በመዲናዋ ለ300 ሺህ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ ነው

– በሩብ ዓመቱ ከ28 ሺህ በላይ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት ለ300 ሺህ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ። በሩብ ዓመቱ ከ28 ሺህ በላይ ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉም ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰብሃዲን ሱልጣን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፣ በከተማዋ በ2017 በጀት ዓመት ለ300 ሺህ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።

በ2017 ዓ.ም በሩብ ዓመቱ ከ28 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚነት የሥራ እድል መፈጠሩን አስታውሰዋል።

በሩብ ዓመቱ 76 ሺህ 113 ዜጎች ተመዝገበው የሥራ ፈላጊነት መታወቂያ ወስደዋል ያሉት አቶ ሰብሃዲን፣ አሁን ላይ ለ32 ሺህ 572 ዜጎች ከአንድ ወር እስከ ሁለት ወር የሚቆይ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ይገኛል ብለዋል።

ከሥልጠናው በኋላ ሠልጣኞችን ከተቋማት ጋር የማስተሳሰር፣ የማስቀጠር እንዲሁም በማህበራት የሚሠሩትን ደግሞ የማደራጀት ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

በተያዘው ዓመት በሩብ ዓመት ለ45 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መቅታቀዱን ጠቅሰው፤ ለ28 ሺህ 499 ዜጎች በቋሚነት የሥራ እድል መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል።

የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል 64 በመቶ ወጣቶችና 57 በመቶ ሴቶች መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ዜጎች በቋሚነት በተለያዩ የግል ድርጅቶች፣ በመንግሥታዊ ተቋማት፣ በነባር ኢንተርፕራይዞች፣ በመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ጠቁመው፤ በተለያዩ ተቋማትና ፕሮጀክቶች ለ174 ሺህ 146 ዜጎች የሥራ እድሎችን መፍጠር የሚያስችሉ ፀጋዎች መለየታቸውን ተናግረዋል።

ከቅጥር ሥራ ባለፈ ዜጎችን በማደራጀት ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ስድስት ሺህ 83 አንቀሳቃሾችን የያዙ አንድ ሺህ 213 ኢንተርፕራይዞችን በማደራጃት ቋሚ የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል።

እንደየኢንተርፕራይዞቹ ፍላጎት የብድር አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር ድጋፍ እየተሰጠ እንደሚገኝ አመላክተው፤ ለአንድ ሺህ 990 ኢንተርፕራይዞች የመሥሪያ ቦታዎች እንዲተላለፍላቸው መደረጉን አስታውቀዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You