እንስቷ በሐረርጌ ባህላዊ ልብስ እና ጌጣጌጦች ተውበው ታዳሚውን እያስተናገዱ ነው። ከፊት ለፊታቸው ከቦረና የመጡ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ባህል የሚያንጸባርቁ ምርቶችን ለታዳሚው ያስጎበኛሉ። ሌሎች ደግሞ ከቀንድ የተሰሩ መጠጫዎችን እና የተለያዩ አልባሳትን ይዘው ቀርበዋል። ይህ ሁሉ ሰሞኑን በኤግዚቢሽን ማዕከል ከተሰናዳው እና የኦሮሞ ባህልን ለማስተዋወቅ ካለመው ባዛር ጋር ከተያያዙ ክንውኖች መካከል አንዱ ነው። እኔ ግን የእንስቷ ጉዳይ ቀልቤን ስቦታልና ወደ እርሳቸው ተጠግቻለሁ።
ወይዘሮዋ ከሸማቹ ጥያቄ እና ሂሳብ ክርክር ትንሽ ጊዜ ሲያገኙ ጨሌ እና ዶቃዎቻቸውን በክር ውስጥ እያሰረጉ የተለያዩ የአንገት እና የእጅ ጌጦችን ያዘጋጃሉ። አንድ ሸማች መጣና አንዱን በቅል የተሰራ ያማረ የወተት ማለቢያ ባህላዊ እቃ አንስቶ ዋጋውን ጠየቃቸው። ፊታቸው ላይ የሚታየው ፈገግታ ተጨምሮበት በትህትና ደንበኛቸውን አስተናግደው ሲጨርሱ ደግሞ እኔም ጠጋ ብዬ ንግዱን እንዴት እንደተቀላቀሉና ታሪካቸውን እንዲያጫውቱን ጠየቅኳቸው።
ወይዘሮ ፋጡማ ሁሴን ይባላሉ። ችግርን በአግባቡ ቀምሰዋት አልፈዋል ከሚባሉ ሰዎች መካከል ናቸው። ነገር ግን እነዚያን የመከራ ቀናት አሳልፈው አሁን ላይ በጀመሩት ንግድ አማካኝነት ጥሩ ህይወትን እየመሩ ይገኛሉ። ተግባቢ እና አመለሸጋ የሚባሉ ሴት ናቸውና በርካቶች ምርታቸውን ገዝተው አመስግነዋቸው ሲያቀኑ እኔም እማኝ ነበርኩ። በምዕራብ ሐረርጌ ኦዳቡልቱም አካባቢ ነው ወይዘሮ ፋጡማ ሁሴን የተወለዱት። ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ ሲሆኑ የትውልድ ዘመናቸው ደግሞ በ1979 ዓ.ም ነው።
በህጻንነታቸው እናታቸውን የቤት ውስጥ ስራ እያገዙ እንዳደጉ ያስታውሳሉ። ከፍ ሲሉም አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ኡልፈታ በተባለ ትምህርት ቤት ተምረዋል። በወቅቱ ግን ለዘፈን እና ለኪነጥበቡ ከፍተኛ ፍቅር እንደነበራቸው አይዘነጉትም። በት ምህርት ቤቱ ውስጥ ባህላዊ ጭፈራ እና ዘፈን እየሞካከሩ የውስጣቸውን ስሜት ይፈትሹ ነበር። በዚህም ምክንያት በልጅነታቸው በትምህርት ቤታቸው ውስጥ ታዋቂ ከሆኑ ሴት ልጆች መካከል አንዷ ነበሩ።
ከትምህርት ሲመለሱ ደግሞ እናታቸው የስፌት እና ጥልፍ ስራን ያለማምዷቸዋል። የልጅነት ጊዜያቸውን በሰላምና በደስታ እያጣጣሙ ሳለ ግን ያልታሰበው ነገር ተከሰተ። እርሳቸው በማያውቁት ሁኔታ አባታቸው በመታሰራቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ በመጥፋቱ የቤተሰቡ ኑሮ በህይወት እና በሞት መካከል ሆነ። ጭራሽ ብሎም አባታቸው ሁለት ወራትን በእስር እንደቆዩ በመሞታቸው ቤተሰባቸውም ተበታተነ።
እናታቸው ብቻቸውን ሊያሳድጓቸው አቅም ስላልነበራቸው ወይዘሮ ፋጡማ በዴሳ ወደተባለው አካባቢ በጉዲፈቻነት ተወሰዱ። ምንም እንኳን አሳዳጊዎቻቸው በኦሮሞ የጉዲፈቻ ባህል መሰረት የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች እያሳደጉ ቢያኖሯቸውም የወላጅ እናትና አባት ፍቅር ግን ይፈልጉ እንደነበር አይረሱትም። በዴሳ እያሉ የሚያሳድጓቸው አባት ዘጠኝ ልጆችን በአንድ ቤት ተቀብለው ነበርና ወይዘሮ ፋጡማ ከአዲሶቹ ወንድምና እህቶቻቸው ጋር እየተጫወቱ ማህበራዊ ህይወትን እና አብሮ መኖርን ተምረውበታል። በዚያውም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው የአስኳላውን ጉዳይ ቀጥለውበታል።
አሳዳጊያቸው ደግሞ ክረምት ትምህርት በማይኖርበት ወቅት አዲስ አበባ የሚገኙ ዘመዶቻቸው ጋር ሄደው እንዲቆዩ እና የእጅ ስራ እንዲማሩ አድርገዋል። እናም በየጊዜው ክረምት አዲስ አበባ እየመጡ ከቻይናዎች ዘንድ የተለያዩ የእጅ ስራ እና የአልባሳት ዲዛይን ሙያዎችን ይለማመዱ ነበር። ህይወት በዴሳ ላይ ቀጥላ 12ኛ ክፍልን ሲጨርሱ ግን አሳዳጊያቸው በመሞታቸው ዳግም የቤተሰብ መበታተን አጋጠመ።
ቤታቸው ውስጥ ከሚኖሩት ልጆች መካከል የተወሰኑት በጉዲፈቻነት ወደ ውጭ አገር እና ወደ ተለያዩ ቦታዎች ሲበታተኑ ወይዘሮ ፋጡማ ግን እናታቸውም ቀድመው አርፈው ነበርና የሚሄዱበት ዘመድም አልነበራቸውም። ባዶውን ቤት ይዘው በብቸኝነት ጥቂት ቀናትን እንደቆዩ ገንዘብ ካልተገኘ የሚላስ የሚቀመስ እንደማያገኙ ስለሚያውቁት አንድ መላ ዘየዱ። ለዕለት ጉርስ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ስራ መስራት እንዳለባቸው ደግሞ አምነዋል።
አንድ ቀን በጠዋት ሶስት ብር ከ50 ሳንቲም ይዘው የአካባቢው ገበያ በመሄድ አነስተኛ ቅል፣ ቁራጭ ቆዳ፣ ዛጎል እና አነስተኛ ስንደዶ ገዝተው ወደቤታቸው ተመለሱ። የኦሮሞ ባህልን የሚያስተዋውቁ የቤት ውስጥ እቃዎችን እና አልባሳትን እያመረቱ መተዳደር እንዳለባቸው የወሰኑት ወይዘሮ ፋጡማ የመጀመሪያ የሆነውን ከቅል የተሰራ ያጌጠ የወተት ማስቀመጫ አዘጋጅተው በአንድ ቀን ጨረሱ።
በሚቀጥለው ቀን ደግሞ የእጃቸውን የመጀመሪያ ምርት ገበያ ይዘው በወጡ በሰዓታት ውስጥ ስምንት ብር ሸጧት። በዚህ የተበረታቱት እንስቷ በተወሰነው ገንዘብ ለሌላ የባህል እቃዎች ምርት የሚሆን ግብአት ገዛዝተው ወደቤታቸው ተመለሱ። እንዲህ እንዲህ እያሉ በትንሹ የሚያመርቷቸው የባህል ዕቃዎች ተወዳጅነታቸው በዴሳ ላይ ተፈላጊ መሆን ቻለ። በጎን ደግሞ አነስተኛ መጠን ያላቸውን የባህል አልባሳት በእራሳቸው ዲዛይን በማድረግ እና በቀለማት በማስዋብ እያሰፉ ለገበያ ማቅረቡን ጀምረዋል።
የባህል አልባሳትን አስተዋውቀው ገበያ ለማግኘት ሲሉ ደግሞ የሐረርጌ ነጭ ባህላዊ ልብስ ለብሰው በተጠሩበት ሰርግ ቤት ለብሰውት ተገኙ። በወቅቱ ሰርገኛው አይኑ እርሳቸው ላይ ስላረፈ ከየት አመጣሽው እያለ ይወተውታቸው ገባ። እራሳቸው እንደሰሩት ገልጸው ማሰራት የሚፈልግ ካለ ገበያው ክፍት መሆኑን አስረዱ። በዚያች ቀን ብቻ ሶስት የሐረርጌ ባህል ልብስ ትዕዛዝ ተቀብለው ስራቸውን ከፍ አደረጉት። እያንዳንዱን ልብስም በ80 ብር ሰርተው በማስረከብ ንግዳቸውን ማስፋፋቱን ቀጠሉ።
በወቅቱ ግን በማያውቁት ሁኔታ ከተቃዋሚዎች ጋር ፖለቲካ ውስጥ ትሳተፊያለሽ በሚል ለእርሳቸውም ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ወህኒ ወረዱ። በእስርም ኦነግ ነሽ በሚል በ1989 ዓ.ም እግራቸውን በእሳት እስክመጠበስ ያደረሰ መከራ እንዳሳለፉ በሃዘን ይገልጻሉ። ከሶስት ወራት እስር በኋላ ግን ከእስር ሲለቀቁ ባዶ ቤት ነበር የጠበቃቸው።
በእስሩም አቅማቸውም በመዳከሙ አብሯቸው የሚኖር ሰው መፈለግ እንዳ ለባቸው አምነዋል። እናም ልብስ ሲያዘጋጁ የሚሰፋላቸው አንድ ሰው ጋር ሄደው እንዲያገባቸው ጠየቁት። ከዚያም ጎጆ ተመስርቶ አንድ ላይ መኖር ተጀመረ። እርሳቸው የሃገር ባህል ጨርቆችን ሸም ተው ዲዛይኖን አበጃጅተው ሲያቀርቡ ባለቤታቸው ይሰፉና ለገበያ ይቀርባል። ወይዘሮ ፋጡማ ደግሞ በተጨማሪነት ጮጮ እና ሌሎችንም ከቅል የተሰሩ ባህል እቃዎች ማምረታቸውን ቀጥለዋል።
እንዲህ እንዲህ እያሉ ሲሰሩ ደግሞ አራት ልጆችን ወልደዋል። የመጀመሪያው ልጅ ደግሞ በተለየ ሁኔታ ከአባቱ ስር ስር እያለ የወዳደቁ ጨርቆችን በመስፋት በሰባት ዓመቱ ሙከራውን ጀምሯል። ባለቤታቸው ደግሞ በየጊዜው ኦነግ ነህ የሚለው እንግልት እና እስር እርሳቸው ላይም በርትቷል። እናም ቤታቸውን ጥለው ነብሳቸውን ለማዳን ከአገር ጥለው ሲወጡ የወይዘሮ ፋጡማ እና የልጆቻቸው ህይወትም ዳግም አደጋ ላይ ወደቀ።
ይህ ሁሉ ችግር ያልበገራቸው እንስት ግን አስር ዓመት የደረሰውን ወንድ ልጃቸውን በአባቱ የስፌት መኪና ላይ እንዲወጣ በማደፋፈር አብረው ይሰሩ ጀመር። በብዛትም የባህላዊ ምርቶችን በማዘጋጀት ባሌ እና ቦረና ድረስ በመጓዝ ይነግዱ ጀመር። ወደባሌ ባደረጉት ጉዞም የአያታቸውን ፈረስ ላይ ተፈናጠው በአንድ ጎን ጌባ የተሰኘውን ባህላዊ የቡና መጠጫ ምርት ይዘው ነበር። ሁለት መቶ ፍሬ ቡና መጠጫውን ባሌ ሼህ ሁሴን የተባለ ቦታ ላይ አውርደው ለገበያ ቢያቀርቡ እያንዳንዱን 20 ብር ሸጠው እንዳመጣጣቸው በፈረስ ተመለሱ።
ጠንካራዋ እንስት ከባሌ መልስ ከሁለት ሺ ብር በላይ ትርፍ ይዘዋልና በንግዱ ገፉበት። እንዲህ እንዲህ እያሉ በርካታ የባህል ጌጣጌጦችን እና አልባሳትም እንዲሁም የቤት ውስጥ መገልገያዎችን እያመረቱ ታዋቂነታቸው በበርካቶች ዘንድ ተዳርሷል። በእራሳቸው አነሳሽነትም በ2003 ዓ.ም ኦዳ ቡልቱም ላይ ደግሞ በእጃቸው የተጠቡባቸውን የኦሮሞ ባህል አልባሳት ተጠቅመው የፋሽን ትርኢት አሰናዱ።
በወቅቱ በርካታ ለጋሾችን በማግኘታ ቸው ውጤታማ በነበረው ትርኢት ባህል ከማስተዋወቅ ባለፈ ከ100ሺ ብር በላይ አገኙ። ይህ መነሾ ደግሞ ቤት እንዲሰሩ እና በተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ትርኢት ላይ እንዲቀርቡ ምክንያት ሆኗቸዋል። በመቀጠልም በዴሳ ላይ ከልጆቻቸው ጋር በመሆን አንድ የባህል እቃዎች መሸጫ ሱቅ ከፈቱ።
ቹማ፣ ካፋራ፣ የተሰኙ እና ሌሎችንንም የባህል እቃዎችን እና ጌጣጌጦችን ያመርታሉ። የእጅ፣ የአንገት እና የእግር ጌጦችንም በየአካባቢው ይሸጣሉ። ምን አለፋችሁ ወይዘሮ ፋጡማ ሱቅ የማይሸጥ የኦሮሞ ባህል እቃ የለም ይባላል። በእንጨት የተሰሩ ማበጠሪያዎች፣ ጊሌ እንዲሁም የእጅ አምባር ለገበያ ያቀርባሉ። በዚህ አምርቶ የመነገድ ስራ ደግሞ በትርፍ ላይ ትርፍ እየጨመሩ አራት ልጆቻቸውን አስተምረውዋል።
ስራቸው እየታወቀ እና እየተስፋፋ ሲሄድ ደግሞ አዳማ ላይ አንድ የባህል እቃዎች መሸጫ ሱቅ ከፍተው እየሰሩ ይገኛል። በርካታ የመከራ ጊዜያትን ያለፉት ወይዘሮ ፋጡማ አሁን ላይ ንግዱ ጥሩ ገቢ እያስገኘላቸው ይገኛል። አንድ የአርሲ ባህል ልብስ ከሶስት ሺ ብር በላይ ይሸጣሉ። ገበያ ከተገኘ ደግሞ በወር እስከ ስልሳ ልብሶችን አዘጋጅተው የማቅረብ አቅም አላቸው። አሁን ላይ በሁለት ቦታዎች በከፈቱት ሱቅ ልጆቻቸውን ጨምሮ አስር ሰራተኞች አሏቸው። የኦሮሞ ባህል ምርቶችንም ከኢትዮጵያ ውጪ በተለያዩ አገራት ለመሸጥ ውጥን አላቸው።
ከተለፋ የማይገኝ ሃብት የለም የሚሉት ወይዘሮ ፋጡማ፣ አሁን በእራሳቸው ቤት የተደላደለ ኑሮ እንዲኖሩ ያስቻላቸው ጥረው ግረው ያመረቱትን መነገድ በመቻላቸው መሆኑን ያስረዳሉ። በማንኛውም ጊዜ እና ሰዓት ወሬ እና ስንፍናን ከማብዛት ልብ የፈቀደውን ስራ ቢሰሩበት እራስም አገርም ትለወጣለች። በመሆኑም ማንኛውም ሰው ከስንፍና ተላቆ የግሉን ቢጥር ነግዶ ማትረፍ አምርቶ መሸጥ ይችላልና መዘናጋት አያስፈልግም የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው። እኛም የባህል እቃዎችንና ጌጣጌጦችን እያመረቱ በመሸጥ ለበርካቶች ጌጥ የሆኑትን ወይዘሮ ፋጡማ በርቱ እንላለን። ቸር እንሰንብት!!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 24/2012
ጌትነት ተስፋማርያም