲያ የእንጀራ ጉዳይ ሆኖባቸው እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠልተው አይደለም። ኧረ እንደውም ለጉድ ነው የሚወዷቸው። አለ አይደል አንዳንዴ እኮ ፍቅር በዝምታ ይገለጻል። ባለቅኔው መንግስቱ ለማ በአንድ ግጥማቸው ግሩም አድርገው እንደገለጹት …
በቃል ወይ በስራ ፍቅር አይገለጽም፤
ይሻላል መሰለኝ እንዲያው ዝም
እንዲያው ዝም …
ወድሻለሁ ማለት አይጠቅም አይበቃ፤
ፍቅሬ ነሽ ማለትም አይጠቅም አይበቃ፤
ነፍሴ ነሽ ማለትም ልቤን አያርሰው፤
የፍቅራችን ነገር ዝም ነው ዝም ነው።
…ብለው ይመስለኛል ዝምታን የመረጡት።
በቅርቡ ታዳጊዋ ገጣሚ በቤተ መንግስት የወረወረቻቸው ስንኞች በሬክተር ስኬል ለመለካት የደረሰ መንቀጥቀጥ ከፈጠሩ በኋላ የግጥምን ምትሃታዊ ኃይል ይበልጥ ተረድቻለሁ። ስለዚህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሸለም ያዙኝ ልቀቁኝ ያሉትን አንድ አንጋፋ ፖለቲከኛ ሁናቴ በአንጋፋ ገጣሚያን ቅንጭብ ስንኞች መቃኘቴን እቀጥላለው።
እኒህ “አንቱታን” ያተረፉ አንጋፋ
ፖለቲከኛ
ይመራል ይላሉ ኮሶ መጠጣት፤
ይመራል ይላሉ ግራዋና ሬት ፤
እሱስ የሚመረው ወርዶ (ከስልጣን) መለየት። እያሉ ህዝባዊ ግጥሙን ከወረደባቸው ዱብ ዕዳ ጋር አዋህደው በካሳ ተሰማ ዜማ ሲቆዝሙ ከርመዋል። ይህ አልበቃ ብሏቸው የአረጋሽ ሰይፉን ስንኞች ተውሰው …
ለክንዴ አምባር አልል ፣ ወለባ ለጸጉሬ ፤
ማርዳ ድሪ ለጌጥ ፣ አልቦ አልሻም ለግሬ ፤
አልቻለም ደሞዜ ዕቁቤን ጨምሮ፤
አምናን እገዛበት ፣ ቀርቶብኝ ዘንድሮ። ሲሉ ተመኝተዋል።
በኋላም አኩርፈው ከመሸጉበት
ሆነው …
ተጣልተን ተኳርፈን ፤
ተኳርፈን ተቋርጠን፤
ሴጣን ነህ ብለሽኝ፤
አትረቢም ብዬ ፤
አንጎራጉራለሁ አፍዝዞኝ ስቃዬ ፤
አንቺ ደጅ አንቺ ደጅ አንቺ ደጅ
አንቺዬ …
እያሉ ስለ አራት ኪሎ አንጎራጉረዋል።
እኒህ ሰው ሰሞኑን የኖቤል የሰላም ሽልማትን ተከትሎ ከጉሮኗቸው ብቅ ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩን በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቃባይነት የሌላቸውና አክብሮት የማይቸራቸው አድርገው በማቅረብ ሽልማቱ እንደማይገባቸው በመግለጽ ስቃያቸውን አንጎራጉረዋል። እርሳቸውና ቡድናቸው ለሶስት አሥርት ዓመታት በተጠጋ የስልጣን ዘመናቸው ማሳካት ቀርቶ ማሰብ ያልቻሉት ኖቤል ከጉያቸው በወጣ ብላቴና እጅ ሲገባ በደስታ መስከራቸው አያስገርምም። በስካር መንፈስ በሚነገር ነገር መቀየም ደግ አይደለምና አፉ ብያቸዋለሁ። አንዳንዶች ግን በንግግራቸው በሽቀው ለቀናት ርዕሰ ጉዳይ ሲያደርጓቸው ተመልክቻለሁ። እነዚህ ሰዎች የዘነጉት አንድ ነገር አለ። አንጋፋው ፖቲከኛ ከንግግሩ በኋላ ሆቴላቸው ገብተው የጌትነት እንየውን ስንኞች በመዋስ …..
ባዶ ቤት በክረምት
አንች የሌለሽበት
ዝም ጸጥ ብቻ
ሆቴል መጫወቻ።
ጠረንጴዛ ፣ ወንበር
አንድ አልጋ አንድ በር … እያሉ የብቸኝነት እንጉርጉሯቸውን ነው የቀጠሉት።
ጥቂቶች ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተበረከተው ሽልማት ከአቅማቸው በላይ የሆነ ጫና አሳድሮባቸው ተጭኖ ይደፈጥጣቸዋል ብለው ተስፋ በማድረግ የምላስ ሰይፋቸውን በመምዘዝ የታገል ሰይፉን ስንኞች በመዋስ …
ከፍ በል ወደላይ፤
ከስልጣኑ ሰማይ፤
ከስም አደባባይ፤
በሀብት ከፍ ከፍ፤
በሹመት ከፍ ከፍ፤
ከፍ ! ከፍ !
ከፍ ! ከፍ !
ከዚያ የወደቅክ ለት
አጥንትህ እንዳይተርፍ።
ብለዋቸዋል።
እኔ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩን “የጀመርነውን ጨርሰን ሪባን እንቆርጣለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም” ንግግር ሰምተው ከነብይ መኮንን ጋር ሆነው
ብዙ ካየን ወዲያ ምን ያጠያይቃል ፣
ተስፋ ለመቁረጥም ተስፋ ያስፈልጋል። … ከሚሉት ወገን ነኝ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 5/2012
የትናየት ፈሩ