‹‹ዘንድሮ የሚካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?›› የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ብዙዎች ናቸው። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ እንደምትገልፀው ቦርዱ እስከ አሁን 139 ፓርቲዎችን መዝግቧል። ከእነዚህ መካከልም ለመወዳደር የሚያበቃ መስፈርት አሟልተው በቦርዱ የእውቅና የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው 68 ብቻ ሲሆኑ ቀሪዎቹም በሂደት ያሟላሉ ተብለው ይጠበቃሉ።
‹‹ላለፉት አምስት ዙሮች ከተካሄዱት የምርጫ ተሞክሮዎች አኳያ በመስከረም ወር የሚጠበቅ ዝግጅት የለም›› የምትለው ሶሊያና ከዚህ በኋላ ግን የምርጫ ዝግጅት መርሃ ግብሮች በቅደም ተከተል ይከናወናሉ። በአዲስ አደረጃጀት ሥራውን በማከናወን ላይ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፉት ስምንት ወራት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል የማስፈፀም አቅሙን ለማሳደግ የወሰዳቸው እርምጃዎች ቀዳሚ ሲሆኑ፣ በአሠራር የሚጠበቅበትን ተግባር በተሻለ ለመፈፀም አሁንም በሰው ኃይልና በአሠራሩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብላለች።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በምርጫ ቦርድ በኩል ፍጥነት ያለው ሥራ እየተሠራ ነው ብለው አያምኑም። በነበረው ተሞክሮ በዚህ ወቅት አልፎ አልፎ ድርድሮች እንደሚካሄዱ፣ ቦርዱም የጊዜ ሰሌዳውን ስለሚያሳውቅ ፓርቲዎች የቦርዱን መረጃ መሰረት አድርገው እንደሚያንቀሳቅሱ ያስታውሳሉ።
ቦርዱ አሁን ባለው እንቅስቃሴው የወሰደው የማሻሻያ እርምጃና የአደረጃጀት ለውጥ ወረዳ ላይ አልደረሰም። የፀደቀው የምርጫ ምዝገባና የሥነ ምግባር አዋጅ በአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀባይነት አላገኘም ሲሉ ይገልፃሉ።
የፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን ሀሳብ የሚጋሩት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ቦርዱ በአዲስ አደረጃጀት መዋቀሩና እስካሁንም ባከናወናቸው ተግባራት የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀቱን በመልካም ጎን የሚያዩት ቢሆንም የተሟላ በቂ ዝግጅት አድርጓል ለማለት አልደፈሩም።
በዚህ ወቅት ቦርዱ አስፈፃሚዎችን የማደራጀት ተግባር አጠናቅቆ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የምርጫ ሰሌዳ ሊያውቁ የሚገባበት ወቅት መሆን ነበረበት ያሉት አቶ ናትናኤል ቦርዱ መዋቅሩን በየወረዳዎች አለመዘርጋቱ በጊዜ ሰሌዳው ተጽዕኖ እንደሚኖረው እንደምክንያት ያነሳሉ። የሚከናወነው ሥራ ምርጫ ለማካሄድ ብቻ መሆን እንደሌለበትና እውነተኛ ለሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሽግግር መደላድል መፈጠርና ከዚህ ቀደም በምርጫው ላይ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን የሚያስቀር መሆን እንዳለበት ያምናሉ።
ፕሮፌሰር መረራ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉት የፀጥታ ችግሮችም ለምርጫው ሥጋቶች እንደሆኑና ችግሮች የሚታዩባቸውን ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ጉጂና ቦረና አካባቢዎችን ይጠቅሳሉ። በገዥው ፓርቲ በኩል ለምርጫው ያለው ዝግጁነት ግልጽ ሆኖ አለመታየትና ገመድ ጉተታ የሚመስል ነገር በአባል ድርጅቶች መካከል መኖር እንዲሁም ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብረው ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት ገና ብዙ ሥራ እንደሚፈልግ ያስረዳሉ። ክፍተቶቹም ምርጫው ይካሄድ የሚሉና አይካሄድ የሚሉ ሀሳቦች እንዲፈጠሩ ምክንያቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
አቶ ናትናኤልም ሀሳቡን በማጠናከር መንግሥት በሀገሪቷ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሄድ ዝግጁነቱን በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኩል አረጋግጧል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ያለማንም ሦስተኛ ወገን ጣልቃገብነት በጋራ ተስማምተው በፈረሙት የቃልኪዳን ሰነድ መሰረት እንቅስቃሴያቸው በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ መሆን አለበት ሲሉ መክረዋል።
የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚያደርገው የምርጫ ዝግጅት ውጤታማ የሚሆነው ሰላም በሀገሪቷ ውስጥ ሲረጋገጥ እንደሆነ ያሰምሩበታል። ‹ደጋፊ ስላለ ብቻ ሳይሆን ሀገር ስትኖር ነው ምርጫ የሚካሄደው። ሰላም በሌለበት ስለምርጫ ለማውራት ከባድ ነው› በማለት ፓርቲያቸውም በሀገር ደረጃ ሰላም ላይ መሠራት እንዳለበት እንደሚያምን ተናግረዋል።
ወይዘሪት ሶሊያና በበኩሏ ምርጫው ፍትሐዊ፣ ግልጽና ተአማኒ እንዲሆን የሚከናወኑት የማሻሻያ ተግባራት ያልተቋረጠ መሆን እንዳለበት ቦርዱ ቢያምንም ለህዝብ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ እስካሁን የተሠሩትን ሥራዎች በስኬት ያነሳሉ። የቦርዱ ግብም ምርጫው በመራጩ ህዝብ ተአማኒነት እንዲኖረው፣ ነፃና ሰላማዊ እንዲሆን ማስቻል እንደሆነም ትናገራለች።
አስተያየት ሰጭዎቹ እንዳሉት ምንም አይነት ሥጋት ቢኖርም ሀገራዊ ምርጫ መካሄዱ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ያምናሉ። በመሆኑም ከምርጫው ዝግጅት ውስጥ ሰላም ትልቅ ቦታ ካልተሰጠው አጨራረሱ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2012
ለምለም መንግሥቱ