አዲስ አበባ፡- ባለፉት ሶስት ወራት ከአምስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ማገበያየቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቀ። በ25 ምርቶች ላይ ግብይት እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ ትናንትና እንደገለጹት፤ ምርት ገበያው ከአምስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ዋጋ ያለቸው ምርቶችን አገበያይቷል።
በበጀቱ ሩብ ዓመት 124 ሺህ 568 ቶን በላይ ምርት በግብይት ፣በሚዛንና በመጋዘን አገልግሎት መሰጠቱን ጠቁመዋል።
ምርት ገበያው ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ 25 ምርቶችን ወደ ግብይት ሥርዓቱ አስገብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
በበጀት ዓመቱ ተጨማሪ የግብርና ምርቶችን ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለማስገባት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ከግብርናው ምርቶች የጉሎ ፍሬ፣ ተልባ ፣ጤፍና ዳጉሳ፣ ከኢንዱስትሪ ዘርፍ ቆዳና ሌጦና ጨው ፣ እንዲሁም ከማዕድን ሚኒስቴር ጋራ በመነጋገር ኦፓል፣ ሳፋየርና ኤመራልድን ወደ ግብይት ሥርዓት ለማስገባት አስፈላጊ የጥናት ሥራዎች መከናወኑ አስታውቀዋል።
አንዳንዶቹም ምርቶችና ማዕድናት ወደ ዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ለማስገባት የግብይት ውል ጸድቆ በዚሁ በጀት ዓመት ግብይታቸው በይፋ እንደሚጀመር ገልጸዋል።
ምርት ገበያው ከ10 ባንኮች ጋር በመተባባር ለአርሶ አደሩ የፋይናንስ ተደራሽነትና አካታችነትን ለማረጋገጥ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት አስጀምሯል። በሩብ አመቱ ከ 143 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ተመቻችቶ ሥራ ላይ መዋሉን ገልጸዋል።
ይህ የብድር አገልግሎትም አንድ አምራች ወይም ተገበያይ ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጋዘን ምርቱን በማስገባትና የሚቀበለውን የመረከቢያ ደረሰኝ እንደ ማስያዣ በመጠቀም ከምርት ገበያው ጋር በጣምራ ከሚሠሩ ባንኮች ብድር የሚያገኝበት የአሠራር መሆኑ አብራርተዋል።
የምርት ገበያው በተለያዩ አካባቢዎች ለምርት ማስቀመጫ የሚሆኑ መጋዘኖችን በመሥራት ላይ የሚገኝ ሲሆን የኮምቦልቻ መጋዘንም በሩብ አመቱ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል ብለዋል።
አቶ ወንድማገኝ መንግሥት በቅርቡ የውጭ ዜጎች ወደ ገበያው እንዲቀላቀሉ በመፍቀዱ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ገበያው ለመሳብ ዘመናዊ የሆነ አገልግሎት እንደሚያስፈልግ ገልጸው ለዚህም ተቋሙ የኤሌክትሮኒክ ግብይት አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ ሶፍትዌር የማልማትና የማበልጸግ ሥራውን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
መስከረም ሰይፋ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2017 ዓ.ም