እንደምን ሰነበታችሁ ውድ አንባብያን? በዓል እንዴት ነበር? አለፈ አይደል? ከዚህ ቀጥዬ “እንኳን አደረሳችሁ” ለማለት እወዳለሁ፡፡ ምነው ወዳጄ በሰላም ነው “ለየትኛው በዓል ነው እንኳን አደረሳችሁ የምትለን በዓሉ እኮ አለፈ” እንዳትሉኝ፡፡ ለዘመን መለወጫ እና ለመስቀል በዓል ነው እንኳን አደረሳችሁ ያልኳችሁ። አዎ ከአንድ ወር በፊት ላከበርነው የዘመን መለወጫ በዓልና ከተከበረ አስራ ስምንት ቀን ለሞላው ላለፈው የመስቀል በዓል ነው እንኳን አደረሳችሁ ያልኳችሁ፡፡ ለምን ካላችሁኝ በፓርላማው ሰዓት መቁጠር ጀምሬያለሁ ምክንያቱም ደግሞ ሙያዬን ቀይሬ በቅርቡ የማስታወቂያ ባለሙያ ሆኛለሁና፡፡ አሁን ምን ለማለት ፈልጌ እንደሆነ የገባችሁ ይመስለኛል፡፡ እናም እላችኋለሁ “እንኳን ለ2012 የመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ”፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ነጻነት ሞልቶ በፈሰሰባት በዚች በእኛዋ “ዲሞክራሲያዊት” አገር ሕግና ሥርዓት የሚባል ነገር የለም፣ ተፈጥሯዊው የጊዜ ሕግ እንኳን አይገዛህም፡፡ እናም ለምሳሌ የማስታወቂያ “ባለሙያ” ከሆንክ ገና ለሚመጣ በዓል ብቻ ሳይሆን ላለፈ በዓልም “እንኳን አደረሳችሁ” የማለት መብት አለህ፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ብቻ እንዳትገረሙ ገና ለሚቀጥሉት ሦስትና አራት ወራትም ላለፈው የመስቀል በዓል እንኳን አደረሳችሁ እያልኳችሁ እቀጥላለሁ፤ ምክንያቱም የማስታወቂያ ባለሙያ ነኛ፡፡
በቴሌቪዥን አይታችኋቸዋል አይደል “የማስታወቂያ ባለሙያዎቻችን” መስቀል ካለፈ ይኸው ድፍን አስራ ስምንት ቀን ሞላው፡፡ እነሱ ግን አሁንም “እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ፤ ምርቶቻችን ይግዙ…ይሸምቱ… የደንበኞቻችን ፍላጎት ለማርካት ሃያ አራት ሰዓት እንሰራለን…አድራሻችን…” እያሉ ነው (ቂቂቂቂ…በዓሉ ካለፈ እኮ ወር ሊሞላው ምንም አልቀረውም)። እኛ ግን በዓሉ አልፎም እንኳን አደረሳችሁ እንላለን፤ የማስታወቂያ ባለሙያዎች ነና! እንኳን አንድ ሃያ ቀን ለምን ሃያ ሳምንት አያልፈውም፤ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታችንን እንቀጥላለን፡፡
ከማስታወቂያዎቹ በስተጀርባ
እኔ ምለው ግን እነዚህ የበዓል ሰሞንን ጠብቀው በሁሉም ሬዲዮ ጣቢያዎችና ቴሌቪዥኖች በየደቂቃው እየተደጋገሙ የሚሰሙት ማስታወቂያዎች ለምንድነው ከበዓል በኋላም “እንኳን አደረሳችሁ” እያሉ ሰውን የሚያሰለቹት? አንደኛ ነገር ከሁለት ወይም ከሦስት ሳምንት በፊት ተከብሮ ለዋለ በዓል ዛሬ ላይ ሆኖ “እንኳን አደረሳችሁ” ማለት የጊዜን መሰረታዊ ሕግ የሚጥስ፤ የቋንቋውን ሰዋሰውም ያልተከተለ ስህተት አካሄድ በመሆኑ አስተዋዋቂውን አካል ትዝብት ውስጥ የሚጥል አሳፋሪ አገላለፅ ነው፡፡ ለተደራሲው ህብረተሰብም ክብር አለመስጠት ነው፡፡ ሰው እኮ ለበዓል እንኳን አደረሳችሁ የሚባባለው በዋዜማውና በዕለቱ ነው፡፡ ለባህሉና ወጉ ለዕለት የሰላምታ ልውውጡ ሳይቀር ከፍተኛ ክብር የሚሰጥ(አሁን አሁን እየላላ ቢሆንም) ህብረተሰብ ውስጥ እኮ ነው ያለነው፡፡ ላለፈ በዓል እንዴት እንኳን አደረሳችሁ ይባላል? እንዴያውም ከሰሞኑ ከዚሁ ከበዓል ጋር በተያያዘ የታዘብኩትን እውነተኛ ገጠመኝ ላጫውታችሁ፡፡
በጣም የምወደው ጓደኛዬ ነው፤ ሁሌም በዓል ሲመጣ በስልክ የእንኳን አደረሰህ መልዕክት እንለዋወጣለን። ባለፈው የመስቀል በዓል ግን የሚመች ሁኔታ ውስጥ ስላልነበርኩ በዋዜማውም ሆነ በእለቱ የእንኳን አደረሰህ መልዕክት አልላኩለትም፡፡ ሆኖም ከነጭራሹ ከሚቀር ይሻላል ብዬ በበዓሉ ማግስት በእጅ ስልክ አጭር የእንኳን አደረሰህ መልዕክት ላኩለት፡፡ ታዲያ ከአራት ቀን በኋላ ተገናኝተን ቡና እየጠጣን በምንጫወትበት ወቅት “የበዓል ቴክስት እኮ ልኬልህ ነበር፤ አልደረሰህም እንዴ?” ምን ቢለኝ ጥሩ ነው፤ “ካለፈ በኋላ ነው እንዴ እንኳን አደረሰህ የምትለኝ?” ከቅርበታችን የተነሳ ጉዳዩን ቀለል አድርገን አይተን በቀልድ ተሳስቀን አለፍነው እንጂ በዚህ ምክንያት እስከ መኮራረፍና ግንኙነታቸው እስከማሻከር ደረጃ የሚደርሱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህም በህብረተሰቡ ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ እንደ መልካም ምኞትን መግለጽ የመሳሰሉ የሰላምታ ልውውጥ ዕሴቶች ያላቸውን ትልቅ ቦታ የሚያሳይ ነው፡፡
ታዲያ ማስታወቂያዎቻችን “የወደፊት፣ የአሁን፣ እና ያለፈ ጊዜን” መለየት አቅቷቸው ላላፈ ጊዜ “እንኳን አደረሳችሁ” የሚሉን ለምን ይሆን? ለእንዲህ ዓይነቱ ቀይ ስህተት፣ ዓይን ያወጣ ሥርዓት አልበኝነትና ነጭ ውሸት የዳረጋቸው ነገርስ ምንድነው? መቼም የወጡበትን ህብረተሰብ ባህል የማያውቁ ሆነው አይመስለኝም፡፡ የጊዜና የድርጊት ዝምድናን የሚያስረሳ የቋንቋ ችግርም አለባቸው ብዬም አላስብም፡፡ ስንትና ስንት ስሜትን የሚያቀጣጥሉና ፍላጎትን ጣሪያ የሚያስነኩ ምስል ከሳችና አማላይ ቃላትን በመፍጠር የተካኑት የማስታወቂያ ባለሙያዎቻችን ሁነቶች ከጊዜ አንጻር እንደሚገለጹ ማወቅ እንዴት ያቅታቸዋል? ታዲያ ከወር በፊት የተከበረን አንድን በዓል ስም እየጠሩ “እንኳን ለእንትን በዓል በሰላም አደረሳችሁ” የሚሉት በመገናኛ ብዙሃን የሚለቀቁት ማስታወቂያዎቻችን ይህንን የቋንቋ ሕግና የህብረተሰቡን ባህል የማያውቁት ሆነው ይሆን? ወይስ እያወቁትም ቢሆን ሆዳቸውን ተረግጦ በግዴታ የሚያስለፈልፍ አለቃ ኖሮባቸው ይሆን?
ህሊናን የሚያስረሳው አደገኛው አለቃ
እኔ ሁለተኛው ነው የሚል ጥርጣሬ አለኝ – እያወቁትም ቢሆን በግዴታ የሚያስለፈልፍ አለቃ አለባቸው የሚለው፡፡ የአለቃው ስምም “ብሩ” ይባላል (የኔ ጥርጣሬ ነው እንግዲህ)፡፡ የማስታወቂያዎቻችንና የማስታወቂያ ባለሙያዎቻችን አለቃም “አለቃ ብሩ” ይመስለኛል፡፡ ለምን በሉኝ አንድ በዓል ካለፈ ከሶስት ሳምንት በኋላ “እንኳን ለበዓሉ በሰላም አደረሳችሁ” በሚል መግቢያ ጀምሮ በቴሌቪዥን ወይም በኤፍ. ኤም ሬዲዮ ሲተላለፍ የሰማችሁት ወይም ያያችሁት ማስታወቂያ ልብ ብላችሁ ሰምታችሁልኝ ከሆነ ማስታወቂያው የሚያልቀው “ለየት ያደርገናል”፣ “ተሸላሚ ሆነናል”፣ “ተመራጭ ሆነናል”፣ “ደንበኞቻችን ኮርተውብናል” …ወዘተ በሚሉ የምረጡኝ ቅስቀሳዎችና መፈክሮች ነው፡፡ ይህም የሚያመለክተው ድርጅቶቹ ደንበኛን በብቸኝነት ጠቅልሎ ለመያዝና ኢኮኖሚያዊ የበላይነትን ለማምጣት ከፍተኛ የእርስ በእርስ ፉክክር ውስጥ መግባታቸውን ነው። ይህን ለማድረግ የተሻለው አማራጭ ደግሞ በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ደንበኛን ማብዛት ነውና ረብጣ ገንዘብ ከፍለው ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ለብዙሃኑ ያስተዋውቃሉ፡፡
ሚሊዮን ሸማቾችን በማፍራት እና በርካታ ደንበኞቹን በመሳብ ከተፎካካሪ ድርጅቶች ልቆ ለመገኘትና ገበያውን ለመቆጣጠር የማስታወቂያ ባለሙያውም ከሌሎች አስተዋዋቂዎች በልጦ ለመታየት ተፈላጊ ለመሆን የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ረብጣ ገንዘብ የተከፈለው አስተዋዋቂ የተከፈለውን ገንዘብ ለማካካስ በበላው ልክ መጮህ ሥራው ይሆናል፡፡ በዚህ መካከል የሰው አለቃው ህሊናው መሆኑ ቀርቶ የሚያገኘው ብር ይሆናል፡፡ የሞራል ዋጋ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፣ ምን ይሉኝ ይጠፋል፡፡ እናም ለእውነት መኖር ይቀራል፣ ስህተት መሆኑ እየታወቀ ስህተት ይሰራል፣ ስህተት መሰራቱ ብቻም ሳይሆን ስህተቱ ይደጋገማል፡፡
በአለቃ ብሩ ስር ሆኖ መስራት ደግሞ ከባድ ነው። ከአለቃ ብሩ ጋር እየሰሩ አምቢ ማለት አይቻልም- ውሸትም ቢሆን ስህተትም ቢሆን ትሰራለህ ከተባልክ ትሰራለህ፡፡ ህሊናዬ…ሞራሌ…ምናምኔ አይፈቅደውም እዚህ ጋር አይሰራም፡፡ እናም ውሸት መሆኑን እያወክ ትሰራዋለህ፣ ስህተት መሆኑን እያወክም ትሳሳታለህ፡፡ ማስታወቂያዎቻችንና የማስታወቂያ ባለሙያዎቻችንም ያጋጠማቸው “ችግር” ይሄው ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ እኛ ባልገባን ነገር ከአለቃ ብሩ ጋር መስራትን “ችግር” አልነው እንጅ ከአለቃ ብሩ ጋር መስራት “ሽግግር” የሆነላቸውም በርካቶች ናቸው፡፡ በተለይም እውነት…ህሊና…ሞራል ምናምን እያልክ “ሰበብ ሳታበዛ” አለቃህን በታማኝነት ካገለገልክ ሥራህ አስቸጋሪ አይሆንብህም። እንዲያውም በተቃራኒው ያሻህን የምታደርግ፣ አንተ ከፈለክ በሰማይ እንኳን መንገድ የምታገኝ፣ ሁሉ የሞላልህ ኃይለኛ ሰው ትሆናለህ፤ ገንዘብ አለህና፡፡ እናም መስከረም አስራ ሰባት ላይ ያለፈውን በዓል ከሦስት ሳምንት በኋላ እንደ አዲስ አንስተው “እንኳን አደረሰህ” ይሉሃል፡፡ ይኼ ይገርማችኋል እንዴ፤ ገና ደርሶባቸው “እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሰህ” ማለት እስኪጀምሩ ድረስ ላለፈው የመስቀል በዓል “እንኳን አደረሰህ” እያሉ ገና ያደነቁሩናል፡፡ እንዲያውም እዚህ ላይ ከገና ቀጥሎ ቶሎ ሌላ በዓል (ጥምቀት) ስለሚመጣ ነው እንጂ በሌላው ጊዜማ ነገሩ የባሰ ነው፡፡ ለምሳሌ የትንሳኤ ወይም የአረፋ በዓል ከተከበረ በኋላ ቀጣዮችን ሁለት ወይም ሦስት ወራት ኤፍ ኤሞቻችንና ቴሌቪዥኖቻችን ላይ “እንኳን ለአረፋ/ለትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ” የሚሉ በንጉሱ ጊዜ መቁጠር ባቆመው የፓርላማው ሰዓት የሚቆጥሩ ማስታወቂያዎችን መስማት የተለመደ ነው፡፡ እኛስ ምን አደረግን? በዓሉ ከመድረሱ በፊት ገና አንድ ወር ሲቀረው ጀምሮ በየቀኑ ስንት ሺ ጊዜ “እንኳን አደረሳችሁ” እንባላላን፡፡
ያኔ እንኳን “አይ ችግር የለውም ለበዓሉ እንድንደርስ ካላቸው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ እንደደረስን ቆጥረውት ነው” ብለን ዝም አልናችው፡፡ በዕለቱ “የመስቀል በዓል” (ወይም ሌላ ማንኛውም በዓል ሊሆን ይችላል) ቀኑ “የማስታወቂያ ቀን” የሚከበርበት በዓል እስኪመስለን የበዓሉ አከባበር ቀርቶ በየመካከሉ “እንኳን አደረሳችሁ” እየተባልን በይግዙ ይሸምቱ ማስታወቂያዎች ቀልባችን ሲጠፋ ይውላል፡፡ ይኸኔም አይ ስለሚወዱን ነው ብለን ዝም አልን፡፡ አሁንስ ካለፈ በኋላ ምን አድርገናቸው ነው? እንደገና ወደ ኋላ እየተመለሱ ለበዓሉ የሚያደርሱን? ነው ወይስ ሁል ጊዜም ወደ ኋላ መሄድ ልምዳችን ነው ብላችሁ ነው?
ብልህና ብልጥ የሚያደርጉ ምክረ ሃሳቦች
በመጨረሻም ለእናንተ በአለቃ ብሩ ተታልላችሁ ከህሊናቸሁም ከህብረተሰባችሁም ተጣልታችሁ ለምትኖሩ ወገኖች ለወደፊቱ ብትችሉ እንዲህ ዓይነት ግልጽ ስህተቶችን ላለመስራት ጥረት ብታደርጉ ከአሁኑ የተሻለ ህይወት መምራት ትችላላችሁ የሚል ምክሬን ልለግሳችሁ እወዳለሁ፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ነገር ምንም እንኳን አለቃችሁ አቶ ብሩ አስገድዷችሁ፣ የዘመናችን ገዥ የንግሥት ብሪቱ ነገር አልሆንላችሁ ብሎ መቶ ሚሊዮን ህዝብ እየሰማችሁ በአደባባይ መዋሸት ነውር ስለሆነ ሆዳችሁ ቢመቸውም ለህሊናችሁ መልካም አይደለም፡፡ ህሊና የመልካምና ክፉ ነገሮች ሁሉ መመዘኛ፣ የእውነተኛው ዳኛ መቀመጫ መንበረ እግዚአብሔር ነውና ውሸት እረፍት አይሰጠውም፡፡ የሚዋሸው ህዝብ ሲሆን ደግሞ የበለጠ ያማል፡፡ እናም “ሰው አየ፣ እግዚአብሔር አየ” ነውና፣ የህሊና ሰላም ባለበት ደረቅ ቆሎ በክህደት ከሚበላ ጮማ ይበልጣልና እንድትዋሹ የሚያስገድዳችሁ ገንዘቡ ከሆነ ተውት፡፡
ሁለተኛ ነገር ለህዝቡ እዘኑለት፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ ለህዝቡ እዘኑለት፡፡ ህዝቡ የሚዋሸው አላጣም፤ ከአፉ ትቶ ያስተማራቸው ምሁራኖቹ ይዋሹታል፣ “መንግስትና እግዚአብሔር አንድ ናቸው” እያለ እንደፈጣሪው አምኗቸው ስልጣኑን የሚሰጣቸው መሪዎቹ ይዋሹታል፣ ዓይንና ጆሮ ይሆኑኛል ያላቸው ጋዜጠኞቹ፣ ነጋዴዎቹ፣ ሃኪሞቹ፣ መሃንዲሶቹ ሁሉም ይዋሹታል፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ በውሸት የተሰላቸ፣ የሚታመንለት ያጣ ምስኪን ህዝብ ነው፡፡ ቢያንስ እናንተ እዘኑለት፣ ተውት አትዋሹት! ምክንያቱም ብዙዎቻችን እንደምናስበው ሳይሆን ህዝቡ ታላቅ ህዝብ ነው፡፡ መምህርና ደራሲ ታዬ ቦጋለ እንዳሉት የተማሩ መሃይማን ሊያፈርሷት የሚታገሏትን አገር ሳይማር በጥበብ ገንብቶ ታላቅ አገር ለትውልድ ወረሰ ታላቅ ህዝብ ነውና፤ ክብር ይገባዋል! ክብሩም ይቅርና ቢያንስ ግን ስለ እውነት ብሎ ከመሸበት የሚያድረውን፣ ኩራቱ እራቱ፣ ክብሩ ሞቱ የሆነውን ህዝብ “ላለፈ በዓል እንኳን አደረሳችሁ፤ ትናንትናን ዛሬ ነው እያላችሁ” በአደባባይ እየዋሻችሁ ተዋርዳችሁ አታዋርዱት፡፡
ሦስተኛ የአለቃ ብሩ ነገር የማይሆንላችሁ፣ የእውነትና የህሊና ነገር የማያስጨንቃችሁ “ሆድ አምላኩ” ከሆናችሁ ደግሞ ቢያንስ ከስድብ የሚያድናችሁን የብልሃት ባይሆንም የብልጠት ምክር ልምከራችሁ። ይኀውም ነገሩ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” በመሆኑ ከትዝብት ባያድናችሁም ብልህን ማሞኘት ለጅል ዕውቀት ይመስለዋልና የበዓል ሰሞን “የእንኳን አደረሳችሁ” ማስታወቂያችሁ ላይ የቃላት ማስተካከያ ብታደርጉ የሚል ምክሬን በነጻ ልለግሳችሁ ነው፡፡ ፕሮፖዛሉ ምን መሰላችሁ፤ ማለትም በዓል ካለፈ በኋላ “እንኳን አደረሳችሁ” ላላችሁ ጅልነታችሁ ጥርሱን አግጥጦ ወጥቶ ከሚሳቅባችሁ ለምን “እንኳን አሳለፋችሁ” በሚል አታስተካክሉትም? እውነቴን ነው የምላችሁ በማይቆጥር በቆመ ሰዓት እየቆጠራችሁ ህዝብ ከሚስቅባችሁ ቢያንስ ራሳችሁን ሸውዱና ይችኛዋን ዘዴ ተጠቀሙ፡፡ ከውርደት ባያድናችሁም ቢያንስ ስለቃላት አጠቃቀማችሁ በአዕምሯችሁ ፋራ ብትሆኑም የአፍ አራዳ ትሆናላችሁ፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 5/2012
ይበል ካሳ