የአንጋፋው ስቴድየም መጫወቻ ሜዳ አሁንም ጥርጣሬ ፈጥሯል

አንጋፋው የአዲስ አበባ ስቴድየም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ ካቆመ ከአራት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል:: ስቴድየሙ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ጀምሮ የካፍን ዝቅተኛ መስፈርቶች እንዲያሟላ በተጠየቀው መሠረት እድሳት ላይ የሚገኝ ቢሆንም እስካሁን ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት አልቻለም:: በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነዚህ ዓመታት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎቹን በገለልተኛ ሜዳ ለማከናወን ተገዷል:: ይህም በበርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ ይገኛል:: ይሁን እንጂ አሁንም ስቴድየሙ ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት የካፍን መስፈርት በሚያሟላ መልኩ እየታደሰ እንደሚገኝ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል::

በ1930ዎቹ አጋማሽ ተገንብቶ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ማስተናገድ ከጀመረ በኋላ ለሶስት ጊዜያት ብቻ እድሳት እንደተደረገለት የሚነገረው የአዲስ አበባ ስቴድየም፣ የተለያዩ የሀገር ውስጥና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ሲያስተናግድ የቆየው ይህ እድሜ ጠገብ ስቴድየም ከ20 ዓመታት በላይ ሳይታደስ አገልግሏል:: ካፍ እገዳ ከጣለበት ወዲህ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ እንዲታደስ የማድረግ ሥራው ከዓመታት በፊት ቢጀመርም አሁንም ድረስ ተጠናቆ ለውድድር ክፍት ባለመሆኑም ቅሬታ እየቀረበበት ይገኛል::

ሁሉንም የስታድየሙ ክፍሎችና ሜዳውን የሚያጠቃልለው እድሳትና ማሻሻያው በቅርቡ የካፍን መስፈርት ባሟላ መልኩ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሻዊት ሻንካ ተናግረዋል:: ኢትዮጵያ በቅርቡ የካፍን ጠቅላላ ጉባዔ ለማስተናገድ የምታደርገውን ዝግጅት አስመልክቶ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ ሚኒስትሯ ሻዊት ሻንካ፣ የአንጋፋው ስቴድየም እድሳት ከተጀመረ መቆየቱን አስታውሰው አሁን ላይ ግን ውድድሮችን ማስተናገድ በሚችልበት ደረጃ እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል::

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፣ ካፍ አንድ ስቴድየም የእግር ኳስ ውድድሮችን ለማስተናገድ እንዲያካትት የማሻሻያ ነጥቦችን ለማሟላት ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት እየታደሰ ይገኛል:: ለዚህም ከፍተኛ የሆነ በጀት በመመደብ እንዲሁም አብዛኞቹ ሥራዎች በልዩ ክትትል ተሠርተው ተጠናቀዋል:: ይሁን እንጂ ካፍ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የመጫወቻ ሜዳ የሳር ተከላ ጉዳይ በትክክል መሠራቱ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱን ጥርጣሬ ውስጥ እንደከተተው ሚኒስትሯ ስጋታቸውን አልሸሸጉም::

ለዚህም የሳሩን ደረጃ ለመወሰን ባለሙያዎች ማረጋገጥ የሚገባቸው በመሆኑ ከስፔን አንድ ባለሙያ ናሙናውን የወሰደ ሲሆን፣ የውጤቱ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ ትክክለኛው ሳር መሆኑ ከተረጋገጠ የማንጠፍ ሥራው በፍጥነት ተከናውኖ ለውድድር ክፍት ይደረጋል ብለዋል:: በተቀመጠው የካፍ መስፈርት መሠረት ሜዳው ምዘና ተደርጎለት የብቃት ማረጋገጫ እንዲያገኝና ለውድድሮች ምቹ እንዲሆን በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል:: በስቴድየሙ እድሳት የሚቀሩ ሌሎች ሥራዎችንም ቀንና ማታ በትኩረት ክትትል በማድረግ በዘላቂነት ውድድር ማስተናገድ እንዲችልና ብሔራዊ ቡድኑ በሀገር ውስጥ እንዲጫወት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥረቱን እደቀጠ አክለዋል::

የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ስድስት የተለያየ መጠን ያለው ተመልካች የመያዝ አቅም ካላቸው ስቴድየሞች በተጨማሪ ደረጃቸውን የጠበቁ 12 መለማመጃ ሜዳዎች ያስፈልጋሉ:: ኢትዮጵያ የ2029 አፍሪካ ዋንጫን ለማሰናዳት ጥያቄ ስታቀርብ በዋናነት የአዲስ አበባ ስቴድየምን ጨምሮ፣ በግንባታ ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ስቴድየም፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ አበበ ቢቂላ፣ ባህርዳርና ድሬዳዋ ስቴድየሞች መኖራቸው መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ተብሎ ታስቧል:: በቀጣይ ሁለት ዓመታትም የአዲስ አበባ ስቴድምንና የተጀመሩትን የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች በከፍተኛ ርብርብ ደረጃቸውን እንዲያሟሉ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ሚኒስትሯ አስረድተዋል:: በዚህም ከሜዳና ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ጋር የሚነሳው ጥያቄን በሚፈለገው ደረጃ ለማሟላት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው አክለዋል::

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ስቴድየም እድሳት ከዚህ በፊት ያልነበሩትን ነገሮች በማካተት መታደሱን አንስተው፣ የኢንጂነሪንግ ክፍሉ በደንብ መሠራቱን ጠቁመዋል:: ሆኖም ቅሬታው ያለው የመጫወቻ ሜዳው ላይ በመሆኑ ከካፍ ጋር በመተባበር ከስፔን ሀገር ባለሙያ መጥቶ ሳሩን ገምግሞ የሚያቀርበው ሪፖርት እየተጠበቀ እንደሚገኝ አስረድተዋል:: የካፍ ክለብ ላይሰንስ ክፍል ኢትዮጵያ የሚገኝ በመሆኑ ብሔራዊ ቡድኑ በጊዜያዊነት የቻን ማጣሪያ ጨዋታውን አዲስ አበባ ስቴድየም እንዲያደርግ በደብዳቤ መጠየቃቸውንም ጠቁመዋል::

የመጫወቻ ሜዳው ሳር ከተቀመጠው ደረጃ ጋር ሲታይ አሳሳቢ ነገሮች እንዳሉት የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ በተጨማሪም የሚዲያ፣ የክብር እንግዶችና ቡድኖች ወደ ጨዋታ ሜዳው የሚገቡበት በር መለየት እንዳለበት ገልፀው፣ ጥቃቅን ነገሮች እንዳልተጠናቀቁ አብራርተዋል:: ኢትዮጵያ የጠየቀችውን የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ እድል የምታገኝ ከሆነ የስቴድየም ሥራውን መንግሥት ለስድስት የውጪ ኮንትራክተሮች በመስጠት ከሠራ ረጅም ጊዜን እንደማይወስድም አቶ ኢሳያስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል::

የሚድያ ባለሙያዎችና የክብር እንግዶች መቀመጫ፣ ላውንጅ፣ የሚዲያ ቀጥታ ስርጭት ክፍል፣ ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል፣ የተመልካቾች መቀመጫና መጸዳጃ ቤቶች እንዲሁም አራት የመልበሻ ክፍሎች ካፍ ባስቀመጣቸው መስፈርት መሠረት መሠራታቸው ተገልጿል:: አዲስ አበባ ስቴድየም በወንበር 24 ሺ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ ያለ ወንበር 35 ሺ ተመልካቾችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ይታወቃል:: የ1962፣ 1968 እና የ1976 አፍሪካ ዋንጫን ያስተናገደው ስቴድየም የአሁኑን ጨምሮ እአአ በ1960 እና 1990 እድሳት እንደተደረገለት የሚጠቁሙ መረጃዎች ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ግን እድሳት እንዳልተደረገለት ይገልፃሉ::

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You