ክረምቱ አልፎ፣ ብርሃኑን ያሳየን ፈጣሪያችንን በደስታ ለምናመሰግንበት ቀን ኢሬቻ እንኳን በሠላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። በዚህ ቀን ሰዎች ከየቦታው ተሰብስበው አብረው ፈጣርያቸውን ያመስግናሉ፣ ይደሰታሉ። ደስታ ደግሞ በሳይንስ የተረጋገጠ የጤና ጥቅም እንዳለው በዚሁ ልንገራችሁ።
1. ስንደሰት በሰውነታችን የሚገኙ በሽታን የሚከላከሉ ሴሎች ይበዛሉ፤ በዚህ ምክንያት በሽታን የመከላከል አቅማችን ይጨምራል።
2. የልባችን ጤንነት ከድሮ የበለጠ የተጠበቀ ይሆናል።
3. በጭንቀት ምክንያት የሚመጡ በቁጥር የበዙ በሽታዎች እንዳያጠቁን ይከላከላል።
4. መደሰት በህመምም ሆነ በሌላ ምክንያት የሚመጡብን የህመም ስሜቶች እንዳይሰሙን በማድረግ አጠቃላይ ጤንነታችን ጥሩ እንዲሆን ያደርጋል።
5. ከላይ በተጠቀሱ እና በሌሎች ምክንያቶች ኣብዛኛውን ጊዜ የሚደሰቱ ሰዎች፤ ከማይደሰቱ ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ ረዥም ዕድሜ እንደሚኖሩ በዙ ጥናቶች ያረጋግጠሉ። ይህንን ካልኩ በኋላ ዛሬ ይዤላችሁ ወደ ቀረብኩት ርዕሰ ጉዳይ ላምራ፡-
ክፍል 1፡- የነቀርሳ በሽታ (Tuberculosis)
የነቀርሳ በሽታ (Tuberculosis) ምንድነው? ምን ያህል ነፍስን/ ህይወትን ይቀጥፋል?
የነቀርሳ በሽታ (Tuberculosis) በአይን ከማይታዩ (Mycobacteria Tuberculosis) ተብለው ከሚጠሩ ባክቴሪያዎች የሚመጣ ነው። ከባክቴሪያ ከሚመጡ በሽታዎች ይህንን በሽታ ልዩ የሚያደርገው አጠቃላይ የሰዎችን አካል የሚጎዳ መሆኑ ነው። ቢያንስ 2 ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በዚህ ነቀርሳ ባክቴሪያ ተይዘዋል። ይሁን እንጂ በዚህ ባክቴሪያ መያዝ ማለት በነቀርሳ በሽታ መያዝ ማለት አይደለም። ብዙውን ጊዜ ሰውነታችን ይህንን በሽታ ተቋቁሞ በማሸነፍ ባክቴሪያው በሽታ ሆኖ ምልክት እንዳያሳይ ያደርጋል። ስለዚህ በሽታን የመከላከል ችሎታቸው ደካማ የሆኑ ሰዎች እንደ ኤች አይቪ/ ኤድስ፣ ካንሰር እና የሰውነት የበሽታ መከላከል አቅምን ዝቅ የሚያደርጉ መድሃኒቶች ለዚህ በሽታ በጣም ያጋልጣሉ።
እ.ኤ.አ. 2003 ውስጥ 8.8 ሚሊዮን የሆኑ ሰዎች በበሽታ ተይዘው 1.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው በዚሁ በሽታ አልፏል። በኢንፌክሽን እንደሚተላለፉ ሌሎች በሽታዎች የነቀርሳ በሽታ ይበልጥ የሚቀጥፈው በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ህዝቦችን ነው። የአለም የጤና ድርጅት ሪፖርት ባደረገው መሰረት ኢትዮጵያ የነቀርሳ በሽታ ከሚበዛባቸው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ 3ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ስትሆን ይህም በሽታው ምን ያክል አገራችንን እየጎዳ እንደሚገኝ በግልፅ የሚያመላክት ነው።
በሽታው የሚተላለፈው በእንዴት አኳኋን ነው?
ይህ በሽታ በትንፋሽ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን የነቀርሳ በሽታ ያለበት ሰው በሚያስልበት ጊዜ ጥቃቅን የውሃ እንጥብጣቢዎች ወደ አየር ይለቀቁና ጤናማ ወደ ሆኑ ሰዎች አፍ ባክቴሪያው ሲገባ ነው። ከሳምባ ውጪ በሆኑ ነቀርሳዎች (ለምሳሌ የአጥንት ነቀርሳ፣ የአንጎል ነቀርሳ፣ የአንጀት ነቀርሳ እና የመሳሰሉት) በሽታዎች ያለበት ሰው ይህንን በሽታ ወደ ሌላ ሰው አያስተላልፍም፤ እንደዚሁም የሳምባ ነቀርሳ በሽታ ያለበት ሰው ደግሞ ህክምና ከጀመረ አንድ ወር በኋላ (ከመድሃኒት ጋር የተላመደ ነቀርሳ ካልሆነ) ወደ ሌላ ሰው የመተላለፉ እድል በጣም ዝቅተኛ ነው። ይህ ነቀርሳ አንዳንድ ጊዜ በተለይም ህፃናት ያልፈላ የላም ወተት ቢጠጡ በዚህ በሽታ ሊያዙ ይችላሉ። ነቀርሳን ታክመው መዳንም ሆነ መከላከል ይቻላል።
የነቀርሳ በሽታን እንዴት እንከላ ከላለን?
በአካባቢያችን አየር በቀላሉ እንዲተላለፍ (እንዳይታፈኑ) ማድረግ አንዱ የበሽታው መከላከያ መንገድ ነው። ይህ በሽታ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው ብዙውን ጊዜ ሰዎች በሚበዙበት ቦታ እና አየር በትክክል ገብቶ የማይወጣበት (የታፈነ) ቦታ ነው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት (Public Transport) ነው። ብዙውን ጊዜ በህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ውስጥ ተቀራርበው የተቀመጡ ሰዎች በተለይም የመኪናው መስኮት ካልተከፈተ የሰው እስትንፋስ ከአንዱ ወደ ሌላው በመግባት ወደ ጤናማ ሰው የመተላለፍ እድሉ ከፍተኛ ነው። ብዙውን ጊዜ በህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ውስጥ በምንቀመጥበት ጊዜ ‹‹ንፋስ እንዳይመታኝ መስኮቱን ዝጋልኝ›› ሲባል እንሰማለን። በተለይም አንዳንድ ሰዎች ከሰው ትንፋሽ ይልቅ ከውጪ የሚመጣ አየርን በጣም ሲፈሩ ይታያሉ። እንዲህ አይነቱ ልማድ ያለባቸው ሰዎች በሳምባ ነቀርሳ የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል ማለት ነው።
ለህጻናት ወተት በሚሰጥበት ጊዜም ሆነ ወተት በሚጠጡበት ጊዜ በሚገባ አፍልቶ መስጠት ግድ ይላል። ከሳምባ በሽታ ምልክቶች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ምልክቶችን ካዩ (በተለይም ከሁለት ሳምንታት በላይ መሳል) ወደ ሀኪም ቤት መሄድ ለራሳቸው ከመዳናቸውም ባሻገር ወደ ሌላ ሰው እንዳይተላለፍ ያደርጋል።
የሳምባ ነቀርሳ በሽታ ያለበት መሆኑ የተነገረው ሰው እንዲሁም ከሁለት ሳምንታት በላይ ሳል ያለበት ሆነው ወደ ሀኪም ቤት ሄዶ ያልታየ ሰው ሲያስለው ወደ ሌላ ሰው እንዳይተላለፍ አፉን በጨርቅ ይዞ መሳል የሚጠበቅበት ግዴታ በመሆኑ ይህን ግዴታውን መወጣት አለበት። ከመድሃኒት ጋር የተላመደ የሳምባ ነቀርሳ በሽታ ያለበት ሰው ደግሞ ታክሞ እስኪድን ወይም በሚያክመው ባለሙያ ከቤተሰብ ወይም ከማህበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀል እስኪነገረው ድረስ ሀኪም ቤት ቆይቶ ለእንዲህ አይነቶቹ ሰዎች ታስቦ በተዘጋጀው ቦታ ሆኖ መታከም ግዴታው ነው።
የነቀርሳ በሽታ የሚጎዳቸው የሰውነታ ችን አካላት የትኞቹ ናቸው?
የነቀርሳ በሽታ ከላይ እንደተገለጸው ከሰው ልጅ አካል ውስጥ የማይጎዳው ቦታ የለም ማለት ይቻላል። ነገር ግን በብዛት ከሚጎዳቸው የሰውነት አካላት ውስጥ፡- ሳምባ፣ አንጀትን፣ አንጎልን፣ አጥንትን፣ ኩላሊትን፣ የሽንት ቧንቧን እና የልብ ሽፋንን ይጎዳል።
በአጠቃላይ የነቀርሳ በሽታዎች ከሳምባ ነቀርሳ እና ሌሎች ነቀርሳዎች (የአንጀት ነቀርሳ፣ የአንጎል ነቀርሳ፣ የአጥንት ነቀርሳ፣ የኩላሊት ነቀርሳ፣ የሽንት ቧንቧ ነቀርሳ፣ የልብ ሽፋን ነቀርሳ እና የመሳሰሉት) በማለት በሁለት ቦታዎች ለይተን ማየት እንችላለን።
የሳምባ ነቀርሳ፡- ከሰው አካላት ውስጥ ሳምባ ብዙውን ጊዜ በነቀርሳ የሚጠቃ ሲሆን በማህበረሰቡ ውስጥም ‹‹የሳምባ ነቀርሳ በሽታ›› ሲባል ሳምባን ብቻ እንደሚይዝ የሚታየው ለዚህ ነው። የሳምባ ነቀርሳ በሽታ ምልክቶች ሳል (በተለይም ከሁለት ሳምንታት በላይ ያስቆጠረ ሳል)፣ ምግብ ማስጠላት፣ የሰውነት ክብደት ከመጠን በላይ መቀነስ፣ ማታ ማታ ከባድ ላብ (ልብስን እስኪያረጥብ ድረስ) ማላብ እና ትኩሳት ናቸው። የሳምባ ነቀርሳ በሽታ ‹‹አክታ››ሊኖረውም፤ ላይኖረውም ይችላል፤ እንዲሁም አክታው ደምም ሊኖርበት ይችላል። በሽታ የመከላከል አቅማቸው/ችሎታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች ማለትም ኤች አይቪ በሽተኞች እና መሳል የማይችሉ ትናንሽ ህጻናት ላይ ብዙም ምልክቶች ሳይታይባቸው በዚህ በሽታ ሊያዙ ይችላሉ።
ከሳምባ ነቀርሳ ውጪ የሆኑ ነቀርሳዎች፡ ከሳምባ ነቀርሳ ውጪ የሆኑ ነቀርሳዎች እንደየ ቅደም ተከተሎች ብዙውን ጊዜ የሊምፍ እጢዎች፣ የአጥንት፣ የአንጎል ሽፋን፣ የሆድና የልብ ሽፋን ነቀርሳዎች ናቸው። እነዚህ ብዙውን ጊዜ ሰዎችን የሚያጠቁ ሲሆኑ የነቀርሳ በሽታ ማንኛውንም የሠውነት አካል ሳይለይ የሰውንም አይን ጭምር ሊይዝ ይችላል። ከሳምባ ነቀርሳ ውጪ የሆኑ ነቀርሳዎች ምልክቶች ነቀርሳው በጎዳው አካል ላይ የሚንተራስ ይሆናል። የሊምፍ እጢ ነቀርሳ በተለይም ብዙውን ጊዜ በአንገት ላይ የሚገኝ ነቀርሳ ሲሆን ምልክቶቹም በአንገት አካባቢ በሚገኙት የሊምፍ እጢዎች ላይ እብጠት ይታይባቸዋል። እነዚህ ያበጡ እጢዎች ብዙ ጊዜ ጫን ጫን ስንላቸው የህመም ስሜት የሌላቸው እና እብጠታቸው እያደገ የሚሄድ ነው። ሳይታከም ከቆየ ይህ ያበጠው እጢ ፈንድቶ ወደ ውጭ መግል የሚመስል ፈሳሽ ወደ ውጪ ሊያፈስ ይችላል። ብዙውን ጊዜ የሆድ ነቀርሳ ቀስ ብሎ እያደገ የሚመጣ የሆድ ማበጥ፣ ተከታታይ የሆድ ህመም እና የሰውነት ትኩሳትን ያሳያል። የአንጎል ነቀርሳ ምልክቶች የራስምታት ህመም፣ የአንገት አለመንቀሳቀስ (ካንቀሳቀሱት ስለሚያም)፣ የሰውነት ትኩሳት፣ ሳይታከም ከቆየ ራስን ማሳት፣ የሰውነት መንቀጥቀጥ እና የመሳሰሉትን ማሳየት ይችላል።
ይቀጥላል…
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 24/2012