አዲስ አበባ፡- ከወርቅ የሚገኘው የወጪ ንግድ ገቢ በስድስት ዓመት ውስጥ ከ400 ሚሊየን ዶላር በላይ ቅናሽ ማሳየቱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች የማዕድን ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ተወልደ ብርሃን አባይ እንደተናገሩት፤ በ2005 ዓ.ም ከወርቅ የወጪ ንግድ 445 ሚሊየን ዶላር የተገኘ ሲሆን በ2011 ወደ 32 ሚሊየን ዶላር በታች ወርዷል።
ከወርቅ የሚገኘው ገቢ እንዲያሽቆለቁል ካደረጉት ምክንያቶች ዋነኛው የኮንትሮባንድ ንግድ ነው ያሉት አቶ ተወልደ ብርሃን፤ የወርቅ ምርት በሚገኝባቸው አካባቢዎች ሕገ ወጥ ደላሎች መበራከትና ወርቅ የሚረከቡ ማዕከላት በየአካባቢው አለመኖራቸው ለኮንትሮባንድ ንግዱ መስፋፋት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልፀዋል።
በሚኒስቴሩ የገበያ ልማት፣ ትስስርና ትንበያ ዳይሬክተር አቶ በትሩ ሃይሌ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ከጉምሩክ ኮሚሽንና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ አቶ በትሩ ማብራሪያ፤ የወርቅ ግብይት ላይ በሚስታዋሉ ችግሮች ዙሪያ ጥናት ተካሂዷል። ወርቅ በሚመረትባቸው በአንዳንድ አካባቢዎች የግብይት ማዕከላት ባለመኖራቸው ወርቅ ለማስረከብ እስከ 500 ኪሎ ሜትር ለመጓዝ ሲገደዱ ነበር። ይህ ደግሞ የወርቅ ኮንትሮባንድ አንዱ መንስኤ ሆኖ ቆይቷል።
ችግሩን ለመቅረፍ ከብሔራዊ ባንክና ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ወርቅ በሚመረትባቸው አካባቢዎች የግብይት ማዕከላትን የመገንባት ሥራ እየተሠራ ነው። የግብይት አዋጅ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ካለ ህጋዊ የማዕድን ማዘዋወሪያና የንግድ ፈቃድ የሚያዛውሩትንም በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ይረዳል።
በጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ሕግ ተገዥነት ዘርፍ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አሸናፊ ባሳ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲሰራ ቆይቷል። የሀገር ኢኮኖሚ ላይ እያሳደረ ያለውን ጉዳት ከግምት በማስገባት፤ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ከሚሰራው የሕግ የማስከበር ሥራ ባሻገር የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራም እየሠራ ነው።
ኮንትሮባንድን ለመከላከል ለሚደረገው እንቅስቃሴ የህብረተሰቡ ትብብር ወሳኝ ነው ያሉት አቶ አሸናፊ፤ ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል። ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዲችል ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የመጠቆሚያ ስልክ ቁጥርም ይፋ ማድረጉን አንስተዋል። ስልክ ቁጥሩ 638 መሆኑን ያብራሩት አቶ አሸናፊ በዚህ ስልክ የኮንትሮባንድ ንግድን ለሚጠቁሙት ወሮታ እንደሚከፈልም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2012
መላኩ ኤሮሴ