ወደ መስቀል አደባባይ በሚወስደው መንገድ ላይ አንድ ወጣት ‹‹የኢትዮጵያ መስቀል›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ሥዕል ሸራ ወጥሮ፤ ቀለም ነክሮ ሲጠበብበት ተመለከትኩኝ። አላፊና አግዳሚው ቆም ብሎ ግማሹ በአድናቆት ግማሹም ደግሞ አመል ሆኖበት ቆሞ ይመለከታል። ልጁ ግን ሥራ ላይ ነው። የዓይኖቹ እንቅስቃሴ፣ የአንገቱ ዘንበል ደፋ ቀና ማለት በራሱ ለሥራው የሰጠውን ትኩረት ለመረዳት ብዙም መመራመር አያስፈልግም። ከአጠገቡ በርካታ ቡርሽና ቀለማትን አስቀምጧል። ሥራቸው ተጠናቋል የሚባሉ ሥዕሎች ተደርድረዋል።
የሥዕል ጥበብ ከሳሎን ወደ ጎዳና ወጥታ ከአድናቂዎቿ ጋር እንድትገናኝ የራሱ ጥረት እያደረገ ያለ ወጣት ነው። በእርግጥ ይህን እያደረገ ያለው ከችግር የተነሳ እንጂ ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነውለት አይደለም። እኔም በመስቀል አደባባይ በዕለተ ደመራ እንዳየሁት ስልክ ተለዋውጠን የምንገኛኝበትን ቀን ተነጋግረን ተለያየን፤ እነሆ የዛሬ እንዲህም ይኖራል እንግዳችሁ ይህ የጥበብ ሰው ነው።
ኤርሚያስ ደረጄ
በ1984 ዓ.ም ወደ አምቦ መውጫ መናገሻ ተወለደ። አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃውን በዚያው በተወለደበት አካባቢ መናገሻ ኮሎቦ ትምህርት ቤት ነው የተማረው። አስረኛ ክፍል የሚፈለገውን ያክል ውጤት ስላላመጣ ወደ 11ኛ ክፍል መግባት አልቻለም። ወዲህ ደግሞ ቤተሰቡ ላይ ሸክም መሆን አልፈለገም። የተገኘውን ሁሉ ለመስራት ወሰነ። በ2001 ዓ.ም ሳሪስ አካባቢ ንፋስ ስልክ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ገብቶ በማታ መርሐግብር በኮንክሪት ወርክ መማር ጀመረ።
ጎን ለጎንም ዲኤች ገዳ የሚባል ድርጅት ውስጥ እየሰራ ነበር የተማረው። ፋብሪካው 24 ሠዓት የሚሰራ ስለሆነ ለትምህርቱ እንዲመቸው ፈረቃ የሚሰሩ ሰዎችን እየቀየረ ነው ነበር የተማረው። በደረጃ ሦስት ከተመረቀ በኋላ በተማረበት ሙያ ሥራ ማፈላለግ ጀመረ። በንፋስ ስልክ ቴክኒክና ሙያ ሲማር በየወሩ ለትምህርት ቤት 68 ብር ይከፍል ነበር። በዚህ ወቅት ደመወዙ 1000ሺ ብር ሲሆን ይህችን እያብቃቃ ነበር የሚጠቀመው። በመቀጠል ደግሞ በአቃቂ ብረታ ብረት ብየዳም የስድስት ወር ኮርስ ወስዶ ሌላ ሥር ማፈላለግ ጀመረ።
በተማረበት ኮንክሪት ሙያ ቂሊንጦ አካባቢ 2005 ዓ.ም በቀን 80 ብር እየተከፈለው ሥራ ቢጀምርም ስላልተመቸው ከዚያም ለቆ ወጣ። በመቀጠል ደግሞ መከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት (መኮድ) ውስጥ በእንጨት ሥራ ለመስራት ገባ። ሙያውንም በሚገባ ለመደ።ይህን ተቋም ሲለቅ 4000 ብር ደመወዝተኛ የነበረ ሲሆን፤ በዚህ ብር ቤት ተከራይቶ ምግብ በልቶ እና ሌሎች ነገሮችን አሟልቶ ለመኖር ጥረት አድርጓል። ግን አሁንም ቢሆን ደስተኛ አልነበረም።
ኤርሚያስ በ2011 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ሥራውን አቆመ። ከዚያ አራተኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ አወጣ። ግን አሁንም ሥራ ሊያገኝ አልቻለም። በዚህ ሁሉ ጥረት ውስጥ ግን አይከፋም። ለዚህ ሁሉ መሽከርከር ያደረሰውም ዋነኛ ምክንያት ገና በልጅቱ በልቡ ላይ ተስሎ የነበረው የሥዕል ሥራ ስላሸተተው ነው። በእርግጥ የሥዕል ሥራን በተለምዶ እንጂ በትምህርት ቤት ያገኘው አይደለም። ግን በ2011 ዓ.ም ክረምቱን ለሁለት ወራት ከመናገሻ እየተመላለሰ ኢንላይትመንት በሚባል ተቋም የተወሰነ እውቀት ቀስሟል።
ጥበብ በመንገድ ላይ
በዕለተ መስቀል የተወሰኑ ሥዕሎቹን ይዞ በመስቀል አደባባይ ብቅ ብሏል። በርካታ ህዝባዊ ትዕይንቶች በሚኖሩበት ቦታ ሥራውን ለማሳየትና በቀጥታ እየሠራ ሰዎች ችሎታውን እንዲገነዘቡለት ቢሞክርም ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመጋፈጥ ይገደዳል። ደንብ አስከባሪዎችና ፖሊሶች መንገድ ላይ ያልተፈቀደ ሥራ አትስራ ይሉታል። ብቻ ኤርሚያስ በሥዕል ስራ ብቻ ኑሮውን መደጎም አልቻለም። ሌላ ሥራም ለመስራት ጥረት ያደርጋል።
በአሁኑ ወቅት ከ500 እስከ 600 ብር እየተቀበለ የሰዎችን ፎቶ በፖርተሬት መልክ በስዕል ይሰራዋል። ኮላ እና ነጭ ቀለም ቀብቶ ሸራ ወጥሮ በአቦጀዴ ጨርቅ በወረቀት ላይ ያሉ ፎቶዎችን ወደ ሥዕል ይቀይራቸዋል። ምንም እንኳን ሥራው አዋጭ ባይሆንም ለእርሱ ውስጣዊ ስሜቱን ስለሚገልፅለት ደስተኛ ነው።
ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያ ፕሬሚርሊግ ጨዋታ ሲኖር የተመለካቾችን ፊት አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለም እየቀባ አምስት ብር እየተቀበለ ኑሮውን ይደጉማል። በዚህ ስራም ከ600 እስከ 800 ብር ያገኛል። ነገር ግን ጨዋታ በሌለ ጊዜ ገቢው ይቆማል። ግን ይህን ሁሉ የሚያደርገው የሥዕል ሥራውን ፍላጎት በአንድም በሌላም ለመግለፅ እንጂ ለብሩ አሊያም ደግሞ አዋጭ ሆኖ አይደለም። ‹‹እኔ ምንም ዓይነት ሥራ አልንቅም›› የሚለው ኤርሚያስ ህይወትን ለመምራት ብዙ ውጣ ውረዶችን እያለፈ መሆኑን ይናገራል።
ጠንካራ ጓደኛ
መቅደስ አለማየሁ እንደ ስሟ የተቀ ደሰችና የግራ ጎኑ ለመሆን እየተንደረደረች ያለች እንስት ናት። እርሷ የግራ ጎኑ ብቻ ሳትሆን በሥራ ከጎኑ ሆና የምታበረታታው ናት። ለዚህም ያመሰግናታል፤ በሞራሏ ይበረታታል። የእርሷ ማበረታቻዎችና ጠን ካራ ቃላት በሥራው ላይ እንዲጠነክርና ለነገ ሕይወቱ ብዙ ብርሃን እንዲያይ እያደረገው ነው። እርሱ ለቤቱ ሁለተኛ ልጅ ነው። አራት ታናናሾች አሉት። እናቱ ጉልት እየሰሩ ቤተሰባቸውን ይደጉማሉ። አባቱ ጠንካራ እና ታታሪ ኦዲተር የጥንካሬው ምንጭ እንደሆኑ ይናገራል።
ሥዕል ቢዝነስ ቢሆን!
በኢትዮጵያ ውስጥ የሥዕል አብዮት ገና አልተነሳም የሚለው ሰዓሊ ኤርሚያስ ብዙ ነገሮች ጎደሎ መሆናቸውን ይናገራል። የሥዕል ትምህርት ቤቶች ከማነሳቸውም በተጨማሪ እንደ አገር የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው። ቢዝነስ ከመሆን አኳያም ገና ይቀረዋል። ሥዕል እንደሌሎች ጥበባት ቢዝነስ ቢሆን ብዙዎች ይለወጡ ነበር ይላል።
በአሁኑ ወቅት ኤርሚያስ ግንበኛ፣ ቀለም ቀቢ፣ ሰዓሊ፣ አሽከርካሪ፣ በያጅ፣ የእንጨት (ፈርኒቸር) ብቻ ብዙ ሙያ ባለቤት ነው። ይሁንና ይህን ሁሉ ሙያ ቢይዝም በሚፈልገው መንገድ አሊያም ደግሞ በሙያው ሊሠራ አልቻለም። በጥበብ ሊገፋ ቢፈልግም ብዙ ውጣ ውረዶች አሉበት። ከምንም በላይ ግን ሥዕሎቹ ስለሚያስደስቱት ተስፋ አይቆርጥም። ሥዕል የሙሉ ጊዜ ሥራው አድርጎ ለመንቀሳቀስ ሲያስብ ደግሞ ፕሮፌሽናል ላልሆነ ሰው ከባድ እንደሆነ ይናገራል።
ገጠመኝ
በመንገድ ላይ ሥዕል እየሰራ ሳለ በርካታ ሰዎች ስልክ ይቀበሉታል፤ ግን አይደውሉም። የሥዕሉን ዋጋ ይጠይቁታል እርሱም በጣም ቆንጆ የሚለውንና ብዙ ልፋት ያወጣበትን ሥዕል እስከ 1ሺ500 ብር ይጠራላቸዋል። ግን ሰዎች በመገረም ለሥዕል ይህን ያህል ብር እያሉ ሲያንጓጥጡ እና ሲያሾፉበት ብዙ ጊዜ እየሳቀ ያልፋል።
በአንድ ወቅት ደግሞ መገናኛ አካባቢ አንድ የዕደ ጥበብ መሸጫ ቤቶች ያሉት ሰው ሦስት ሥዕሎችን ይወስድና የሁለቱን ዋጋ ብቻ ከፍሎ ሌላውን ሂሳብ ከልክሎታል። ከመናገሻ መገናኛ በተደጋጋሚ ተመላልሶ ቢጠይቀውም ብሩን ሊሰጠው አልቻለም። እርሱም አይ የሰው ነገር፤ ተከድኖ ይብሰል ብሎ ውስጡ እርር እያለ ትቶታል። ብዙ ጊዜ በሥራ ላይ ሳለ በስንት መከራ ገንዘብ አጠራቅሞ የገዛት ቀለም ፈሳበት ተናዷል፤ አይ አጋጣሚ እያለ በራሱም ተገርሟል። ኤርሚያስ በዚህ ሥራ ላይ የሰዎች አስተያየት በራሱ ከገጠመኞች በላይ እንደሆነ ይናገራል።
ነገስ?
ኤርሚያስ ትናንትን በውጣ ውረድ አልፏል፤ ዛሬ በእጅጉ ይተጋል፣ ነገን ደግሞ በእጅጉ ይናፍቃል። ለራሱ ብቻ ሳይሆን በርካቶችን በሥዕል ጥበብ ሊያስደስታቸው ይፈልጋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሥዕል አብዮት የሚመጣበትን ቀን እየናፈቀ የራሱን ሥራ ለማስተዋወቅ ብዙ ነገሮችን ያስባል። ይህ ወጣት ዕድሜው ወደ 28 ዓመት ለመግባት እየተንደረደረ ነው። የኖረውን ብቻ ሳይሆን የሚኖረውን ሕይወት በጥበብ ያማረ እንዲሆን ይፈልጋል። ስዕል የህመም ፈውስ የሚሆንበትን ጊዜ ይናፍቃል። የሆነው ሆኖ ሥዕል የእርሱን የአዕምሮ ሠላም ሰጥቶታል።
ወጣት እና ጥበብ በተገቢው አውድ ላይ የሚገናኙበት ጊዜ ይኖር ዘንድ ምኞቱ ነው። መንግስትም መሰል ወጣቶችን የሚያበረታታበት አውድ ቢኖር ፍላጎቱ ነው። ኤርሚያስ በውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈች ሕይወት አንድ ቀን የሚገባትን መንበር ማግኘቷ እንደማይቀር ይናገራል። ታዲያ በፈተናዎች ውስጥ ያሉ ወጣቶችን ዓላማ ሊኖሯቸውና ነገንም አሻግረው ሊመለከቱ እንደሚገባ ይመክራል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር