ከዳግማዊ አጼ ምኒሊክ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ድረስ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዋነኛ የመንግስት ማዕከል ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው ቤተመንግስት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሩን ለጎብኚዎች ክፍት አድርጓል:: በ40 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ካረፈው የተንጣለለው የቤተ መንግስቱ ምድረ ግቢ የተወሰነው ክፍል ነው ‹‹አንድነት ፓርክ›› በሚል ስያሜ ለሕዝብ ክፍት የሆነው።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የቤተ መንግስቱን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርቡ ለጋዜጠኞች አስጎብኝቷል። በዚህ ወቅት ከጽ/ቤቱ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ስለይዘቱ ማብራሪያ የሠጡት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተከናወኑት ተግባራት ሦስት ዋና ዋና ነጥቦችን ታሳቢ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
“አንዱ የነበረውን ታሪክ ሳይዛባ በልኩ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ፣ ሁለተኛው በታሪካችን ውስጥ የሌሉን አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ የሚመስሉ ነገሮችን መጨመር፣ ሦስተኛው ደግሞ አካባቢውን ለጎብኝዎች ምቹ ማድረግ ናቸው” ብለዋል።
በዚህ መሰረትም ቤተመንግሥቶችና ተያያዥነት ያላቸው ሕንፃዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ መጠገናቸውን፣ የሚመለከታቸው ሠዎችም አስተያየት እንዲሰጡባቸው መደረጉ ተነግሯል።
ከአዳዲሶቹ ግንባታዎች መካከልም የጥቁር አንበሳ ፓርክ፣ የክልሎች እልፍኝና የጥንታዊ ዕጽዋት ማሳያው በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በክልሎቹ እልፍኝ ውስጥ የየክልሎቹ መገለጫ የሆኑ ዋና ዋና የባህልና ቱሪዝም እሴቶች እንዲቀመጡ የተደረገ ሲሆን፤ ጎብኚዎች ከተመለከቱ በኋላ ወደየክልሎቹ ሄደው እንዲጎበኙ ያነሳሳል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል አካባቢውን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ በማሰብ በአረንጓዴ ስፍራ የተዋቡ የእግረኛ መንገዶች፣ መመገቢያና ማረፊያ ቦታዎች፣ መጸዳጃ ቤቶችና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መንቀሳቀሻ ስፍራዎች በአዲስ መልክ ተገንብተዋል፡፡
የዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ህንጻዎች ስብስብ፣ የመመገቢያና የጸሎት ቤታቸው፣ የግብር አዳራሽና የመጠጥ ማቀዝቀዣ እንዲሁም የንጉሱ የጦር ሚኒስትር የነበሩት የፊትአውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) መኖሪያ ቤት የጎብኚዎችን ቀልብ ይስባሉ ተብለው ተነስተዋል፡፡
በጉብኝቱ የተሳተፉት በርካታ ቁጥር ያላቸው የግልና የመንግሰት መገናኛ ብዙሀን ባለሞያዎችም ባዩት ሁሉ መደነቃቸውን ተናግረው ሁሉም ህብረተሰብ ስለታሪኩ እንዲያውቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት በሞያቸው ለማገዝ ቃል ገብተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና በሌሎች የጎረቤት ሀገራት መሪዎች በደማቅ ስነስርአት ተመርቆ የተከፈተውን የቤተመንግስቱን አንድነት ፓርክ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመደበኛ 200 ብር፣ በልዩ መስተንግዶ ወይም ቪ አይ ፒ ደግሞ 1000 ብር በመክፈል መጎብኘት ይችላል ተብሏል፡፡
አንድነት ፓርክ ምን የሚጎበኝ ነገር አለው?
የተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መሪዎች በተገኙበት መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀው የታላቁ ቤተ መንግሥት አንድነት ፓርክ በቀን 1500 ጎብኚዎችን ያስተናግዳል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዳብ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ (ፋርማጆ)፣ እንዲሁም በርካታ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ዕድሳት ሲደረጉላቸው ቢቆዩም ለሕዝብ ጉብኝት ክፍት ሳይሆኑ የቆዩ ሰባት ታሪካዊና ከ100 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ሕንፃዎችን ጨምሮ ስድስት መስህቦችን ይዟል፡፡
ፓርኩ ከዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት አንስቶ እስከ ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዘመነ መንግሥት ድረስ የተሠሩ ሥራዎች በዓውደ ርዕይ ቀርበውበታል፡፡ ሕንፃዎቹን ጨምሮ በዓውደ ርዕይነት የቀረበው ይህ ታሪካዊ ሥፍራ የፓርኩ ዋና መስህብ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ የአንድነት ፓርክ ግቢ የ130 ዓመታት ታሪክ እንዳለውም ተጠቅሷል፡፡
በቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ የተሰራው አንድነት ፓርክ አምስት ቢሊየን ብር ተመድቦለት የተገነባ ነው። ይህንን ፓርክ ለመገንባት የገንዘብ ድጋፍ የተገኘው ከዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለጋዜጠኞች ባስጎበኘበት ወቅት ተናግሯል።
ዘጠኝ ወር የፈጀው ግንባታ እየተከናወነ ባለበት የቁፋሮ ስራ ወቅት የሰው አፅምን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተሽከርካሪዎች ተቀብረው ተገኝተዋል:: ቤተ መንግሥቱ በ40 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ በውስጡ ሦስት ዋነኛ የቱሪስት መስህቦች ይገኙበታል።
1. ታሪካዊ መስህብ
ከ1880ዎቹ ጀምሮ የተገነቡ የነገሥታት መኖሪያና ጽህፈት ቤቶች በዋነኝነት እዚህ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን፤ በዚህ ፕሮጀክት የነበሩበትን ይዞታ ሳይለቁ ዕድሳት እንደተደረገላቸው ተገልጿል።
የአባ መላ ቤት
በዚህ ሥፍራ መጀመሪያ የምናገኘው የፊት አውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን (አባ መላ) መኖሪያን ነው። አባ መላ የአጤ ሚኒሊክ የጦር ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን፤ ይኖሩበት የነበረ ትንሽ የእንጨት ቤት ከአጤ ምኒሊክ መኖሪያ ቤት ጎን ላይ ይገኛል።
አጤ ሚኒሊክ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ እንደ መኖሪያና ቢሮ ሆኖ ጥቅም ላይ ውሎ ነበር። ይህ ቤት ፈርሶ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ሙሉ በሙሉ ታድሷል።
የታችኛው ዙፋን ቤት
የአጼ ኃይለሥላሴ ዙፋን ችሎት የነበረ ሲሆን፤ የሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ቢሮ ሆኖም አገልግሎ ነበር:: አጼ ኃይለ ሥላሴ በደርግ ተገድለው የተቀበሩትም በዚሁ ህንጻ ምድር ቤት ነበር::
የቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አቶ መለስ ዜናዊ እና አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ይኖሩበት የነበረው ህንፃ የቤት እቃዎች ገብተውለት የእንግዳ መሪዎች ማረፊያ እንዲሆን ተስተካክሏል።
አጤ ሚኒሊክ መኖሪያ
የአጤ ሚኒሊክ ባለ አንድ ፎቅ መኖሪያና ጽ/ቤት በሮች በእንጨት የተሠሩ ሲሆን፤ በሚያምር መልኩ ከአበባና የሐረግ ጌጥ ፍልፍል የተሰራ ነው። ይህ ቤት ከሁለት ሌሎች ቦታዎች ጋር በድልድይ ይገናኛል። አንደኛው በሰሜናዊ አቅጣጫ የአጤ ምኒሊክ የፀሎት ቤትና የሥዕል ቤት ሲሆን፤ እንቁላል ቤት በመባል ይጠራል። አንዳንዴም እንደ ጽ/ቤት ይጠቀሙበት ነበር።
እንቁላል ቤት
የፀሎት ቤቱና የሥዕል ቤቱ ባለ ሁለት ፎቅ ነው። ሁለተኛው ፎቅ ላይ ከፍ ብላ የተሠራች በመስታወት የተሸፈነች ቤት አለች፤ ይህች ቤት ‘ቴሌስኮፕ’ ያላት ሲሆን፤ አዲስ አበባን በሁሉም አቅጣጫ ማየት ታስችላለች።
በዚች እንቁላል ቤት መገናኛው ድልድይ ጋ የመጀመሪያው ስልክ የገባበት ቤት ይገኛል። ቤቱ ከድንጋይና ከእንጨት የተገነባ ነው። አርክቴክት ዮሐንስ የኪነ ህንፃውን ጥበብ ሲገምቱ ከአርመኖችና ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ሕንዶች ሳይሳተፉበት እንደማይቀሩ ይገምታሉ። ይህ ቤት በደርግ ጊዜ የውይይት ክበብ በመሆን አገልግሏል።
የእቴጌ ጣይቱ ቤት
ሌላኛው ከአጤ ሚኒሊክ ቤት ጋር በድልድይ የሚገናኘው የእቴጌ ጣይቱ ቤት ነው። ይህ ቤት ከቤተ መንግሥቱ በምሥራቃዊ አቅጣጫ የሚገኝ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ነው።
የዙፋን ግብር ቤት
በምድር ቤት የዙፋን ግብር ቤት ይገኛል። ይህ ቤት የነገሥታቱ መመገቢያ አዳራሽ ሲሆን፤ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ምግብ የሚመገቡበት ክፍል ነበር፤ ቤቱ በደርግ ጊዜ የደርግ ምክር ቤት መሰብሰቢያ በመሆን አገልግሏል።
የዘውድ ቤት
ሌላኛው የዘውድ ቤት ነው። ይህ ህንፃ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ነገሥታትንና ዲፕሎማቶችን ከተለያዩ ሀገራት ተቀብለው ያስተናግዱበት ነበር።
በዚህ ህንፃ ከተስተናገዱ የውጪ ሀገራት እንግዶች መካከል በ1965 ንግሥት ኤልሳቤጥ 2ኛ፣ በ1966 የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ቻርልስ ደጋሌ እንዲሁም በ1956 የዩጎዝላቪያው ፕሬዚደንት ቲቶ ይገኙበታል።
ደርግ የዚህን ህንፃ ምድር ቤት የአጼ ኃይለሥላሴን ባለስልጣናት አስሮ ለማሰቃየት ተጠቅሞበት እንደነበር ታሪክ ሰነዶች ያስረዳሉ።
የምኒሊክ የግብር አዳራሽ
ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው የሚኒሊክ የግብር አዳራሽ ሲሆን፤ ንጉሡ በዚህ አዳራሽ እንግዶቻቸውን ያስተናግዱ እንደነበር ታውቋል።
የአዲስ አበባ ወንዞችና ዳርቻዎቻቸውን የማልማት ሥራን ለመተግበር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ታቅዶ በነፍስ ወከፍ አምስት ሚሊዮን ብር በማበርከት የእራት ድግስ የተካሄደበት ‹‹ገበታ ለሸገር›› መርሃ ግብር የተደረገውም በዚሁ በታደሰው አዳራሽ ውስጥ መሆኑ ይታወሳል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ልጅ የተዳረችውም በዚሁ አዳራሽ እንደሆነ በጉብኝቱ ወቅት ተነግሯል፡፡ እኚህ የታሪክ ቅርሶች ሦስት ጊዜ እድሳት እንደተደረገላቸው በገለፃው ወቅት መረዳት ተችሏል።
እድሳቱ የመጀመሪያው በ1963 ዓ.ም በኃይለ ሥላሴ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደርግ 10ኛ ዓመቱን ሲያከብር፣ ሶስተኛው ደግሞ ቫርኔሮ በሚባል የኮንስትራክሽን ድርጅት ነው።
2. የተፈጥሮ መስህቦች
በፓርኩ ከተሰሩ መስህቦች መካከል የእንስሳት ማቆያና አኳሪየም (የውሃ አካል) አንደኛው ነው። በዚህም ውስጥ የጥቁር አንበሳ መኖሪያ፣ የዝንጀሮ መጠለያ፣ የአሳ ማርቢያን (አኳሪየም) ጨምሮ 46 ዓይነት ዝርያ ላላቸው 300 ለሚሆኑ እንስሳት መጠለያ የሚሆን ስፍራ ይገኛል።
ለእንስሳቱ ምግብ የሚዘጋጅበትና ሕክምና የሚሰጥበት ስፍራም በዚሁ አለ። ይህ የእንስሳት መጠለያ ሕዳር 2012 ስራ እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል።
በዚሁ አቅራቢያ በፓርኩ የጓሮ አትክልት፣ የሚገኝ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር አቀማመጥ በጠበቀ መልኩ ተሰርቷል።
3. ባህላዊ መስህብ
በአንድነት ፓርክ ከተካተቱት አንዱ የብሔር ብሔረሰቦች ባህል የሚንፀባረቅበት ስፍራ ነው። ይህ ስፍራ የተገነባው በብሔር ብሔረሰቦች ቤት፣ ባህል፣ ምጣኔ ኃብትና የሕዝቦችን አኗኗር መሰረት በማድረግ ነው። በዚህ ሕንፃ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውን እንዲያንፀባርቁ እንደሚደረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
መኪና ማቆሚያ
ለመኪና ማቆሚያ የሚሆን ሌላ ሰፊ ግንባታ ከግቢው ውጪ ተጀምሯል። ይህም ተጨማሪ አንድ ነጥብ አምስት ቢልዮን ብር ይፈጃል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ከሰኞ ማለትም ከጥቅምት ሦስት ቀን 2012 ጀምሮ ማንኛውም ዜጋ 200 ብር እንዲሁም በቪ.አይ.ፒ (VIP) 1000 ብር በመክፈል ቤተ መንግስቱን መጎብኘት ይቻላል የተባለ ሲሆን፤ 1000 ብር የሚከፍሉ ጎብኝዎች ታሪካዊ ቁሳቁስ የሚገኙበትንና ሌሎች እንግዶች እንዲያዩ ያልተፈቀደላቸው ስፍራ መጎብኘት እንደሚችሉ ለመረዳት ችለናል።
እንደመሰናበቻ
አንድነት ፓርክ በቀን 1500 ጎብኚዎችን ያስተናግዳል። ይህ ምን ማለት ነው? በወር 45 ሺ፣ በዓመት ከ 547 ሺ በላይ ሕዝብ ይጎበኘዋል ማለት ነው፡፡ በአጭሩ ይህን ያህል ሕዝብ ስለትላንትናና ስለ ዛሬ ታሪኩ በተጨባጭ ያውቃል፣ መረጃም ያገኛል ማለት ነው፡፡ ይህ ኹነት በተለይ ታሪክን ለማንበብ፣ ለማወቅ፣ ለመመርመር ሳይታደሉ በሰሙት ተረት ተረት “ሚኒልክ ገሏል …ቆርጧል” በሚል ቂምና ጥላቻን ለሚያስፋፉ የዘመኑ አክራሪ ብሔርተኞች የሚዋጥ አይሆንም፡፡ እነዚህ አክራሪ ብሔርተኞች ቤተመንግሥቱ መታደሱን ከሰሙ በኋላ “ዐቢይ ለነፍጠኞች ሸጠን” እስከማለት የደረሰ ወቀሳ ለማቅረብ መድፈራቸው ስለታሪክ እንጥፍጣፊ ግንዛቤ እንደሌላቸው ከማሳየት ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም፡፡
ናዚ ከ80 ዓመታታ በፊት በእስራኤል (አይሁዶች) ሕዝብ ላይ ያደረሰው በደልና ግፍ ዛሬ በሙዚየም በክብር ተቀምጦ ይጎበኛል እንጂ፤ ናዚ የነካው ሁሉ ይፍረስ፣ ይጥፋ የሚል ትውልድ በእስራኤል አልበቀለም፡፡ ስለታሪክ ስንነጋገር ከጥሩው እና ከመጥፎው እየተማርን ነጋችንን እያበራን እንሄዳለን እንጂ በትላንት ትርክት ጎራ ለይቶ መቆራቆሱ የሚያስገኘው አንዳችም ፋይዳ ሊኖር አይችልም፡፡
እናም ክቡር ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የሚኒሊክ ቤተመንግሥት በክብር ታድሶ ለትውልድ ለጉብኝት እንዲከፈት በማድረጋቸው፣ ወጣቱ ትውልድ ታሪክ እንዲያውቅ፣ በዕውቀት ላይ ተመስርቶም እንዲጠይቅ፣ እንዲመራመር ዕድል በመፍጠራቸው ትልቅ ክብር ይገባቸዋል፡፡
(ለዚህ ጽሑፍ ጥንቅር ፡- ቢቢሲ አማርኛ፣ ሪፖርተር፣ ኢዜአ ድረገጽ፣ የኤልያስ መሠረት ገጽ፣ የዮሐንስ መኮንን ገጽ፣ በግብአትነት ተጠቅሜያለሁ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2012
ፍሬው አበበ