በከባድ ሁኔታ ውስጥ ራስን መቀየር

አንድ ዶላር በሁለት ዲጂት ከመመንዘር አልፎ ወደ ሶስት ዲጂት አድጓል:: ይህ ማለት የዛሬ አምስት ዓመት በ27 ብር ይመነዘር የነበረው ዶላር አሁን 105 ብር ደርሷል:: አራት እጥፍ ማለት ነው:: ይህም የምንገዛቸው እቃዎች በሙሉ በአራት እጥፍ አድገዋል እንደ ማለት ነው:: የምንለብሰው ልብስ፣ የምንበላው ምግብ፣ ሸቀጣሸቀጡ፣ መኪናው፣ ቤቱ ሁሉም አራት እጥፍና ከዛ በላይ ጨምሯል::

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መጋቢት 2024 ባወጣው ሪፖርት መሠረት 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቋል:: ይህ ማለት የቺሊን ወይም የዛምቢያን ጠቅላላ ሕዝብ የሚያክል ኢትዮጵያዊ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ይፈልጋል ማለት ነው:: ዩኒሴፍ ደግሞ ግንቦት 2024 ባወጣው ሪፖርት 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆን ኢትዮጵያዊ ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆኑን ጠቁሟል:: ይህም ድፍን የሲውዘርላድ ሕዝብን የሚያክል ኢትዮጵያዊ ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆኗል ማለት ነው::

ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላው ትልቁ አጀንዳችን ደግሞ የሰላም ጉዳይ ነው:: ታውቃላችሁ! በሰሜኑ ጦርነት ብቻ የብዙ ሰው ሕይወት ተቀጥፏል:: ከሞት ተርፎ አካሉን ያጣ፣ ቤት ንብረቱ የወደመበት፣ ቢዝነሱንና ሥራውን ያጣ፣ የተፈናቀለውም ቁጥሩ ቀላል አይደለም::

እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነትና ሌላም ሌላም በርካታ ችግሮች እንዳሉብን ግልፅ ነው::የችግራችን ትልቀትና ጥልቀት ላይ ከተግባባን ግን አንድ ነገር መርሳት የለብህም:: እኛ መቀየር የምንችለው ነገር አለ:: መቀየር የማንችለውም ነገር አለ:: እኛ መቀየርና መቆጣጠር የምንችለው ግን ራሳችንን ነው:: ከባድ የሆነ ዝናብ ቢዘብም እናንተ ልታቆሙት አትችሉም:: የምትችሉት ዣንጥላ መዘርጋት ነው:: በዛ ዣንጥላ ራሳችሁንና የምትወዷቸውን ልትከልሉ ትችላላችሁ:: ስለዚህ መጀመሪያ መቆጣጠር የምንችለው ራሳችንን መቀየር ነው::

ራሳችንን ስንቀይር ለምንወዳቸውና በዙሪያችን ላሉ ሰዎች እንተርፋለን:: ሁሉም ሰው ደግሞ ኃላፊነቱን ከተወጣ ኢትዮጵያ ልትቀየር ትችላለች:: ከዚህ አንፃር እንዴት አድርገን በከባድ ሁኔታ ውስጥ ራሳችንንና ሕይወታችንን መቀየር እንዳለብን ማወቅ ይኖርብናል::

1ኛ. አዕምሮ ላይ መሥራት

አዕምሮ የምንም ነገር መነሻ ነው:: አሜሪካንን ከቀየሩ ትላልቅ ሰዎች መካከል ቤንጃሚን ፍራንክሊን አንዱ ነው:: እርሱ ‹‹ሰዎች የእድል ሳይሆን የአዕምሯችን ባሪያ ነን›› ይላል:: ነገሮች ሊስተካከሉ እንደማይችሉና እንዳበቁ የሚያሳምንህ አዕምሮህ ነው:: ምንም ነገር ከመጋገሩ በፊት የሚቦካው አዕምሮ ውስጥ ነው:: ምንም ነገር እውነት ከመሆኑ በፊት በአዕምሮ ታስቦ ነበር:: ለዛ ነው መጀመሪያ አዕምሮ ላይ መሥራት የሚያስፈልገው::

አዕምሮህ የስልክ ቀፎ ቢሆን አመለካከትህ ደግሞ ስልክህ ላይ የተጫኑ መተግበሪያዎች ናቸው:: እነዚህ መተግበሪያዎች ባይኖሩ ስልክህ ባዶ ቀፎ ነው:: ዋናው መተግበሪያው ነው:: ስለዚህ አዕምሮህ ውስጥ ያሉት አመለካከቶችህ ናቸው መተግበሪያዎቹ:: አመለካከትህ ነው ከፍም ዝቅም የሚያደርግህ:: እንዳበቃልህ የምታሰብ ከሆነ፣ ሕይወትን የምትረዳውም እንደዛ ከሆነ አብቅቶልሃል:: አልችልም! ካልክ ‹‹አዎ! አትችልም›› ይልሃል አዕምሮህ:: እችላለሁም ካልክ ‹‹አዎ! ትችላለህ›› ይልሃል::

ስለዚህ አልችልም ካልክ አዕምሮህ ላይ ትቆልፍበታለህ:: እንዴት አድርጌ ሕይወቴን ልቀይር ለማለት እንኳን እድሉ አይኖርህም:: ለምን አልችልም ብለሃል:: በመሆኑም የገጠመኝ ችግር ከባድ ነው፣ ግን መቀየር እችላለሁ ማለት ነው ያለብህ:: ከባድ ነው ማለት አይቻልም ማለት አይደለም:: ኑሮ እየከበደ ነገሮች እየተቀያየሩ በሄዱ ቁጥር አልችልም ካልክ ቁጭ ብለህ የበይ ተመልካች ሆነህ ነው የምትቀረው:: ማማረር ይሆናል ሥራህ:: ሲሳካላቸው ታይና መቅናት ብቻ ይሆናል ሥራህ:: ራስህን አትቀይርም:: እችላለሁ ካልክ ግን የሆነ ነገር ትሞክራለህ::

አዎ! ጠንካራ መሆን በጣም ከባድ ነው:: በጣም ጠንክሮ ማሰብ ይጠይቃል:: ሕይወቴን የሚቀይረው ምንድን ነው፣ ምንድን ነው መሥራት ያለብኝ፣ ምኑ ጋር ራሴን ላሻሽል፣ እንዴት ገቢዬን ላሳድግ ብሎ ማሰብ ይጠይቃል:: ማሰብ ብቻ ግን አይደለም:: የተግባር ሰው መሆን ይጠይቃል:: ያሰብካቸውን ነገሮች ወደመሬት የማውረድ፤ ከዛ ደግሞ ለውጡ እስኪፈጠር ድረስ በፅናት መቀጠልና መትጋት ያስፈልጋል::

2.ጊዜን በአግባቡ መጠቀም

ወጣት ስትሆን እድሜህ ከሃያ እስከ ሃምሳ አምስት ዓመት ሲሆን ትልቁ እየመነዘርክ ኢንቨስት የምታደርገው ሀብትህ እድሜህ ነው:: ወጣትነትህ ነው:: ያውም በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የሚባክን ጊዜ መኖር የለበትም:: አንድ ነገር የምታወጣው ወይም ኢንቨስት የምታደርገው ተመልሶ ያ ገንዘብ ከትርፍ ጋር እንዲመጣልህ ነው:: እኔ በማወጣው ልክ ምን እያገኘሁ ነው ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል::

ስለዚህ ያንተ ትልቁ ሀብት ደግሞ ወጣትነትህና ጊዜህ ከሆነ አንተ ለሆነ ነገር ጊዜህን ኢንቨስት ስታደርግ ምን እያገኘህ ነው? የሚለውን ማጤን ይገባል:: ሁሉንም ነገር ማሰብ ያለብህ ከዚህ አንፃር ነው:: ሁሉም ነገር ሰጥቶ መቀበል ነው:: አንተ እየሰጠህ ነው:: እርሱ ምን ሰጠህ?፣ አንተ እድሜህን ቀንሰህ ሰጠኸው፤ እርሱ ግን ምን የሚጠቅም ሃሳብ ሰጠህ? ለዛም ነው ታላቁ የሥነ ልቦና ሊቅ ጂም ሮል ወይ ቲ ‹‹ታያለህ ወይ ሀብታም ትሆናለህ›› የሚለው:: አንዱን ምርጥ የሚለው ለዛ ነው::

እስኪ አስበው የትኛው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ነው፣ የትኛው የዩቲዩብ ቪዲዮ ነው፣ የትኛው የቲክቶክ ቪዲዮ ነው ያንተ ሕይወት ላይ የሆነ በጣም የሚጠቅም ነገር የሰጠህ? ራስህን እንድታሻሻል፣ ገቢህን እንድታሳደግ የረዳህ? ወይ ደግሞ ከሰዎች ጋር ያለህን ግንኙነት በጣም እንድታሳምር ያገዘህ? መንፈሳዊ ሕይወትህን እንድታሻሻል ያደረገህ ምንድን ነው? ይህንን ነው መጠየቅ ያለብህ:: እነርሱ እየተጠቀሙብህ ነው:: ምክንያቱም ምንም ነገር በነፃ የምታገኝ ከሆነ የምትሸጠው አንተ ነህ ስለሚባል ነው:: እያንዳንዱ የምታባክነው ጊዜ መልሶ የሚያመጣው ውጤት ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል::

ስለዚህ ለጊዜ ትልቅ ቦታ ከሰጠኸው ያስከብርሃል:: ጊዜህን ከናቅከው ደግሞ ከሰው በታች ያደርግሃል:: አየህ በዚህ ሰዓት ትልቁ ኃይል ያለው ነገር ጊዜህን የምትሰጥበት ቦታ ነው:: እሱን መምረጥና መወሰን ያንተ ፋንታ ነው::

  1. እድሎችን ለመጠቀም መዘጋጀት

ፈጣሪ በአስቸጋሪና በከባድ ሁኔታዎች ውስጥ ለሰው ልጆች ሁሉ ይዟቸው የሚመጣቸው ትላልቅ በረከቶችና እድሎች አሉ:: ያለ አላማ ወደዚህ ምድር አልመጣንም:: ነገር ግን ፈጣሪ እንድንዘጋጅ ይፈልጋል:: ያንን እድል ሲያመጣው ተቀብለን የምንጠቀምበት አቅምና ትከሻ ያስፈልገናል:: እንደውም አንድ አስተሳሰብ አለ:: ስኬት ልክ እንደ ፎርሙላ ሲመጥ ዝግጅት ሲደመር እድል ነው ይላል::

በጣም የሚዘጋጅ ሰው እድል ሲመጣ ይጠቀምበታል፤ ሕይወቱን ይቀይራል:: ያልተዘጋጀ ሰነፍ ሰው እድል ቢመጣ እንኳን አይጠቀምበትም:: ስለዚህ ተዘጋጅ:: እንዴት ልዘጋጅ? ነው ጥያቄው:: ዝግጅቱ ካለህበት ሁኔታ ጋር ይገናኛል:: ለምሳሌ ተማሪ ከሆንክ አንተ የምትዘጋጀው በጣም ጥራት ያለው እውቀት በመሰብሰብ፣ ችግር የሚፈታና የሚጠቅም ነገር በማግኘት ነው:: በቃ ጥራት ያለው ትምህርት መማር አለብህ:: ምናልባት የውጭ የትምህርት እድል እየሞከርክ ይሆናል:: አንድ ጊዜ ሞክረህ አታቁም:: ከቻልክ ትልልቅ ፈተናዎችን ተፈተን::

ስለዚህ ምንም ነገር ስትሞክር በሙሉ ልብህ ሞክር:: አየህ በደንብ ያልተቀጣጠለ እሳት ብዙ ሙቀት አይሰጥም:: በደንብ ማቀጣጠል አለብህ ለውጡን እንድትፈጥር:: ከዛ እኔ ሠራተኛ ነኝ ካልክ ደግሞ አንተ ከሚጠበቅብህ በላይ ነው መሥራት ያለብህ:: ብዙ ክህሎቶችን መሰብሰብ አለብህ:: በዙሪያህ ያሉ ሠራተኞች የሚሰሩትን አይተህ ከእነርሱ ጋር እኩል ለመሆን ብቻ አታስብ:: የእነርሱን ሥራ ደርበህ መሥራት፣ የአለቃህን ሥራ ደርበህ መሥራት፣ እንደ አለቃዬ ይከፈለኝ ሳይሆን መጀመሪያ እንደ አለቃዬ መሥራት ልቻል ብለህ ራስህን አሳምን::

አየህ ቁጭ ባልክበት የሚመጣ እድል የለም:: በሩ ጋር ቆመህ ማንኳኳት ብቻ ሳይሆን በኃይል መደብደብ ሊኖርብህ ይችላል:: አንዳንድ ጊዜ በሩን ገንጥለኸው ልትገባ ትችላለህ:: ይህ ማለት ሙሉ አቅምህን በየጊዜው መጠቀም አለብህ ማለት ነው:: በዛ ውስጥ ግን ቋንቋህን አሻሽል:: ከቴክኖሎጂ ጋር በደንብ ተቀራረብ:: ብዙ ነገር ለማወቅና ለመልመድ ሞክር:: ብዙ ዓይነት ሞያ ይኑርህ:: ብዙ እውቀት ያዝ:: ዝግጅትህ ደግሞ ፅናት ይጠይቃል:: በርትተህ ስትሰራ ምናልባት አለቃህ ጥረትህን አይቶ ደሞዝህን ላይጨምርልህ ይችላል:: ፈጣሪህ ግን ጥረትህን አይቶ ሊክስህ ይችላል:: ስለዚህ ታጋይ መሆን አለብህ:: ገቢህን በእጥፍ ለማሳደግ መሞከር አለብህ:: ተዛማጅ እድሎችህንም ተጠቀምባቸው::

  1. ፅናትን መለማመድ

ምንም ነገር ውጤቱ የሚለካው እስከ መጨረሻው ድረስ በመጓዝ ነው:: አሸናፊዎች የማያቆሙ ሰዎች ናቸው:: ጃፓኖች ‹‹ሀብት የሚበቅለው በፅናት ዛፍ ላይ ነው›› ይላሉ:: አንድ ሰው ወርቅ ለማግኘት ቆፍሮ ቆፍሮ ታከተው:: ከዛ የሚቆፍርበትና ማሽንና መሬት ሸጦ ለቆ ወጣ:: ቀጣዩ ሰው መጥቶ ያ ሰው ካቆመበት በመቆፈር ጀመረ:: ያ ሰው ቆፍሮ ካቆመበት አንድ ርምጃ በኋላ ወርቁን አገኘው:: ዝምብላችሁ አስቡት ያ ቁፋሮውን አቁሞ የወጣው ሰው እድሜ ልኩን ምን ያህል እንደሚንገበገብ::

በዚህ ዓለም ላይ ጥቂቶች ሲያሸንፉ፣ ሲደሰቱ የምናያቸው ከእኛ የተሻለ እውቀት፣ ልምድ ወይ ደግሞ እድል ኖሯቸው አይደለም:: ከእኛ በተሻለ ስለሚፀኑ ነው:: እስከ መጨረሻው ስለሚጓዙ ነው:: አመለካከቴን ቀየርኩ፣ ራሴን ማሻሻል ጀመርኩ ግን ለውጡን አላየሁትም ልትሉ ትችላላችሁ:: ነገር ግን ራሳችሁን መልሳችሁ መጠየቅ ይኖርባችኋል:: ምን ያህል ፀናህ? በሉት:: አንድ ርምጃ ቀርቶህስ ቢሆን:: የምትፈልገውን ልታገኝ አንድ ርምጃ ብቻ ምናልባት አንድ ሳምንት፣ አንድ ወር፣ አንድ ዓመት ብቻ ቀርቶህ እንደሆነስ?

በዚህ ዓለም ማንም ጥረትህን አይቶ አያደንቅህም:: ውጤትህን ነው ማየት የሚፈልገው:: አንተም ቢሆን የምትረካው ውጤቱን ስታገኝ ብቻ ነው:: ስለዚህ ጥያቄው ውጤቱ እስኪመጣ ድረስ ምን ያህል ፀናህ የሚለው ነው:: ሃሳብህን እየቀያየርክ፣ እያመነታህና ብዙ ነገሮች ውስጥ እየገባህ ለውጥ የለም:: ይህች ዓለም ለሚፀኑና ለሚበረቱ ታደላለች:: እጇን ትሰጣለች:: ከሚጀምሩት ሳይሆን ከሚጨርሱት አንዱ መሆን አለብህ:: አሸናፊዎች ለፅኑዎች ነው:: ስለዚህ ሁላችንም አሸናፊዎች ለመሆንና ድሉን ለማግኘት መፅናት አለብን!!

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You