ግጭት በሰዎች መካከል ሁል ጊዜ ያለ እና የማይነጠለን ክስተት ነው። ነገር ግን የሚያስከትለውን መጥፎ ውጤት በማሰብ ብንሸሸውም እንደ ጥላችን ሁል ጊዜ ይከተለናል። አሁን አሁን ደግሞ ግጭትን ስንሸሸው በአንፃሩ ሲከተለን እናስተውላለን። በመሆኑም ከዚህ ማምለጫ ከሌለው ሽሽት ለመውጣት ቁልፍ መንስኤውን ማግኘት፤ ማወቅና መፍቻውን መንገድ መፈለግ አስፈላጊ ነው።
ግጭት ውስብስብ ባህሪ እንዳለው በተለይ ዛሬ ዛሬ በግልፅ ይታያል። ከውጭ ሲመለከቱትና ወደ ውስጥ ገብተው ሲመረምሩት የተለያዩ ገፆችን ሊያሳየን ይችላል። ከላይ ለሚታዩት የግጭቱ ምልክቶች ብቻ መፍትሄ እየሰጡ መጓዝ ጊዜያዊ መፍትሄ እንጂ ዘላቂ አይሆንም።
ለምሳሌ አንድ በወባ የሚሰቃይ ሰው በበሽታው መያዙን የሚያመላክቱ እንደ ራስ ምታት፣ የሰውነት ቁርጥማት ትኩሳት የመሳሰሉ ምልክቶች እንዳሉ እናውቃለን። ምልክቶቹ ላይ ብቻ በማተኮር እነዚህን የሚያስቆሙ እንደ አስፕሪን እና ፓራሲታሞል የመሰሉ እንክብሎችን /መድኃኒቶችን/ ብንሰጠው የራስ ምታቱንና የቁርጥማቱን ስቃይ መቀነስ አሊያም ማጥፋት ይቻለዋል። ነገር ግን ከወባ በሽታው ተፈወሰ ማለት አይደለም።
እንዲያውም እነዚህን መድኃኒቶች በመውሰድ ምልክቶቹ ስለሚጠፉ በህመሙ መሰወር ምክንያት ዘላቂ ፈውስ ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት ችላ ለማለት ገፊ ምክንያት ሆኖ ሁኔታዎችን ያመቻቻል።
በዚህም ምክንያት ወባው ስር እንዲሰድ እና እንዲባባስ ብሎም ህይወታችን ከባድ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ሰፊ እድል ይሰጣል። ይህ ምሳሌ እንደሚየሳየው የበሽታውን ስረ መሰረታዊ መነሻዎች ሳንመለከት ከላይ ከላይ በሚታዩ ምልክቶች /ችግሮች/ ላይ ብቻ በማተኮር ዘላቂ ፈውስ ለማምጣት ሁኔታው አስቸጋሪ ነው።
የግጭት ጠባይም ልክ እንደ ወባ በሽታ ነው። አንዱ የግጭት መንስኤ ሁከት ነው። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ከሁከት በስተጀርባ ገፊ ምክንያቶች
ይኖራሉ። ያልተመለሱ የመብት ጥያቄዎች፣ በደሎች፣ ኢ-ፍትሀዊነት፣ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች እና ሌሎች ለአብነት የሚጠቀሱ ስረ ምክንያቶች ናቸው።
ስረ ምክንያቶችን ፈልፍሎ ለማውጣት የተጋጩትን ወገኖች የሚያቃርኗቸው ውስጣዊ ፍላጎቶች ምንድን ናቸው? ካሉ የአለመስማማት ምክንያቶች ውስጥ ምን ያህሉ የአቀራረብ ወይም የእይታ ልዩነቶች፣ ምን ያህሉስ ተጨባጭ በሆኑ /Objective/ ጥያቄዎች ላይ የተመሰረቱ አለመጣጣሞች ናቸው? ብሎ መመርመር ያስፈልጋል። ይህ ሲባል ግን የግጭት ስረ መሰረቶችን ማግኘት ቀላል ነው ማለት አይደለም።
በተለይ ለብዙ ጊዜ የተካሄደ ጠብ፤ ሁለቱ ወገኖች ለረጅም ጊዜ አንዱ በሌላው ላይ በፈፀሙት በደልና ጉዳት ምክንያት የተቀሰቀሰ ቁጣ፣ ቂምና እልህ ሊኖሩ ይችላሉ። ወይም ደግሞ ሶስተኛ ወገኖች በባላንጣዎች መካከል ያለውን ክፍተት በመጠቀምና ጣልቃ በመግባት ጠቡን አባብሰውት ከባድ ጥላቻና መጎዳዳት እንዲፈጠሩ አድርገው ሊሆኑ ይችላሉ። በእነዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች ግጭቱን የጀመሩት ዋና ምክንያቶች ተረስተው፤ ገፃቸውን ቀይረው ወይም አለመጠን ተጋነው ሊቀርቡ ይችላሉ።
ከላይ ላይ ላይ ችግር መስለው የሚያሰቃዩንን ችግሮች በተለያዩ ጊዜያዊ መፍትሄዎች ማከምና ህመሙን ለመቀነስ መጣር ዋናውን በሽታ አለመፈወስ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ የበሽታውን ስረ መነሾ እንዳናገኝ ይጋርደናል፤ ይህም ህመሙን የበለጠ ያባብስብናል። በመሆኑም ግጭቱን ከላይ የሚታዩ ጠብ እና ሁከቶችን በማስቆም ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ አይቻልም።
በአንፃሩ ግን እነዚህ የምንወስዳቸው ጊዜያዊ መፍትሄዎች የግጭቱን ስረ መሰረት ስለሚሸፍኑብን ግጭቱ ስር እንዲሰድ በማድረግ ትልቅ አገራዊ ችግር ይፈጥራሉ። ስለዚህ ግጭቶችን ለማስቆምና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ስረ መነሻዎችን መፈለግ እጅጉን ሊተኮርበት ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2012