መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም የታላቁ የምኒልክ ቤተ መንግሥት ቅጥረ ግቢ በጠቅላያችን በጎ ፈቃድ ወለል ተደርጎ ሊከፈት መንግሥታዊ ቀጠሮ ተይዞለታል። ይህ ገናና ቤተ መንግሥት በ1890 ዓ.ም መሠረቱ ተጥሎ መጋቢት 21 ቀን 1891 ዓ.ም በአንድ ዓመት ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር «አጀብ!» ተሰኝቶ የተደነቀው ታሪኩ ከጆሮው በደረሰው በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ነበር። በዘመኑ ሥርዓት መሠረትም አዝማሪ እንዲህ ሲል አድናቆቱን ገልፆ ነበር። ከፊል ግጥሙ እንዲህ ይነበባል።
ሥራተ ሆሳዕና የዳኘው ሥርዓት፣
ድንጋይ አዳራሽህ በአእምሮ አንደበት፣
ሲነገር ሰማነው አያል መጻሕፍት።
ይህ ከመቶ ሃያ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የምኒልክ ቤተ መንግሥት «እምዬ» እየተባሉ ከሚመሰገኑት ንጉሥ በኋላ አባ ጤና ኢያሱ፣ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለሥላሴ፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ሁለቱ «ጓዶች» መለስ ዜናዊና ኃይለማርያም ደሳለኝ በፕሮቶኮሉ መሠረት እና ደህንነታቸውን በሚመጥን ደረጃ በክብር ዘቦቻቸውና በልዩ የኮማንዶ ኃይል ቅጥረ ግቢያቸውን ሲያስጠብቁ ኖረዋል። የግቢውን አጥርም ቢሆን ዜጎችና ቱሪስቶች ፎቶግራፍ እንዳያነሱ በዓይነ ቁራኛ ክትትል እየተደረገባቸው «በጣፋጩ ሥልጣን» ሲምነሸነሹበት ከርመው ሁሉም እንደጠበቁት ሳይሆን ቀርቶ እንዳልሆነ ሆነው በባይተዋርነት ያን ሞገሳማ ግቢ ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።
መሪዎቻችን ስለ ሥልጣን ዘመናቸው ሲጠየቁ «ሀገር የምንመራው በእሳት ላይ ተቀምጠን ነበር» ብለው ሁሉም በብሶት መናገራቸውና መጻፋቸው ጸሐፊውን ሁሌም እንደገረመው ነው። ለማንኛውም የምኒልክን ቤተ መንግሥት ወርሰው የነበሩት መሪዎች ሁሉም በትረ ሥልጣናቸውን አስቀምጠው ወይንም ተነጥቀው ከግቢው ውስጥ የተሰናበቱት አንዳንዱ በክብር፣ አንዳንዱ በውርደት፣ አንዳንዱ በስደት፣ አንዳንዱ በተፈጥሯዊ ሞት በመሸኘት ሲሆን፤ መንበረ ሥልጣኑ ወር ተረኛውን ጎልማሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ጠርቶ ነዎሩ ካላቸው ገና ዓመት ከመንፈቃቸው ነው።
እኒህ ባለራዕይ መሪ በፍልሚያና በፍትጊያ በታጀበ ትግል የምኒልክን ግቢ ከተረከቡ በኋላ «ምንም የታላቅ ሕዝብ መሪ ብሆን ብቻዬንስ አንድ ጋሻ መሬት (አራት መቶ ሺህ ሜትር ካሬ) ጠቅልዬ አልይዝም» በማለት ምኒልክ ቤተ መንግሥታቸውን አሰርተው ባስመረቁ ልክ በ120ኛ ዓመቱ ጠቅላዩም ግቢውን በማሳደስ እነሆ ለእኛ ለተራ ዜጎች «ምሥጢራዊ መጋረጃውን» ቀደው በይፋ ለማስጎብኘት የቀረው የሃያ አራት ሰዓት ዕድሜ ብቻ ነው።
እንደ አልጋ ወራሻቸው እንደ ምኒልክ ሁሉ ጠቅላዩ ዐብይ አህመድም የቤተ መንግሥቱን እድሳት አጠናቀው ለሕዝብ ክፍት እንዲሆን የተጉት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መሆኑ ከግንባታው ጊዜ ጋር ግጥምጥሞሹ ሰምሯል። ክቡር ሆይ! ምሥጋናችን ይድረስዎ!
መቼም ያለመታደል ሆኖ ከታሪክ አንክርት ላይ እሳቱን ሳይሆን አመዱን መጫር ስለሚቀለን የራሳችንን ነባር ክብር እያዋረድንና በታሪካችን እየተሳለቅን መዝቀጥ እንደ ባህል ቆጥረነው ስለኖርን እንጂ ከእነ ምልዓት ጉድለታቸውም ቢሆን በተለይ በቀዳሚ ነገሥታቱ የተሠሩት ታላላቅ ሥራዎች አመድ ለብሰው መደበቅ አልነበረባቸውም። ተከራካሪ እና ተሟጋች በሌለበት ሁኔታ የአንበሳ ለምድ ለብሰን ባለፉት ታሪኮቻችን ላይ የምናገሳባቸውን አጋጣሚዎች ብናስብ አመለካከታችን ምን ያህል እንደ ድንቢጥ እንደሚያንስ ለመገንዘብ ህሊናችንን ብቻ ብናማክር እውነታው ፍንትው ብሎ ይታየናል።
እንደ የትኛውም ሀገር ሁሉ የሀገራችን ቀደምት መሪዎችም ሺህ በሺህ ጥፋቶች ፈጽመዋል ብንል እንኳን ስህተት ናቸው ብለን ከታሪክ ጋር ግብግብ የምንፈጥርባቸው ፉከራዎች ሁሉ ግማሹ ጥቂት የእውነት ጠብታ ቢኖረውም አብዛኛው መከራከሪያ ሀሰት፣ ከፊሉም ፈጠራ የታከለበት ሊሆን ይችላል። ከዚህ ሁሉ በላይ ስህተት ናቸው ብለን ከበሮ የምንደልቅባቸው፣ መሰንቆ የምንከረክርባቸውና ለበቀል ጋሻና ጦር የምንወለውልባቸው «ጥዩፍ ያልናቸው ታሪኮቻችን» ምናልባትም ለነገሥታቱ የዘመናቸው ይትባህል በአሜንታ ያፀደቀላቸው ቅቡል አስተሳሰቦችም ሊሆኑ ይችላሉ።
በየራሱ ሀገረ መንግሥት ምስረታ ወቅትም የትኛውም ሀገርና ሕዝብ ያለፈባቸው ተሞክሮዎችም ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል። ይሄም ሁሉ ባይሆን እንኳ «የተሰሩ ስህተቶችን» እየነቀሱ በሥርዓቱ ውስጥ ላልተወለደውና ስመ ንግሥናቸውን ሳይቀር ከታሪክ መጻሕፍት ብቻ ካልሆነ በስተቀር በአግባቡ መርምሮ ላላረጋገጠው «ምስኪን ትውልድ» ለእርስ በእርስ ፍልሚያ ሻምላ መዝዘን ናና እንሰያየፍ መባባሉና በከንቱ ለመጠፋፋት መጠራራቱ ምን ረብ ይኖረዋል?
ዳግማዊ አጤ ምኒልክም ቢሆኑ በዘመነ ሥልጣናቸው ካበረከቷቸው እጅግ በጎ ተግባራት ጎን ለጎን «በዛሬው የጀብድ ትርክታችን ስንመነዝረው» አንዳንድ በእንክርዳድ የሚመሰሉ አመራሮችን ሰጥተው ይሆናል። በዙሪያቸው የነበሩት ሹማምንትና የየአካባቢው ሀገረ ገዢዎችም ቢሆኑ ዘመኑና ጊዜው በሚፈቅድላቸው የአመራር ዘይቤ መሠረት ያበጁትን አበጅተው ያጠፉትን አጥፍተው አልፈዋል። ይህ ትውልድ መሰል ጥፋት ወይንም አዲስ ውልድ ላለመድገም መጠንቀቁና ለትምህርት እንዲሆን ከማስተማር ይልቅ ታላቁ የሀገራችን ባለቅኔ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ እንደተቀኙት «መቃብር ቆፍረን አጥንቶችን በመለቃቀም» በፍርድ ወንበር ፊት በወንጀለኝነት እንገትራቸው ብንል እንኳንስ ቅን ፈራጁ ፈጣሪ ቀርቶ ራሷ ተፈጥሮ ተቆጥታና ፊት ነስታ በአጥፊነት ሳትፈርጀን የምትቀር አይመስለንም።
«ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ፤ ባለዕዳ አይቀበለውም» ብሂል ለታሪካችንና ለፈጠርነው ትርክታችን እጅግም የሚሰራ አይመስለኝም። ለምን ቢሉ እኛ አርክሰን ያቀለልነው «የታሪክ አሞሌ» በውጭ ሀገራት የታሪክ ጠበብትና የዓይን ምስክሮች ዘንድ እጅግ ከፍ ያለ ቦታ እየተሰጠው ሲመሰገንና ሲደነቅ መኖሩ ለእኛ ቢገርመንም እውነታው ግን እውነት ነው።
ለምሳሌ፤ በአራት ዋና በሮችና በአራት ምክትል በሮች (ዋናዎቹ፤ ፊት በር፣ እቴጌ በር፣ ሠረገላ በር፣ ስርቆሽ በር ሲሆኑ ምክትሎቹ ደግሞ ብር ቤት በር፣ ጎተራ በር፣ ገብርዔል በር እና ቄራ በር) የሚገባበትና በአድናቆት የሚያፈዘው ታላቁ የግብር አዳራሽ ፊት ለፊቱ ባለ ሦስት ጣሪያዎች ሆኖ እያንዳንዱም ዘውግ ሃምሳ፣ ሃምሳ ጉልላቶች አሉት። ሦስቱ የጣሪያው ዘውጎች የጎዣም፣ የሸዋ እና የጎንደር ተብለው መሰየማቸው በታሪክ ይረጋገጣል። በሕንዶችና በአረቦች የሙያ እገዛ የተሠራው ታላቁ አዳራሽ በውስጡ በርካታ ክፍሎች ያሉት ነበር።
እንደ ታሪክ ዘጋቢው እንደ ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል ገለፃ አዳራሹ ስልሳ ሜትር ርዘመትና ሰላሳ ሜትር ወርድ ያለው ሆኖ በበርካታ ክፍሎች የተደራጀ ሲሆን እኩሉ ለጠጅ እኩሉ ለሥጋ፣ እኩሉ ለእንጀራ፣ እኩሉ ለወጥና ለመጠጥ ተከፋፍሏል። በግብር ሰዓትም ጠጅ የሚተላለፍበት ባለ ሰላሳ ሜትር ቧንቧ ተዘርግቶ ነበር። አጀብ የሚያሰኝ ነው። ይህ አደረጃጀት በታደሰው አዳራሽ ውስጥ እንደነበረ ተጠብቆ ስለመገኘቱ እርግጠኛ አይደለሁም።
ሰኔ 13/2011 ዓ.ም ለመጎብኘት ዕድል ባገኘሁበት አጋጣሚ ለምን አስጎብኝዬን ከመጠየቅ እንደተዘናጋሁ አላውቅም። ምናልባትም ያየኋቸው ታሪካዊ ቅርሶች በሙሉ አፍዝዘውኝ ሊሆን ይችላል። በዚህ አዳራሽ ውስጥ ዓጤ ምኒልክ በመጀመሪያ ግድም ለሠራዊታቸው እሁድ፣ ማክሰኞና ሐሙስ ግብር ያገቡ ነበር። ሠራዊቱ እየበዛ ሲሄድም እሁድ፣ እሁድና ለበዓላት ቀን ብቻ ማድረጋቸውን የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል።
የምኒልክን የግብር ሥርዓት በተመለከተ ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካንን የልዑካን ቡድን በመንግሥታዊ ኦፊሴል እየመሩ እ.ኤ.አ በዲሰምበር ወር በ1903 የመጡት ቆንስል ጄኔራል ሮበርት ስኪነር ስለ ታላቁ ንጉስ እንዲህ ሲሉ ምስክርነታቸውን እንደሰጡ ወዳጄ ደራሲ ንጉሤ አየለ ተካ ባዘጋጀው «ታላቁ ጥቁር- ኢትዮ አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክ» በሚለው መጽሐፍ ውስጥ እንደሚከተለው ገልጾታል። «አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ በቆየን ቁጥር የተደረገልን አቀባበል ምን ያህል ከልብ የመነጨ እንደሆነ ለማጤንና በዓለም ላይ በሕይወት ያሉትን የታላቁን ጥቁር ሰው ደግ ባህርያት ለመረዳት የሚያስችሉ የበለጡ አጋጣሚዎች ነበሩን» ይሉናል።
ለእኒሁ ለስኪነር የተዘጋጀላቸው ንጉሣዊ የክብር ምሳ የተገለፀው አንዲህ ተብሎ ነበር። «ለእንግዶቹ የተዘጋጁት ምግቦች የአበሻም የአውሮፓም ዓይነቶች ነበሩ። ከሾርባ ጀምሮ የአበሻውንም የአውሮፓውንም ምግብ ተስተናገዱ። ፊት ጥሩ ሥጋን እያዩት ወደ አበሾቹ ገበታ አለፈ። በርበሬ ወጥና እንጀራን፣ ጎመንና ጥብሱን ግን ቀማምሰዋል። የፈረንሳይ ዘመናዊ ዳቦም ነበር። ከዚህ በኋላ ለአስራ ሦስት ዙር ተከታትሎ የቀረበላቸው የአውሮፓ ምግብ በሙሉ እጅግ ጥሩ እንደነበርና የቤተ መንግሥቱ የአውሮፓ ምግብ ባለሙያ ግሪካዊ መሆኑ ጭምር ተነግሯቸዋል። » እጅግ የሚገርመው በየአንዳንዱ እንግዳ ጠረጴዛ ፊት ለፊት ስማቸውና ማዕረጋቸው የተጻፈበት ካርድ መቀመጡና የአፍ ማበሻ መሃረቡም አለመጉደሉ ነበር። አይ ሥልጣኔ!
በዚያ ታላቅ አዳራሽ ውስጥ በአስራ ሁለት ወንበሮች የተዘጋጁት ጠረጴዛዎች በሙሉ አስራ አንዱ ወንበሮች ብቻ ተቀማጭ ሲኖርባቸው አንድ አንድ ወንበር በትርፍነት ይስተዋል ነበር። ይህ አንዱ ትርፍ ወንበር የንጉሡ ወንበር ነበር። የዚህ ትርፍ ወንበር ምሥጢር ንጉሡ ባይቀመጡባቸውም በእያንዳንዱ ጠረጴዛ ዙሪያ ከተገኙ ከእንግዶች ጋር ግርማዊነታቸው ተገኝተው አብረው እንደተመገቡ በምሳሌ፤ ፈቃድ አክብሮታቸውን ለመግለጽ ታስቦ ነበር። ይገርማል! ምናልባትም በገበታው ላይ በመጠጥ ሞቅታ ንጉሡ እንዳይታሙ የተዘየደ ዘዴም ሊሆን ይችል ይሆናል።
ነገ ለሕዝብ ይፋ በሚደረገው የቤተ መንግሥቱ ቅጥረ ግቢ ውስጥ የሚገኘው ታላቁ አዳራሽ ብቻ ሳይሆን እጅግ በርካታ ታሪካዊ ሕንፃዎችና ቁሳቁሶችም ይገኛሉ። ለጉብኝቱ አፒታይት መክፈቻ ያህል ይህንን ያህል የወፍ በረር ቅኝት ለማድረግ እንጂ ዝርዝሩማ በጉብኝቱ ወቅት በአግባቡ ይብራራል። ለማንኛውም አንዳንድ አስተያየቶችን አክዬ ጽሑፌን መቋጨት እፈልጋለሁ።
የዙፋን ችሎቱ አደባባይ በእጅጉ ቀልብን ይስባል። የዓፄ ምኒልክ መኝታ ቤት የነበረውና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን እንግዳ መቀበያ የሆነው ድንቅ ባለደርብ ሕንፃ ወደ ኋላ ዘመን በትዝታ ብዙ ያጓጉዘናል። የቤተ መንግሥቱ ልዩ መታወቂያ የሆነው የዕንቁላል ቤት በዘመነ ደርግ የቅጥረ ግቢው የኢሠፓ መሠረታዊ ድርጅት መሰብሰቢያ ሆኖ መጎሳቆሉንና ስናስተውል የሀገር ታሪክን ለማፍረስ እጅግ የተጋውን ወታደራዊ ሥርዓት በመኮነን ጭምር ነው።
ከታሪካዊዎቹ ሕንፃዎች በተጨማሪ የታነፁ በርካታ አዳዲስ ሕንፃዎችም መጨመራቸው በእጅጉ የሚያስመሰግን ሥራ ነው። ለታሪክ ደንታ ቢስ የሆኑ ቀደምት መሪዎች እነዚያን ታሪካዊ ሕንፃዎች አንዳንዶቹን የእስረኞች ማጎሪያ፣ አንዳንዶቹንም የቅራቅንቦ ማጠራቀሚያ፣ አንዳንዱንም የእስረኞች ማሰቃያ አድርገው ሲጠቀሙ መኖራቸው ሲነገረን ደግሞ ውስጣችንም ውጪአችንም በኀዘን ይመታል። የአንዳንድ የቅርብ መሪዎቻችን ሚስቶች በዚያ ታሪካዊ ግቢ ውስጥ አውገርግረው የሠሯቸው ዛኒጋባ መጠለያዎች ከቦታቸው እንዲወገዱ መደረጋቸውም አሹ የሚያሰኝ ነው። የብሔር ብሔረሰቦችን የቤት አሠራር የሚወክሉ ልዩ ግንባታዎችም ተከናውነዋል። ሙሉውን ታሪክ ጎብኚዎች በቦታው ሲገኙ ምኒልክ ነዎሩ ብለው ስለሚቀበሏቸው ያኔ ዝርዝሩን በሚገባ ለማወቅ ይቻላል።
የወደፊቱን የግቢውን ታሪካዊ አቅም ይበልጥ ለማጎልበት የሚከተሉት ጉዳዮች ትኩረት ቢሰጥባቸው ሊጠቅሙ እንደሚችሉ ጸሐፊው ያምናል። ቀድሞ ታስቦባቸው ከሆነም እሰየው። ለማንኛውም ለወደፊቱ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግና በዘመነ ምኒልክ የተቀረፁት ፊልሞች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተሰባስበው ለጎብኚዎች እየተቀነጫጨቡ የሚቀርቡበት ሁኔታ ቢመቻች የቤተ መንግሥቱን ክብርና ሞገስ ይበልጥ ያጎላዋል።
እስካሁን አልታሰበበትም ለማለት ባይቻልም ቤተ መንግሥቱን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች ይበልጥ ሳቢና ማራኪ ለማድረግ የታሪክ ቡድን፣ የልዩ ልዩ ኪነ ጥበባት አደራጅ ቡድኖች፣ የኪነ ሕንፃ ቡድን ወዘተ… ታስቦበት ከወዲሁ ቢቋቋምና ኃላፊነቱን ተረክበው የጎደለውን የቤተ መንግሥቱን ታሪካዊ አሻራዎች ማደራጀትና ማሰባሰብ ቢችሉ ነባር ታሪካችንን ይበልጥ ማጉላት ይቻላል። በተለይም የወቅቱን ግለሰቦችና ወቅቱን የሚወክሉ የቅርፃ ቅርፅ ምስሎች ከፎቶግራፎች በተጨማሪ በስፋት ቢታከሉበትና የታሪኩን ሰንሰለት ጠብቀው በየቦታቸው ቢሰደሩ ትርጉም የመስጠት አቅሙን ከፍ ማድረግ ይቻላል።
በአደራ ጭምር ቤተ መንግሥቱን ለሚያደራጀው አካል አንድ ማስታወሻ ላኑር። የዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ የቅርብ አማካሪ የነበሩት ሁለቱ የውጭ ሀገራት ዜጎች አልፍሬድ ኢልግና ሊዎን ሸፈኔን የሚያስታውስ አንድ መታሰቢያ እንዲቆም አደራ ማለቱን ወድጃለሁ። ኢልግ በትውልድ የስዊዝ ዜጋ ሲሆን ሸፈኔ ደግሞ ፈረንሳዊ ነው። እነዚህ ሁለት ባለውለታዎች ታሪካቸውና ምስላቸው ተዘጋጅቶ ለጎብኚዎች ቢታይ ትርጉሙ ብዙ ይሆናል። ካስፈለገ ስለ ሁለቱ ሰዎችና ስለ ምኒልክ ግንኙነት ዝርዝር መረጃ ወደፊት ማቅረብ ይቻላል።
ይህንን ጽሑፍ እያዘጋጀሁ ሳለ በሃሳብ ጭልጥ ብዬ ተጓጓዝኩኝ። ምኒልክ በታደሰው ቤተ መንግሥታቸው ውስጥ ሆነው ጎብኚዎችን በታሪካዊ ትዝታ ነዎሩ ብለው ሲቀበሏቸው በዓይነ ህሊናዬ ታየኝ። ዝግጅቱ ወደ ፍጻሜ እየተቃረበ መሄዱን ሳስብም የደስታ ሙቀት ለብ እያደረገኝ በለሆሳስ ቋንቋ ለራሴ እንዲህ አሰብኩኝ። ተርታው ሕዝብ ጥቅጥቅ ብሎ ገብቶ ቤተ መንግሥቱን እየጎበኘ ሲያደንቅ እኔም ተገርሜ የምመለከት መሰለኝ። ቀዳሚው ሰልፈኛ ጎብኝቶ ሲወጣ ከውጭ የሚጠባበቁት ተረኞች በተንጠለጠለ ልብ ጉጉታቸው ከፍ ብሎ ወጪዎችን ሊተኩ ሰልፋቸውን አሳምረው ሲቆሙ በዓይነ ህሊናዬ ተመለከትኩ። ሌላው ረድፈኛም እንዲሁ ተራው እስኪደርስ በጉጉት ተሰልፎ መጠባበቁን እያየሁ በሃሳብ ነጎድኩ። ለጉብኝት የሚሰለፈው ሰው ሁሉ ይህ ግጥም ይጠፋው ይሆን ብዬም አሰብኩ።
ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፣
ግብሩ ዕንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ።
መልካም ጉብኝት ቀን ሲፈቅድልን እዚያው አንገናኝ።
ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012