በበረከት የተትረፈረፍንበት የክረምቱ የዝናብ ወቅት አልፎ በለምለሙ መስከረም ወር መጨረሻ በዕለተ ሰኞ መስከረም 26/2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደራሴዎች መሰብሰቢያ የሆኑት የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባቸውን አካሂደዋል።
በመክፈቻ ስብሰባው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ፣ የሃይማኖት አባቶች ታዋቂ ግለሰቦችና አምባሳደሮች የታደሙበት ነበር። በእለቱ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በ2012 በጀት ዓመት የሚተገበሩ የመንግስትን ዋናዋና የስራ ዕቅዶች አቅርበዋል።
በክብርት ፕሬዚዳንቷ የሚቀርበው የመክፈቻ ንግግር በበጀት ዓመቱ በመንግስት የሚከናወኑ ተግባራት የሚታወቁበት እንደመሆኑ በበርካታ ዜጎች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ ነው። ክብርት ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው መግቢያም “ያለፈው ዓመት በሀገራችን የጀመርነው የለውጥ እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ እንዲተገበር ጥረት ያደረግንበት ወቅት ነበር።
በፖለቲካ፣ በዲሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ በፍትሕ ሥርዓት እና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የነበረብንን ሀገራዊ ጉድለት ማስተካከል የጀመርንበት ነው። ይሁንና ጉድለቱን በተሟላ ሁኔታ ያቀናንበት ደረጃ ላይ ግን ገና አልደረስንም”ብለዋል።
“በ2012 ዓ.ም. የለውጡን ጉዞ የተሻለ መሠረት የምናስይዝበት ይሆናል” ያሉት ፕሬዚዳንቷ “እንደሚታወቀው የለውጡ ጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አነሳሽነት በመተግበር ላይ የሚገኘውን የመደመርን ዕሳቤ መሠረት አድርጎ የሚጓዝ ነው። ይህ ዕሳቤ ደግሞ በሦስት ዋነኛ ሀገራዊ ዓላማዎች ላይ የተመሠረተ ነው።
እነርሱም፡ – በሀገሪቱ የነበሩ መልካም የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎችን ጠብቆ ማስፋት፣ – ባለፉት ዘመናት የተሠሩ ስህተቶችን ማረምና – የመጪውን ትውልድ ፍላጎትና ጥቅም ማሳካት ናቸው። የእነዚህ ዓላማዎች ዋነኛው ማጠንጠኛ ሦስቱን ግቦች ለማሳካት መቻል ነው። እነዚህም፡- የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት ማስጠበቅ፣ የሕዝቧን ክብር ከፍ ማድረግና – ብልጽግናን ማምጣት ናቸው።” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ በ2012 በጀት ዓመት በመንግስት የሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን የዘረዘሩ ሲሆን ከሁሉ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንደሚሰራ የገለጹት ግን የአገሪቱንና የህዝቦቿን ሰላም ማረጋገጥ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ “ሠላምና መረጋጋትን ማረጋገጥን በተመለከተ ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ሀገራችንን ወጥረው ከያዟት ችግሮች አንዱ የውስጣዊ መረጋጋት እጦትና በየቦታው የሚከሠቱ የተለያየ ይዘት ያላቸው ግጭቶች መፈጠር ነው።
ግጭቶቹን ተከትሎ የመጣው የውስጥ መፈናቀልም በታሪካችን ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ምዕራፍ ሆኗል። በተመሳሳይ ዓመት አገራችን ከጎረቤት አገራት የተሰደዱትን ማስተናገዷን የቀጠለችውን ያህል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ በገዛ ሀገራቸው ተፈናቃይ የሆኑበትን አሳዛኝ የታሪክ ገጽ አልፈናል። ይሁን እንጂ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ባለፈው አንድ ዓመት በጋራ ባደረጉት ርብርብ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የነበረው የውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከመቶ ሺ የማይዘል ሆኗል። እርሱንም ፈትተን ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ወደ ታሪክነት ለመቀየር እየተሠራ ነው” ብለዋል።
ከዚህ አንጻር በተያዘው በጀት ዓመት “በመልሶ ማስፈርና ዘላቂ ማቋቋም መርሐ ግብር ወደ ቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን ወደ ተሟላ መደበኛና የተረጋጋ ኑሮ የመመለስ ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። መሰል ክስተቶች ዳግም እንዳይፈጠሩ መፍትሔ አምጪ ሥራዎች ይከናወናሉ። የደኅንነት ተቋማት ችግሮች ከመከሠታቸው በፊት ቀድመው የማነፍነፍ አቅማቸው እንዲያድግና ችግር ሲከሠትም በአጭር ጊዜ የማስቆም ብቃታቸው እንዲጎለብት የሚያስችሉ የአቅም ማሻሻያ ተግባራት ይሠራሉ።
በዚህ ረገድ ፌዴራል ፖሊስ ብቁ አቅም እንዲኖረው ለማድረግ የተጀመረው የሪፎርም ጥናት ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ይሸጋገራል። በሂደቱም የአሠራርና የሕግ ማዕቀፎቹን በማሻሻል በአጭር ጊዜ በጠንካራ ዶክትሪን የሚመራ ጠንካራ የፌዴራል ፖሊስ ይኖረናል። የክልል ፖሊሶችም አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያደርጉ ተግባራት ይከናወናሉ። እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊታችን በሙያ አቅም የላቀ እንዲሆን እየተሠሩ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ” ሲሉ ዘርዝረዋል።
እውነት ነው እንኳን አገራዊ የግልና ቤተሰባዊ ዕቅድ እንኳን ሊተገበር የሚችለው ሰላም ሲሰፍንና ሲረጋገጥ ብቻ እንደመሆኑ መንግስት በዓመታዊ ዕቅዱ ለሰላም ይህን ያህል የቅድሚያ ትኩረት መስጠቱ ይበል የሚሰኝና የሚበረታታ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ያለ ሰላም የዓመቱን ይቅርና የቀንና የሰዓት ዕቅድን እንኳን በአግባቡ ማከናወን እንደማይቻል ከማንም የተሰወረ አይደለምና።
አፋኝ ህጎች በተወገዱበት፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ያለምንም ገደብ በተፈቀደበትና የሃሳብ ወድድር መድረክ ብርግድ ብሎ በተከፈተበት በዚህ ወቅት በሰበብ በአስባቡ ሰላምን ማደፍረስና አገርንና ህዝብን ማተራመስ በፍጹም ሊፈቀድ አይገባም። ይህንን ዕውን ለማድረግ ደግሞ ህዝባዊ ወገንተኝነትን የተላበሰውን የጸጥታ ኃይሉን አቅም በየደረጃው ለማጎልበትና ህዝቡን የሰላሙ ጠባቂ ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ያለማወላወል በስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2012