የገዳ ስርዓት የኦሮሞ ህዝብ በረጅም ዘመን ታሪኩ የመሰረተው ተቋም ነው። እሬቻ ደግሞ በገዳ ስርዓት ውስጥ አንድ የምስጋና ተቋም ነው።እሬቻ ማለት ምስጋና ማለት ሲሆን ለተደረገልን መልካም ነገሮች ሁሉ ፈጣሪን ማመስገን ነው። ዝናቡን ላዘነበ ቡቃያውን ላለመለመ አምላክ ለምለም ሳርና ቄጤማ እንዲሁም አበባ ተይዞ ምስጋና ይደረጋል፤ እርቀ ሰላምም እንዲሰፍን ፈጣሪውን ይማጸናል።
ከኦሮሞ ህዝብ ባህላዊ ወግ ውስጥም በጋራ በመሆን ፈጣሪውን የሚያመሰገንባቸው ወቅቶች አሉ። እነዚህ ወቅቶች በመስከረም ወር መጨረሻና በመጋቢት ወር የሚደረጉ የኢሬቻ ቀናቶች ናቸው። በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚከበረው (የሆራ ፊንፊኔ) የኢሬቻ በዓል የዚሁ ክብረ በዓል አንዱ አካል ነው።
የመስከረም ወር ከሐምሌና ነሐሴ የዝናብ ወራት ተላቀን ብርሃን የምናይበትና በክረምቱ ወቅት የነበሩ አስፈሪ ሁኔታዎች በሙሉ አልፈው ለአዲስ ብርሃንና ተስፋ የምንደርስበት ብሩህ ጊዜ በመሆኑ የኦሮሞ ህዝብ ለዚህ ወቅት በመድረሱ ፈጣሪውን ያመሰግናል። በአንድነት በመሰባሰብም ምስጋናውን ያቀርባል።
የኢሬቻ በዓል ክረምቱና የጎርፉ፤ የደመናው፤ የጭጋጉ ወዘተ ጫና አልፎ አዲስና ሳቢ ዑደታዊ ለውጥ ምድር በምትላበስበት ወቅት መከበሩ በዓሉን ውብ ያደርገዋል። ኢሬቻ አደይ አበባ ሲፈነዳ፤ ምንጩ ሲጠራ ምድር አረንጓዴ በምትለብስብት በመስከረም ወር አጋማሽ ጀምሮ ይከበራል። ወቅቱ ጨለማው ተገፎ ብርሃን የሚፈነጥቅበትና ምድር በአበባ የምታጌጥበት አስደሳች ወቅት ነው። ይህ ደግሞ በሰዎች አዕምሮና መንፈስ ላይ በጎና ብሩህ ስሜት ይፈጥራል።
ኢሬቻ የአንድነት፤ አብሮነት፤የፍቅርና የምስጋና በዓል ነው። በክረምቱ ወራት ቤተዘመዶችና ቤተሰቦች ተራርቀው ይቆያሉ፤ ናፍቆቱ ቢኖርም የክረምቱ ኃይለኛ ዝናብ እስኪያልፍ መጠበቅን ግድ ይላል። በመስከረም ወር ግን ጭጋጉ ይነሳል፤ዝናቡ ያባራል፤የተነፋፈቁም ቤተሰቦችም ይገናኛሉ።
አንድነት፤ አብሮነት ይነግሳል፡ ምድሪቱም በፍቅርና በሰላም ትሞላለች። ይህን ሁሉ መልካም ነገር ላደረገ ፈጣሪ ደግሞ ምስጋና ይገባዋልና የኦሮሞ ህዝብም ዛሬ ይህን ነው የሚያደርገው።
ኢሬቻ አሁን ላላቸው ኢትዮጵያ ትልቅ ትምህርትን የሚሰጥና ችግሮቻችንን በሙሉ በሰላም፤በፍቅር፤ በመቻቻልና በአብሮነት መፍታት እንደምንችል ምስክር የሚሆነን አኩሪ ባህላችን ነው። ኢሬቻ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ ነውና እራሳችንን ከጨለማ ወደ ብርሃን ልናወጣ ይገባል። ቂም፤ ጥላቻ፤ ዘረኝነት፤ ክፋት፤ምቀኝነት የመሳሰሉትን ዕኩይ ስሜቶች ከክረ ምቱ ጋር ጠራርገን አስወግደን ፍቅር፤ መከባበር፤መዋደድ፤ መተሳሰብ፤ መረዳዳት የመሳሰሉትን በጎ ስሜቶች የግላችን ልናደርጋቸው ይገባል።
ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመታት በኋላ ኢሬቻ በአገሪቱ መዲናና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ መከበሩ የአዲስ አበባን ህብረ ብሄራዊነት ከማድመቁም በላይ ለአዲስ አበባ ነዋሪ ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅም መገንቢያ ይሆናል። ስለሆነም መላው የአዲስ አበባ ነዋሪ ወንድም የሆነውን የኦሮሞ ህዝብ በፍቅር ሊቀበልና ሊሸኝ ይገባዋል።
መፈናቀል፤መገዳደል፤መሰደድ፤መጠፋፋት ከክረምቱ ጨለማ ጋር አብረው የነጎዱና በምትካቸውም አብሮ መኖር፤ አብሮ መስራትና ማደግ፤ በሀገር ሰርቶ መለወጥና መበልጸግ በኢሬቻ ወቅት ከሚያብቡት አደይ አበባዎችና ከጠሩ ምንጮች ጋር አብረው በውስጣችን ሊጎመሩ ይገባል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 24/2012