የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን ሕጋዊ እና ምቹ በማድረግ ሕገወጥ ስደትን ለመከላከል እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ:- ሕገወጥ ስደትን ለመከላከል ሕጋዊ አሠራርን በማቀላጠፍ፣ ቀላልና ምቹ እንዲሆን በማድረግ ዜጎች በሚፈልጉት ሀገር ለሥራ የሚሰማሩበትን እድል ለመፍጠር እየተሠራ እንደሚገኝ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በህጋዊ መንገድ የሚኬድባቸውን የመዳረሻ ሀገራትን ቁጥር በመጨመር፤ የሥልጠና እድሎችን በማስፋት እና ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት ሕገወጥ ስደትን ለመከላከል እየተሠራ ይገኛል።

ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትለው በየቀኑ ከአንድ ሺ 800 እስከ አንድ ሺህ 900 ዜጎች ወደ ውጭ ሀገር እንደሚጓዙ ጠቁመው፣ በዚሁ መሠረት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ከሀገር መውጣታቸውን ገልፀዋል።

ዜጎች ሕገ ወጥ ሥራ ስምሪትን የሚመርጡት ሕጋዊ መንገዱ ሲጠብ እንደመሆኑ አሰራሩን ሪፎርም በማድረግ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን ህጋዊ እና ምቹ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሕጋዊ የውጭ ሥራ ስምሪት እየሰፋ ሲሄድ ሕገ ወጥ መንገድ እየጠበበ ይሄዳል፣ በሂደትም ይዘጋል የሚል እምነት አለን ብለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ በሕጋዊ መንገድ ወደ ተለያዩ መዳረሻ ሀገራት ለሚሄዱ ዜጎች ከመዳረሻ ሀገራቱ ጋር በመነጋገር ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል በማስቀመጥ እንዲሰማሩ እየተደረገ ይገኛል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት አሰራሮችን በማዘመን የውጭ ስምሪት ከሰዎች ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ እንዲከወን በማድረግ ዜጎች ወደቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሄደው ሲመዘገቡ በዲጂታል ሥርዓት መረጃቸው የሚቀመጥበት አሠራር ተዘርግቷል።

በርካቶች በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ገብተው እየሰለጠኑ ናቸው። ሥልጠናውን እንዳጠናቀቁ በተዘረጋው ዲጂታል ሥርዓት ምዝገባ በማከናወን ስምሪት የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀትም ወደ ውጭ ሀገር በሥራ ለሚሰማሩ ዜጎች ፓስፖርት ቅድሚያ እንዲሰጥ እየተደረገ ይገኛል ሲሉም ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) አመልክተዋል።

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር በታክስ ፎርስ እየተሠራ ቢሆንም አሁንም እዚህም እዚያም በደላሎች የሚሞከሩ ነገሮች ይኖራሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሕጋዊ ስምሪቱ ከሰፋ ዜጎች ሕገወጥ ስምሪቱን የሚመርጡበት ሁኔታ አይኖርም ብለዋል።

መዳረሻ ሀገራትን የማስፋት ሥራም እየተሠራ ነው። ከዚህ በፊት የተጀመሩና ዜጎች እየተሰማሩባቸው የሚገኙ ዱባይ፣ ሳዑዲ አረቢያና መሰል ሀገራት ላይ ተወስኖ የነበረውን በማስፋት በአውሮፓ ሀገራት እየተመቻቸ ይገኛል ሲሉም አብራርተዋል።

በጀርመን እና በስዊድን በብቃት የሰለጠነ የሰው ሃይል ማቅረብ ለመጀመር ታቅዶ ድርድር እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥ ሶስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሥራ ለመፍጠር እቅድ መያዙን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በገጠርና በከተማ አበረታች ሁኔታዎችን እየተመለከትን ነው፤ ያሉ ጸጋዎችን ለይቶ በስፋት የማሰማራት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ዜጎች በሀገር ውስጥ መንግሥት ትኩረት በሰጣቸው የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የኮንስትራክሽን፣ የቱሪዝም፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ እንደሚበረታቱ አመልክተው፣ ክህሎት መር የሥራ እድል ፈጠራ እንዲስፋፋ እየተደረገ እንደሚገኝና ዜጎች ወደ ሥራ ከመሠማራታቸው አስቀድሞ በቂ ክህሎት፣ እውቀት፣ ተነሳሽነትና የንግድ አስተዳደር ክህሎት እንዲጨብጡ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You