ከሰሞኑ 70 የፖለቲካ ፓርቲዎች የረሃብ አድማ ለማድርግ መዘጋጀታቸውን እወቁልኝ ብለዋል። ምን ሲሆን መራብን መረጣችሁ? ሲባሉም ‹‹በምርጫና ፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ላይ በተደጋጋሚ ተቃውሞ በማሰማት እንዲሻሻል ብንማፀንም ምላሽ ማግኘት ባለመቻላችን ነው ›› ብለዋል።
የፖለቲካ ድርጅቶቹ ፓርላማው ሥራ ሲጀምር በሁለት የሥራ ቀናት ውስጥ አቤቱታቸውን የማያይ ከሆነ ጥቅምት አምስት እና ስድስት ቀን 2012 ዓ.ም የረሃብ አድማ ለማድረግ ዝተዋል። አያይዘውም በረሃብ አድማው ወቅትም የኢትዮጵያ ህዝብ ለክብሩ፣ ለነፃነቱ፣ ለእኩልነቱ፣ ለሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱ መከበር፣ ለሠላምና ለፍትህ መስፈን ስንል ለምናደርገው የረሃብ አድማ በመንፈሱ እንዲያስበን፣ በጾም በፀሎትም እንዲያግዙን፣ በሃሳብ እንዲረዳንና ከጐናችን እንዲቆም ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል። ከረሃብ አድማው ማግስት ጀምሮም የተቃውሞ ድምጽ ፊርማ እንደሚያሰባስቡ ገልፀዋል።
በመግለጫቸው በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል በንፁሃን ዜጐችና በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እንዲሁም በጋዜጠኞችና በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ እየደረሰ ነው ያሉት ጥቃትና እሥራት እንዲቆምና ታስረዋል የሚሏቸው ወገኖች እንዲፈቱ መጠየቃቸው ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅ ነው።
ነገር ግን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የትኛውንም አይነት ፖለቲካዊ ትግል ለማድረግ አመቺ ሁኔታዎች ባሉበት ወቅት ፓርቲዎቹ የመረጡት የትግል ስልት በበኩሌ ግርምትን የሚያጭር ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሰባዎቹን ፓርቲዎችና ምርጫ ቦርድን እያወዛገበ ያለው ዋነኛ ጉዳይ የአገር አቀፍና የክልል ፓርቲዎች ለመመስረት የሚያስፈልገው የመስራች አባላት ቁጥር ነው። አዋጁ አደገኛ የሆኑ የማያሳትፉ አንቀጾችን የያዘ አፋኝና ፀረ ዲሞክራሲ ነው የሚሉት ሰባዎቹ ፓርቲዎች አገር አቀፍ ፓርቲዎች ሲመሰረቱ የመስራች አባላት ቁጥር ሦስት ሺ፤ የክልል ፓርቲዎች ደግሞ አምስት ሺ እንዲሆን ከምርጫ ቦርድ ጋር ተስማምተን ነበር። ይህ ተቀይሮ ነው የመጣው ሲሉ ይከሳሉ። ምርጫ ቦርዱ በበኩሉ ሕግ ለማርቀቅ ግብዓት ተጠየቀ ማለት የተገኘው ግብዓት ሁሉ ሕግ ይሆናል ማለት አይደለም ሲል ይመልሳል።
እኔ የምለው … ፓርቲዎቹ የፓርቲ መስራች አባላት ቁጥር ዝቅ እንዲልላቸው ለመጠየቅ ከሚሰበሰቡ በመሀከላቸው ያለውን ልዩነት አጥብበው ውህድ ፓርቲ ለመሆን ቢሠሩ አይሻልምን ? አንድ አሊያም ሁለት መሆን ቢችሉ ተፈላጊውን የመስራች አባላት ቁጥር ከማሟላት አልፈው የህዝባቸውን ጥያቄዎች መመለስ የሚችሉበት ቁመና ላይ መገኘት ይችሉ ነበር። አሁን የያዙት መንገድ ግን አዋጁ ሥራ ላይ ከዋለ የፖለቲካ ድርጅቶች መሆናችን ያበቃና የእንጀራ ገመዳችን ተበጥሶ ለዓመታት እንራባለን፡፡ ስለዚህ ሁለት ቀን ተርበን አዋጁ እንዲሻሻል እናድርግ የሚል ይመስላል።
አዋጁ ሲፀድቅ በምክር ቤቱ ተገኝቼ ነበር። አንድ የምክር ቤቱ አባል የአገር አቀፍ ፓርቲዎች የመስራች አባላት ቁጥር 10 ሺ መሆኑን አስመልከተው ሀሳባቸውን ሲገልፁ፣ ከአንድ መቶ ሚሊየን በላይ ህዝብ ባላት አገር ውስጥ 10 ሺ መስራች አባላት ማሟላት የማይችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘርፍ ቀይረው በሌላ መስክ ቢሰማሩ ይሻላል ብለው የፓርላማ አባላቱን ሳቅ ጋብዘው ነበር። እንደኔ የምክር ቤት አባሉ ትክክል ናቸው። የመስራች አባላት ቁጥርን ማሟላት ያልቻለ ፓርቲ፣ ሲሆን ከሌሎች ጋር መዋሐድ፤ ካልሆነ ደግሞ በፎርፌ መውጣት እንጂ ከቁጥር ጋር መቋጠር የለበትም።
የረሃብ አድማው አስተባባሪዎች አንዳንድ አስቂኝ ንግግሮች ሲያደርጉ ተደምጠዋል። ለምሳሌ ውሃ ትጠጣላችሁ ወይ? ተብለው ሲጠየቁ ‹‹ገና አልተወሰነም፤ መስከረም 27 ቀን ዝርዝር መግለጫ እንሰጣለን›› ብለው እርፍ። አመራሮቹ አንበላም አንጠጣም ብለው አድማ ሲመቱ “እኔን የራበኝ ቁጥር ነው” በሚል ሙዚቃ ብቻ ይታጀባሉ ብለን ስንጠብቅ ውሃ ላይ ለመጨከን ማመንታት ላይ መሆናቸውን ተረዳን። ማን ያውቃል ውሃው የሚፈቀድ ከሆነ ደግሞ ወደ ሚደጋገም ውሃ ከፍ ሊል ይችላል። እንዲህ እንዲያ እያለ የፓርቲዎቹ የረሃብ አድማ ፓርቲ ሆኖ እንዳይገኝ ያሰጋል።
ሌላው ገራሚ ጉዳይ አዋጁ እንዲሻሻል ህዝቡ በጾምና በጸሎት እንዲያግዛቸው መጠየቃቸው ነው። ህዝብ በጾምና በጸሎት መትጋት ያለበት አገር እንድትጠበቅና ሰላም እንድትሆን ነው። የምርጫ አዋጁ እንዲሻሻል የፈለገ የፖለቲካ ድርጅት ህዝብን በማንቀሳቀስ ፖለቲካዊ ትግል ማድረግ እንጂ ጾምና ጸሎት ማወጅ የለበትም። ይህች ባቄላ ካደረች … እንዲሉ እንዲህ ያለ አዝማሚያ በጊዜ መስመር እንዲይዝ ካልተደረገ ሕግ አውጪዎች ያጸደቁት አዋጅ ያልጣመው የፖለቲከ ድርጀት ሁሉ ብድግ እያለ በጾምና በጸሎት አግዙኝ ሊለን ነው። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ድርጅቶች ጉባኤ፤ የለም ጾምና ፀሎት ያለቦታው አትጥቀሱ ፖለቲካና ሃይማኖት ለየቅል ናቸው ማለት አለበት።
የ70ዎቹ ፓርቲዎች አስተባባሪ ኮሚቴ ፀሐፊ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ የረሃብ አድማ ምን ያህል አዋጭ የፖለቲካ ትግል ነውን? ተብለው ተጠይቀው ሲመልሱ ‘‘ሕሊና ያለው አካል፣ ለሕዝብ ደንታ ያለው አካል፣ የሕዝብ ብሶት፣ ሮሮ፣ ጥያቄ፣ ሊሰማና ሊደመጥ ይገባል የሚል መንግሥታዊ ሥልጣን ላይ የተቀመጠ አካል ካለ፣ ከረሃብ አድማ በላይ አስከፊና አስነዋሪ ተቃውሞ የለም። አንድ ሰው ራሴን ለረሃብ አጋልጣለሁ ሲል እሞታለሁ ከሚል በምንም አይተናነስም። ስለዚህ ወደዚህ ተቃውሞ የሚገቡ አካላት ለምንድን ነው ወደዚህ ተቃውሞ የሚገቡት ማለትና መስማት የሚችል ባለሥልጣን በሀገራችን ካለ፣ ዲሞክራት መሪ ካለ ይኼ ተቃውሞ መንግሥት ሊሰማውና ሊያዳምጠው የሚገባው ተቃውሞ ነው።
ነገር ግን መንግሥት ላይ ድንጋይ እንደመወ ርወር፣ ጥይት እንደመተኮስ ወይንም የሆነ ተቋም እንደማቃጠል፣ አስደንጋጭ ላይሆን ይችላል። አምባገነን መንግሥታት ጥይት ሲተኮስባቸው፣ ድንጋይ ሲወረወርባቸውና የሆነ የሚፈነዳ፣ የሚያቃጥል ነገር ሲመጣ ነው የሚደነግጡት። ለእንደዚህ ዓይነት ተቃውሞ ጆሮም ግድም አይሰጡም። ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ካለ ግን ከጥይት ጩኸትና ከቦምብ ፍንዳታ በላይ ይህ ትክክለኛ ተቃውሞ ነው’’ ብለዋል።
ይህ ንግግር ፓርቲዎቹ አሁን ያለው ሥርዓት ዲሞክራሲያዊ መሆንና አለመሆን ላይ ገና አቋም እንዳልያዙ ገላጭ ነው። ብዙውን ጊዜ የረሃብ አድማ ግለሰቦች መብቶቻቸው ተገድበው መንም አይነት ፖለቲካዊ እንቅስቀሴ ማድረግ ሳይችሉ ሲቀሩ ምርጫ በማጣት የሚያደርጉት ትግል ነው። የረሃብ አድማን ለዓለም ያስተዋወቀው ማህተመ ጋንዲ ጥሩ ምሳሌ ነው። በረሃብ አድማ ብዛት ከስቶና ገርጥቶ ይታይ የነበረው ጋንዲ በ 1940 ዓ.ም ህይወቱ በሰው እጅ እስከጠፋበት ዕለት ድረስ የእንግሊዞችን ከፋፋይ ሥርዓት ታግሏል። ጋንዲ የህንድን ሕብረተሰብ ያዳክማል በሚል እንግሊዞች የመምረጥ መብትን በዘርና በጎሳ መከፋፈላቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ እስር ላይ በነበረበት ወቅት የመጀመሪያውን የረሃብ አድማ ለአራት ቀንና ሌሊት ካደረገ በኋላ የእንግሊዞችን እጅ መጠምዘዝ ቻለ። ጋንዲ የረሃብ አድማን በተደጋጋሚ በማድረግ መደበኛ የትግል ስልት አደረገው። መራቡ የፖለቲካ መሣሪያውና መደራደራያ አቅሙ ነበር። የኋላ ኋላም ያለመታከት የመራው ሰላማዊ ተቃውሞ ህንድ ነጻነቷን እንድትቀዳጅ አደረጋት።
አንድ ህጋዊ እውቅና ያለው ፓርቲ ግን የረሃብ አድማ ሐዲድ ላይ ቢገኝ የሚያምርበት የማያፈናፍን አፋኝ ሥርዓት ሲሰፍን ነው። መገናኛ ብዙኃንን ጠርቶ ይህን መግለጫ መስጠት የቻለ የፓርቲዎች ስብስብ መደበኛ የፖለቲካ ድርጅት የትግል ስልቶችን ወደጎን ብሎ ዘሎ የረሃብ አድማ ላይ ፊጥ ማለቱ ሳይወዱ ያስፈግጋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
የትናየት ፈሩ