የማራቶን እንቁዋ የኦሊምፒክ ህልም

ሶስት ወራት ብቻ ለቀሩት 33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ ሀገራት አስቀድመው ቡድናቸውን ማሳወቅና ማዘጋጀት ጀምረዋል። ከእነዚህ መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን በተወሰኑ ርቀቶች የመጀመሪያ ምርጫ ውስጥ የተካተቱ አትሌቶች ጥሪ እንደተደረገላቸው ይታወቃል። በኦሊምፒክ መድረክ በአትሌቲክስ ስፖርት በስኬታማነት ተጠቃሽ የሆነችው ኢትዮጵያ በተለይ ለውጤታማነት ከምትጠበቅባቸው ርቀቶች መካከል አንዱ ማራቶን ነው። በዚህ ርቀትም አትሌቶች ሀገራቸውን ለመወከል እንዲያስችላቸው በተለያዩ ውድድሮች ተሳትፈው ምርጥ ሰዓትን ለማስመዝገብ የግል ጥረታቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በሴቶች ማራቶን በዓለም አቀፍ ደረጃ በአስደናቂ ብቃታቸው በቀዳሚነት ከሚነሱ አትሌቶች መካከል አንዷ የሆነችው ጎይተቶም ገብረሥላሴም፤ በዚህ ኦሊምፒክ ለመመረጥ የሚያስችላትን ሰዓት ለማስመዝገብ ጥረቷን አጠናክራ ቀጥላለች። እአአ በ2022 በኦሪጎን የማራቶን የዓለም ቻምፒዮን የነበረችው አትሌት በቀጣዩ ዓመትም ቡዳፔስት ላይ በርቀቱ የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ የሚታወስ ነው። እአአ የ2021 የበርሊን ማራቶን አሸናፊዋ አትሌት ከዓለም ቻምፒዮና መልስ በስፔን እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በተካሄዱ ሁለት የግማሽ ማራቶን ውድድሮች ላይ ተካፍላ ውጤታማ መሆን ችላለች።

በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆናም ሀገሯን በማስቀደም ለድል የምትተጋው ጠንካራዋ አትሌት ጎይተቶም ህልሟ በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ማውለብለብ ነው። ለዚህ እንዲያግዛትም በተያዘው የውድድር ዓመት በተለያዩ ውድድሮች ላይ በመካፈል ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ በቡድኑ የመካተት ጥረቷን አጠናክራ ቀጥላለች። የተያዘውን የውድድር ዓመት በጃፓን ንጎያ ማራቶን ላይ የጀመረች ቢሆንም እንደተጠበቀው ውድድሩን መፈጸም ባለመቻሏ አቋርጣ መውጣቷ የሚታወስ ነው።

ሩቅ አላሚዋ ብርቱ አትሌት በአንድ ወር ልዩነት ቀጣዩን ተሳትፎዋን ከቀናት በፊት በጀርመን በተካሄደው የሃምበርግ ማራቶን ማድረግ ችላለች። በዚህም 2ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመሮጥ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች። አትሌቷ በዚህ አቋሟ ሀገሯን በታላቁ የኦሊምፒክ ውድድር ላይ ከመወከል ባለፈ በታሪክ ማህደር ስሟ የሰፈረ ስኬታማ አትሌት የመሆን ምኞቷ ገና በጅምር ላይ መሆኑን ነው የምትገልጸው። የ29 ዓመቷ ጎይተቶም ከዓለም አትሌቲክስ ጋር በነበራት ቆይታ ያለመችውን ታሪካዊ አትሌትነት ስኬት ለማጣጣምም ፓሪስ ላይ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለባትም እምነቷ ነው።

‹‹ኢትዮጵያ እና ሩጫ የተሳሰሩ ናቸው›› የምትለው አትሌቷ ታላቁ አትሌት አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሀገሩን ወክሎ በመሮጥ ውጤት ማስመዝገቡን ለዚህ እንደ ማሳያ ታነሳለች። ‹‹እኔም አትሌት በመሆኔ እጅግ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል። ኦሊምፒክን ሳስብ የአትሌቶች ሁሉ የመጨረሻ ግብ እንደሆነ ነው የምረዳው›› ስትልም የአትሌትነት ሕይወት ግቧ የኦሊምፒክ ሜዳሊያን ማጥለቅ ስለመሆኑ ታስረዳለች። ከኢትዮጵያ ታሪካዊ አትሌቶች መካከል አንዷ የሆነችው ጥሩነሽ ዲባባ አድናቂ ስትሆን በተለይ እአአ በ2008 ቤጂንግ ኦሊምፒክ በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያጠለቀችበት ውድድር ሁሌም ከትውስታ ማህደሯ አይሰረዝም።

ይህንን ስኬት ለማጣጣም ትጋቷን አጠናክራ የቀጠለችው ጎይተቶም ‹‹በርግጥ እኔም በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አሸናፊ በመሆን ሀገሬን ለስኬት አብቅቻለሁ። የዓለም አትሌቲክስ ድልም በአትሌቶች ዘንድ ትልቅ ዋጋ ያለው ነው። ነገር ግን ይህንን ስኬት በኦሊምፒክ በመድገም ህልሜን እውን ለማድረግ ጠንክሬ እየሠራሁ ነው›› ስትልም ትናገራለች። በሩጫ ስኬታማ ለመሆን የግል ጥረት ብቻውን በቂ አለመሆኑን የምትገልጸው አትሌቷ፤ በልምምድም ሆነ በውድድር ወቅት ጠንካራ አትሌቶች መኖራቸው በእጅጉ ያግዛል። ምንም እንኳን የአትሌቶቹ አቅም የሚመጣጠን ባይሆንም አንዱ ሌላውን በመመልከትና በመካከላቸው የፉክክር መንፈስ በመፍጠር ማጠንከር እንደሚችል በመግለጽም፤ የተፎካካሪዎቿን አትሌቶች ጥቅም አብራርታለች።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You