አዲስ አበባ፡- የከባድ ጭነት ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ገደብ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት አጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጅሬኛ ሂርጳ ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የከተማዋን ትራፊክ እንቅስቃሴ ለማሳለጥና አሁን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች የእንቅስቃሴ ገደብ ላይ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡
በተሻሻለው መመሪያ መሠረትም፤ ማንኛውም የከባድ ጭነት ተሽከርካሪ ከጠዋቱ 12፡30 እስከ 4፡00 ሰዓት እና ከቀኑ ከ10፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ካለው ጊዜ ውጪ መንቀሳቀስ የሚፈቅድ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት እስከ ቀኑ 10፡00 ሰዓት ድረስ በከተማዋ ውስጥ መዘዋወርና ማንኛውንም አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም፤ ቅዳሜ፤ እሁድና የበዓል ቀናት ማንኛውም የጭነት ተሽከርካሪ ያለምንም መንቀሳቀሻ ፍቃድ በየትኛውም ሰዓት ወደ ከተማዋ መግባትም ሆነ መንቀሳቀስ፤ እንዲሁም ዕቃ የመጫንና የማራገፍ ተግባር ማከናወን እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም፤ የከተማዋ ትራፊክ ፖሊስና የደንብና ቁጥጥር አካላት የተደረገውን ማሻሻያ በመረዳት እንደወትሮው ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ በከተማዋ ውስጥ ሰላማዊና ምቹ የሆነ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር ጥረት እንዲያደርጉ ዋና ዳሬክተሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኤጀንሲው የመንገድ አጠቃቀም ሥርዓት የሚያሻሽል የጭነት፣ ማሽነሪዎችና መሰል ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁጥር 03/2011 መነሻ በማድረግ በከተማዋ የጭነት ተሽከርካሪዎች የሚፈጥሩትን ተፅዕኖ ለመቀነስ መመሪያ አዘጋጅቶ ከሰኔ 30/2011 ዓ.ም ጀምሮ በተግባር ላይ ማዋሉ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 30
ተገኝ ብሩ