በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን ከፍ ያደረጉ ታዳጊዎች

ዜና ሀተታ

ተማሪ ያሬድ ሰለሞን ይባላል። የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነው። በአቡጊዳ ሮሆቦቲክስና የቴክኖሎጂ ማዕከል በተከታተለው ሥልጠና አማካኝነት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የአየር ንብረት ሁኔታውን በመከተል የሚያሞቅና የሚያቀዘቅዝ ጃኬት ሠርተዋል። በዚህ የፈጠራ ሥራ አማካኝነት በአሜሪካ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሮሆቦቲክስ ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን ወክለው በመሳተፍ አሸናፊ መሆናቸውን ይናገራል።

በመድረኩ ተሳትፎ ከማሸነፍ በተጨማሪ በርካታ የተማርኳቸው ነገሮች አሉ። በዚህም በሌሎች ሀገራት የሚገኙ የእኛ እኩዮች ያሉበትን ደረጃ መገንዘብ ችያለሁ የሚለው ተማሪ ያሬድ፤ በውጭ ሀገራት የሚሠሩ የቴክኖሎጂ ሥራዎች ከጥራታቸው ይልቅ የውጭ ውበት ላይ በማተኮር የዜጎችን ቀልብ ለመሳብ እንደሚሞክሩ አይቻለው፤ ነገር ግን ይህ ተገቢ ባለመሆኑ በሁሉም ላይ አተኮሩ መሥራት ያስፈልጋል ይላል።

ተማሪ ያሬድ አሸናፊ ስለሆኑበት ጃኬት እንደሚናገረው፤ በዋናነት ሆስፒታል ተኝተው ለሚታከሙ፣ ለጥበቃና ለመስክ ሠራተኞች ያገለግላል። ለለባሾቹ ሙቀት በሚሆንበት ወቅት በማቀዝቀዝ፣ ቅዝቃዜ በሚኖርበት ጊዜ ደግሞ በማሞቅ ያገለግላል። በተጨማሪም በሰውነታችን ላይ ለውጦችን ሲመለከት በተገጠመለት ሥርዓት አማካኝነት ወደእጅ ስልካቸው የህክምና ተቋም ሄደው እንዲታከሙ መልዕክት ይልካል።

ተማሪ ቶላዋቅ አጥናፉ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ከተማሪ ያሬድ ጋር በመሆን ጃኬቱ ለውጤት እንዲበቃ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። በውድድር መድረኩ ሀገሬን ወክዬ በመቅረቤ ኩራት ተሰምቶኛል የሚለው ተማሪ ቶላዋቅ፤ በውድድሩ ላይ የነበሩ ሌሎች ሀገራት ባላቸው ሁሉ ነገር ሃያላን በመሆናቸው ኢትዮጵያን አሳንሰው ቢመለከቱም በሠራነው የፈጠራ ሥራ አሸናፊ ልንሆን ችለናል ይላል።

በውድድሩ በማሸነፋቸውም ካገኙት የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት በተጨማሪ የመሰናዶ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በአሜሪካን ሀገር ትምህርታቸውን ለመከታተል የሚያስችል የስኮላርሺፕ እድል ማግኘታቸውንም ይጠቅሳል።

ተማሪ ቶላዋቅ ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሲገባ የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ በመማር በቀጣይ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የቴክኖሎጂ ካምፓኒ ለመክፈት ማቀዳቸውን ይናገራል። ሌሎች በእሱ የእድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊዎችም በውስጣቸው ያለውን የቴክኖሎጂ ክህሎት በትምህርት በማዳበር የተሻሉ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት እንደሚችሉ ይጠቁማል።

ጃኬቱ በሚሠራበት ወቅት የእሱ ሚና የሀርድ ዌር አካሉን መሥራት እንደነበር የሚናገረው ሌላኛው የፈጠራ ባለሙያ የ11ኛ ክፍል ተማሪው ራጂ ለማ ነው። ይህ ጃኬት አሁን ላይ የተሠራው ለማሳያነት ነው። ለወደፊትም የራሳችንን ካምፓኒ በማቋቋም ጃኬቱን በስፋት በማምረት ለተጠቃሚዎች ለማድረስ አስበናል ነው የሚለው።

አሁን ላይ የጃኬቱ ዲዛይን ተሠርቶ የተጠናቀቀ በመሆኑ በስፋት አምርቶ ወደ ገበያ ለማስገባት ስፖንሰር የሚያደርገን ወይም አብሮን የሚሠራ አካል እንፈልጋለን የሚለው ተማሪ ራጂ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀጣይም በተሻለ ሁኔታ ጃኬቱ በስፋት ተመርቶ ወደገበያ የሚገባበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ቃል መግባታቸውን ይናገራል።

ጃኬት ለመሥራት የተነሳሳነው በሆስፒታል ተኝተው የሚታከሙ ታማሚዎችንና በአየር መንገድ የሚሠሩ ዜጎችን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ነው። ወደፊትም አሁን ካለበት ደረጃ በማሻሻል ወደገበያ ለማቅረብ ሃሳብ አለን ሲልም ያክላል።

በዓለም አቀፍ ሮቦቲክስ ውድድር ላይ በመሳተፍ አሸናፊ ለሆኑ ተማሪዎች የማበረታቻና እውቅና ለመስጠት በተካሄደው መርሀግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለታዳጊ ወላጆች ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያውያን መገንዘብና ማወቅ ብቻ ሳይሆን መጋፈጥ የሚገባን እውነታ አለ፤ ላለፉት ብዙ መቶ ዓመታት ድሆች ምንም የሌላቸው፣ የማይፈጥሩና የሚረዱ ተብለን በዓለም እንድንታወቅ የተደረግን ሕዝቦች ነን። ዓለምም የሚያውቀው ይህን በመሆኑ አሁን ያለውን ትውልድ በማብቃት ድህነትን በልጆቻችን መበቀል መቻል አለብን ነው ያሉት።

“የእኛ ልጆች እንደኛ የደሀ ሀገር ዜጎች ሳይሆኑ ሌሎችን የሚረዱና የሚያግዙ ሰዎች እንዲባሉ ልጆቻችን ላይ አብዝተን መሥራት ይኖርብናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብዙ ውስብስብ ችግሮች በውስጡ ያሉት በመሆኑ ድህነትን በአንድ ጀንበር ማጥፋት አይቻልም፤ ነገር ግን እንደቤተሰብና ሀገር በልጆቻችን ላይ ኢንቨስት ካደረግን ድህነትንና ኋላ ቀርነትን መበቀል እንደሚቻል ገልጸዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ታዳጊዎቹ ዛሬ ላይ የሠሩት ሥራ በዓለም ላይ ባሉ ትላልቅ ኩባንያዎች ተሠርተው ለአፍሪካ ገበያ ከሚቀርቡ መካከል የሚመደቡ ናቸው። ታዳጊዎቹ በጤና፣ በሃይል፣ በኮንስትራክሽን፣ በኢነርጂ እና በበርካታ ሴክተሮች ላይ ሮሆቦቲክስን ጥቅም ላይ ለማዋል ማሰባቸው የሚደነቅ ነው።

ቤተሰብና ሀገር ከወሰነ ኢትዮጵያን የሚቀይሩ ልጆችን ማፍራት እና የበራላቸውን ታዳጊዎች ማግኘት ይቻላል። እነኚህ ታዳጊዎች ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው፣ እነሱን ስናይ ተስፋን እንሰንቃለን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ከተባበሩት አረብ ኤሜሬት ጋር በመተባበር በኮዲንግ ሴርቲፊኬሽን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥልጠና እድል መመቻቸቱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መላው ኢትዮጵያውያን መምህራን እና ተማሪዎች እድሉ እንዳያመልጣቸው የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You