ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ካላቸው ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነች ። በዚህ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪኳ ሕዝቦቿ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። ሀገረ መንግሥቱን ለማስቀጠልም ብዙ መስዋእትነቶችን ከፍለዋል። የታሪካቸው ሰፊ ምእራፍ እና ደማቅ ቀለምም በዚሁ እውነታ ያሸበረቀ ነው።
ሕዝቦቿ በሀገር ጉዳይ ላይ የፈጠሩት ጠንካራ ማህበረሰባዊ ሥነ ልቦና በየትውልዱ ስለ ሀገር እራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ዜጋ በማፍራት ሂደት ውስጥ ትልቅ ጉልበት ሆኗል። ለሀገር እና ለሕዝብ ክብር መሞት ትልቅ ማህበራዊ እሴት ከመሆን አልፎ የዜጎች ማንነት ዋነኝ መገለጫ የሆነበት ደረጃ ላይም ተደርሷል ።
ኢትዮጵዊነትን ከሀገር ክብር ፤ ከነጻነት እና ከፍትህ ከሚመነጭ ማህበረሰባዊ ማንነት ጋር የማስተሳሰሩ እውነታ ዓለም አቀፍ እየሆነ ከመጣ ዘመናት ተቆጥረዋል ። ይህ ማህበረሰባዊ ትርክታችን ከኛ አልፎ ለብዙ የነጻነት እና የፍትህ ትግሎች የመንፈስ እና የሥነልቦና ምንጭ በመሆን አገልግሏል ፤ አሁንም እያገለገለ ነው ።
ይህም ሆኖ ግን የሰላም ወቅትን ፤ ለሀገር ነገዎች ብሩህ አቅም አድርጎ መጠቀም የሚያስችል የመደማመጥ ሀገራዊ የፖለቲካ ባህል መፍጠር አለመቻላችን ፤ በየዘመኑ በብዙ የእርስ በርስ ግጭቶች ውስጥ እንድናልፍ ተገድደናል ። እያንዳንዱ የግጭት ታሪክም የሌላ ግጭት እርሾ እየሆነ እንደሀገር ያልተገቡ ዋጋዎችን ከፍለናል ።
ከነበርንበት የታሪክ ከፍታ ወርደን ፤ የኋላ ቀርነት እና የድህነት ምሳሌዎች ሆነናል። የምንበላውን እና የምንለብሰውን ሳይቀር ከሌሎች ጠባቂ የሆንበት አንገት የሚያስደፋ ፤የታሪክ ትርክት ውስጥ ለዘመናት ለማሳለፍ ተገድደናል። በዚህም እንደ ሀገር ለኛ በጎ ለማይመኙልን ጠላቶቻችን የተመቸን ሆነናል።
በዚህ ኋላቀር ከዘመኑ የተጣላ የፖለቲካ ባህላችን ምክንያት ጠላቶቻችን ትናንታችንን ብቻ ሳይሆን ዛሬን ፤ ከዛም አልፈው ነገዎቻችንን እንዲያበላሹ እድል ፋንታ ሰጥተናቸዋል። እራሳችን የራሳችን ጠላት ሆነን በራሳችን ላይ እንድንነሳ ሆነናል። ይህንን የጥፋት ጉዞ መግራት አቅቶን የጠላቶቻችን የአደባባይ መሳቂያ ሆነናል።
ከዚህ የረጅም ዘመን የጥፋት መንገድ መማር ባለመቻላችን ፤ ስለችግሩ በአደባባይ ከፍ ባለ ድምጽ እየጮህን ዛሬም ተጨማሪ ያልተገባ ዋጋ ከመክፈል እራሳችንን ማቀብ አልቻልንም ። ስለ ስልጡን የፖለቲካ አስተሳሰብ እያወራን ፤ብዙ ዜጎችን ለአስተሳሰቡ ተግባራዊነት እየገበርን ተጨባጭ የሆነው ተግባራችን ግን ዛሬም እንደትናንቱ ያው ነው ።
በቀና መንፈስ ሀገር እና ሕዝብን ያስቀደመ መነጋገር ፤ ለዚህ የሚሆን እርቅ እና ሆደ ሰፊነትን በፖለቲካ አመለካከታችን ውስጥ አለመኖር ፤ ዳተኝነት እና በቀለኝነት ፤ሴራ እና ራስ ወዳድነት ፤ የፖለቲከኞቻችን የአደባባይ ማንነት የመሆኑ ጉዳይ ፤ የታሪክ ጉዟችንን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አድርጎታል።
ይህ የፖለቲካ ባህላችን በቀደመውም ዘመን ሆነ አሁን ፣ ከዛም በላፈ በመጪው ጊዜያት የሀገሪቱ እጣ ፈንታ ላይ ሊፈጥር የሚችለው አዲስ ነገር የለም ። የሕዝባችንን የሰላም እና የልማት ፍላጎት ከማክሰም፤ሀገርን የበለጠ የከፋ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ከመክተት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። ይኖረዋል ብሎ ማሰብ በሕዝብ ላይ ከማፌዝ የሚተናነስ አይሆንም ።
ከዚህ በዘመናት ሲንከባለል ከመጣ ሀገራዊ ችግር መውጣት የዚህ ትውልድ ጥልቁ ሃላፊነት ነው ለመለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ሀገራዊ የፖለቲካ ባህላችን ላይ ተሀድሶ ማድረግ ያስፈልጋል ። የሀገር እና የሕዝብን ፍላጎት በአግባቡ አውቆ ለፍላጎቶቹ በቅንነት እራስን አሳልፎ መስጠት ፤ ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት መፍጠር ያስፈልጋል።
በተለይም ፖለቲከኞቻችን ፤እራሳቸውን ሀገርእና ሕዝብን መታደግ በሚያስችል ፤ ዘመኑን በሚዋጅ የፖለቲካ አስተሳሰብ እራሳቸውን መግራት ፤ያልተገባ ዋጋ ካስከፈሉን የትናንት ታሪኮቻችን በአግባቡ በመማር ሀገር እና ሕዝብን ወደ አዲስ የታሪክ ምእራፍ ማሻገር የሚያስችል አዲስ የማንነት ግንባታ ማካሄድ ይኖርባቸዋል ።
ከዳተኝነት እና ከበቀለኝነት ፤ ከሴራ እና ከራስ ወዳድነት መጥተው ፤ ለሕዝባችን የሰላም እና የልማት ፍላጎት ተገዥ ለሆኑ የፖለቲካ እሳቤዎች እራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት ፤ አዲስ ዘመኑን የሚመጥን የፖለቲካ ሥርዓት በመገንባት ሂደት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን የማይተካ አስተዋጽኦ ለማበርከት በተለወጠ ማንነት እራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።
በሚያልፍ ፍጥረታዊ ማንነታቸው በትውልዶች መካከል ህያው የሚሆን የማያልፍ የታሪክ ባለቤት ለመሆን ፤እራሳቸውን ከጊዜና ከቦታ በላይ የሚያደርጋቸውን በእጃቸው ያለውን ተመካክሮ ሀገርን እና ሕዝብን ከትናንት ፈተና የማሻገር እድል ሊጠወቀሙበት ይገባል ። ለዚህም እንደሀገር የጀመርነውን ብሄራዊ ምክክር ወሳኝ አቅም አድርጎ መውሰድ ያስፈልጋል ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም