መስከረም በርካታ የአደባባይ በዓላት የተከበሩበት ወር ነው። በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በአደባባይ በመውጣት ያከበረው የደመራ፣ የወላይታ የዘመን መለወጫ /ጊፋታ/፣ የሃዲያ የዘመን መለወጫል /ያሆዴ/ እንዲሁም ትናንትናና ከትናንት በስቲያ በብዙ ሚሊዮን ህዝብ የታደመባቸው የፊንፊኔና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓላት ወሩን ያደመቁ ክብረበዓላት ሆነው አልፈዋል። እነዚህን በዓላት ሁሉ የሚያስተሳስረው የዓለም የቱሪዝም ቀንም በዚሁ ወር በድሬዳዋ ከተማ መከበሩ ይታወሳል።
እነዚህ በዓላት ደግሞ በአንድ በአኩል በህዝቦች መካከል ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አገራዊ አንድነትን ለመፍጠር ትልቅ ፋይዳ የነበራቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለአገራችን ትልቅ የቱሪዝም መስህቦች ናቸው። በነዚህ በዓላት ላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያዩ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከመሳተፋቸውም በላይ በርካታ የውጭ አገር ቱሪስቶችም ታድመውባቸዋል።
እነዚህ በዓላት ከመከበራቸው በፊት የተለያዩ ስጋቶች እንደነበሩ ግን አይዘነጋም። በተለይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የታደመበትና ከአንድ መቶ አምሳ ዓመት በኋላ በፊንፊኔ ከተከበረው የኢሬቻ በዓል ቀደም ብሎ የተለያዩ የሰላም ስጋቶች እንደነበሩ ይታወሳል። ይህን በዓል ለማደናቀፍና በህዝብ መሃል ግጭት ለመፍጠር እቅዶች እንደነበሩም ይታወሳል። ለዚህም በበዓሉ ላይ ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ማሳያ ነው።
ያም ሆኖ ግን በፀረ ሰላም ኃይሎች የታሰበው ሰላምን የማደፍረስ ፍላጎት ከምኞት አላለፈም። በህዝቦች መካከል ግጭት በመቀስቀስ ከሚፈጠረው እልቂት የሚወርደውን ደም ለማየት የጓጉ ጠላቶችም ከግጭት ይልቅ መከባበርና አንድነትን፣ ከብጥብጥ ይልቅ ደስታና ፍቅርን ሳይወዱ በግድ መመልከት ችለዋል። ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ በአንድ በኩል ሰላም ወዳድ በሆነው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳትፎ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለሰላም በቁርጠኝት በቆሙ የፀጥታ አካላት ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምን የሚያደፈርሱ አካላት የመሸከም ታሪክም የለውም። በተለይ ህዝብና ህዝብን የሚያጋጩና የእርስ በርስ ግጭቶችን የሚፈጥሩ ድርጊቶችን ለመዋጋት ወደኋላ ያለበት ታሪክ የለውም። ለዚህም ሽብርተኛ ቡድኖች በኢትዮጵያ ጥቃት ለመፈፀም በተደጋጋ የሚ ያደርጓቸው ሙከራዎች መክሸፋቸው ማሳያ ነው።
በተለይ አልሸባብና አልቃይዳን የመሳሰሉት የሽብር ቡድኖች በሌሎች አገራት ያደረሱትን ጥቃት በኢትዮጵያ ለመድገም በተደጋጋሚ ፍላጎት እንዳላቸው ቢያሳዩም ሊሳካላቸው አልቻለም። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በዋናነት የህዝቡ ጥረትና ለዚህ ተግባር ተባባሪ አለመሆን ነው። ህዝቡ እንዲህ አይነት ተግባራትን አጥብቆ ስለሚጠየፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት ለሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት በመጠቆምና ከፀጥታ አካላት ጋር አብሮ በመስራት ሰላም እንዳይደፈርስ ሲሰራ ቆይቷል፤ አሁንም እየሰራ ይገኛል።
በሌላ በኩል እነዚህ በዓላት በዚህ መልኩ በሰላም መከበራቸው የፀጥታ አካላት ብቃት አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመላክት ነው። በዚህ ወር እንዳየነው በተከታታይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አደባባይ ወጥተው በዓሎቻቸውን በሰላም ማክበራቸውና ያለምንም ኮሽታ ወደቤታቸው መመለሳቸው የፀጥታ አካላት ሰላምን የመጠበቅ ብቃታቸው አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመላክት ነው።
በአገራችን በዚህ የበዓል ሰሞን የታዩት የፀጥታና የአንድነት መንፈሶች ደግሞ ዘላቂ ሊሆኑ ይገባል። በተለይ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀውን የአገራችንን ለውጥ ተከትሎ እዚህም እዚያም ሲከሰቱ የነበሩ ግጭቶችና የዜጎች መፈናቀሎች ቆመው እንደሰሞኑ የህዝብ አንድነት የሚፈጠርበት ሁኔታ ሊጎለብት ይገባል።
የተለያዩ የግጭት አጀንዳዎችን እየፈጠሩ ህዝብና ህዝብን ለማጋጨት የሚጥሩ አካትም ከዚህ ድርጊታቸው ታቅበው በአገራችን ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከሰሞኑ የክብረበዓል ተሞክሮ ወስደን ልንጠቀምበት ይገባል።
እነዚህ ክብረበዓላት ያስተማሩን ትልቅ ፍቅርና አንድነት ነው። ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎቸ የተሰባሰቡ ብሄር ብሄረሰቦች የየራሳቸውን አልባሳት ለብሰውና በራሳቸው ቋንቋ ደስታቸውን እየገለፁ የሌላውን በዓል ሲያደምቁ ማየት የኢትዮጵያ ህዝብ ጥልቅ ውስጣዊ አንድነትና ውህደት ያለው መሆኑን የሚያመላክት ነው። በመሆኑም ይህንን የአንድትና የፍቅር ገመድ ለመቁረጥ ለሚጥሩ አካላት መቀስ ማቀበል ፈጽሞ ሊቆም ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት የኖረና መቼም የማይነጣጠል መሆኑን በመገንዘብም ግጭት የሚፈጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እናድርግ።
አዲስ ዘመን መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም