አንድ የእግር ኳስ ሜዳ ከባድ አይደለም!!

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን “ኪሳራ ላይ ነኝ” ሲል በቅርቡ ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አሳውቆ ነበር። ለኪሳራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሜዳው ማድረግ የነበረበትን ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ ማድረጉ አንዱ ምክንያት ነው ብሏል። ፌዴሬሽኑ በግራፍ አስደግፎ ባቀረበው ሪፖርት በ2016 የበጀት ዓመት ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንዳጋጠመው አብራርቷል።

ገቢውን ከወጪው ባነፃፀረበት ግራፉ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 186 ሚሊዮን 757 ሺህ 138 ብር ከ73 ሳንቲም ገቢ ማግኘቱን ሲጠቁም፣ ወጪው በአንፃሩ 214 ሚሊዮን 90 ሺህ 240 ብር ከ93 ሳንቲም መሆኑ አሳይቷል። በዚህም ከገቢ ወጪ 27 ሚሊዮን 333 ሺህ 102 ብር ከ20 ሳንቲም ኪሳራ እንዳጋጠመው ተናግሯል። በዓመቱ ለሴቶች ዋናው እና የዕድሜ እርከን ቡድኖች 51 ሚሊዮን 758 ሺህ 919 ብር ከ08 ሳንቲም ወጪ ሲሆን፣ ለወንዶች ዋናው እና የዕድሜ እርከን ብሔራዊ ቡድኖች ደግሞ በአጠቃላይ 44 ሚሊዮን 789 ሺህ 623 ብር ከ90 ሳንቲም ወጪ ሆኗል።

በተለይም ለወንዶች ብሔራዊ ቡድኑ የወጣው አብዛኛው ወጪ በሜዳው ማድረግ የሚገባውን ጨዋታዎች ከሜዳ ውጪ በማድረጉ የተመዘገበ መሆኑ ተገልጿል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ብሔራዊ ቡድኑ ሀገሩ ላይ ጨዋታዎችን ማድረግ ቢችል ኖሮ ቢያንስ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን እንችል ነበር ብለዋል። በአንዲት ድሃ ሀገር ክለቦች ከመንግሥት ካዝና እያወጡ አንድ ርምጃ ፈቀቅ ለማለት ለተሳነው እግር ኳስ የሚረጩት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲቆጨን አንድ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ ሜዳ ጠፍቶ ይሄን ያህል ገንዘብ ሲባክን ማየት ያሳፍራል።

ፌዴሬሽኑ በአንድ ዓመት ብቻ ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው ባለመጫወቱ 22 ሚሊዮን ብር ካወጣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ምን ያህል ሲያወጣ እንደነበረ ማስላት ቀላል ነው። አሳዛኙ ነገር በሦስቱ ዓመት ያወጣውን ወጪ ትተን የአንዱ ዓመት ወጪ ብቻ የፊፋና የካፍን መስፈርት የሚያሟላ መጫወቻ ሜዳ ማዘጋጀት አይቻልም ወይ? የሚለው ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያን ያህል ከመቶ ሃያ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት ሀገር እንዴት አንድ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ ሜዳ ታጣለች? ጥያቄው ደረጃውን የጠበቀ ስቴድየም አይደለም፣ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ነው። ፊፋና ካፍ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚችል ዝቅተኛውን መስፈርት የሚያሟላ ስቴድየም ሳይሆን በዋናነት የመጫወቻ ሜዳ የላትም ብለው ነው ያገዷት። ይህ ከሦስት ዓመት በላይ የዘለቀ እገዳ አንዳች መፍትሄ እንዲበጅለትና ብርቅየውን ዋልያ ከስደት መታደግ እንዲቻል ድምፁን ያላሰማ የለም። መፍትሄው ግን እንደሰማይ ርቋል። ይህም ብሔራዊ ቡድኑ በየውድድር መድረኩ በተሸነፈ ቁጥር ለአሠልጣኞች እንደ አንድ ምክንያት እየተጠቀሰ ቡድኑ ለሚገጥመው የውጤት ቀውስ ማምለጫ እየሆነ ነው።

ለአንድ ቡድን በሜዳና በደጋፊ ፊት መጫወት ጥቅም እንዳለው ማንም ሊክድ አይችልም። ብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ለማጣቱ አንዱ ምክንያት በሜዳው አለመጫወቱ መሆኑን አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩ አሠልጣኞች ከኢትዮጵያ ውጪ ፈልጎ ማግኘት አይቻልም ቢባል አልተጋነነም። አንድ አሠልጣኝ ቡድኑን የሚያዘጋጀውና ውጤታማ የሚያደርገው የሜዳ ላይ ጨዋታውን ብቻ አሸንፎ አይደለም።

ከሜዳው ውጪ በየትኛውም ሁኔታ የሚያሸንፍ ቡድን እስካልተገነባ ድረስ አሁንም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ ሌላ ሰላሳ አንድ ዓመት ለመጠበቅ እንደምንገደድ የሰሞኑ የዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ውጤት ማሳያ ናቸው። አሠልጣኞች ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት አለባቸው።

አንጋፋውን የአዲስ አበባ ስቴድየም እያሳደሰ የሚገኘው ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እድሳቱን በቅርብ ጊዜ እንደሚያጠናቅቅ ከገለፀ ቆይቷል። ጊዜው ምናልባትም ለእድሳት ሳይሆን እንደገና ለመሥራትም በቂ ሳይሆን አይቀርም። ያምሆኖ እድሳቱ በቅርቡ ይጠናቀቃል በተባለበት ወቅት ካፍ እንዲስተካከል ከጠየቃቸው ዝርዝሮች መካከል የመፀዳጃ ቤት፣ መልበሻ ክፍልና ሌሎች ጉዳዮች ተጠናቀው የቀረው የመጫወቻ ሜዳው ብቻ ነበር።

እሱም ቢሆን የሳር ተከላው ታይቶ በማይተወቅ መልኩ ዓለም አሁን ከደረሰችበት ደረጃ እጅግ ኋላ ቀርና በጉልበት ሠራተኞች ሲተከል አይተናል። ሚዲያውና የስፖርት ቤተሰቡ ይህ ትክክል እንዳልሆነና ብዙ ርቀት እንደማያስኬድ ድምፁን ቢያሰማም ሰሚ አላገኘም ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ገንዘብ ወጪ ከተደረገ በኋላ የሳር ተተከላው እንደ አዲስ ሊከናወን መሆኑ ተገለፀ። ዛሬም ግን ተጠናቀቀ ወይም እዚህ ደረጃ ደረሰ የሚል ነገር የለም።

በዚህ ሂደት ውስጥ የእግር ኳስ ቤተሰቡ ብሔራዊ ቡድኑ በሀገሩ ሲጫወት ለመመልከት ሳይታደል ከሦስት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ፌዴሬሽኑም በየዓመቱ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ እያወጣ የኪሳራው ቀጥሏል። ይህ በአንድ ዓመት ወጪ የሚደረግ ገንዘብ ግን ቢያንስ ሌሎቹን እድሳቶች ላጠናቀቀው የአዲስ አበባ ስቴድየም ዘመኑን የዋጀና ደረጃውን የጠበቀ የመጫወቻ ሜዳው የሳር ንጣፍ ከበቂ በላይ ነው። የበለጠ ወጪ ቢጠይቅ እንኳን ከታሰበበት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የወጣው ወጥቶ ሜዳውን ማስተካከል እንደሚቻል ለአቅመ ማገናዘብ የደረሰ ሰው ሁሉ የሚስተው ጉዳይ አይደለም።

ይህ ችግሩ የገንዘብ እንዳልሆነ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው። ችግሩ ስፖርቱን በእውቀትና ከዘመኑ ጋር በሚራመድ አስተሳሰብ እንዲሁም ለዘርፉ ተቆርቋሪ ሆኖ አለመምራት ነው። ለዚህ ደግሞ መፍትሄው ከባድ አይሆንም። በሀገር ውስጥ ሰው ቢጠፋ እንኳን በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ ጠቅላላ ጉባዔውን ለሚያደርገው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ሙያዊ እገዛ እሻለሁ ብሎ መጠየቅ አያሳፍርም።

የሚያሳፍረው የአፍሪካ መዲና የሆነችና የአፍሪካ የስፖርት አባት የሆኑት ይድነቃቸው ተሰማ ሀገር አንድ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ ሜዳ ማጣቷ እንጂ። የባህርዳር ስቴድየም በቀጣይ አራት ወራት ተጠናቆ ዝግጁ እንደሚሆን ሰሞኑን ተዘግቧል። ያምሆኖ የመጫወቻ ሜዳው ጉዳይ አሁንም ቢሆን ጥያቄ እንዳይነሳበት በርካቶች ስጋት አላቸው። ሜዳው ከላይ ሲታይ የሚያምር ሳር መልበሱ ብቻ በቂ አይደለም። በዚህ ረገድ በካፍና በፊፋ እውቅና የተሰጣቸው ኩባንያዎች እንዲሰሩ ማድረግ ለምን እንዳልተቻለ ግልፅ አይደለም።

በቀጣይ አምስት ዓመት ውስጥ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት እቅድ ያላት ሀገር ዛሬ ላይ ብሔራዊ ቡድኗ ጨዋታዎቹን በስደት ሲያደርግ ማየት ለብዙዎች አልዋጥ ቢል አይፈረድባቸውም። የአፍሪካ ዋንጫን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ መታሰቡ ይበል የሚያሰኝ ነው። ከታሰበበትና በትጋት ከተሠራ ይሳካል። ነገሩ ከጋሪው ፈረሱ ቀደመ እንዳይሆን ግን በቅድሚያ ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው የሚጫወትበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ለካፍ ጥያቄ ማቅረቡም ሀገርን ትዝብት ላይ እንዳይጥል ማሰቡ ተገቢ ነው።

የአፍሪካ ዋንጫውን ለማዘጋጀት ሲታሰብ የብሔራዊ ስቴድየሙን ጨምሮ በየክልሉ የተጀመሩ ስቴድየሞችን ማጠናቀቅ ይቻላል በሚል እምነት መሆኑን የማይረዳ የለም። ያምሆኖ የአፍሪካ ዋንጫው መስተንግዶ ሲታሰብ ስቴድየም ብቻ ማዘጋጀት በቂ አይደለም። አሁን ካለው የተሻለ ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን መገንባትም ለነገ የሚባል የቤት ሥራ አይደለም። ለዚህ ደግሞ ፌዴሬሽኑ አሁን እየገጠመው ከሚገኘው ኪሳራ መላቀቅና ቡድኑም በሜዳው ጨዋታዎችን እያከናወነ በቀጣዮቹ የአፍሪካ ዋንጫዎች ደጋግሞ እየተሳተፈ መገንባት ይኖርበታልና ነገሮችን በሁሉም አቅጣጫ ማየቱን ማስታወስ ተገቢ ነው።

ልዑል ከካምቦሎጆ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You