አዲስ አበባ፡- በዓመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኛል ተብሎ የሚጠበቀውና የኢትዮጵያ መንግሥት ከእንግሊዙ ቱሉ ካፒ ኩባንያ ጋር በጣምራ የሚያከናውኑት የወርቅ ማዕድን የማውጣት ሥራ በተያዘው በጀት ዓመት እንደሚጀመር ተገለፀ።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ገንጂ ወረዳ ላለፉት 10 ዓመታት ጥናት ሲደረግበት የነበረው ፕሮጀክት፣ የወርቅ ማዕድን የማውጣት ሥራው በዚህ ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ ኡመታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስታውቀዋል።
አስተዳዳሪው እንደገለፁት፣ የፕሮጀክቱ 20 በመቶ ድርሻ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ 80 በመቶው ደግሞ የእንግሊዙ ኩባንያ ነው። ወርቅ የማውጣት ሥራው ሲጀመርም እስከ 10 ሺ ለሚደርሱ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ለዚሁ የወርቅ ማዕድን የማውጣት ሥራ ሲባል ለሚነሱ 374 አባወራ አርሶ አደሮች ተተኪ መሬት የተዘጋጀላቸው ሲሆን፣ እስከ 604 ሚሊዮን ብር ካሳ እንደሚከፈላቸውም አቶ ኤልያስ ገልፀዋል።
እንደ አቶ ኤልያስ ማብራሪያ፤ በምዕራብ ኦሮሚያ የአካባቢውን ወጣቶች ወደ ሥራ የማስገባት ውስንነት አለ። ይህም በኢንቨስትመንት እጥረት ምክንያት በመሆኑ በአካባቢው ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን ኢንቨስትመንት ስለሚስፋፋበት ሁኔታ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ቡና በአካባቢው በብዛት የሚመረት በመሆኑ በደረቁና ታጥቦ የሚቀርበው ምርት እሴት ተጨምሮበት በኅብረት ሥራ ማህበራትና በግለሰቦች እንዲላክ በማድረግ ለአርሶ አደሩ የተሻለ ገቢ ለመፍጠር መታቀዱን የገለፁት አቶ ኤልያስ፤ ከደዴሳ ጀምሮ እስከ አሶሳ መግቢያ ባለው አካባቢ የሚመረተውን የማንጎ ምርት ታሳቢ በማድረግም የጭማቂ ማምረቻዎችን ለመትከል ጥናት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ይርዳው ነጋሽ በበኩላቸው፤ መንግሥት በማዕድን ማውጣቱ ሥራ ከእንግሊዙ ኩባንያ ጋር ሽርክና ያለው በመሆኑ በአስተዳደር ሥራው ይሳተፋል። በዚህም የተነሳ ምን ያህል ቶን ወርቅ እንደተመረተና እንደተሸጠ መረጃዎች ግልጽ ስለሚሆኑ በተጠቃሚነት ደረጃ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2012
ዘላለም ግዛው