አኪያ… ‹‹ እሺ ብለናል ››

ከቄራ -አምባሳደር

የቄራ ልጅ ነው፡፡ ልጅነቱን በሰፈሩ አሳልፏል፡፡ እሱም እንደ እኩዮቹ ደብተሩን ይዞ ትምህርትቤት ተመላልሷል፡፡ ከባልንጀሮቹ  ሮጦ  የቦረቀበት፣ አፈር  ፈጭቶ ያደገበት  መንደር  ዛሬም ድረስ  ትዝታው ነው ፡፡  ሄኖክ አስፋው  የወጣትነት ጅማሬው፣ የህይወቱ   ክፉ በጎ  ገጽታ  ያደገበት ሰፈር  ትውስታ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ የትናንት  ማንነቱን  አይዘነጋም፡፡

ከዓመታት በፊት የነ ሄኖክ አካባቢ  ለልማት ተፈለገ፡፡ ይህኔ እነሱና ሌሎች ነዋሪዎች ስፍራውን መልቀቅ ግድ አላቸው፡፡ እነ ሄኖክ  ቄራን ሊተዉት ፣ሊርቁት ሆነ፡፡ እሱ  በወቅቱ ራሱን አልቻለም ፡፡ ኑሮው  ከቤተሰቡ ከእናቱ  ጋር ነው፡፡ አጋጣሚ ሆኖ እሱና ቤተሰቦቹ ወደ  አምባሳደር አካባቢ አቀኑ፡፡ በዚህ ስፍራ  አጎቱ ይኖራሉ፡፡ የራሳቸው መኖሪያ አላቸው፡፡ እነሄኖክን አልተዋቸውም፡፡  ህይወት በአዲስ መልክ ቀጠለ፡፡

ሄኖክ ስፍራውን  በወጉ ለመደው፡፡ አምባሳደርና  ዙሪያው  ሞቅ ያለ  ሰፈር ነው፡፡ ከፍ ያሉቱ  የንግድ ቦታዎች አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ተስፋዎች  ናቸው፡፡ አካባቢው  እንደ አቅም ውለው ያድሩበታል፡፡ ትልልቆቹ ነጋዴዎች ለሌሎቹ መኖር ምክንያት ሆነዋል፡፡ ሁሉም እንደ አቅሙ፣ ሮጦ፣ ተላልኮ፣ ይኖራል፡፡ እንደ ለፍቶ አዳሪው  ተቀምጦ ገልማጩ፣ መንትፎ አምላጩ ፣  ብዙ ነው፡፡

ሄኖክ  ራሱን የሚያስችል እንጀራ አላጣም፡፡ መኪኖችን ተራ ማስከበር ያዘ፡፡ የአምባሳደርን ሰፈር  ከልቡ ወደደው፡፡ ውሎ አድሮ  ከአንድ ሱቅ ውስጥ መስራት ጀመረ፡፡ አጋጣሚው ከብዙዎች  አስተዋወቀው፡፡ ከሁሉም  ግን ከአንዲት ወጣት ጋር  በተለየ  ቅርበት ተግባቡ፡፡

ፈጣኑ ውሳኔ

ሄኖክና ልጅቷ በመሀላቸው የተፈጠረው ቅርበት በተለየ መተሳሰብ ተገለጠ፡፡ ቅርበታቸው የፍቅር ቢሆን አብሮነቱን ገፉበት፡፡ ቆይታቸው እንደብዙዎች  ወራትን፣ ከዓመታት አልቆጠረም፡፡ በአጭር ቀናት ፍቅር  ቁምነገርን አስበው ጎጆ ሊወጡ  ወሰኑ፡፡ ውሳኔያቸው አልቀረም፡፡ ዕቅዳቸው ዕውን ሆኖ በአንድ ቤት ተጠቃለሉ፡፡ እንደዋዛ የተጀመረው የሶስት ጉልቻ ወግ ፈተና አልጣለውም፡፡ ችግሩን፣ ክፉ አጋጣሚውን እያለፈ ወራትን ተሻገረ፡፡

አምባሳደርና አካባቢው ለጥንዶቹ መልካም ሆነ፡፡ ፍቅራቸው ስብራት አላገኘውም፡፡ ጠብና ወረት  አላየውም፡፡ አሁን ነፍሰጡሯ ወይዘሮ መውለጃዋ ቀርቧል፡፡ ከጥቂት ግዜ በኋላ ልጇን  አቅፋ ትስማለች፡፡ ይህን  እውነት አባወራው ሄኖክ ጭምር  ይጋራዋል፡፡ ይህን ቀን ሁሉም በናፍቆት ይጠብቁታል፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ የሄኖክ ባለቤት  ወንድ ልጅ መውለዷ ተሰማ፡፡ ይህ ስጦታ ለባልና ሚስቱ የመጀመሪያ ፍሬ ነው፡፡ ህጻኑ ለቤቱ እንግዳ ሆኖ መምጣቱ ሁለቱንም  አስደስቷል፡፡ ልጅ ማሳደግ ቢከብድ ቢፈትንም በሆነው ሁሉ ደስ ብሏቸዋል፡፡

እናት ከወለደችበት ሆስፒታል ከመውጣቷ አስቀድሞ  በህፃኑ ጀርባና እግሮች  ላይ አንድ  ችግር   መኖሩ ታወቀ፡፡ ይህ  ምልክት ከዚህ ቀድሞ  በሌሎች ጨቅላዎች ላይ ያላዩት  ነበር፡፡ ልጃቸው  በጀርባው በኩል  ክፍተት አለው፡፡ ሁለት እግሮቹም በአፈጣጠራቸው እኩል አይደሉም፡፡  ይህን እውነት  ከሀኪሞች ጠይቀው ሀቁን  አረጋግጠዋል፡፡  ችግሩ  ‹‹ሀይድሮ ሴፋለስስ›› ይባላል፡፡ በእርግዝና ወቅት በሚያጋጥም የ‹‹ፎሊክ አሲድ››  እጥረት ምክንያት የሚከሰት  ነው፡፡  እናት  እንደአራስ ልማድ  ከቤቷ ገብታ ወግ ማዕረግ አላየችም፡፡    ፡፡ ስለልጇ መኖር  ከሆስፒታሉ ውሎ ማደር የግድ አላት፡፡   ባልና ሚስት እንዳሰቡት በአጭር  ቀናት ከሀኪምቤት  አልወጡም፡፡  ልጃቸው ግዚያትን የሚያስከፍል   ተከታታይ ሕክምና ያሻዋል፡፡

       አኪያ

‹‹አኪያ›› ይሉት ቃል በእብራይስጥ ቋንቋ ‹‹እግዚአብሔር ወንድሜ ነው›› እንደማለት ነው፡፡ ይኸው ቃል ወደ  ጉራጊኛ  ቋንቋ ሲመለስ  ደግሞ  ‹‹እሺ፣ይሁን ›› በሚል  ቃል  ይተረጎማል፡፡ ሄኖክ  የመጀሪያ  ልጁ ላይ በተከሰተው ክፉ አጋጣሚ  ከልቡ አዝኗል፡፡ ይህን ስሜቱን ግን በዝምታ ብቻ ሊያልፈው አልፈለገም፡፡ የልቡን  ሀሳብ የውስጡን እንፋሎት ለማሳየት ‹‹እሺ፣ይሁን›› በሚል እውነት  ገለጸው፡፡ ትንሹ አኪያ  ለእሱ ከፈጣሪው  የተበረከተ ታላቅ ስጦታ  ነው፡፡  ‹‹እሺ፣ይሁን፣›› ሲል በጸጋ ተቀብሎታል፡፡

ትንሹ አኪያ ከእናት አባቱ ጋር የሆስፒታል   ህይወት ቀጥሏል፡፡ ጨቅላ አካሉ  ተከታታዩን  ህክምና  ችሎ ሊቀበለው   ቀላል አልሆነም፡፡ እያንዳንዱ የግዜ ሂደት  ልዩ ጥንቃቄን ይሻል፡፡ ሄኖክና ባለቤቱ  ወደቤታቸው  የመመለስ ህልማቸው ራቀ፡፡ አኪያን ይዘው ለአንድ አመት ከስምንት ወራት በሆስፒታሉ አልጋ አሳለፉ፡፡

አባት  ሄኖክ ልጁ አኪያ የአንድ ዓመት ልደቱን ባከበረ ማግስት  በአካሉ ላይ የተፈጠረውን  ለውጥ ፈጽሞ አይረሳውም፡፡ ህጻኑ የጀርባው  ክፍተት ለሁለት ግዜያት  በቀዶ ህክምና ከተዘጋ  በኋላ  ኢንፌክሽን ተፈጥሮበት ነበር፡፡ በወቅቱ  የቁስሉ  ስፌት   ደርቆ  ይገጥም ዘንድም   በንጹህ ማር  ተቀብቶ እንዲድን ሆኗል፡፡

ይህን ሁሉ  በድል ያለፈው አኪያ  ከቀናት በአንዱ   ያልታሰበ ለውጥ ታየበት፡፡    ለውጡ ግን   የሚጠበቅና  አስደሳች    አልነበረም፡፡ በህጻኑ ጭንቅላት ውስጥ የገባው ‹‹ሸንት››የተባለ ማገዣ  ጤናውን እንደሚያሻሻል ይታመናል፡፡ በእንዲህ አይነት ችግር ወስጥ ለሚገኙ ህጻናት ይህን ማድረግ የተለመደ ነው፡፡

ሄኖክ  እንደሚለው ግን   አኪያ ላይ  ለውጥ የታየው  ‹‹ሸንት ››ከገባላትና ጀርባው ከገጠመ በኋላ ነበር ፡፡ የአኪያ   ጀርባ   በወጉ ገጥሞ    እንዳበቃ  የጭንቅላቱ  ዕድገት ቅጽበታዊ ሆነ፡፡ በሚያስደነግጥ ፍጥነት ጭንቅላቱ እያደገ ገጽታው መቀየር  ጀመረ፡፡

    ያልታሰበው

አሁን  ሲወለድ የነበረው የህጻኑ  ጤናማ ፊት ፍጹም  ተለውጧል፡፡ ሲተኛ ዓይኖቹ አይከደኑም፣ አፉ አይገጠምም፡፡ እናት አባት በሆነባቸው አጋጣሚ  በእጅጉ ተጨነቁ፡፡ በእነሱ ላይ የወደቀውን ሀዘን በቀላሉ  የሚችሉት አልሆነም፡፡ በሀዘን አንገታቸውን ደፍተው በለቅሶ  ፈጣሪያቸውን ተማጸኑ፡፡

ጥንዶቹ ለትዳርና ልጅ  አዲስ  ናቸው፡፡  በወጣትነት ዕድሜ ያገኙት የመጀመሪያ ልጅ ከፈተና መውደቁ  ውስጣቸውን ሰብሮታል፡፡ መልካም ለውጥን ሲጠብቁ ያልታሰበው   በመከሰቱ   ምላሽ  ጠፍቷቸዋል፡፡  ሄኖክ አሁንም በአቋሙ  እንደጸና ነው፡፡  ልጁን  ‹‹አኪያ››ን  ‹‹አሜን..  ‹‹እሺ››  ሲል በይሁንታ  ተቀብሎታል፡፡

ውሎ አድሮ ሄኖክና ባለቤቱ በሀኪሞች ምክር ታገዙ፡፡ ይህ ችግር በእነሱ ልጅ ብቻ  እንዳልሆነ  በገባቸው ግዜም  ቀስ በቀስ ወደ ራሳቸው ተመለሱ፡፡  ከሆስፒታል  ቆይታ በኋላ  ልጃቸውን ይዘው ወደመኖሪያቸው ሲመለሱ ህይወት አልጋ በአልጋ ሆኖ አልቆያቸውም፡፡

ጥንዶቹ አሁን ብቻቸውን አይደሉም፡፡ ለመኖር ብዙ ከሚያሻው ልጃቸው ጋር አዲስ ህይወት ጀምረዋል፡፡ ስለ ጋራ ኑሯቸው ከትናንቱ ይበልጥ  ብዙ  ሊሮጡ ፣ሊለፉ ግድ ነው፡፡ ትንሹ አኪያ  የውስጡን ችግር  ማስረዳት አይችልም፡፡ መራብ ፣ መጠማቱ ፣ መታመም   መዳኑን  የሚውቅለት የለም፡፡

ሄኖክ ከትውልድ  መንደሩ ቄራ  ወደ አምባሳደር  ከመጣ  ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአምባሳደር  ዙሪያ  ራሱን ለማሸነፍ ያልሆነው የለም፡፡ አሁንም ግን የትናንት ታሪኩ ሊደገም ግድ ሆኗል፡፡ ይህም  ስፍራ ለልማት እየተፈለገ፣ ነዋሪዎች እየተነሱ ነው፡፡  ባጋጣሚው   የእሱና  የቤተሰቡ ህይወት ከአደጋ መውደቁ አልቀረም፡፡

የእስከዛሬ ኑሮው  በአጎቱ  ቤት ነበር፡፡ አሁን  አጎቱ ምትክ ቤት አግኝተው  መንደሩን ርቀዋል፡፡ ቤታቸው ስለፈረሰ  ሄኖክና ቤተሰቡ መጠጊያ የላቸውም፡፡ ብቸኛ   ምርጫቸው  ጎዳና ላይ መውጣትና  ለሚመለከታቸው አከላት ‹‹አቤት›› ማለት  ሆነ፡፡

    ህይወት በጎዳና 

ምርጫ አልባው ቤተሰብ ወራትን በጎዳና ጥግ  አሳለፈ፡፡ ብርዱ፣ ዝናቡ፣ ጎርፍና ጨለማው በነአኪያ ቤት ብርቅ አልሆነም፡፡ ሄኖክና ቤተሰቡ ጎዳና የመውጣታቸው  ምክንያት መልካም ዓይኖች እንዲያዩዋቸው ፣ሰፊ እጆች እንዲያቅፏቸው ነበር፡፡ ያሰቡት ግን  አልተሳካም፡፡ አይደለም እነሱን ብዙ ትኩረት የሚያሻውን ልጅ  በጨረፍታ እንኳን  ያየው  የለም፡፡

የጎዳና ላይ ኑሮ  ያስከፋል፡፡ እያንዳንዷ ደቂቃና ሰኮንድ ፤ ቀንና ለሊት ከስጋት ጋር ያልፋል፡፡ በተለይ ጭር ባለ ስፍራ ፣በፈረሰው  መንደር   የሚሆነው አይታወቅም፡፡ ሁኔታዎች  ያስፈራሉ፣ያስጨንቃሉ፡፡ ከሁሉም ግን ከቀናት በአንዱ በነሄኖክ  የላስቲክ  ጎጆ የተከሰተው  እውነት  አሳዛኝ  ሆኖ  አለፈ፡፡

ቀኑን በየራሳቸው ጉዳይ ሲደክሙ የዋሉት ሄኖክና ባለቤቱ በላስቲክ ጎጇቸው ሌቱን አንግተው ማለዳውን ነቅተዋል፡፡ እናት ከጎኗ የተኛውን አኪያ እንደልማዷ እየዳሰሰች  በፍቅር  ታየዋለች ፡፡ የለበሰችው አንሶላ ያለወትሮው  በላይዋ  መለጠፉ አልተመቻትም፡፡ እንደምንም ከሰውነቷ አንስታ ልትወረውረው ሞከረች፡፡ በዋዛ  አለቀቃትም፡፡ አሁንም አንዳች  ነገር አጣብቆ ያዛት፡፡

እናት ዓይኖቿን ከጨርቁ  ላይ ጥላ በትኩረት አፈጠጠች፡፡ ያየችውን እውነት እያመነችው አይደለም፡፡ አንሶላው አንዳች  ነገር ተለጥፎበት  በደም ተነክሯል፡፡ እየተንቀጠቀጠች የልጇን አካል ዳሰሰችው፡፡ የእግሮቹ ጣቶች  ተንጠልጥለው ይደማሉ፡፡ ክው ብላ ደነገጠች፡፡  ሶስቱ ጣቶች …  ዓይኖቿን ጨፈነች፡፡ መልሳ ገለጠች ፡፡ የሆነው  አልጠፋትም፡፡ አይጦቹ    ሌሊቱን   ጣቶቹን  ሲበሉት  አድረዋል ፡፡

ቁስሉ አሁንም እየደማ ነው፡፡ ትንሹ አኪያ ግን  በእሱ  ላይ የሆነውን አላወቀም ፡፡ ጣቶቹ  ስሜት አልባ ናቸውና  የእናቱን   ጭንቀት  የተቀበለው  በተለመደው ፈገግታ ነበር፡፡ ዕለቱን ተሯሩጠው ሆስፒታል  ወሰዱት ፡፡ በአይጥ ከተበሉት ጣቶቹ አንደኛው እንዲሰፋ ሆኖ ሌሎች በሂደት እንዲገጥሙለት መድሀኒት ታዘዘ፡፡ እንዲህ በሆነ ማግስት ከፈረሱት ቤቶች  የአንደኛው ግድግደ  ተገምሶ እጁ ላይ ጉዳት ደረሰ፡፡ ይህኛው ህመም ግን ትንሹን አኪያ  ክፉኛ አሰቃየው፡፡

    ዝምታና ስጋት

አምባሳደርና አካባቢው የቀድሞ መልኩ የለም፡፡ ጎረቤት፣ትራንሰፖርት፣ወጪ ወራጅ  ይሉት ጉዳይ  ከተረሳ ቆይቷል፡፡ ዙሪያ ገባው የወንዝ ዳርቻ በመሆኑ ‹‹እፎይ››  ብለው አያድሩበትም፡፡ እዚህም፣እዚያም ላስቲክ ወጥረው የሚኖሩ የጎዳና  አዳሪዎች   የዘንድሮን ክረምት ያለፉት በታላቅ ስጋት ነው፡፡

የሄኖክ ባለቤት  ባጋጠማት ጭንቀት   ሰላም ኖሯት አያውቅም፡፡ የስኳር ታማሚ ናትና   ራሷን ኢንሱሊን ትወጋለች፡፡ በቅርቡ የተወለደችው የአኪያ ታናሽ  እህት እንክብካቤ የምትሻ ጨቅላ ናት፡፡ ይህ  ሀላፊነት የእናቲቱ ድርሻ  ነው፡፡ ህይወት በከበዳት፣በተጫናት  ግዜ ስታስብ፣ ስትጨነቅ  ትውላለች፡፡

አኪያን አዝላ  ስትጓዝ አዙሯት የምትወድቅበት ግዜ ብዙ  ነው፡፡ ይህ አጋጣሚ ለእናትና ልጅ በየግዜው መፈንከትና  መጎዳት ምክንያት ሆኗል፡፡ችግሩን ደጋግሞ የሚያየው ሄኖክ ቀደም ሲል  ሰርቶ ባጠራቀመው ጥቂት ገንዘብ  ለልጁ ዊልቸር መግዛት ይፈልጋል፡፡ ያለው አቅም ግን የፍላጎቱን የሚያደርስ አልሆነም፡፡እንዲያም ሆኖ ተስፋ አልቆረጠም፡፡የእጁን ይዞ ኤልያስ ከተባለ ልበ ቀና ዘንድ በመሄድ ‹‹አግዘኝ›› አለው፡፡ኤልያስ አልጨከነም፡፡የጎደለውን ከራሱ  ሞልቶ ዊልቸሩን ገዝቶ  አስረከበው፡፡

ዛሬ አኪያ በዊልቸር ላይ ተቀምጦ ይውላል፡፡አባቱ ሄኖክ  ዊልቸሩ ለረጅም ጉዞና ለዘለቄታው ጥቅም እንደማይሆን ያውቃል፡፡ ወደፊት አከርካሪውን እንዳይጎዳበትም  ስጋት አለው፡፡ለግዜው ግን ልጁንና  ቤተሰቡንና  ከድካም አሳርፏል፡፡በሚሄድበት መንገድ ዊልቸሩ አጋዥ ነው፡፡ እየተገፋ ፣እያዘገመ ከታሰበው ያደርሳል፡፡

ሄኖክ አልፎ አልፎ  ከሰዎች ያልተገባ  ንግግር ይሰማል፡፡አንዳንዶች ችግሩን ከባዕድ አምልኮ ያዛምዱበታል፡፡ ሌሎች ደግሞ እንደ እርግማን ቆጥረው ይኮንኑታል ፡፡ ይህ ሁሉ ለእሱና ለባለቤቱ  ፈተና ነው፡፡እንዲያም ሆኖ  ተገርሞ እንጂ ተከፍቶ አያውቅም፡፡ሁሌም በምስጋና ውሎ ያድራል፡፡

አሁን አኪያ ስድስት ዓመት ሆኖታል፡፡ዛሬም ግን ከወላጆቹ በቀር የቅርብ ረዳት የለውም፡፡አሁንም  ጤናው አልተመለሰም፣ አንደበቱን እንዳሻው ባያዝም፣ በመጠኑ ይግባባል ፡፡እግሮቹ  አይራመዱም፡፡ ሁሌም  የዳይፐር ተጠቃሚ ነው፡፡ ዓዕምሮው  ግን   ፍላጎቱን  ለመጠቆም በእጅጉ ፈጣንና ቀልጣፋ ነው፡፡ ነው፡፡

አንዳንዴ አኪያ ወላጆቹን ለምን? ሲል  ይጠይቃል፡፡እኩዮቹን ባየ ግዜም እንደነሱ ቦርሳ ማዘልና፣  መማር   ያምረዋል፡፡ የመሮጥና  መራመድ ፍላጎቱም ልዩ ነው፡፡    ጥያቄውን  መመለስ የማይችሉ ወላጆች ግን ሁሌም  ምላሻቸው በፈገግታ የተሞላ ዝምታ ነው፡፡

በቅርብ ርቀት የሚኖሩት የሄኖክ እናት ኑሯቸው ከእጅ ወደአፍ ነው፡፡እንዲያም ሆኖ ከቤተሰቡ ተነጥለው አያውቁም፡፡ አኪያን ፍቅር ይሰጡታል፡፡ በአደራ ይጠብቁታል፡፡ድህነት  ከእነሱ አርቋቸው አያውቅም፡፡ በሴፍቲኔት  ከሚያገኙት ጥቅም  ኑሯቸውን ሲመሩ   ቆይተዋል፡፡

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የቤተሰቡ ሀላፊነት ከብዷል፡፡እነ ሄኖክ  አኪያን   ትተው፣ ‹‹አደራ››  ብለው መውጣት አይችሉም፡፡ከአንድ  ወር በፊት ወይዘሮዋን  በድንገቴ ሞት አጥተዋል፡፡የሄኖክ እናት ካረፉ ወዲህ  ክፍተቱ ሰፍቷል፡፡  አኪያ አያቱ ቤት    እንዳይውል፣ ከእሳቸው  እንዳይጫወት  ሆኗል፡፡ይህ ህጻን ካለበት የጤና እክል ጋር  የሚገኝበት  የኑሮ ደረጃ በእጅጉ አሳሳቢ ነው፡፡በጎዳና ውሎ ማደር፣በችግር አማራጭ ማጣት በእጅጉ ይከብዳል፡፡

‹‹አኪያ››  የይሁንታው ምላሽ

ትንሹን አኪያ ቀረብ ብዬ አጫወትኩት፡፡በሚጣፍጥ አንደበቱ ሰላምታ አቀረበልኝ፡፡ንግግሩን አልጠበኩትምና የደስታ ሲቃ ያዘኝ፡፡ ልግባባው አልተቸገርኩም ፡፡በፈገግታው  ተማረኩ፡፡የልጅ ለዛው አስደነቀኝ፡፡ ይህን እያሰብኩ  የወላጆቹን  ድካም ልፋት አሰላሁት፡፡ጥንካሬያቸው ከቋጥኝ በላይ ገዝፎ ታየኝ፡፡ከልቤ አክብሬ አደነኳቸው፡፡

ይህኔ  የእሺታው   ስያሜ ትርጓሜው ዘልቆ ተሰማኝ፡፡  አዕምሮዬ  ‹‹አኪያ››  ይሉትን  ቃል  ደጋገመው፡፡ ‹‹እሺ፣ይሁን››  ዳግም  አቃጨለብኝ፡፡  ‹‹እሺ፤ይሁን›› አኪያ  ከቃል በላይ፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You