ጓደኝነትን በሥራ አጋርነት ያደረጁ ብርቱ እጆች

አስር የሚደርሱ ድርጅቶችን በስሩ ይዟል። በሪልስቴት፣ በኮንስትራክሽን፣ በሪልስቴት ማርኬቲንግ፣ በሪል ስቴት ሕግ የማማከር አገልግሎት እና ንብረት አስተዳደር፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ ከ20 በላይ የሪል ስቴት ቴክኖሎጂ መተግበርያዎች፣ በትሬዲንግ እንዲሁም እንደ ሀገር ብዙም ትኩረት ባልተሰጠው ቤቶችን ከቴክኖሎጂ ጋር የማስተሳሰርና ስማርት የማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል። አፍታ ሜይራ ግሩፕ ኃ/የተ/የግ/ማህበር።

የድርጅቱ መስራቾች ጓደኛሞቹ ኢንጂነር ፍሬው ታምሬና አሚር አብዱልዎሃብ ይባላሉ። ጓደኝነትን ከሙያ አጋርነት አጣምረው በተለይም በሪልስቴትና ሪል ስቴት ነክ በሆኑ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩና የሕግ፣ የማማከር አገልግሎት ጭምር የሚሰጡ የሥራ ባልደረቦች ናቸው። በተለይም ለትውልድ የሚተላለፍ ሕጋዊ ድርጅት እና ሀብት መገንባት ላይ ትኩረት አድርገው ይሠራሉ፤ እነዚህ ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ›› ያሉት ብርቱ ጓደኛሞች አዲስ የሆነውን ‹‹ፊውቸሪስቲክ ኦርጋኒክ ግሪን›› /FUTURISTIC ORGANIC GREEN (FOG)/ የተባለውን ፕሮጀክት በኢትዮጵያ መጀመራቸው ልዩ ያደርጋቸዋል።

ኢሉባቦር/ኢሉ አባ ቦራ/ መቱ አንበጣ በምትባል የገጠር መንደር ተወልዶ ያደገው ፍሬው የትምህርት ጊዜውን በጅማና በሆሳዕና አሳልፏል። የመጀመሪያ ዲግሪውን በሲቪል ኢንጂነሪንግ ሁለተኛ ዲግሪውን አርበን ፕላኒንግና ዴቭሎፕመንት ተከታትሏል። ፍሬው ሥራ ከጀመረበት የወጣትነት ጊዜው ጀምሮ የኮንስትራክሽን ግንባታ ፈቃድ በማውጣት የግንባታ ሥራውን ተቀላቅሎ ዛሬም ድረስ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ይገኛል። ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከላይ ታች ሲል የቆየው ፍሬው፤ አዲስ አበባ ውስጥ ያለው ሰፊ የኮንስትራክሽን ሥራ በመዲናዋ አስቀርቶታል።

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እስከ ግል ድርጅቶች የግንባታ ፕሮጀክቶች ድረስ ሙያውን፣ ዕውቀቱንና ልምዱን ተጠቅሞ የሠራው ፍሬው፤ በዘርፍ ከተቆጣጣሪ መሃንዲስነት እስከ ኃላፊነት እንዲሁም በትላልቅ ሪልስቴቶች የሽያጭ ባለሙያም ሆኖ ሰርቷል። ይህም የሪልስቴት ዘርፉን በሚገባ እንዲያውቀውና እንዲረዳው አግዞታል። ከዚህም በላይ በዘርፉ የሚስተዋሉ በርካታ ክፍተቶችን የመረዳት ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል።

በሪልስቴት ዘርፍ በቆየባቸው ዓመታት በርካታ ክፍተቶችን መታዘብ እንደቻለ የገለጸው ፍሬው፤ ዘርፉ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ገንዘብ ያለው ሰው ያለ ዕውቀት በዘፈቀደ ሲመራው የነበረና ብዙዎች ሲያለቅሱበት የቆየ ስለመሆኑ ተናግሯል። ፍሬው እና ባልደረቦቹም ክፍተቱን በማስተዋል ለዓመታት በነፃ የማማከር አገልግሎት ሰርተዋል፣ ይህንንም ችግር በልኩ መረዳት በመቻላቸው ዘርፉን በዕውቀት፣ በሕግና በሥርዓት መምራት እንደሚገባ በማመን ፍሬው የሽያጭ ባለሙያ ሆኖ ከሚያውቀው ጓደኛው አሚር ጋር በመሆን አፍታ ሜይራ ግሩፕን መሠረቱ።

አሚር አብዱልዎሃብ ሀረር ሂርና ነው ተወልዶ ያደገው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ሂርና የተከታተለ ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አዲስ አበባ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል። የመጀመሪያ ዲግሪውንም ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ አግኝቷል። ከትምህርት በኋላ የሥራ ዓለምን ሲቀላቀል ትንሽ በሚባል ሥራ ጀምሮ አሁን የሪልስቴት ግንባታ ሥራ ላይ ደርሷል።

የታሸገ ውሃ ከፋብሪካዎች ተረክቦ በተለያዩ አካባቢዎች የማከፋፈል ሥራ ሲሰራ ነበረው አሚር፤ ከውሃ ሽያጭ በተጨማሪም የተለያዩ የሳሙና ምርቶችን ከፋብሪካ ተረክቦ ለክልል ከተሞች በማከፋፈል ሠርቷል። ከዚህ ከፍ ሲልም የኮስሞቲክስ ዕቃዎችን በማከፋፈል ታዋቂ እንደነበር አጫውቶናል። ቢዝነሱን ለማሳደግ በነበረው ተነሳሽነትም አሚር የኤክስፖርት ሥራን ተቀላቅሎ ከቡና ውጭ ያሉ የግብርና ምርቶችን ማለትም ጫት፣ ሰሊጥ እና ማርን ጨምሮ ጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ በመላክ በኤክስፖርት ዘርፍ ላይ ሰርቷል።

በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በየግላቸው ሲውተረተሩ የነበሩት ጓደኛሞቹ ፍሬውና አሚር፤ በሪልስቴት ማርኬቲንግ በጋራ የመሥራት አጋጣሚንም አግኝተዋል። አጋጣሚውም ጓደኝነታቸውን ይበልጥ አጠናክረላቸው። የራሳቸውን ሥራ በጋራ ለመሥራት ወስነው ወደ ተግባር መግባታቸውም ለዚሁ ነው።

ጓደኛሞቹ በአሁኑ ወቅት በጋራ ከሰሩት የሪልስቴት ሽያጭ ባለሙያነት በተጨማሪ በየግላቸው በትምህርትና በሥራ ልምድ ያካበቱትን ዕውቀት እንዲሁም ተሞክሮ በመደመር አፍታ ሜይራ ግሩፕን በማቋቋም የሪልስቴት ኢንቨስትመንት ሥራ ውስጥ ገብተዋል።

‹‹የምንገነባው ለሀገር ከቤት ባሻገር ነው›› የሚሉት ጓደኛሞቹ፤ FUTURISTIC ORGANIC GREEN (FOG) ዘላቂ ተፈጥሯዊ አረንጓዴ ቤቶችን መገንባት በሚል ጽንሰ-ሃሳብ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራቱን ተያይዘውታል፤ ጽንሰ-ሃሳቡም Eco-Friendly ወይም ተስማሚ ግንባታን የሚያመለክት ነው። ዘላቂ የሆኑ ቁሳቁስን፣ ኃይል ቆጣቢ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ የተፈጥሮ ውህደት፤ አረንጓዴ ቦታዎች፣ መናፈሻዎች፣ ቋሚ የአትክልት ሥፍራዎችን ማልማት፣ ስማርት ቴክኖሎጂዎች፤ የቤት አውቶሜሽን፣ የኢነርጂ አስተዳደር እና የአይኦቲ ውህደትን መከተል፣ ደህንነትን ማዕከል ያደረገ ንድፍ፤ ክፍት አቀማመጦች፣ የተፈጥሮ ብርሃን፣ የአካል ብቃት መገልገያዎችን ማካተት የሚሉት በጽንሰ ሃሳቡ የተካተቱ ናቸው። የማህበረሰብ ቦታዎችን በሚመለከት የከተማ እርሻን ጨምሮ የጋራ የመዝናኛ ሥፍራዎችና የውጭ ዝግጅቶችን ያካትታል።

ጓደኛሞቹ፤ ከሪልስቴት ኢንቨስትመንት በተጨማሪም አስር የሚደርሱ የተለያዩ ለትውልድ የሚተላለፉ ድርጅቶችን መስርተው ጤናማና ዘላቂነት ያለው ትልቅ ራዕይ ሰንቀው እየሠሩ ናቸው።

በሪልስቴት ዘርፍ ሲሰሩ ያስተዋሏቸው በርካታ ክፍተቶች እንዳሉም ይጠቁማሉ። ያም ሆኖ በዘርፉ ሰፊ ፍላጎት በመኖሩ የሪልስቴት ኢንቨስትመንቱ ከነክፍተቶቹ ተጉዞ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉም ይገልጻሉ። እነሱ እንዳሉት፤ በትንሹ ለመጥቀስ እንደ ሀገር ራሱን የቻለ የሪልስቴት ሕግ አለመኖሩ አንዱና ዋናው ችግር ነው።

ይሁንና ድርጅቱ ወደ ዘርፉ ሲገባ እነዚህንና መሰል ችግሮችን በሚገባ አጥንቶና በተግባር ፈትሾ በመሆኑ በዘርፉ የራሱን ድርሻ ለመወጣት አቅዶ ይሠራል። በተለይም ለአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆኑ ልምምዶችን፣ ዘላቂ ተስማሚ የኪነ-ሕንፃ ባህሪያትን እና የተዋሃደ የተፈጥሮ እና የከተማ ኑሮን ያጣመረ የግንባታ ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርጓል።

የሪልስቴት ኢንቨስትመንት ትላልቅ ስህተቶች ሲፈጸምበት የኖረ ዘርፍ ነው ብለው የሚያምኑት ጓደኛሞቹ፤ ጥፋቶችን ለማረም የተዘጋጁና በተለይም ዘርፉ በዕውቀትና በጥናት መመራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። በሪልስቴት ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ያስገደዳቸው በዘርፉ ያካበቱት ዕውቀትና ያሳለፉት ዕውነት እንደሆነ አመላክተው፣ በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ሲሰማሩ ገና ከመነሻው ጀምሮ በጥናት መመስረታቸውን ይገልጻሉ። ልማታቸው የተሻለ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል ያማከለ እንደሆነም አጫውተውናል።

አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል ያማከለ ሲባል የሚገነቧቸው ቤቶች በካሬ አነስተኛ ሆነው ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ማለት ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያታቸው በከተማው ውስጥ ያለው የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና ያለው አቅርቦት ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ነው። ተመጣጣኝ ዋጋ ሲባል ድርጅቱ የሚገነባቸው ቤቶች ዋጋ አዲስ አበባ ውስጥ ካሉት ከየትኛውም ሪልስቴቶች ዋጋ ተመጣጣኝ እንደሆነና በካሬ ሜትር ከ32 እስከ 75 ሺ ብር መሆኑን ጓደኛሞቹ ይጠቁማሉ። ያም ሆኖ ሽያጩ ያዋጣል ሲሉ ይገልጻሉ። ምክንያቱም አፍታ ሜይራ ግሩፕ ዓላማ አድርጎ የሚሰራው መጠነኛ በሆነ ትርፍ አብዛኛውን ማህበረሰብ መድረስ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችንም እንዲሁ መቅረፍና ለደንበኞች ጥራት ያላቸውን ቤቶች በወቅቱ በማድረስ ተቀባይነትንና ታማኝነትን በማትረፍ የድርሻቸውን መወጣት ሌላው የልማታቸው ማዕከል ነው። ለዚህም አስፈላጊውን ጥናትና ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ እንደቻሉ የሚጠቅሱት ጓደኛሞቹ፤ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና በሌሎች ዘርፎችም ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ትኩረት አድርገው እየሠሩ ያሉት በሪልስቴት ኢንቨስትመንት እና ተያያዥ ዘርፎች ሲሆን፤ በአፍታ ሜይራ ግሩፕ ስር የሚገኙ በሽያጭ ላይ ያሉ ስድስት ፕሮጀክቶች በሥራ ላይ ይገኛሉ።

በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ 15 የሚደርሱ የሪልስቴት ግንባታ ፕሮጀክቶችን አዲስ አበባ ውስጥ መጀመር እንደቻሉ የገለጹት ጓደኛሞቹ፤ በቀጣይም እነዚህን 15 ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ ለማስገባት አቅደው እየሠሩ ነው።

የሪልስቴት ኢንቨስትመንቶች አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ ታጭቀው መቅረት የለባቸውም የሚል እምነትም አላቸው። ወደ ክልል ከተሞች ወጣ በማለት የሪልስተቴት ኢንቨስትመንቱን ለማስፋት እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል። በጅማ፣ ቢሾፍቱ እና ሆሳዕና ከተሞች የሪልስቴት ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም መቀሌ ላይ በጥናት ደረጃ ያሉ ፕሮጀክቶች ስለመኖራቸው ያነሱት ጓደኛሞቹ፤ ሀገር አደገች፤ ከተማ ተገነባ የሚባለው ተቀራራቢ የሆነ ዕድገትና ስልጣኔ ያላቸውን ከተሞችን ማስፋፋት ሲቻል ነው ይላሉ።

ጥራትና ዘመናዊ ዲዛይን ያላቸው ቤቶች በክልል ከተሞች መቅረብ እንዳለባቸው በማመን በክልል ከተሞች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ አስረድተዋል። አዲስ አበባ ላይ በተለይም ምሳሌ መሆን የሚችሉ የሪልስቴት ግንባታዎችን ለመሥራት እንጥራለን የሚሉት ጓደኛሞቹ፤ እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶችን ውጤታማ ለማድረግ ሁለት ነገሮች ማለትም አቅምና ፕሮጀክት ማኔጅመንት ሲስተም ወሳኝ እንደሆኑ ያስገንዝባሉ።

አቅም ሲባል የተለያዩና አስፈላጊ የሆኑ ሀብቶች ናቸው። ለአብነትም ፕሮጀክቶችን አብዝቶ መያዝ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ባለው አቅም ልክ ሊሰራ የሚችል ሥራ ለመሥራት መወሰን የግድ ነው። ፕሮጀክቶችን ለሕንፃ ተቋራጮች በመስጠት እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚቻልና እዚህ ላይ ደግሞ ቁጥጥርና ክትትል ዋናው ጉዳይ ነው። ለዚህም አፍታ ሜይራ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ሲስተም በተባለ ቴክኖሎጂ ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋል።

ቴክኖሎጂው በእያንዳንዱ የሥራ ቀን ምን ያህል ግብዓትና ሠራተኛ እንዳለና በግብዓቱና በሠራተኛው ልክ ሥራው መሠራትና አለመሠራቱን መቆጣጠር የሚያስችል ሲሆን፤ ሥራው ሳይሰራ ቢቀርም እንዲሁ በምን ምክንያት ሳይሠራ እንደቀረ በቀላሉ መቆጣጠርና መለየት የሚያስችል ነው ይላሉ። ይህም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ወሳኝ በመሆኑ እየሠሩበት እንደሆነ ነው ያስረዱት።

በቴክኖሎጂው ፕሮጀክቱን ከመቆጣጠር ባለፈ ቤት የገዛ እያንዳንዱ ደንበኛ የፕሮጀክቱን የየዕለት ተግባርና አጠቃላይ ሂደቱን መከታተል የሚችልበትን ሥርዓትም ተዘርግቷል። ማንኛውም ቤት ገዢ የትም ሀገር ሆኖ በእጅ ስልኩ ፕሮጀክቱን መከታተል የሚችልበት ዕድል አለው። ግልጽነት የአፍታ ሜይራ ግሩፕ አንዱና ዋናው ዓላማ ሲሆን፤ ይህም ለድርጅቱም ሆነ ለደንበኛው ጉልህ አበርክቶ ያደርጋል።

ጓደኛሞቹ ወደ ግንባታ ከመግባታቸው አስቀድሞ የነበሩበት የሪልስቴት ሽያጭ ሥራ እንዳለ ሆኖ ነፃ የሕግ የማማከር አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር በማስታወስ፤ ሰዎች በተለይም የሪልስቴት ሕግና አሠራር እንዲሁም የኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግን አውቀው የግንባታ ሕጉንም ጭምር ተገንዝበው እንዲሸጡና እንዲገዙ የማማከር ሥራ ሲሰሩ ቆይተዋል። አሁንም እየሠሩበት ይገኛሉ። ይህም በርካታ ደንበኞችን ማፍራት እንዲችሉ ያገዛቸው በመሆኑ የሪልስቴት ኢንቨስትመንቱን በቀላሉ መቀላቀል ችለዋል።

የቤት አቅርቦት ላይ ገና ብዙ ሥራ ይጠይቃል የሚሉት ጓደኛሞቹ፣ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የክልል ከተሞች ለአብነትም ቢሾፍቱና ዱከም ቪላ ቤቶችን እየገነቡ እንደሆነ ተናግረዋል።

አፓርትመንትም ሆነ ቪላ ቤቶችን ለመገንባት መሬት የሚያገኙበት አማራጮች በዋናነት ሶስት ናቸው። አንደኛው መሬት ገዝተው የሚገነቡበት አሠራር ሲሆን፣ ሁለተኛው የአብሮ ማልማት አማራጭ ነው። ይህም ማለት የመሬት ባለይዞታ የሆነ አንድ ሰው መሬት ኖሮት ነገር ግን የመገንባት አቅም ከሌለው፣ እነሱ አቅማቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ያላቸውን ሀብት በሙሉ ተጠቅመው ቦታው ላይ በመገንባት እንደየቦታው ሁኔታ ስሌት ተሰልቶ ለባለይዞታው የድርሻውን በመስጠት ቀሪውን ለራሳቸው በማድረግ በሽያጭ ያስተላልፋሉ። ሶስተኛው በቅርቡ የተጀመረው በመንግሥትና በግል አጋርነት/ PPP/ የሚገነባ ሲሆን፤ ለጊዜው መሬት በግል በመግዛትና በአብሮ ማልማት አማራጮች እየሠሩ ይገኛሉ።

አዲስ አበባ ላይ ብቻ 15 የሪልስቴት ፕሮጀክቶች ያሉት አፍታ ሜይራ ግሩፕ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ሥራ የገቡና ሽያጭ ላይ ያሉት ስድስት ፕሮጀክቶች ናቸው። በክልል ከተሞችም ቢሾፍቱ፣ ዱከም፣ ጅማና ሆሳዕና መሬት አዘጋጅተው ወደ ግንባታ ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

አጠቃላይ በተቆጣጣሪነት የሚሠሩ ሠራተኞችን ጨምሮ 52 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለው አፍታ ሜይራ ግሩፕ ኃ/የተ/የግ/ማ፣ በቀጣይ ያቀዳቸውን ፕሮጀክቶች ዕውን በማድረግ በሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሪልስቴት ዘርፉ ትርጉም ያለውና ከስህተት የጸዳ ሥራ ለመሥራት ትልቅ ራዕይ ሰንቋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You