በክልሉ ከሦስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ሥራ ተከናውኗል

አዲስ አበባ፡- ዘንድሮው በኦሮሚያ ክልል በ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ከድር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ የተፈጥሮ ሀብትን ለመንከባከብ እና የተጎዳውን የአካባቢ ሥነምህዳር ለማስተካከል የተፋሰስ ልማት ሥራ በትኩረት ተሠርቷል፡፡

በዚህም ዘንድሮ በክልሉ በተሠራው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት በ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የተፋሰስ ልማት ለማካሄድ ታቅዶ እንደነበር አንስተው፤ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራም ከ 6 ሺህ 460 በላይ ተፋሰሶችን በማልማት 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መሸፈን መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በተፋሰሱ ሥራም እርከን መሥራትን ጨምሮ የአፍርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተሠራ ሲሆን፤ በ 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎና የዜግነት አገልግሎት ተከናውኗል፡፡ ይህም አገልግሎት በገንዘብ ሲተመን 9 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ዋጋ የሚገመት ነው ብለዋል፡፡

አቶ ኤሊያስ እንደገለጹት፤ 539 ሺህ ሄክታር መሬትን ከሰውና እንስሳት ከንክኪ ነጻ ለማድረግ ታቅዶ 638 ሺህ ሄክታር መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነጻ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህንም የአፈር ለምነትናን ምርታማነትን የሚጨምር ነው፡፡

በክልሉ በሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ የአፈርና ውሃ ጥበቃ በመሠራቱ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ፣ ለግብርናው ምርትና ምርታማነት በማሳደግ፣ የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ በማስቻል ለአወንታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉልህ ሚና የሚጫወት ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የከርሰ ምድር ውሃ እና የተለያዩ ኩሬዎች በቅርበት ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ነው ያሉት አቶ ኤሊያስ ፤ማህበረሰቡ በተለያዩ ዘርፎች ማለትም በንብ ማነብ፣ ፍራፍሬዎች በማልማትና በመሰል መስኮች እንዲሠማራ የሥራ እድል በለመፍጠርና ከገጠር ወደ ከተማ ያለውን ከፍተኛ ፍልሰት ለመቆጣጠር የሚያስችልም ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች የግብርና ምርትና ምርታማነት በመጨመር ትላልቅ ውጤቶች እንዳመጡ አቶ ኤሊያስ ተናግረዋል፡፡

ቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ እንክብካቤ እና የልማት ሥራን በትኩረት እየተሠራ ነው ብለው፤ ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ህብረተሰቡ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ያለውን ጠቀሜታ ተረድቶ ተሳታፊነቱን እንዲጨምር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በስፋት የሚሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You