ይርጋጨፌ፦ በሃሳብ አለመግባባቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን በውይይት በመፍታት የሕዝብንና የሀገርን አንድነትን ማጽናት እንደሚገባ የጌዴኦ የባህል ሽማግሌዎች ገለጹ።
በጌዴኦ ዞን በይርጋጨፌ ከተማ የባህል ሽማግሌ የሆኑት ሀይቻ እምነቱ ጀጎ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የሃሳብ ያለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ባህል ባለመዳበሩ በተለያዩ አካባቢዎች በየጊዜው ግጭቶች ሲነሱ ቆይተዋል። ይህ አሁንም ማብቂያ ያልተገኘለት ጉዳይ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሔን ይሻል።
ሀገሪቱን ወደ ችግር፣ ሕዝቡን ደግሞ ወደ ስቃይና ስደት የሚወስዱ አጓጉል ድርጊቶች በመላ ኢትዮጵያውያን መወገዝ አለባቸው ያሉት ሀይቻ እምነቱ፤ በሃሳብ አለመግባባቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን በውይይት በመፍታት አንድነትን ማጽናት ይገባል ብለዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ ሰላምን ለማምጣት እያከናወነ ያላቸውን ተግባራት ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም ዕርቅን በማጎልበት መደገፍ ይገባል ያሉት ሀይቻ እምነቱ፤ የሀገር ሽማግሌዎች እሴቶችን ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ በተግባር የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
የትናንት እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ማንነት ከዘመኑ ጋር አብሮ እንዲንጸባረቅ ሁሉም መሥራት አለበት። በእልህና በጦረኝነት ስሜት ወደ ቀውስ የሚያንደረድሩ አላስፈላጊ ድርጊቶች በፍጥነት መቆም እንዳለባቸው የሀገር ሽማግሌው ገልጸው፤ በተለይ ብሔርንና መሰል ልዩነቶችን እያቀነቀኑ ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ ለማለያየት የሚጥሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል። ሕዝቡም አምርሮ ሊታገላቸው እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።
ሀገራዊ አንድነታችንን እና ሰላማችንን እየተፈታተኑ ያሉ ጉዳዮች ዘመን አመጣሾች እንጂ በኢትዮጵያዊ ማንነት ውስጥ ከዚህ ቀደም የሚታወቁ አይደሉም ያሉት ሀይቻ እምነቱ፤ ልዩነትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮች ቢገጥሙን እንኳ በደም ያስተሳሰረንን የአንድነት መሠረት በማሰብ አብሮነትን ማጽናት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ወጣቱ የሰላም እና የአብሮነት እሴቱን አውቆ ያለውን ለም መሬት በጋራ አልምቶ ራሱን እና ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ እንጂ ግጭትን እየፈጠረ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ሊያስፋፋ አይገባም ሲሉም ተናግረዋል።
የሀገር ሽማግሌው ሀይቻ ጉሉ ሌጌ በበኩላቸው፤ ባህላዊ እሴቶችን ለዘላቂ የሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና ታሳቢ በማድረግ ማልማትና መጠቀም ይገባል። ነባር እሴቶች ለሰላም ግንባታ ያላቸውን ጠቀሜታ በሚያሳይ መልኩ የምክክር ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ለመደገፍ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በማህበረሰብ ውስጥ ያለመግባባት ሲፈጠር ውሎ ከማደሩ በፊት በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት የሚያስችል ባህላዊ እሴቶች ያላት ሀገር ነች ያሉት ሀይቻ ጉሉ፤ ዕሴቶቹ ለአሁናዊ ሀገራዊ ችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ከመሆን አንጻር የላቀ ሚና ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ባህላዊ ሥርዓቶቻችን ተገቢ ትኩረት በማጣት እየተሸረሸሩ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አቅማችን ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ቆም ብሎ ማጤን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በሽምግልና ሥርዓት ያጠፋውን ገስፀው ግጭትን አስወግደው ሰላምን የሚያወርዱ ባህላዊ የእርቅ እሴቶችን በማስተዋወቅ ለትውልድ በተግባር ማሸጋገር ይገባል። በየአካባቢው የሚገኙ ሀገር በቀል የሰላም እሴቶችን በጥናት ጭምር አስደግፎ ወደ ተግባር በመለወጥ ለችግሮቻችን ሀገርኛ መፍትሄ ማምጣትን መለማመድ ቢቻል ውጤቱ የላቀ መሆኑንም አመልክተዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2017 ዓ.ም