በውብ ተፈጥሮ ያጌጠች፣ የራሷ ፊደልና የዘመን አቆጣጠር ያላት፣ የታላላቅ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ባለቤት፣ የሰው ዘር መገኛ፣ ቀደምት የስልጣኔ ምንጭ፣ በቅዱሳት መጽሐፍት ተደጋግማ የተጠቀሰች፣ ስለ ሰብዓዊነቷና ስለደግነቷ “አትንኳት” የተባለች፣ በክብሯ በመጡባት ላይ ደግሞ በአስደናቂ ጀግንነት ጠላቷን አንበርክካ አንፀባራቂ ድልን የተቀዳጀች አኩሪ ታሪክ ያላት አገር ናት-ኢትዮጵያ።
በተለይም ደግሞ ሁኔታዎች ተመቻችተውላት በአንፃራዊነት በጉልበት በልጦ በመገኘቱ እንደሚጠፋ እንስሳ በኃላፊ ጠፊ ጡንቻው ተመክቶ፣ በሳጥናኤላዊ “የእኔ እበልጣለሁ” ትዕቢቱ በሰው ልጆችና በሰውነት ላይ ይቅር የማይባል ወንጀል በፈፀመው አምባገነን ወራሪ ላይ የተቀዳጀችው ማንም ያልቻለው ዘመን አይሽሬ ድል በእርግጥም ኢትዮጵያን የዓለም የነፃነትና የእኩልነት ተምሳሌት መሆኗን አስመስክሯል።
ስለሆነም ዛሬም ነገም ዓለም ሁሌም ስለ ኢትዮጵያ በአድናቆት ቢዘምር እውነትና የእውነት መመዘኛ ሚዛነ-ህሊናው አስገድዶት እንጅ ማንም፤ እኛ ልጆቿም ብንሆን ከሌላው የተለየ ኢትዮጵያን አብዝተን እንድናደንቅ ልዩ ጥቅም ተጠብቆልን ወይንም ማበረታቻ ተሰጥቶን አይደለም። እንዲያውም እኛ ልጆቿስ (በተለይም ቀሽሞቹን ሰምቶ በቀሽሙ የብሔር ፖለቲካ ከታላቅነቱ የቀነጨረው የእኔ ትውልድ) “ውበቷ አይታያችሁ፣ ሚስጥሯ አይገለጽላችሁ” ተብለን የተረገምን ይመስል እንኳንስ ልናደንቃት በሚገባት ደረጃ የምናውቃትም አይመስለኝም። ኧረ እንዴውም በክፉ መሪዎቻችን ምክንያት የተጣባን ክፉ አጋንንት እስኪለቀን ድረስ አገራችንን ማወቁ፣ መውደዱና ማድነቁ ይቅርና ስም አጠራሯ የሚያስጠላንና ጭራሹንም የእኛ ባትሆን የምንመኝም አንጠፋም።
እናም “በእጅ የያዙት ወርቅ” እንዲሉ አበው እኛ ዜጎቿ እንደ ቀላል ስለምንመለከታት ታሪኳን ማንነቷን ለማወቅ ያን ያህል ትኩረት ባይኖረንም ዓለም ግን ኢትዮጵያን ሁሌም በልዩነት ይመለከታታል። ሆኖም በእውነታው ላይ ተመስርተው ውበትን ለውብነቱ ብቻ የሚያደንቁ ቅኖች እንዳሉ ሁሉ ከአንገት በላይ አድናቂ መስለው ሁሌም የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ ብቻ ለማሳካት በማር የተለወሰ መርዛቸውን ከማቀበል የማያርፉ ውስጥ ለውስጥ የሚሄዱ ቅንቅን አድናቂዎች መኖራቸውንም መጠርጠር ይገባል። ስለሆነም በአገራችን ታላቅነትና ተደናቂነት መኩራታችንና መደሰታችን እንዳለ ሆኖ አድናቂዎቻችን እያመሰገንን የአድናቆቱን ውስጠ ወይራ ደግሞ እየመረመርን እንክርዳዱን ከምርቱ እየለየን መሄድ ይጠበቅብናል። የዛሬው የዕይታ መነጽሬም በዚሁ ላይ ያነጣጠረ ይሆናል።
ቅንቅኑ የኢትዮጵያ አድናቂ
ኦሊቨር ሮቢንሰን ይባላል። መቀመጫውን በልዕለ ኃያሏ አገር አሜሪካ ያደረገው በምህፃሩ ሲ.ኤን.ኤን በመባል የሚታወቀው ዝነኛ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ላይ የሚሰራ ታዋቂ ጋዜጠኛ ነው። የሲ.ኤን.ኤን የጉዞ አምድ ዋና አዘጋጅ ሲሆን በየክፍለ ዓለሙ እየተዘዋወረ በየአገሩ የሚገኙና የአገራቱ ልዩ መታወቂያ የሆኑ ድንቃ ድንቅ ጉዳዮችን ለዓለም ህዝብ ያስነብባል (ያስተዋውቃል) ቢባል ይቀላል። ታዲያ ተጓዡ የሲ.ኤን.ኤን ጋዜጠኛ ሚስተር ሮቢንሰን እነ ሄሮዳተስ የጎበኟትን፣ እነ ሆሜር የተቀኙላትን፣ እነ ፓልስትራክ ጀብዱዋን የተረኩላትን የእኛዋን ቀደምት እመቤት ኢትዮጵያንም የመጎብኘት ዕድል ገጥሞታል። በዚህም ታላቋን አገር ተዟዙሮ ጎብኝቶ፣ ባየው ነገር ሁሉ “ተደስቶ” እና ተደንቆ ተመለሰ። ተደንቆም ብቻ አልቀረም “ብዙ አይቻለሁ፣ ኢትዮጵያ ግን ልዩ ናት” በማለት ይመስላል “ኢትዮጵያን ከዓለም ልዩ የሚያደርጓት አስሩ ነገሮች” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያን ልዩ አገርነት “በአድናቆት” ተሞልቶ በሲ.ኤን.ኤን የጉዞ አምዱ ላይ ጽፎ ለዓለም ህዝብ አስነበበ።
ሆኖም በእኔ ዕይታ ጋዜጠኛ ሮቢንሰን “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንደሚባለው የአያቶቹ የአውሮፓውያን “የነጭ የበላይነት” በሽታ በዘር ተላልፎበት ይሆን አለያም በተፈጥሮው የሚበልጠውን ማድነቅ የማይችል ደካማ ምቀኛ ሰው ሆኖ ይሆን አላውቅም አድናቆቱ ከላይ እንደጠቆምኩት ፍፁም በመርዝ የተለወሰ ማር ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ምክንያቱም አሊቨር ሮቢንሰን ኢትዮጵያን ከዓለም ልዩ የሚያደርጓት ብሎ ከዘረዘራቸው አስር ነገሮች መካከል በአንደኛ ደረጃ ያስቀመጠው “በዓለም ላይ ምርጥ የሚባሉ የኢጣሊያ ምግብ ቤቶች” የሚል ነው። እንደ ጋዜጠኛ ሮቢንሰን የሲ.ኤን.ኤን ዘገባ አዲስ አበባ ውስጥ በጫጫታማው ማህተመ ጋንዲ ጎዳና ከትሞ የሚገኘው “ካስቴሊ የጣሊያን ምግብ ቤት” ኢትዮጵያ ተለይታ ከምትታወቅባቸው ነገሮች መካከል የመጀመሪያው ነው።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ በጣሊያናዊው ወታደር ፍራንችስኮ ካስቴሊ አማካኝነት በኢትዮጵያ ዋና ከተማ ለተከፈተው ለዚህ ምግብ ቤት “የዓለም ምርጡ የጣሊያን ምግብ ቤትነትን” ማዕረግ የሰጠው በ1967 ዓ.ም ኢትዮጵያ በድርቅ ክፉኛ በተጎዳችበት ወቅት ባደረገው ትልቅ ውለታ “የኢትዮጵያ ወዳጅ” በመባል የሚታወቀው ታዋቂው አየርላንዳዊ ሙዚቀኛ ቦብ ጊዶልፍ ነው ይላል ቅንቅኑ የኢትዮጵያ አድናቂ ጋዜጠኛ ኦሊቨር ሮቢንሰን።
ቦብ በድርቁ ምክንያት በረሃብ ክፉኛ የተጎዱ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹን ህይወት ለመታደግ ከፖፕ ሙዚቃ ንጉሡ ማይክል ጃክሰን (ለማመሳከሪያ የተሰመረ) ጋር በመተባበር ባዘጋጀው “ሁላችንም አንድ ነን” የሚል ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ድግስ እንደ አንጀሊና ጆሊና ብራድ ፒትን የመሳሰሉ ታላላቅ የሆሊውድ ኮከቦች ተገኝተው ለኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲደረግ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ታዲያ ያኔ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አዲስ አበባ በሰነበቱበት ወቅት ቆይታቸውን ያደረጉት በካስቴሊ ምግብ ቤት ነበር። በዚያም ዓለም አቀፋዊ ታዋቂነትን አገኘ ይላል (ለማመሳከሪያ የተሰመረ)። እስቲ ተመልከቱ እንግዲህ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያሳውቃትና ከዓለም ልዩ የሚያደርግ ሌላ ነገር ታጥቶ ለወረራ የመጣ የጣሊያን ወታደር በአምስት ዓመታት የአዲስ አበባ ቆየታው ከርሱን ሊሞላበት የገነባው አንድ ተራ የጣሊያን ምግብ ቤት ልዩ ቅርሷ ሆኖ ማንነቷን ለዓለም ሲያስተዋውቅላት።
የሚገርመው እኮ ኢትዮጵያን ልዩ ከሚያደርጓት አስር ነገሮች ዋነኛውና የመጀመሪያው ሆነው የጣሊያኑ ምግብ ቤት ለዓለም አቀፍ ዕውቅና የበቃው ደግሞ ኢትዮጵያ ክፉኛ በድርቅና በረሃብ በመጎዳቷ ዕርዳታ ለማሰባሰብ የመጡ ዝነኛ ምዕራባውያን ዘፋኞች ስላረፉበት ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ በማር የተለወሰ መርዝ አለ እንዴ!? ደፋር! አለማፈሩ። በዓለም ላይ ስሟን የሚያስጠሯት ስንትና ስንት ተቆጥረው የማያልቁ አስደናቂ ገፅታዎች ባለቤት፤ ከአልማዝ ከቀይ ዕንቁ በላይ የምትወደደው ውቢቷ ኢትዮጵያን እንዴት እነ ቦብ ጊዶልፍ ምሳቸውን የበሉበት ካስቴሊ የጣሊያን ምግብ ቤት ተለይታ የምትታወቅበት አርማዋ ሊሆን ይችላል?
ግርምቴ እየጨመረ መጥቶ ፀሐፊውን እንድታዘበውና “ተናግሮ “አናጋሪ” እንዲሉ ስለ ጽሑፉ አንዳንድ ነገሮችን እንድናገር ያስገደደኝ ደግሞ አቶ ሮቢንሰን (ቅንቅኑ ሮቢንሰን) ኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርጋት ነገር ብሎ በሁለተኛ ደረጃ ያስቀመጠውን ነገር ሳነብ ነው። ዛሬም ድረስ የተንሸዋረረውን የነጮች አፍሪካውያንን የሚመለከቱበት ዕይታ “ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች” እንዲሉ ለሲ.ኤን.ኤኑ የጉዞ ዘጋቢ ለአቶ ሮቢንሰን ኢትዮጵያን ከዓለም ልዩ የሚያደርጋት ሁለተኛው ነገር አሁንም በድጋሚ ከቅኝ ገዥዎች የተወረሰ ነው ተብሎ የታሰበው “የጣሊያን የቡና አፈላል ሥርዓት” ነው።
“የሞሶሎኒ ሰዎች ምንም እንኳን ኢትዮጵያን በቅኝ የመግዛት ችሎታ እንደሌላቸው በሽንፈታቸው አረጋግጠው ቢወጡም በአብዛኞቹ ካፌዎችና ምግብ ቤቶች በፈራረሱ ትንንሽ አሮጌ የመንገድ ዳር ሻይ ቤቶች ሳይቀር የጣሊያን “እስፕሬሶ ቡና” ማፍያ ማሽኖች መገኘታቸው ጣሊያኖች በአገሪቱ የነበራቸውን የስልጣንና የንብረት ይዞታ የሚያረጋግጡ ናቸው” ይላል ትንሽ አፉን ሳይዘው።
ይኸኛው የሮቢንሰን አገላለጽ “ዛሬም ድረስ የተንሸዋረረውን የነጮች አፍሪካውያንን የሚመለከቱበት ዕይታ” የሚለው አባባሌ ስህተት አለመሆኑን አረጋገጠልኝ። ለካ አጅሬ የጣሊያን ምግብ ቤት፣ የጣሊያን ቡና አፈላል ወዘተ እያለ የሚቀባጥረው እውነትም የኢትዮጵያ መለያ ነገሮች ሆነው ሳይሆን “ጣሊያኖች በኢትዮጵያ የነበራቸውን የስልጣንና የንብረት ይዞታ የሚያሳዩለት፣ የነጮችን ሌጋሲ የሚያስታውሱ ስለሆኑለት ነው”። ካልሆነማ የጣሊያን ምግብ ቤት፣ የጣሊያን ቡና አፈላል ለእኛ ምናችን ነው? እንዴትስ የኢትዮጵያ መለያ ሊሆን ይችላል? ደስ የሚለው ነገር የድንቢጥ ምስክሩ ሚስተር ሮቢንሰን በአድናቆት ስም የአያቱን የሞሶሎኒን “ሌጋሲ”፡- የጣሊያን ቡና አፈላልን የኢትዮጵያ መለያ ለማስመሰል በዓለም አቀፍ የሚዲያ አደባባይ ቢለፍፍም እሱ ራሱም ቢሆን በገደምዳሜ ዕውነቱን ሳይመሰክር አልቀረም።
በቅናት አንጀቱ እያረረም ቢሆን ህሊናው ሞግቶት የቡና ባለቤትነታችንን መስክሯል። ይህንንም “ኢትዮጵያውያን ቡናቸውን በጣም ይወዱታል፤ “ጥቁሩ ወርቃችን” እያሉ ይጠሩታል። የቡና መገኛ አገር በመሆናቸውም ከፍተኛ ኩራት ይሰማቸዋል፤ ለዚህም በ1998 ዓ.ም የሰሩትን ዘጋቢ ፊልም ማየት ትችላላችሁ” በማለት ጽፏል። ከሃዲ በገዛ ምላሱ ይጠመዳልና ይህ አባባሉም ምቀኝነቱን ሳያሳብቅበት አልቀረም። ምክንያቱም “የቡና መገኛ የሆነች አገር እንዴት በጣሊያን የቡና አፈላል ትታወቃለች?” የሚል የአመክንዮ ጥያቄ ያስነሳበታልና!
እርግጥ ነው ለአንተና ለመሰሎችህ የሌሎች ታላቅነት ለማይዋጥላችሁ ድኩማን ራስ ወዳዶች እንጂ እኛማ ቡናው ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ በልዩነት ደምቀን የምንታወቅበት የጣሊያን ሳይሆን ዓለም ያደነቀው ግሩም ድንቅ የሆነ የራሳችን የቡና አፈላል ሥርዓት አለን! ሚስተር ሮቢንሰን፤ እንደ ምታውቀው እኛ ኢትዮጵያውያን ስለራሳችን መናገር አንወድም። አንተው እንድንናገር ካደረከን ዘንዳ ግን እስኪ ትንሽ ስለራሳችን እንንገርህ። በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙ አርባ የሚደርሱ የሣር ዝርያዎች መካከል ወደ ሰላሳ የሚጠጉት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚበቅሉ ናቸው።
አስር ያህሉ ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጭ የትም የማይገኙ ብርቅየ የኢትዮጵያ ብቻ ስጦታዎች ናቸው። በዓለም ላይ ከሚገኙ 277 ትልልቅና መለስተኛ ጡት አጥቢ የዱር እንስሳት መካከል ሰላሳ አንዱ እንደዚሁ ከኢትዮጵያ ውጭ በየትኛውም ዓለማት የማይገኙ ዝርያዎች ናቸው። በተመሳሳይ በዓለም ላይ ከሚገኙ ከ 9 ሺ 100 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች መካከል 862ቱ የሚገኙት በኢትዮጵያ ሲሆን ወደ ሰላሳ የሚጠጉት ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም ላይ ከሚኖሩ 201 ዓይነት የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎች መካከል አስሩ፣ በየብስና በውሃ ውስጥ ከሚኖሩ 63 የእንስሳት ዝርያዎች መካከል ሰላሳዎቹ፣ ከ324 ቢራ ቢሮ ዝርያዎች መካከል ሰባቱ እንዲሁም ከ150 የዓሣ ዝርያዎች መካከል አራቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ተለይተው የታደሉ ናቸው።
ሌላም ልጨምርልህ። በዓለም ላይ ከ6500 እስከ 7000 የሚደርሱ የዕፅዋት ዓይነቶች እንዳሉ ጥናቶች ያመለክታሉ። ታዲያ ከእነዚህ መካከል አስራ ሁለት በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ይህም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ የሰብል ዝርያዎች ይገኛሉ። ታዲያ በዓለም ላይ ለግብርና ምርት በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ከእነዚህ ሁለት መቶ የሰብል ዝርያዎች መካከል ከ38 ያላነሱት አሁንም የመጀመሪያ ወይም ሁለተኛ የዘር መገኛቸው ኢትዮጵያ ነች።
ከእነዚህ መገኛቸው በኢትዮጵያ ብቻ ከሆኑት መካከል ደግሞ እንጀራ ለሚባለው የኢትዮጵያውያን ልዩ ባህላዊ ምግብ መስሪያ የሚያገለግለው ጤፍ፣ ቡና፣ ዳጉሳ፣ ገብስ፣ እንሰት፣ ኑግ፣ ሰሊጥና ጫትም የተገኙት እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ይህ እንግዲህ በተፈጥሮ ብቻ ነው። ስልጣኔን ቀድመው ለዓለም ያስተማሩ ጥበበኛ ልጆቿ የአዕምሮ ውጤት የሆኑትና ዓለምን ያስደነቁት እነ አክሱም፣ ላሊበላ ፋሲልና ጀጎል የመሳሰሉት ሌሎችም ተዘርዝረው የማያልቁ ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ባህላዊ ሀብቶቿ ሲጨመሩ ደግሞ ኢትዮጵያን ከአድናቆትም በላይ የሆነች እጅን በአፍ የምታስጭን “የማይደረስባት ምስጢር” ያደርጓታል።
ታዲያ ከዚህ ሁሉ ለእኛ ብቻ በብቸኝነት ከተሰጡ ልዩ ስጦታዎች ጋራ ቡናም ከዚሁ ከእኛው ምድር በቅሎ በልዩነት የእኛ ሆኖ እያለ እንዴት ኢትዮጵያ “በጣሊያን እስፐሬሶ ቡና” ልትታወቅ ትችላለች? ደግሞ እኮ ኢትዮጵያ የምትታወቀው በቡና መገኛነቷ ብቻ አይደለም። ቄጤማ ተጎዝጉዞለት፣ እጣን ተጭሶለት አንተ እንዳልከው “በጣሊያን እስፐሬሶ ቡና” ሳይሆን በራሳችን በኢትዮጵያውያን ዕደ ጠበብቶች በሰሩት ውብ ጀበና ተፈልቶ ማጣጫ ቁርስ ቀርቦለት፣ በአቦል፣ ቶና፣ በረካ በሚሉ የክብር ስሞች የራሱ ጊዜ ተመድቦለት በክብር ተዘጋጅቶ በፍቅር የሚጠጣ በየትኛውም ዓለም የሌለ የቡና አፈላል ሥርዓቷ ጭምር እንጂ! ኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርጋትም ይኸው በየትኛውም ዓለም የሌለው ባህላዊ ልዩ የጀበና ቡና አፈላልና አቀራረብ ሥርዓቷ እንጂ በማሽን የሚፈላው “የጣሊያን እስፐሩሶ ቡና” አይደለም።
ምናልባትም “እስፐሬሶ” ቃሉ ጣሊያንኛ ስለሆነ የጣሊያን አልከው እንጂ ትርጉሙ “በማሽን የተፈላ ቡና” ማለት ነው። ቡናን በማሽን የምታፈላው ደግሞ ጣሊያን ብቻ አይደለችም። እናማ ወንድሜ አትሳሳት በማሽን የተፈላ ቡና በአንተ ማደናገሪያ “የጣሊያን ስፐራሶ ቡና” እንኳንስ በራሷ ቡና አፈላል ዓለም ለሚያውቃት ኢትዮጵያ ይቅርና ለራሷ ለጣሊያንም ተለይቶ መታወቂያዋ ሊሆናት አይችልም። የራሷን ቡና በራሷ ጀበና ከምታፈላው ከኩሩዋ ኢትዮጵያ በስተቀር በአብዛኛው የዓለም ክፍል ቡና የሚፈላው በማሽን ነውና!። ገባህ!?
ቅን አድናቂዎች
ከነሮቢንሰን በተቃራኒው ኢትዮጵያ ድሮም ዛሬም ከልብ የሚወዷት፣ በእውነት የሚያከብሯት፣ ከአንጀት የሚያደንቋት ተዘርዝረው የማያልቁ ቅን አድናቂዎች አሏት። ከክርስቶስ ልደት በፊት ቅድመ ዓለም እነ ሆሜር መጥተው ሳያይዋት በምናብ ቅኔ ተቀኝተውላታል፣ በታላቁ የምዕራባውን ሥነ ጽሑፍ ኦሊያድና ኦዲሴ ላይ በግጥም አሞካሽተዋታል። የታሪክ አባት በመባል የሚታወቀው ሌላው ታላቅ ግሪካዊ ሄሮዳተስ በበኩሉ ግዮን ዓባይ ምንጭ ድረስ መጥቶ፣ ምድሯንና ህዝቦቿን ጎብኝቶ፤ “በጦርነት ካልሆነ በቀር በበሽታ የማይሞቱ፣ ረጃጅሞችና መልካቸው የሚያምር፣ አማልክት የሚሰግዱላቸው ውብ ህዝቦች ያሉባት ምድር” ድሮ ገና ያኔ መንግሥታት ሳይመሰረቱ፣ ዓለም በድንኳን በነበረችበት ሰዓት ታሪኳን ጽፎታል።
ኧረ ምኑ ተቆጥሮ አሁንስ እነ አዶልፍ ፓርልሳክ ከምስራቅ አውሮፓ ድረስ መጥተው፣ ከጀግኖች አባቶቻችን ጋር ጦር ሜዳ ዘምተው፣ ታንክ በምድር እየተሽከረከረ እሳት እየተፋባቸው፣ ርቡላ በሰማይ መርዝ እየዘነበባቸው ነፍሳቸውን አስይዘው ታሪክና ጀብዷን የጻፉላት ይህችው የእኛዋ አስደናቂዋ አገር ታላቋ ኢትዮጵያ አይደለችምን?
ብቻ ይህን ተነግሮ የማልቀውን አስደናቂውን ታሪኳን ለጊዜው ቆየት እናደርገውና አሁን አሁን ከሰሞኑ መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ እውነተኛ አድናቂዎቿ ያሉትን እንመልከት። በእርግጥ ይችኛዋ በሙያዋ የኦሊቨር ሮቢንሰን አጋር ናት። ኑሮና ሥራዋም እዚያው በምዕራቡ ዓለም አገረ እንግሊዝ ውስጥ ነው። ጃኒ በስማን የሌላኛው ዝነኛ የምዕራባውያን ሚዲያ የእንግሊዙ ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ የጉዞ አምድ አዘጋጅ ናት። ይሁንና ጃኒ ከሮቢንሰን የምትለየው ለኢትዮጵያ ባላት ከአድልኦ የፀዳ አመለካከቷና በእውነት አክባሪነቷ ነው። ጃኒ እንደ ሮቢንሰን የምታደንቅ መስላ አታደቅም (“ቅ” ጠበቅ ብሎ ይነበብ)።
የዴይሊ ሜይሏ ጋዜጠኛ ከሰሞኑ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ አገራችንን ተዟዙራ ጎብኝታ ኢትዮጵያን ከልቧ አድንቃ ስለ ኢትዮጵያ ዴይሊ ሜይል ላይ ዓለምን ያስገረመ ጽሁፍ አስነብባለች። ጋዜጠኛዋ አዲስ አበባን፣ አዳማን፣ ሀዋሳን፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ላሊበላ ከተሞችን ጊዜ ሰጥታ በሚገባ ተዟዙራ ከጎበኘች በኋላ ባየችው ነገር ሁሉ እጅጉን ተደምማለች። በአዲስ አበባ የሚገኘውን የሰባት መቶ ዓመታት የዕድሜ ባለፀጋ ከተራራ የተፈለፈለ ገዳም ዋሻ ሚካኤልን “ልብን በፍቅር የሚሞላ ውበት የተጎናጸፈ የእጅ ሥራ” በማለት አባቶቻችን ጥበብ በፍቅር መማረኳን ገልጻለች። በስምጥ ሸለቆዋ እመቤት አዳማ ከተማ የሚገኘውን የሳፋሪ ሎጅ ሆቴል ደግሞ “የመንኮራኩር ዓይነት ቅርጽ ያላቸው፤ አፍሪካ ውስጥ እጅግ በዓይነቱ ልዩ የሆነ መኝታ ክፍሎች ያሉት ሆቴል” በማለት አድንቃ ጽፋለች የዴይሊ ሜይሏ ዘጋቢ ሚስስ ጃኒ ቡስማን።
እንዲህ እንዲህ እያለች ሀዋሳን፣ ባህር ዳርን፣ ባሌን፣ ጎንደርን፣ ላሊበላን በአካል ተዟዙራ ከጎበኘች በኋላ “በአጠቃላይ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርሶቿ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ ራሷ ከሰባቱ የዓለማችን አስደናቂ ነገሮች መመደብ የሚገባት ልዩ አገር ናት” በማለት የኢትዮጵያን ድንቅነት ለዓለም ጽፋለች። በእርግጥ ከዚህ ቀደምም አንድ ጀርመናዊ ተጓዥ ስለ ኢትዮጵያ ብዙ፣ ብዙ ካደነቀ በኋላ “ምን አለፋችሁ ኢትዮጵያ ማለት የማይደረስባት ሚስጥር ናት፣ ዜጎቿም ስለራሳቸው ማውራት አይወዱም እንጅ ገነት ማለት ኢትዮጵያ የምትባለው የራሳቸው አገር ናት” ብሎ ጽፏል። እኛም እንዲህ ዓይነት ቅን አድናቂዎቻችንን እናመሰግናለን፣ ቅንቅን አድናቂዎቻችን ደግሞ ስማችንን ለማጥፋት አትልፉ፣ “እኛ ማለት የማይደረስብን ሚስጥር ነን” እንላቸዋለን። ቸር እሰንብት!
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
ይበል ካሳ