አዲስ አበባ፡- የኢህአዴግ ውህደት መዘግየት እህት ድርጅቶቹ እርስ በእርሳቸው እንዳይተማመኑና አንዱ በሌላው ላይ ጣት እንዲቀሳሰር ማድረጉን የደኢህዴን አባላት ገለፁ፡፡
የደኢህዴን ፅህፈት ቤት አባል የሆኑ የደቡብ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማህበራት ክላስተር ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ሚኖቶ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ የውህደቱ መዘግየት በእህት ድርጅቶች መካከል ያለመተማመን እና ያለመግባባት እንዲፈጠርና አንዱ በሌላኛው ላይ ጣት መቀሳሰርን አስከትሏል፡፡ያለመተማመኑ ደግሞ ወደጠላትነት ፍረጃ እንዲገባና በአገሪቱ ውስጥ አሁን እየተስተዋሉ ያሉ ቀውሶች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡
እንደአባላቱ ገለፃ፤ የውህደቱ መዘግየት እህት ድርጅቶቹ በውስጣቸው ያለውን ችግር ከመፍታት ይልቅ አንዱ ከሌላው የሚለየውን አጥር እንዲያበጅ አደርጓል። ይህ አይነት አካሄድም ለኪራይ ሰብሳቢነት፤ ብሎም ላለመተማመን በር ከፍቷል፡፡አለመታዘዝና የመሳሰሉት ነገሮች እንዲያቆጠቁጡና ምንም እንኳን ግንባሩ መልካም ዓላማ የነበረው ቢሆንም ዜጎች ግንባሩን እንዲጠሉ አድርጓል፡፡ይህ የሚስተካከል ከሆነና ውህደቱ ከተካሄደ ደግሞ ዜጎች ከድርጅቱ ጐን ይቆማሉ፡፡
አቶ ብርሃኑ እንደተናገሩት፤ ኢህአዴግ ቀደም ሲል ሲያስቀምጣቸው ከነበሩ ዓላማዎች አንዱ ውህደት ነው፡፡ አንዳንዶች መዋሃድ የግንባሩ ስርዓት የሆነውን ፌዴራሊዝምን የሚያጠፋ አድርገው ቢናገሩም፤ ፌዴራሊዝምን ይበልጥ የሚደግፍ እንጂ የሚፃረር አይደለም፡፡ የፌዴራሊዝም እሴት ራስን በራስ የማስተዳደር፤ እንዲሁም በአካባቢው ያለውን ማህበረሰብ ለልማት የማንቀሳቀስ ሂደት ነውና ይህ ውህደት ፌዴራሊዝምን በምንም አይነት ሁኔታ የሚነካ አይደለም፡፡
አቶ ጥላሁንም በበኩላቸው፤ ‹‹አንዳንዶች እንደሚሰጉት መዋሃድ የተማከለ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ የዜጎችን መብትም የሚደፈጥጥ አይደለም፡፡ ራስን በራስ በማስተዳደሩ በኩልም ችግርም አያመጣም፡፡ ውህደቱ ኢህአዴግ የሚታወቅበትን የፌዴራሊዝም ስርዓት የበለጠ የሚያግዘው እንጂ የሚፃረረው አይሆንም፡፡ ኢህአዴግ በዋናነት የያዘውን የብሄር ብሄረሰቦችን መብትና እኩልነት በአግባቡ የሚያስኬደው ነው።›› ብለዋል፡፡
ሁለቱም አባላት የመዋሃዱን ፋይዳ ሲናገሩ እንዳብራሩት፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያን ለህዝብ ቀድሞ መምራት የግድ ይላል፡፡ህዝቡ ከቀደመ በኋላ ከኋላ የሚከተል የፖለቲካ ፓርቲ መኖር የለበትም፡፡ህዝቡ በአሁኑ ሰዓት ስለአንድነት እየሰበከና በአንድነት ይህቺን አገር ምሩ በማለት ላይ ነው፡፡
ስለሆነም፤ ከህዝቡ ስሜት ቀድሞ ነው ውህደትን በማድረግ መምራት የሚጠበቀው፤ ፋይዳውም ህዝቦችን ከጫፍ እስከጫፍ በአንድነት ስሜት በአንድ ልብ እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል፤ ከጋራ መተማመን ውስጥም ያስገባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ የአገራቸውን ሉዓላዊነት የሚያረጋግጡበት ተጨማሪ እሴት ይሆናቸዋል፡፡በተጨማሪም፤’ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ግንኙነት የሕዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ ያግዛል፡፡
በውስጠ ድርጅት የታዩትን ጉድለቶችና ክፍተቶች ማረም በሚያስችል አግባብ ለመሄድም ያግዛል፡፡ከዚህም በላይ የአጋርም ሆነ የእህት ድርጅቶችን ተመጣጣኝ የሆነ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያጎለብታል፡፡ለምሳሌም ደቡብ ክልል ላይ ያለ የአዴፓ አባል የሚያስበው ስለአማራ ክልል ሳይሆን ከሌሎችም ጋር ሆኖ እንደ ኢህአዴግ ስለሚሆን የየብቻ አስተሳሰብን የሚያስቀር ነው፡፡
‹‹የደቡብ ክልል ለውህደቱ የራሱ የሆነ ልምድ አለው፡፡›› ያሉት አቶ ብርሃኑ እንደገለፁት፤ ደቡብ ቀደም ሲል በርካታ ድርጅቶች የነበሩበት ክልል ነበር፡፡ከማንነት አኳያ በጣም የተሳሰሩና የተዛመዱ እንደመሆናቸው መጠን የተለያየ ሆኖ ከመጓዝ ይልቅ አንድ መሆንን በመምረጥ ደኢህዴንን በመመስረት ጠንካራ ሆነው በጋራ ተዋህደዋል።
አሁን ደግሞ አራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች መርሃግብራቸው፤ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስርን ለማስፈፀምና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችልና ዓላማቸውም ተመሳሳይ እስከሆነ ድረስ አገራዊ አንድነትን፤ እንዲሁም አገራዊ ፓርቲን መመስረታቸው ታሪካዊ ግዴታም ጭምር ነው፡፡
በኢህአዴግ ቤት ውስጥ ውህደት አዲስ ሐሳብ አይደለም፡፡ውህደቱ አራቱን እህት ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን አጋር ድርጅቶችንም ወደ ኅብረት እንደሚያመጣ ቀደም ሲልም የታቀደ ጉዳይ ነውና ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2012
አስቴር ኤልያስ