ኢሬቻ በአደባባይ ከሚከበሩና ህዝብ አሳታፊ ከሆኑ ታላላቅ በዓላት አንዱና ዋነኛው ነው። ኢሬቻ በዓመት አንድ ጊዜ የመስቀል በዓል ካለፈ በኋላ ሁሉም የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት፣ በሰላም፣ በፍቅር እና በይቅርታ የሚያከብረው በዓል ነው።
በዚህ በዓል የሃይማኖት፣ የጾታ እና የዕድሜ ልዩነት ሳይደረግ ሁሉም የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት ወጥቶ ለፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል። ጨለማውን ወራት አሳልፈህ፣ የሰማዩን ጭጋግ ገፈህ ብርሃን አመጣህልን፣ ለምለም አሳየህን፣ የወንዙን ሙላት አጉድለህ የተራራቅነውን ሰዎች አገናኘህን፣… ብለው እርጥብ ሳር ጨብጠው ለአምላካቸው ምስጋና የሚያቀርቡበት ዕለትም ነው። ታዲያ ይሄ ምስጋና የሚደርሰው ዝም ብሎ በደፈናው ሳይሆን የተጣላ ካለ ታርቆና ሰላም ወርዶ ነው። “ቂም ይዞ ጸሎት ሳል ይዞ ስርቆት” በኢሬቻ የማይታሰብ ነውና! በኢሬቻም ቂምና ጥላቻ ይዞ ለምስጋና አይወጣም። ትናንት በሆራ ፊንፊኔ፣ ሆነ ዛሬም በሆራ አርሰዴ ኢሬቻ ሲከበር በዚሁ እሳቤ ነው። በአጠቃላይ ኢሬቻ ልብን ንጹህ አድርጎና በፍቅር እና በአንድነት ተሁኖ የሚከበር ልዩ በዓል ነው።
በሀገራችን የተለያየ የአደባባይ በዓላት አሉ። አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና መስቀልን የመሳሰሉ በዓላት ከተከበሩ በኋላ ነው ኢሬቻ የሚከበረው። በእነዚህ የአደባባይ በዓላት ላይ ከሁሉም ሃይማኖት እና ብሔር የበዓሉ ታዳሚ በመሆን በዓሉን ያከብራል። በበዓሉ ላይም ከሀገር ውስጥ ዜጎች በተጨማሪ የውጪ ሀገር ቱሪስቶችም ታዳሚ ይሆናሉ።
እነዚህ ህዝብን ከህዝብ የሚያገናኙ፣ የአንዱን ባህል ከሌላው ጋር የሚያስተዋውቁና የህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያጠናክሩና የአንድነት በዓላት ናቸው። ኢሬቻም ከእነዚህ የህዝብና የአደባባይ በዓላት አንዱ እና በኦሮሞ ማህበረሰብ የሚናፈቅ በዓል ነው።
የኦሮሞ ህዝብ፣ የጾታ፣ የእድሜ፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይገድበው በጋራ ባህሉንና ታሪኩን፣ አንድነቱን፣ ወንድምና እህትማማችነቱን የሚገልጽበት ከመሆኑም ባሻገር፣ ባህሉን ለማደስ፣ ለማጠናከር፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ቃል የሚገባበት፣ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት እንዲሁም ለቀጣዩ ደግሞ መልካም ነገር እንዲገጥመው የሚመኝበትና ቃልኪዳኑን የሚያጸናበት፣ ሰላምንና አንድነትን ማጠናከሪያ በዓል ነው።
ኢሬቻ የክረምቱ አስከፊ ሁኔታ የወንዝ ሙላት፣ የበረዶ፣ የነጎድጓድና የጎርፍ ጊዜ አልፎ እየተመናመነ የመጣው ጎተራ በአዲስ ሰብል ሊሞላ ተስፋ የሚሰነቅበት ብሩህ ጊዜ ከፊት ለፊት መምጣቱን ማብሰሪያ ምልክት ነው። እናም በበዓሉ የሰው ልጆች ሁሉ ብሩህ ተስፋ እያዩ ለዚህ ያበቃቸውን ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፤ መጪው ዘመን የተሻለ እንዲሆንላቸውም በፀሎት ይማጸናሉ።
የብሔር ብሔረሰቦች መናኸሪያ በሆነችው አዲስ አበባ የአሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሶለልና መስቀል በዓላት በቅርብ ጊዜ በድምቀት ተከብረዋል። ትናንት ደግሞ ሆራ ፊንፊኔ አዲስ አበባ ላይ ልዩ በሆነ ህብረ ዜማ፣ ጭፈራ እና ሽለላ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በደመቀ ህብርና በአስደናቂ ሁኔታ ተከብሯል።
ይሄ አንድነትን የማጠናከሪያ በዓልና ባህልን ማስተዋወቂያ መድረክ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል። በዓሉን ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ወንድምና እህት ከሆኑት የኦሮሞ ህዝቦች ጋር በአንድነት፣ በፍቅር እና በመተሳሰብ አሳልፈዋል። ይሄ በጣም የሚያኮራና ኢትዮጵያን ወደ አንድ ከፍታ የሚያወጣ ነው። በመሆኑም ለበዓሉ ድምቀትና ከፍታ የመንገድ ርቀት ሳይገድባቸው፣ ገንዘባቸውንና ውድ ጊዜያቸውን ሰውተው የተገኙ ዜጎች ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።
በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ወጣቶች ህዝቡን በማስተባበር፣ እንግዶቻችን የሁላችንም በሆነችው መዲናችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የሚበሉትና የሚጠጡት በማዘጋጀት በፍቅር ተቀብለው በሰላም በመሸኘት እንግዳ ተቀባይነታቸውን አስመስክረዋል።
ብርድና ሙቀት ሳይበግራቸው ሌት ተቀን ለሰላም ዘብ በቆሙ የጸጥታ ኃይሎች ሥራና በሰላም ወዳዱ ህዝብ ጥረትም በሁሉም አቅጣጫ እንግዶቹ በሰላም መጥተውና በፍቅር እና በደስታ በዓሉን አክበረው በሰላም ተመልሰዋል። ለዚህም አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሁሉ ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል።
ይህንን አኩሪ የጋራ እሴት ዘላቂ አድርጎ መጠቀም፣ ብሎም በህዝቦች መካከል ፍቅርና አንድነት ማጽኛ ድልድይ ማድረግ ይገባል፡፡ በዓሉ የህዝቡ ፍቅርና አቃፊነት አደባባይ የወጣበትና እኛ ኢትዮጵያውያን በፍቅር ተሳስረንና ተደጋግፈን ለመኖራችንም ምስክር ነው፡፡ ይሄው አኩሪ አንድነት፣ ፍቅርና ድምቀት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል!
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2012