
ዓለም አሁን በምትገኝበት በዚህ ውጥረት በተለያዩ ሸቀጦች ላይ የዋጋ መናር በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለውጥረቱ እንደ አንድ ምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ ዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ውስጥ መግባት አንዱ ሲሆን የሁለቱ ሀገራት ጦርነት በዓለም የስንዴ ምርት ግብዓት አቅርቦት ላይ ጫና አሳድሯል።
ሰሞኑን ደግሞ በእሥራኤል እና በኢራን መካከል የተፈጠረው ውጥረት በነዳጅ ዋጋ ላይ ለውጥ እየፈጠረ እንደሚገኝ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መረጃዎችን እያወጡ ይገኛሉ።
ወደሀገራችን ስንመጣም የኑሮ ውድነት ማኅበረሰቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት እየፈተነው ይገኛል። መንግሥት የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ቢሆንም አሁንም ቢሆን ጫናው ከባድ ነው።
በአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣምና በተለያዩ ብልሹ አሠራሮች ምክንያት በየቀኑ እየጨመረ የሚሄደውም የሸቀጦች ዋጋ መናር በዜጋው ላይ ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን በመፍጠር ሕዝቡን ለ ምሬት እየዳረገው ነው።
መንግሥት እያደረገ ካለው ጥረት ጎን ለጎንም የምግብ ዘይት ምርቶች እና የቡና ዋጋ በየጊዜው ከፍተኛ የሚባል የዋጋ ጭማሪ እያሳዩ የሚገኙ ምርቶች በገበያው ላይ ይስተዋላሉ። ታዲያ በኅብረተሰቡ ዘንድም ቢሆን ሸቀጦች ላይ የሚስተዋሉ ምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ጥያቄ ከማስነሳቱም ባሻገር በተለይም በሀገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ መናር አነጋጋሪ ሆኖ ዘልቋል።
በተለይም ኅብረተሰቡ በዕለት ተዕለት በሚጠቀም ባቸው መሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜጎችን ሕይወት እጅግ እየተፈታተነው ይገኛል። በእህል፣ በጥራጥሬ፤ በአትክልት ምርቶች፤ በግንባታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪው አሳሳቢ ሆኗል። ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ ያለው የምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ መሆኑ ነው። ትራንስፖርት፣ የትምህርት ቤት ክፍያና የመሳሰሉት ሲጨመሩበት የሕዝቡን ኑሮ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ እያደረገው ነው።
የኑሮ ውድነት አልያም ዋጋ ንረት እንዲከሰቱ ከሚያደርጉ ተግባሮች ውስጥ አንዱ የኢኮኖሚ አሻጥሮች እንደ ዐቢይ ምክንያት ማንሳት ይቻላል። ምርት በገበያ ላይ እያለ በገበያው ላይ ትክክለኛ ያልሆነ ወይንም አርቴፊሻል የዋጋ ጭማሪ ማድረግ በገበያው ላይ የሚገኙ ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ይደረጋል። ገበያ ላይ የለም፣ የዕቃ እጥረት አለ ወዘተ በሚሉ ውሃ የማይቋጥሩ ምክንያቶች የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ብዙ ናቸው።
የኢኮኖሚ አሻጥሩም የሚከናወነው ከአምራች ነጋዴው ጀምሮ፣ የጅምላ አከፋፋዮች እና በቸርቻሪዎች ነው። አሻጥሩም ሲታሰብ የደላሎች ሚና የሚናቅ አይደለም። ምርቱ በበቂ ከአምራቹ እየገባ በቀጣይ ሳምንት ይጠፋል በሚል ወሬ ከማስወራት ይጀምሩና ነጋዴዎች ምርት እንዲደብቁ ከዚያም አልፎ ጨምረው እንዲሸጡ ይመክራሉ። አለፍ ሲልም ቸርቻሪው ዋጋ ጨምሮ እንዲሸጥ የሚያስገድዱበት ሁኔታም አለ።
‹‹አይ እኔ ባላችሁኝ ዋጋ አልሸጥም›› የሚለውን ነጋዴም ከገበያ ውጭ የሚያደርጉበትም አጋጣሚ ሰፊ ነው። ይሄ ስለሚታወቅም ከጅምላ አከፋፋዮች እስከታች ቸርቻሪዎች በመመሳጠር ዋጋን ይጨምራሉ ሳይሆን ይከምራሉ።
እዚህ ጋር ልብ ልንለው የሚገባው ነገር አንድ ምርት ከነጋዴው ወደ ሻጩ ከዛም ወደገበያው የሚገባበትን ሥርዓት ነው። ምክንያቱም አምራቹ ገበሬ በቅናሽ ዋጋ አምርቶ የሚሸጠውን ምርት ወደተጠቃሚው ለማድረስ የሚኖረው ደካማ የግብይት ሠንሠለት ምክንያት እጅግ በጣም በተጋነነ ዋጋ ወደ ሸማቹ የሚቀርቡ ነጋዴዎች እጅ ላይ ሊወድቅ ይችላል።
በንግድ ሥርዓት ውስጥ የሕጋዊነት ሥርዓት በአብዛኛው የሚነሳ እና ቁልፍ ጉዳይ ሲሆን፤ ሕጋዊ የገበያ ሥርዓት ውስጥ የሚሠሩ ነጋዴዎች በእዚህ የአቅርቦት ሠንሠለት ውስጥ የተለያዩ ምርቶችን ከገበያው አምጥተው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለሌሎች ነጋዴዎች ያስረክባሉ። ይህ ሕጋዊ የክፍያ ሥርዓትን የማያካትት አልያም ደረሰኝ የሌላቸው ነጋዴዎች በዚህ ውስጥ በመሐል የሚገቡ ደላሎች ሕጋዊ ነጋዴውን ሲጎዱት ይታያሉ።
ይህንን ምንም እንኳን አሁን አሁን ላይ መንግሥት ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ በርካታ የተሳካ ሙከራ እያደረገ ቢሆንም ለደላሎች አሻጥር መሳካት ዋነኛ ሚና የሚጫወተው የኢትዮጵያ የክፍያ እና የግብይት ሥርዓት አለመዘመኑ ወይም ዲጂታላይዝድ አለመሆኑ ነው። ዲጂታላይዝ የግብይት ሥርዓትን ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት የተደረጉ ክፍያዎችን ለመቆጣጠር ምቹ ሲሆን፤ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓትን በማዘመን የተረጋገጠ የደረሰኝ አገልግሎት እንዲኖር ያስችላል። ለዚህም እንደ ጅምር ማሳያ የምናደርጋቸው የቴሌ ብር የክፍያ አገልግሎት ላይ ለሚፈጸሙ ክፍያዎች የሚሰጠውን ዲጂታል ደረሰኝ መመልከት ይቻላል።
አሁን ላይ ተቋማት ይህንን የኦንላይን የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ እያደረጉ የሚገኙ ሲሆን ዲጂታላይ የግብይት/ ክፍያ ሥርዓትን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ በቀላሉ ወደሲስተሙ የተሳሳተ መረጃ እንዳይገባ ለማድረግም ቀላል ነው።
በዚህም ማን፤ በስንት ገዝቶ፤ ስንት አውጥቶ፤ በስንት ሸጠ የሚለውን በቀላሉ መረጃን በማግኘት ቁጥጥሩን ማዘመን ይቻላል። ከዚህም ባለፈ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ ይዞ በስጋት ከመንቀሳቀስ እና ፎርጂድ የሆኑ የገንዘብ ስርጭቶችን በመከላከል ከሚያግዘው በላይ ነጋዴዎች የሚኖራቸውን ወጪ የሚፈጽሟቸውን ግብይቶች በዚህ የዲጂታል ሲስተም በቀላሉ እንደሚዘግቡ ያስችላቸዋል።
ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊነት ለማረጋገጥ የራሱ የሆነ ሂደት ያለው ሲሆን አስቀድሞ ግንዛቤ መፍጠር፣ ሰዎች በቀላሉ የሚገበያዩበትን ሥርዓት ለመዘርጋት ከተጠቃሚዎች ጋር የሚተዋወቅበትን መንገድ መፍጠር እንዲሁም በዲጂታል ግብይት ሥርዓት መዘርጋት ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች ማበረታታት የዲጂታል ግብይት ሥርዓትን ለማስፋፋት የሚያግዝ ነው።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም