እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
የዋስትና ዓይነቶች
ባለፈው ሳምንት ጽሑፋችን ስለ ዋስትና እና ልዩ ባህርያቱ በዝርዝር አንስተን ሰፊ ግንዛቤ ማግኘታችን ይታወሳል። በዚህኛው ጽሑፋችን ደግሞ ዋስ በባለገንዘቡ ተከሶ ለፍርድ በሚቆምበት ወቅት ሊያነሳቸው የሚገቡ ሕጋዊ መከራከሪያዎቹን በዝርዝር እንዳስሳለን። የዋሱ መከራከሪያዎች እንደ ዋሱ ዓይነት የሚለያዩ በመሆናቸው መከራከሪያዎቹን በዝርዝር ከማየታችን አስቀድመን የዋስትና ዓይነቶችን በወፍ በረር ቃኘት አድርገን ማለፉ ጠቃሚ ነው።
በኢትዮጵያ የዋስትና ሕግ መሠረት ዋስትና ሁለት ዓይነት ነው። እነዚህም የአንድነትና የነጠላ (የማይነጣጠል) እንዲሁም ተራ ዋስትና ይሰኛሉ። የአንድነትና የነጠላ ዋስትና ከስሙ እንደምንገነዘበው ዋስ የሆነ ሰው በማይከፋፈል (በማይነጣጠል) ኃላፊነት ከዋናው ባለዕዳ ጋር እኩል ተጠያቂ የሚሆንበት ነው። በአንድ በኩል «የአንድነት» የሚለው ቃል የሚያመለክተው ዋሱና ባለዕዳው በማይከፋፈል ኃላፊነት የተቆራኙ መሆናቸውን ሲሆን፤ ባለገንዘቡ የሚጠይቀው ዕዳ (ግዴታ) በሁለቱም ጫንቃ ላይ ሳይነጣጠል የወደቀ መሆኑን ነው።
በሌላ በኩል «የነጠላ» የሚለው ደግሞ ባለገንዘቡ በዋሱና በባለዕዳው ላይ የተጣለውን የማይከፋፈል ዕዳ እንደምርጫው ከሁለቱ አንዱን በመክሰስ የማስከፈል መብት ያለው መሆኑን ያመለክታል። ለዚህም ነው የፍትሐብሔር ሕጋችን ቁጥር 1933 «ዋሱ አንድነት በሆነ ዋስትና የጋራ ባለዕዳ ወይም በሌላ በማናቸውም ተመሳሳይነት ሥም በመሆን ከዋናው ባለዕዳ ጋር የሚገደድ እንደሆነ ባለገንዘቡ ለዋናው ባለዕዳ ከመናገሩ በፊት በዋሱ ላይ ክስ ማቅረብና በእጁ ያለውንም መዋዣ ለመሸጥ ይችላል» በማለት የሚገልጸው።
በአንድነትና የነጠላ ዋስትና የባለገንዘብ መብት ሰፊ ከመሆኑም በላይ ዕዳውንም በአስተማማኝ ዋስትና ውስጥ እንዲቆይለት ያግዘዋል። በዚህ ዓይነቱ ዋስትና ባለገንዘቡ በዋናው ባለዕዳና በዋሱ ላይ ተመሳሳይ መብት ይኖረዋል። ዋናውን ባለዕዳ ከመጠየቅ ወይም ከመክሰሱ በፊት ዋሱን «ዕዳውን ክፈል (ግዴታውን ተወጣ)» ብሎ ለመጠየቅ ወይም ለመክሰስ ይችላል። አልያም ከሁለቱም ወይም ከአንዳቸው ለዕዳው (ለግዴታው) መያዣ ተቀብሎ ከሆነ መያዣውን ሸጦ ገንዘቡን የመውሰድ መብት አለው።
ተዋዋይ ወገኖች በመካከላቸው የአንድነትና የነጠላ የዋስትና ትስስር ለመመስረት ከፈለጉ ታዲያ ዋስትናው የአንድነትና የነጠላ ዋስትና መሆኑን በግልጽ በዋስትና ውላቸው ውስጥ ማስፈር አለባቸው። በውላቸው ውስጥ በግልጽ የአንድነትና የነጠላ ዋስትና መሆኑን ካላመለከቱ ግን ዋስትናው ተራ ዋስትና እንደሆነ በሕጉ ግምት ይወሰድና ውጤቱና የዋሱም መከራከሪያዎች የተለዩ ይሆናሉ። ስለዚህ ሁለተኛው የዋስትና ዓይነት ተራ ዋስትና ነው ማለት ነው።
በመሠረተ ሃሳብ ደረጃ የዋስትናን መሠረት ከሚደነግገው የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 1920 እንደምንረዳው ዋስትና ለግዴታ አፈጻጸም ዋስ የሚሆን ሰው ባለዕዳው ግዴታውን ያልፈጸመ እንደሆነ ለባለገንዘቡ ይህንን ግዴታ ሊፈጽም ይገደዳል። ይህ ማለት ዋስትና በመሠረቱ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ባደረጉት ውል ወይም በእነርሱ መካከል ባለ የባለገንዘብነትና የባለዕዳነት ግንኙነት ውስጥ ከእነርሱ ውጪ የሆነ ሦስተኛ ሰው «ባለዕዳው ዕዳውን በሙሉ ወይም በከፊል ያልከፈለ እንደሆነ ወይም ግዴታውን በአግባቡ ያልተወጣ እንደሆነ እኔ በእርሱ ስፍራ ሆኜ ገንዘቡን እከፍላለሁ ወይም ግዴታውን እወጣለሁ» በማለት ለባለገንዘቡ ማረጋገጫ የሚሰጥበት ነው።
ከዚህ በቀላሉ የምንገነዘበው በመሠረቱ ዋስ አላፊ የሚሆነው ከባለዕዳው ቀጥሎ ነው፤ ወይም ከዋሱ በፊት ባለዕዳው መጠየቅ እንዳለበት ነው። ስለዚህ ዋስትና ሲባል ቀድሞ ወደህሊናችን የሚመጣው ከባለዕዳ ቀጥሎ መጠየቅ በመሆኑ ስለዋስትና ሲነገር የመጀመሪያው ግንዛቤያችን ተራ ዋስትና የሚለው ይሆናል። ነገር ግን ተዋዋዮች ዋሱና ባለዕዳው በማይነጣጠል ኃላፊነት እኩል እንደሚጠየቁ በግልጽ ካመለከቱ ዋስትናው የአንድነትና የነጠላ ዋስትና ይሆናል። በግልጽ ካላመለከቱ ግን ተራ ዋስትና ይሆናል። በተራ ዋስትና ደግሞ ዋስ የሚጠየቀው ከባለዕዳው ጋር በአንድነት ወይም በነጠላ ሳይሆን ከባለዕዳው ቀጥሎ ነው። ለዚህም ነው ሕጉ «ዋናው ባለዕዳ ግዴታውን የማይፈጽም ካልሆነ በቀር ዋሱ ለባለገንዘቡ እንዲከፍለው አይገደድም» በማለት የሚያስቀምጠው።
እዚህ ላይ አንድ መሠረታዊ ግንዛቤ ጨብጦ ማለፍ የግድ ነው። «…ዋናው ባለዕዳ ግዴታውን ያልፈጸመ እንደሆነ…» የሚለው የሕጉ አነጋገር «ዋናው ባለዕዳ ግዴታውን አልፈጸመም የሚባለው መቼ ነው?» የሚል ወሳኝ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። ዋስትና አንድ የውል ዓይነት በመሆኑ ዋናው ባለዕዳ ግዴታውን አልፈጸመም ሊባል የሚችለው በተለያዩ ምክንያቶች ሲሆን፤ በርካታ ጸሐፍት የሚስማሙባቸው ሦስት ሁኔታዎች ናቸው።
የመጀመሪያው ዕዳው ሲበስል ወይም የመክፈያው ጊዜ ሲደርስ ነው። በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 1857 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሠረት ውሉ ጊዜ ተወስኖለት ከተቀመጠ ወይም የአንድን ሁኔታ መሟላት ወይም አለመሟላት መሠረት ያደረገ ከሆነ የተባለው ጊዜ ሲጠናቀቅ ወይም ሁኔታው ሲፈጸም አልያም ሁኔታው ሲቋረጥ ዕዳው በስሏል ወይም የመክፈያው ጊዜ ደርሷል ማለት ነው።
ሁለተኛው ባለገንዘቡ ለባለዕዳው ዕዳህን ክፈል (እንደውሉ ፈጽምልኝ) ብሎ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶት እንደውሉ የማይፈጽም ከሆነ ዋናው ባለዕዳ ግዴታውን አልፈጸመም ማለት ነው። ሦስተኛው ባለገንዘቡ ዋናውን ባለዕዳ ክስ መስርቶበት በፍርድ ዕዳውን መክፈል ካልቻለም ግዴታውን አልተወጣም ሊባል ይችላል። ስለዚህ እነዚህ ሁኔታዎች ዋናው ባለዕዳ ግዴታውን አልተወጣም ያሰኛሉ።
መኪናቸውን ሸጠው ቀሪ ክፍያ የነበራቸው ባለገንዘብ ባለዕዳውንና ዋሱን በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በአንድነት ከከሰሱ በኋላ ባለዕዳው በችሎት ባለመቅረቡ ጉዳዩ በሌለበት ይቀጥላል። ፍርድ ቤቱም ዋሱ ተራ ዋስትና የገባ በመሆኑ ዋሱ ሊጠየቅ የሚገባው ባለዕዳው መክፈል ካልቻለ ነው በማለት ዋሱን በነፃ በማሰናበት በባለዕዳው ላይ ውሳኔ ያሳልፋል። ባለገንዘብም በውሳኔው ቅር ተሰኝተው ይግባኝ ያሉበት ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔውን አጸናው።
ዶሴያቸውን ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመውሰዳቸው ችሎቱ ባለዕዳው ገንዘቡን መክፈል መቻል ያለመቻሉ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ዋሱን ሙሉ በሙሉ ከክሱ ነፃ ማድረግ ሕጉን የተከተለ አለመሆኑን በመጥቀስ ውሳኔውን አርሞታል። ዋሱም ባለዕዳው መክፈል ካልቻለ እንዲከፍል ፈርዶበታል። ከዚህ የምንገነዘበውም በአንድ በኩል ዋሱ ለዕዳው ተጠያቂ የሚሆነው ባለዕዳው ግዴታውን ለመወጣት የማይችል መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑንና በሌላ በኩል ዋሱ ከኃላፊነት ነፃ የሚሆነውም ባለዕዳው ግዴታውን መወጣት ከቻለ መሆኑን ነው።
በመቀጠል የዋስን መከራከሪያዎች እንመ ልከት።
ከባለዕዳው ጋር ተከራከር የማለት መብት
በመርህ ደረጃ ባለገንዘብ ከባለዕዳው ላይ ለሚጠይቀው ዕዳ ባለዕዳውም ዋሱን የመጠየቅ መብት አለው። ያም ሆኖ በተራ ዋስትና ዋሱ የሚጠየቀው ባለዕዳው ግዴታውን ያልፈጸመ እንደሆነ ነው። ይህ ማለት ግን ዋናው ባለዕዳ የግድ አስቀድሞ መከሰስ አለበት ለማለት አይደለም።
ባለገንዘቡ ባለዕዳውን ሳይከስስ ዋሱን ሊከሰው ይችላል። በዚህ ወቅት ዋሱ «ወደእኔ ከመምጣትህ በፊት ሄደህ ከባለዕዳው ጋር ተከራከር ወይም በባለዕዳው ንብረቶች ወይም ከባለዕዳው በመያዣነት በተቀበልከው ንብረት ላይ መብትህን አስከብር» የሚል ክርክር ማንሳት ይችላል። በእንግሊዝኛው Benefit of Discussion የሚባለው ነው። ይሁንና ባለዕዳው ዕዳውን ለመክፈል ችሎታ ማጣቱ በፍርድ ቤት ከተረጋገጠ ባለገንበዙ ከባለዕዳው ጋር እንዲከራከር ዋሱ የመጠየቅ መብት አይኖረውም።
ዋሱ ይህንን መከራከሪያ ቢያነሳ ይጠቀማል። ካላነሳው ግን በባለዕዳው እግር ተተክቶ ዕዳውን ለመክፈል ይገደዳል። ዋሱ በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ መከራከሪያውን ካነሳው የቀረበበት ክስ ለጊዜውም ቢሆን ይቋረጥለታል። ምክንያቱም ሕጉ «ዋሱ እንደተከሰሰ ወዲያውኑ ባለገንዘቡን ከባለዕዳው ጋር ተከራከር ካላለ በቀር ባለገንዘቡ ከዋናው ባለዕዳ ጋር ለመከራከር ግዴታ የለበትም» ይላል።
ዋሱ ይህንን መከራከሪያ በሚያቀርብበት ወቅት ከእሱ የሚጠበቁ ግዴታዎችም አሉ። «ከባለዕዳው ጋር ተከራከር» በሚልበት ወቅት የባለዕዳውን ንብረቶች የመምራትና ለዚሁም ክርክር የሚያስፈልገውን ወጪ አስቀድሞ ለባለገንዘቡ የመስጠት ግዴታ አለበት። የባለዕዳውን ንብረት መምራት ማለትም ንብረቶቹ የት እና በምን ሁኔታ እንዳሉ በተለይም ከክርክር የጸዱ፣ በባለዕዳው እጅ የሚገኙና በአገር ቤት ያሉ ንብረቶችን የመጠቆም ኃላፊነት ነው። ይህ ሲባል ታዲያ ዋሱ በውጭ አገራት የሚገኙ ንብረቶችን ወይም በክርክር ላይ የሚገኙ ወይም ባለዕዳው ሌላ ዕዳ በመያዣ የሰጣቸውን ንብረቶች እንዲመራ ይገደዳል ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል።
ዋሱ ከባለዕዳው ጋር ተከራከር ብሎ ለባለገንዘቡ ካስታወቀውና የባለዕዳውንም ንብረቶች ከመራው እንዲሁም ለክርክሩም አስፈላጊውን ወጪ ካወጣ በኋላ ባለገንዘቡ ባለዕዳውን ሳይከስስ በመቆየቱ ምክንያት ባለዕዳው የመክፈል ችሎታውን ያጣ እንደሆነ ግን ኃላፊነቱ የባለገንዘቡ ይሆናል ማለት ነው። ይህም ማለት በባለገንዘቡ ዳተኝነት ምክንያት ባለዕዳው ቢከስር፣ ንብረቱን ቢያሸሽ ወይም ቢያስተላልፍ የዋሱ ግዴታ ለባለገንዘቡ በመራው ንብረት ልክ ይወርድለታል ማለት ነው።
በባለዕዳው ላይ ክስ መስርት የማለት መብት
ይህ መብት በባለገንዘቡ ክስ ሳይመሰረት ወይም ባለገንዘቡ ከመጠየቁ በፊት ዋሱ የሚየቀምበት ወሳኝ መብት ነው። ዋሱ የዕዳው የመክፈያ ጊዜ በሚደርስበት ወቅት ወይም ዕዳው በበሰለ ጊዜ ባለገንዘቡን በባለዕዳው ላይ ክስ መስርትበት ብሎ ለማስገንዘብ ይችላል። በእንግሊዝኛው Summons to Proceed ይሉታል። ይህንን መብት በመጠቀምም ዋሱ በስድስት ሳምንታት ውስጥ ከባለዕዳው ላይ የመብቶቹን አፈጻጸም ይጠይቅ ዘንድ ክስ እንዲያቀርብ ባለገንዘቡን ሊያስገድደው እንደሚችል ነው ሕጉ የሚገልጸው።
ዋሱ ይህንን በማድረጉ ከፍተኛ ጥቅም ያገኛል። ዋሱ የነገረውን ባለገንዘቡ ያልፈጸመ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የዋሱን ማስገንዘቢያ በጄ ብሎ በባለዕዳው ላይ ክስ ከመሰረተ በኋላም ቢሆን ክሱን በሚገባ ትጋት ካልቀጠለ ዋሱ ከገባበት የዋስትና ግዴታ ነፃ ይሆናል። ባለገንዘቡና ባለዕዳው ተመሳጥረው ዋሱን ለመያዝ የዕዳ መክፈያ ጊዜው ሲደርስ ባለዕዳው ሆነ ብሎ ንብረቱን በማሸሽ ወይም ሌላ ክፋት በማድረግ ራሱን የመክፈል ችሎታ የሌለው ሰው ቢያደርግ ዋስ መጠየቁ ስለማይቀር ዕዳው እንደበሰለ ባለገንዘቡ በባለዕዳው ላይ ክስ እንዲመሰርት ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ብልህነት ነው።
በባለዕዳው ላይ ክስ መስርት ከማለት መብት ጋር በተመሳሳይ ዘውግ ውስጥ የሚመደብ ሌላው መብት ዕዳን ልክፈል የማለት መብት ነው። ዕዳው ሲበስል ወይም የመክፈያ ጊዜው በሚደርስበት ወቅት ዋሱ የሚከፍለውን ዕዳ እንዲቀበለው ባለገንዘቡን ለማስገደድ ይችላል። ባለገንዘቡ አልቀበልም ያለው እንደሆነ ወይም በዋስትና የተሰጡትን መያዣዎች አልመልስም ያለ እንደሆነ ዋሱ ነፃ እንደሚሆን ሕጉ ያስገነዝባል።
ዕዳን የመከፋፈል መብት
ለአንድ ባለዕዳ ለአንድ ዕዳ ብዙ ሰዎች ዋስትና ሊገቡ ይችላሉ። ይህ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። ዕዳው ወይም ግዴታው ከፍተኛ ከሆነ ወይም የሥራ ዋስትና በሚሆንበት ጊዜ ቀጣሪዎች በሚጠይቁት መስፈርት ምክንያት ለአንድ ሰው ለተመሳሳይ ግዴታ ብዙ ሰዎች ዋስ ይሆናሉ። ለምሳሌ በመስሪያ ቤቱ ስፖንሰርነት ወደ ውጭ አገር አቅንቶ ዶክትሬት ዲግሪውን ለሚማር ሠራተኛ ሦስት ሰዎች በጋራ ዋስትና ሊገቡ ይችላሉ። ዕዳን የመከፋፈል መብት (Benefit of Division) የሚባለው መብት የሚሰራውም ለአንድ ባለዕዳ ለአንድ ዕዳ ዋስትና ለገቡ ለእንዲህ ዓይነት ሰዎች ነው።
የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 1951 እንደሚደነግገው ለአንድ ባለዕዳ ለአንድ ዕዳ ብዙ ዋሶች በአንድ ጊዜ ዋስ ከሆኑ እነዚህ ዋሶች ለየራሳቸው ድርሻ እንደ ተራ ዋስ የሚጠየቁ ሲሆን፤ ለሌሎቹ ዋሶች ደግሞ እንደ አረጋጋጭ ዋሶች ሆነው ይቆጠራሉ። አረጋጋጭ ዋስ (የዋስ አረጋጋጭ) የሚባለው በአጭር አገላለጽ የዋሱ ዋስ ማለት ነው። በበርካታ አገራት ሕጎች ለዋናው ባለዕዳ ብቻ ሳይሆን ለዚህ ባለዕዳ ዋስ ለሆነው ሰውም ጭምር ዋስ መሆን ይቻላል። ይህም ዋሱ ለባለዕዳው የገባውን የዋስትና ግዴታ የማይፈጽም ከሆነ ለዚህ ግዴታ በዋሱ ተተክቶ የሚፈጽም የዋስ አረጋጋጭ ይሆናል። በዚሁ መሠረት ለአንድ ዕዳ ብዙ ሰዎች ዋስ በሚሆኑበት ወቅትም ለየድርሻቸው እንደተራ ዋስ ሲሆኑ፤ እርስ በእርሳቸው ደግሞ አረጋጋጭ ዋሶች ናቸው።
ብዙ ሰዎች ለአንድ ዕዳ ዋስ በሚሆኑበት ወቅት ታዲያ ባለዕዳው ግዴታውን ባለመወጣቱ ምክንያት ባለገንዘቡ ከዋሶቹ ውስጥ የፈለገውን መርጦ ስለሙሉ ዕዳው የመክሰስ መብት አለው። ምክንያቱም እያንዳንዱ ዋስ ለየድርሻው ተራ ዋስ፤ ለሌሎቹ ዋሶች ግዴታ ደግሞ አረጋጋጭ ዋስ በመሆኑ በሙሉ ዕዳውም ይከሰሳል። በዚህ ወቅት ነው እንግዲህ የተከሰሰው ዋስ «ምንም እንኳን ለሌሎቹ ዋሶች አረጋጋጭ ዋስ ብሆንም ልከሰስ የሚገባኝ እንደ አንድ ዋስ ድርሻዬ ተለይቶ ስለሆነ ድርሻዬን ለይተህ በድርሻዬ ልክ ክሰሰኝ» በማለት የዕዳ መከፋፈል ጥያቄ የማቅረብ መብቱን ሊጠቀምበት የሚገባው።
እዚህ ላይ ልብ ሊባልበት የሚገባ መሠረታዊ ነጥብ አለ። የተከሰሰው ዋስ የዕዳ መከፋፈል ጥያቄ በማቅረቡ ምክንያት በድርሻው ልክ ክስ ሊመሰረትበት ይችላል፤ አልያም ባለገንዘቡና ዋሶቹ ባደረጉት የዋስትና ውል ውስጥ የእያንዳንዳቸው የዋስትና ድርሻ የተከፋፈለ (የተለየ) ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ባለገንዘቡ ዋሶቹን እንደየድርሻቸው ልክ ነው የመጠየቅ መብት ያለው፤ ዋሶቹም የሚገደዱት በድርሻቸው ልክ ነው። ይሁንና ዋሶቹ የየግል ድርሻቸውን ለመክፈል አቅም ካጡ አቅም ኖሮት የራሱን ድርሻ የተወጣው ዋስ አቅም ያጡትን ዋሶችም ድርሻ ለባለገንዘቡ የመክፈል ግዴታ አለበት። ምክንያቱም እሱ ለሌሎቹም ዋሶች አረጋጋጭ ዋስ ነውና።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
(ከገብረክርስቶስ)