አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም የሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመድረሱ መንግስታዊ ተቋማት እና ማህበራት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ገነት ስዩም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የሴቶች የፖለቲካ እና በፌደራል ደረጃ ባሉ የመንግስት ተቋማት ውስጥ በአመራርነት የመሳተፍ ሁኔታ እያደገ ቢመጣም ወደ ታችኛው መዋቅር ሲወርድ ግን አሁንም ሚናቸው ዝቅተኛ ነው፡፡
ለዚህ በዋናነት የሚጠቀሰው በህብረተሰቡ ዘንድ ለሴቶች ያለው አመለካከት አለመለወጥ ነው፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ መንግስት ባለፈው አመት የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ 50 በመቶ የሚሆነው ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ በሴቶች እንዲያዝ ማድረጉ እንደቀላል የሚታይ አይደለም፡፡
ይሁንና ሴቷ ምንም አይነት ብቃትና እውቀት ቢኖራትም ወንዱን ሰጪ ሴቷን ደግሞ ተቀባይ አድርጎ የመቁጠር ልምድ አሁንም በበርካታ ተማረ በሚባለው ህብረተሰብ ዘንድ ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም በህብረተሰቡ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በየተቋማቱ ባሉ አመራሮች ዘንድ ያለነውና ይህንን አመለካከት የመቀየር ስራ በስፋትና በተከታታይነት መስራት ይገባል፡፡
በዚህ ረገድ ፌዴሬሽኑ በየክልሉ ባሉት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች አማካኝነት እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበርም ለአባላቶቹ የትምህርት እድል እያመቻቸ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ሴቶች ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ምትኩ በበኩላቸው፤ ሴቶች በአገሪቱ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የውሳኔ ሰጭነት ሚና አሁንም ከሚፈለገው ደረጃ መድረስ ያልተቻለው ሁሉም አካል በያገባኛል መንፈስ ያለመስራቱና ያለመደገፉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተለይም ሴቷ የህዝቡን ግማሽ ቁጥር ያየዘች እንደመሆኑ ሴቷን ደግፎ ወደ አመራር ማምጣት ባለመቻሉ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የበኩሏን ድርሻ እንዳትወጣ እንዳደረጋት አብራርተዋል፡፡
«እኛ ሴቶችም ብንሆን ያለንን አቅም በአግባቡ መጠቀም አልቻልንም፤ ያልበቁትን እህቶቻችንን ለማብቃት የሚጠበቅብንን ያህል አልሰራንም» ያሉት ወይዘሮ እመቤት፤ ሴቷን ወደ ፊት የማምጣቱን ኃላፊነት ሁሉም ለነገ ሳይል ሊሰራበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የኦሮምያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እሰካለ ለማ ደግሞ «ሴቷ በቤት ውስጥ ያላትን የመምራት አቅም ለአገር በሚጠቅም ደረጃ ወደ ከፍተኛ ማሻገር ይገባል» ብለዋል፡፡ በተለይም ያለውን ውስን ሃብት በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል፤ በሃላፊነት በጠያቂነት በመስራት ረገድ ሴቶች ከወንዶች የተሻለ ተፈጥሯዊ ክህሎት ያላቸው እንደመሆኑ በሁሉም ቦታዎች ላይ ወደ ውሳኔ ሰጪነት እንዲመጡ ማድረግ ላይ sሁሉም ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝብዋል፡፡
ማህሌት አብዱል