ባለፈው ሳምንት እትማችን የነቀርሳ በሽታ ምንነት፤ መተላለፊያ መንገዶቹንና መከላከያ ስልቶችን በተመለከተ የመጀመሪያውን ክፍል ማስነበቤ ይታወቃል፡፡ለዛሬው መድሃኒት የተላመደ የነቀርሳ በሽታን ከኤች ኤቪ ጋር ያላቸውን ቁርኝት እንመለከታለን፤ መልካም ንባብ፡፡
ብዙውን ጊዜ በማህበረሰብ ውስጥ የነቀርሳ በሽታ የሚባለው ሰዎች የሚያስል በሽታ ሲይዛቸው የሚሰጡት ስያሜ ነው፡ ፡ይሁን እንጂ ነቀርሳ በርካታ ምልክቶች አሉት፤ ማለትም ከሰውነት አካላት ውስጥ የትኛውን አካል ማጥቃቱን መሰረት በማድረግ በርካታ መሆኑን ያሳያል፡፡በአጠቃላይ ነቀርሳ ከሰውነት ክፍሎች ውስጥ ማንኛውንም የሰውነት ክፍል ሲይዝ የሚያሳያቸው ምልክቶች፡ ማታ ማታ ያልባል፣ ምግብ ያስጠላል፣ የሰውነት ክብደት ይቀንሳል (ያከሳል)፣ የሰውነት ትኩሳት እና የጤንነት ስሜት አለመሰማትን ያሳያል፡፡ከላይ ያናሰናቸው ምልክቶች በሌሎች በሽታዎች ላይም ሊታዩ ስለሚችሉ በራሳችን ላይ ስናይ ወደ ሐኪም በመሄድ ለይተን መታከም ግዴታ ነው፡፡
የነቀርሳ በሽታ ከሌሎች በሽታዎች በምን ይለያል?
የነቀርሳ በሽታ ብዙውን ጊዜ ከሌሎች በሽታዎች ጋር ስለሚመሳሰል ታማሚዎች መድሃኒት ከመጀመራቸው በፊት አስቀድሞ ምርመራ ይደረግላቸዋል፡ ፡ይህም ነቀርሳው ባጠቃው የሰውነት ክፍል ላይ መሰረት በማድረግ ይሆናል፡፡ የሳምባ ነቀርሳ ያለበት እና የሚያስል ሰው ሲያስለው የሚወጣውን አክታ በመውሰድ ይህንን የነቀርሳ ባክቴሪያን ማይክሮስኮፕ በመጠቀም ማየት እና የደረት ራጅ (x-ray) በማንሳት ሳምባ መጎዳቱን በማየት ይመረመራል፡፡የዕጢ፣ የሊንፍ ነቀርሳ ያለበትም እንዲሁ የተጎዳውን ዕጢ ላይ ትንሽ ናሙና በመውሰድ ወይም ሙሉ በሙሉ ቆርጦ በመውሰድ መመርመር ይቻላል:: ይሁን እንጂ ማንኛውም ምርመራ ይህንን የነቀርሳ በሽታ መቶ በመቶ መለየት ስለማይችል አንዳንድ ጊዜ ሐኪም ወይም የሚያክመው ባለሙያ ወስኖ መድሃኒት ማስጀመር አለበት፡፡
የነቀርሳ በሽታ በምን አኳኋን ይታከማል?
የነቀርሳ በሽታ እንደ ሌሎች ኢንፌክሽኖች መድሃኒት ያለው ሲሆን ለነቀርሳ የሚሰጠው መድሃኒት እንደሌሎች ኢንፌክሽኖች በሳምንታት የሚሰጥ ሳይሆን ለወራት የሚቀጥል ነው፡፡የያዘው ነቀርሳ ከመድሃኒት ጋር ያልተላመደ ነቀርሳ ከሆነ ብዙውን ጊዜ መድሃኒቱ የሚወሰደው ለ6 ወራት ነው፡፡ይህ የሚሰጠው መድሃኒትም በመጀመሪያዎቹ 2 ወራት ከ4 አይነት ንጥረ ነገሮች የተቀመመ መድሃኒት የሚወሰድ ሲሆን ለቀሩት 4 ወራት የሚወሰደው መድሃኒት ደግሞ ከ2 አይነት ንጥረ ነገሮች የተቀመመ መድሃኒት ነው፡፡
የነቀርሳ መድሃኒት በአግባቡ አለመውሰድ ምን ያስከትላል?
ለነቀርሳ የተሰጠውን መድሃኒት በፍፁም ማቋረጥ ትክክል አይደለም፡፡ ለነቀርሳ የሚሰጡ መድሃኒት አንዳንዴ ከባድ ጉዳት (Side effects) ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ከነዚህም ውስጥ የሽንት መቅላት፣ ማስታወክ፣ የሆድ ህመም፣ የእግር ማቃጠል፣ በቆዳ ላይ አንዳንድ ምልክቶችን ማሳየት፣ የዓይን ቀለም መለወጥ፣ የጆሮ የመስማት አቅም መቀነስና እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ይህንን የነቀርሳ መድሃኒት የሚወስድ ሰው እነዚህን ምልክቶች በራሱ ላይ ካየ ወደ ሐኪም ቤት ሄዶ ከጤና ባለሙያ ጋር መወያየት አለበት እንጂ በፍፁም መድሃኒቱን መቋረጥ የለበትም፡፡
የነቀርሳ መድሃኒት የሚወስድ ሰው መድሃኒቱን ሳያጠናቅቅ ቢያቋርጥ ወይም የጤና ባለሙያ በሰጠው ትእዛዝ መሰረት መድሃኒቱን ካልወሰደ፣ የነቀርሳ ባክቴሪያው ከነቀርሳ መድሃኒቱ ጋር የመለማመድ ዕድሉ ከፍ ይላል፡፡ከመድሃኒት ጋር የተላመደ የነቀርሳ በሽታን ለማከም ደግሞ ከ18 ወራት እስከ 24 ወራት (2 ዓመት) መድሃኒቱን መውሰድ ስለሚያስፈልግ አስቀድሞ መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው፡፡
ከመድሃኒት ጋር የተላመደ የነቀርሳ በሽታ ማለት ምን ማለት ነው?
ከመድሃኒት ጋር የተላመደ የነቀርሳ በሽታ ሲባል ይሰማል፡፡የነቀርሳ በሽታ እንደ አንዳንድ በሽታዎች ከነቀርሳ መድሃኒት ጋር ስለሚላመድ መድሃኒቱ ቢወሰድም ላያድን ይችላል፡፡ይህ ደግሞ በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ችግር ያስከትላል፡፡ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ አንድ ሰው ከነቀርሳ መድሃኒት ጋር የተላመደ የነቀርሳ በሽታ ቢይዘው ይህ በሽታ የሚተላለፍባቸው ሰዎችም በዚህ አይነቱ በሽታ (ከመድሃኒት ጋር የተላመደ የነቀርሳ በሽታ) ይያዛሉ፡ ፡ከመድሃኒት ጋር የተላመደ የነቀርሳ በሽታ በአስከፊነቱ የሚበላለጥ ሲሆን በጣም ከባድ የሆነው ከበርካታ የነቀርሳ መድሃኒቶች ጋር የተላመደ ከሆነ ነው፡፡ ከመድሃኒት ጋር የተላመደ የነቀርሳ በሽታ ከመድሃኒት ጋር ካልተላመደ የነቀርሳ በሽታ ይበልጥ የረጅም ጊዜ ህክምና የሚፈልግ እና እንደዚሁም ህይወት/ነፍስ የመቅጠፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
ከመድሃኒት ጋር በተላመደ የነቀርሳ በሽታ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰዎች፡ በነቀርሳ በሽታ ታመው ታክመው ለሁለተኛ ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ የተመላለሰባቸው ሰዎች፣ የሚሰጣቸውን መድሃኒት በትክክል ወይም በአግባቡ የማይወስዱ ሰዎች፣ በሥራቸው ምክንያት የነቀርሳ በሽታ ካለባቸው ሰዎች በድግግሞሽ ሊገናኙ የሚችሉ ሰዎች (እንደ የጤና ባለሙያዎች ያሉ ሰዎች) በተደጋጋሚ የችግሩ ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የኤች አይቪ /ኤድስ እና የነቀርሳ በሽታ ግንኙነት ምንድነው?
የኤች አይቪ /ኤደስ በሽታ የሰውን ህይወት /ነፍስ የሚቀጥፈው በራሱ ሳይሆን ለሌሎች በሽታዎች በማጋለጥ ነው፡፡ ይህንም የሚያደርገው ከሰውነታችን ውስጥ በሽታ የመከላከል አቅምን (Immunity) የተባለው የሰውነት ሥርዓት እንዳይሠራ በማድረግ ጤናማ ሰዎችን በማያጠቁ በሽታዎች የመጎዳታችን /የመጠቃታችን ዕድልን ከፍ ያደርጋል፡፡የኤች አይቪ በሽታ የሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅምን የሚቀንስ ሲሆን በተለይም ለረጅም ጊዜ ሰው ላይ የቆየ ከሆነ እና ህክምና ያላገኘ ከሆነ ችግሩ የበለጠ የገዘፈ ይሆናል፡፡
ኤች አይቪ የፈጠረላቸውን ዕድል በመጠቀም የሰው ልጆችን ከሚያጠቁ በሽታዎች አንጋፋው የነቀርሳ በሽታ ነው፡፡ይህም የነቀርሳ በሽታ የሳምባ ነቀርሳ በሽታ ብቻ ሳይሆን ከሳምባ ነቀርሳ ውጭ ያሉ የነቀርሳ በሽታዎችም በኤች አይቪ በሽታ በተያዘው ሰው ላይ በስፋት ይታያሉ፡፡
ስለዚህ የነቀርሳ በሽታ ያለበት ሰው ለኤች አይቪ በሽታም መመርመር እና በሽታው ከተገኘበትም መታከም ይኖርበታል፡፡የነቀርሳ በሽታ ከኤች አይቪ በሽታ ጋር በመደጋገፍ ሰውን እንዳያጠቃ ለማድረግ ይህ የኤች አይቪ በሽታ በሰው ላይ ሳይቆይ (ጤናማ ሆነው እያሉ) በመመርመር እራስን ማወቅ እና ለኤች አይቪ የሚሰጠውን መድሃኒት በትክክል /በአግባቡ መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ይህም ለኤች አይቪ የሚሰጠው መድሃኒት በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ በሽታን የሚከላከሉልን የደም ህዋሶች / ሴሎች ብዛታቸው ስለሚጨምር ነው፡፡ይህ መድረክ የነቀርሳ በሽታ ብቻ ሳይሆን ከኤች አይቪ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ለሎች በሽታዎችንም ለመከላከል ይጠቅመናል፡፡
ምንጭ
1. Center for disease control (CDC): Tuberculosis (TB) disease, risk factors and symptoms
2. Harrisons Principles of Internal Medicine: part 5, section 8: Mycobacterium disease, tuberculosis
3. Up To Date: Clinical manifestations and evaluation of pulmonary tuberculosis
4. World Health Organization (WHO): prevalence of tuberculosis
ዶ/ር ጉርሜሳ ሂንኮሳ
አርሲ ዩኒቨርሲቲ
ሆራ ቡላ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
ጌትነት ተስፋማርያም