(ፍሬው አበበ)
“የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የጫት አምባሳደር ሆነዋል” ይላል የማህበራዊ ጥናት መድረክ ከአንድ ዓመት በፊት ያስጠናው ጥናት ውጤት። አዳማ ውስጥ ብቻ ከሦስት ሺ በላይ ጫት መሸጫ ቤቶች አሉ። በተማሪዎች የመኝታ ክፍሎች ውስጥ ጫት መቃም የተለመደ ሆኗል። ያስከተለውም ቀውስ እጅጉን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
የዩኒቨርሲቲዎችን መቋቋም እግር በእግር እየተከተለ የሚደራው የጫት ንግድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እና መምህራኑን ከሌላው ማህበረሰብ በባሰ መልኩ ጫት ቃሚ አድርጓቸዋል ይላሉ፤ ከአንድ ዓመት በፊት ስለጫት ጥናት ያካሄዱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሽዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ።
“የጫት ሱሳቸውን ለማርካት ቤተሰብ የሚልክላቸው ገንዘብ ስለማይበቃቸው ወደ ላፕቶፕ፣ ሞባይል እና ልብስ ስርቆሽ የሚገቡ በርካቶች ናቸው” ይላሉ ዶ/ር የራስወርቅ።
የችግሩን አስከፊ ደረጃ ላይ መድረስ ለማሳየት አጥኚው፣ ከጫት እርሻ ውስጥ ጫት ሊሰርቁ ከገቡ አምስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል አንዱ ከጫት እርሻው ባለቤት ጋር ባደረገው ግብግብ የመገደሉን ክስተት ያነሳሉ። ችግሩ መምህራኑም ጋ መድረሱን ለማሳየት በጫት ሱስ ሳቢያ የመመረቂያ ወረቀት ከሚቀርብበት አዳራሽ ጥሎ ስለወጣው የዩኒቨርሲቲ መምህር ይጠቅሳሉ።
ዶ/ር የራስወርቅ መፍትሄ የሚሉትንም አቅርበዋል – በጫት ምርትና ገበያ በሚቀርብበት ሁኔታ ላይ ጥብቅ መመሪያ ሊወጣ ይገባል ይላሉ።
ዶ/ር ዘሪሁን መሐመድ ጫት ላይ የተሰሩ በርካታ ጥናቶችን ለህትመት ባበቃው የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (FSS) አጥኚ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ጫትን በሚመለከት ሁለት ፅንፍ የያዙ አቋሞች አሉ ይላሉ። “ጫት እያስከተለ ያለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ጉዳት በመመልከት ጫት ይታገድ የሚል አለ። በሌላ በኩል ደግሞ ጫት ለብዙዎች እንጀራና የኑሮ መሰረት በመሆኑ መነካት የለበትም የሚል ሌላ ፅንፍ አለ። ስለዚህ መከተል የሚኖርብን በሁለቱ መሃከል ያለውን መንገድ ነው። ጫት የሚያስከትለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ጉዳት በብዙ ጥናቶች የተረጋገጠ ሲሆን፤ ለጉዳቱ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መጠበቅ የመንግሥትና የማህበረሰቡ ግዴታ ነው። በአንፃሩ ደግሞ ጫትን የሚያመርተው ክፍል ያለው አማራጭ ምንድን ነው? ጫት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያመጣ ያለ በመሆኑ የሚተካውስ በምንድን ነው? የሚሉትን ነገሮች በጥልቀት መመልከት ያስፈልጋል” ይላሉ።
“እዚህ ጋ ጥቅምና ጉዳቱ የገንዘብ ብቻ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ መነሳት አለበት። የገንዘብን ብቻ ከተመለከትን በአሁኑ ወቅት አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ጫት አምራቾች እንዳሉ ጥናቶች ያመለክታሉ። በጫት የተሸፈነው መሬትም ምን ያህል እንደሆነ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል። ይህ የጫት አምራቾች የኢኮኖሚ ጥቅም እያገኙ እንደሆነ ግልፅ ያደርጋል። ጫት በብዛት የሚመረትባቸው እንደ ሐረርጌ፣ ጉራጌ አካባቢና ሲዳማና የተወሰኑ የጌዲኦ አካባቢዎች ሲታዩ ከፍተኛ የህዝብ ጥግግት ያለባቸውና ከፍተኛ የእርሻ መሬት እጥረት ያለባቸው ናቸው። ስለዚህ ጫት በአነስተኛ ቦታ ላይ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ የሚመረት በመሆኑ ገቢው ቤተሰብ ለማስተዳደር ያስችላል። በዚህ የአምራቹ ተጠቃሚነት ጥያቄ የለውም”።
ዶ/ር ዘሪሁን አያይዘውም በሌላ በኩል ከጅምላ ሻጩ ጀምሮ እስከ ቸርቻሪው ድረስ ያለው ሰንሰለት ሲታይ አንድ ጥናት 18 የሚሆኑ ባለድርሻዎችን ይዘረዝራል። ጫት ቆራጭ፣ አደራጅ፣ አመላላሽ (ትራንስፖርት)፣ መጠቅለያ የእንሰት ቅጠል የሚያቀርቡና ሌሎችም።
ስለዚህ ስለ ጫት ሲወራ ጫትን ስላመረተውና ስለተጠቃሚው ብቻ አይደለም። ይልቁንም በመካከል ሰፊ የንግድ ትስስር አለ።
ክልልና ፌደራል መንግሥትም እየተጠቀሙ ነው። በክልሎች ትንንሽ ኬላዎች ላይ ከጫት የሚሰበሰበው ቀረጥ ለአካባቢ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋል። እንግዲህ ይህ ከቀረጥ ብቻ የሚገኝ ጥቅም ነው።
ጫት መቃም ለአንዳንድ ሰው መዝናኛ ነው። ለአንዳንድ ማህበረሰብ ደግሞ ጫት በማህበራዊ ትስስር ትልቅ ዋጋ አለው። ስለዚህ ይህም ጥቅም ነው። ከሃይማኖት ጋርም የሚያያዝበት ሁኔታ አለ።
በተቃራኒው ጫትን አላግባብ የሚጠቀሙ በጣም ይጎዳሉ። ቤተሰብ ይፈርሳል ማህበረሰብና አገር ይጎዳል። በጫት የሚደርሰው የአዕምሮ ጤና ጉዳትም ከፍተኛ መሆኑን ዶ/ር ዘሪሁን ያስረዳሉ።
የአማራ ክልል የጤና ጥበቃ ቢሮ የአማራ ክልልን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የጫት መቃም (ሱስ) ችግር አስመልክቶ በአንድ ወቅት ያወጣውን ምክረ ሀሳብ መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል። ጤና ቢሮው ለሁሉም የዘርፍ መ/ቤቶች በጻፈው ደብዳቤ ይህንኑ አሳውቋል። ለአብነት የሚበቃ እርምጃ በመሆኑ እዚህ ላይ ማንሳት ተገቢ ይሆናል።
ስለጫት ዳራ
ጫት መሠረቱ ምስራቅ አፍሪካ ሲሆን ስርጭቱም እስከ ደቡብ አፍሪካ ከዚያም አልፎ በየመን አፍጋኒስታንና ቱርክ ውስጥ እንደሚበቅል ይታወቃል። ጫት ተራራማና እርጥበታማ በሆኑ ቦታዎች ይበቅላል።
አንዳንድ ታሪክ አዋቂዎች እንደፃፉት ጫት መሠረቱ ኢትዮጵያ በተለይም ሐረርጌ እንደሆነና ከዚህ በመነሳት ወደ ሌሎች አገሮች እየተስፋፋ እንደሄደ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ የመንና ማዳጋስካር በጫት አምራችነታቸውና ተጠቃሚነታቸው በዓለም የታወቁ አገሮች ሲሆኑ የሚያመርቱትም ጫት በተለያየ መንገድ ወደ ጎረቤትና ራቅ ወዳሉ አገሮች በሕጋዊም ሆነ በሕገወጥ መንገድ እንደሚዘዋወር ይታወቃል። በተለይም የአብቃይ አገሮች/ ኢትዮጵያና ኬኒያ/ ጎረቤት የሆኑት ሶማሊያና ጅቡቲ ከፍተኛ የጫት ተጠቃሚ ቁጥር መኖሩ በጥናት ተረጋግጧል።
የጫት ተክል ከቅጠሉ ወይም ከሌላ አካሉ የማነቃቃት ኃይል ያላቸው ካቲን (Catine)፣ ካቲናን (Catahinone) እና ሜትካቲኖን (Methcathinone) የተባሉት ንጥረ ነገሮች ሲኖሩት በሚያደርሱት ከፍተኛ የጤና ጉዳት፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ችግሮች ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።
በሌላ በኩል የአንዳንድ አገሮች /አሜሪካ፣ ካናዳና የተወሰኑ የአውሮፓ አገሮች/ የጫት ተክል በአገራቸው ውስጥ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወርና ጥቅም ላይ እንዳይውል የተጠና የመቆጣጠሪያ ሕግ አውጥተዋል።
በጫት ሱስ የተያዙ ሰዎች በጊዜ ሂደት ለሌሎች ሱሶች ማለትን ለአልኮል፣ ለሲጋራ /ትምባሆ/፣ ሐሽሽ ባስ ሲልም አደገኛ እፆችና መድሃኒቶችን እስከመጠቀም የሚያደርስ ሱስ ውስጥ የመግባት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
1. የጤና ችግሮች
የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ጫት የምግብ ፍላጎትን ይቀንሳል። በዚህም የተነሳ ቃሚው ቫይታሚን፣ ፕሮቲን… ወዘተ በሚፈለገው መጠን ስለማያገኝ በሽታን የመቋቋም ኃይሉ ደካማ ይሆናል። በመሆኑም በተለያዩ በሽታዎች በቀላሉ ሊጠቃ ይችላል።
የሆድ ድርቀት ያመጣል፣ በዚህም የተነሳ ለአንጀት በሽታዎችና ለኪንታሮች (hemorrhoids) ያጋልጣል። የአዕምሮ ሕመም መንስኤ መሆንና ማባባስ፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት፣ ለተላላፊ በሽታዎች ይዳርጋል።
ጫት ብዙውን ጊዜ በቡድን የሚቃም በመሆኑ በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎች ከአንዱ ወደ ሌላው በቀላሉ ሊተላለፍ ይቻላል / ለምሳሌ ሣንባ ነቀርሳ/፣ የስሜት መረበሽና መነጫነጭ፣ ራስን መጣል፣ ለስንፈተ ወሲብ ያጋልጣል። ጫት ቃሚዎች የወሲብ ፍላጎት ቢኖራቸውም ወሲብ የመፈፀም ብቃታቸው ግን የተዳከመ ይሆናል።
በጫት ውስጥ የሚገኙ አነቃቂ ንጥረ ነገሮች ሱስ የማስያዝ ባህሪ ስላላቸው ተጠቃሚዎች ደጋግመው እንዲወስዱ ተጽዕኖ ስለሚያደርጉ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እየተባባሱ ይሄዳሉ።
2. በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት
በሱሰኝነት ምክንያት በግለሰብም ሆነ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል።
በግለሰብ ደረጃ
ሱሰኛው ሱሱን ለማርካት ሲል ከገቢው እየቀነሰ ለመሠረታዊ ፍላጎት ማዋል የሚገባውን ገንዘብ በተሟላ መንገድ ሊያወጣ አይችልም። በተለይም ቤተሰብ ያለው ከሆነ ለቤቱ አስፈላጊውን ወጪ ስለማይሸፍን ቤተሰብ በርሃብና በእርዛት ይሰቃያል።
ሱሰኛው ጤናው የተናጋ ስለሚሆን በተሰማራበት የሥራ መስክ ምርታማነቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ከሥራ ሊባረር ይችላል።
በአገር ደረጃ
አምራች ኃይሉ ጊዜውን በመቃም የሚያሳልፍ ከሆነ ለማምረት የሚያውለው ጊዜና አቅም አናሳ ስለሚሆን የተፈለገውን ያህል አያመርትም፣ ምርታማነት ዝቅተኛ ስለሚሆን የአገር ኢኮኖሚ ይወድቃል።
ሱሰኞች ጤናቸው አስተማማኝ ስለማይሆን መንግሥት ለህክምና ተቋማት ማቋቋሚያ፣ ለባለሙያዎች ስልጠናና ደመዎዝ፣ ለመድኃኒት መግዣ… ወዘተ ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጋል።
ለምግብ እህል፣ አዝርዕትና ፍራፍሬዎች.. ወዘተ ማብቀያ ማዋል ያለበት መሬት (ማሳ) ጫት እንዲበቅልበት ከተደረገ በገበያ ላይ የምግብ እህል አቅርቦት እጥረት ይፈጠራል።
የሀሰት ሰነዶች ይበራከታሉ፣ ገንዘብ አስመስሎ መሥራት የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር እንዲኖ በማድረግ ሕጋዊ ሰነዶችን አስመስሎ መሥራት የባለሥልጣናት ፊርማ አስመስሎ መፈረም ገንዘብና ሌሎች ሰነዶችን በማጭብርበር ኢኮኖሚው ይዳከማል።
3. በማህበራዊ ኑሮ ላይ የሚከሰት ችግር
በሱሰኛው ላይ የሚደርሱ ችግሮች በግለሰብ ደረጃ ብቻ ተወስነው የሚቀሩ አይደሉም። በቤተሰብና በማህበረሰቡም ላይ ከፍተኛ ችግር ይደርሳሉ። በሱስ ምክንያት የቤተሰብ መፍረስ ይከሰታል የፈረሰው ቤተሰብ አባላትም፣ እናት ለሴተኛ አዳሪነት ልትዳረግ ትችላለች፣ ልጆች ደግሞ ለጎዳና ተዳዳሪነት ይዳረጋሉ። ልጆችም ወደ ጎዳና ወደሱስ ወደ ሕገወጥ ተግባራት (ወንጀል)፣ ይሰማራሉ። በዚህ የተነሳ ፀረ ማህበረሰብ (ANTISOCIAL) እርምጃዎች ሊወሰዱ የህብረተሰብ ሰላም ይታወካል።
4. በፖለቲካ መረጋጋት ላይ የሚፈጠር ችግር
የአንድ አገር ፖለቲካ የተረጋጋ የሚሆነው ቀደም ብሎ በተጠቀሱት ጤና ነክ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ሲቀረፉ ነው። አለበለዚያ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የአገርን ፖለቲካዊ ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮች ናቸው። በሱሰኝነት ሳቢ የተለያዩ የፖለቲካ ችግሮች ይደርሳሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል፣
የሙስናና የሥነ-ምግባር ብልሹነት መስፋፋት፣ የመንግሥት ንብረት መመዝበር፣ የአገር ሉአላዊነት አለመከበር፣ የወንጀል ድርጅቶች መበራከት፣ በአገሮች መካከል የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር /ገፅታ መበላሸት/ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ጫት በሀገራችን 7 በመቶ የሚሆነውን ማምረት የሚችል መሬት በሚሸፍን ብዛት በመመረት ላይ የሚገኝ ሲሆን በሁሉም የአገራችን ክፍል በሚባል ደረጃ ጫትን በማምረትና በመጠቀም ተንሰራፍቶ ይገኛል።
ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆን የሀገራችን ዜጎች ከጫት ምርት በሚገኘው ገቢ ህይወታቸውን በመመምራት ላይ ይገኛሉ። ይህ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ፈታኝ ያደርገዋል። ለጫት ሱስ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የጫት አቅርቦት ሲሆን ጫት በሌለባቸውና በማይታወቅባቸው እንደ ደቡብ አሜሪካ አይነት አገሮች ችግሩ አይታይም። የጓደኛ ግፊት፣ የግንዛቤ እጥረት፣ መገለል፣ ሰዎችን ሞዴል /አርአያ ማድረግ፣ ፍልሰትና ሥራ አጥነት ለሱስ አጋላጭ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሶ ለመፍትሔ የሚረዳ ምክረ ሀሳብ ጠቁሟል።
እንደማሳረጊያ
ጫት በትውልዱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ የመምጣቱ ጉዳይ አከራካሪ አይደለም። ጫት ቅሞ ማጥናት ጎበዝ ተማሪ እንደሚያደርግ የሚያምኑ ወጣቶች ዛሬም ድረስ አሉ። እንደዋዛ ለጥናት ተብሎ የተጀመረ ጫት የመቃም ልምድ ወደሱስ ደረጃ አድጎ የማይላቀቁት ችግር የሆነባቸው ወገኖች ብዙ ናቸው። ዛሬ ዛሬ ጫት ቅሞ ክፍል የሚገባ ተማሪ፣ መምህር፣ ጫት ቅሞ ሕሙማንን የሚጎበኝ ሐኪም፣ ካልቃመ ዓይኑ የማይገለጥ፣ አዕምሮው የማይሠራ ጋዜጠኛ እና አክቲቪስት፣ ቅሞ በአገራዊ ጉዳዮች ጭምር የሚወስን ባለሥልጣንና ሹም… ፈልጎ ማግኘት ከባድ አይደለም። ከመቃም ጋር ተያይዞ የምርታማነት ማሽቆልቆልም እንደአገር እያስከተለ ያለው ጉዳት የከፋ ነው።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የጫት ምርትን እንደአንድ ኤክስፖርት ምርት በመውሰድ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የተጀመረው በዘመነ ደርግ ቢሆንም ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ምርቱ በስፋት ለውጭ ገበያ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በአሁን ጊዜ ከኤክስፖርት ዘርፉ በገቢ ደረጃ አንዳንድ ጊዜ ሁለተኛ፣ አንዳንዴ ሦስተኛ ደረጃን ለመያዝም በቅቷል። በአጭሩ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኗል።
“ኢትዮጵያ በጫት ትርፍ አገኘች ተብሎ ትውልድ እንዲጠፋ መተው ወደፊት ትልቅ ዋጋ ያስከፍለናል” ይላሉ በዘርፉ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ። እንደማሳያም “በጫት ንግድ ሐብታም ሆኑ የሚባሉ ሰዎች ልጆች ጭምር በጫት ሳቢያ አዕምሯቸው ተናግቶ በአዕምሮ ሕክምና ተቋማት ውስጥ ገብተዋል” ብለዋል።
“በጫት ለሚገኝ የአጭር ጊዜ ትርፍ አገኘሁ ተብሎ የትውልድ መፃዒ ዕድልን መሰዋት ተገቢ አይደለም” ያሉት ዶክተሩ “ይህ አስከፊ ሁኔታ አደገኛ ከሚባልበት ደረጃ ሁሉ አልፏል” ባይ ናቸው።
በአንድ በኩል በየመንደሩ እየዞረ የጫት ማስቃሚያ ቤቶችን የመዝጋት ቁጥጥር ለማድረግ እየሞከረ በሌላ በኩል በሽያጩ ተሰማርቶ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ምንጭ ከማድረግ ባለፈ አምራቹንና የዘርፉ ተዋያንን በተዘዋዋሪ መንገድ ማበረታታቱ አልሸሹም ዞር አሉ አይነት ነው። በጫት ላይ የሚደረገው ዘመቻ ሁለንተናዊ እንዲሆን በሳይንሳዊ ጥናት ማየትና በጥናቱም መሠረት ሁለንተናዊ የሆነ ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድ ከመንግሥት ይጠበቃል። (ማጣቀሻዎች፡- ቢቢሲ፣ ሸገር ራዲዮ፣ አማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ድርጅት፣ ዛጎል ድረ ገጽ…)
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012