ለግድቡ ግንባታ ቀሪ ሥራ ከዳያስፖራው ሶስት ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- ለዓባይ ግድብ ግንባታ ቀሪ ሥራ የሚሆን ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ሶስት ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይነህ አቅናው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የግድቡ ግንባታ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ የዳያስፖራው ሚና ጉልህ ነው። የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ ድጋፍ በማድረግ ዳያስፖራው እስከ አሁን 55 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አድርጓል።

አሁንም የግድቡን ግንባታ ቀሪ ሥራዎች ለማጠናቀቅ ዳያስፖራውን በማስተባበር ሶስት ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዷል።

ከህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ጋር በጋራ በመሆን አዲስ ኮሚቴ ተዋቅሮ የታቀደውን ገንዘቡ ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ በላይነህ ተናግረዋል።

ሀገር ውስጥ ካሉ ዳያስፖራዎች ጋር በቅርቡ ውይይት መደረጉን የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዓባይ ግድብ በኢትዮጵያውያን ተጀምሮ በመጠናቀቅ ላይ ያለ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት እንደመሆኑ ዳያስፖራው “እንችላለን” በሚል ጠንካራ መንፈስ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ትልቅ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት እንዳለውም አመልክተዋል።

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩባቸው ሀገራት በቀጥታ ገንዘብ ማስገባት የሚችሉበት አዲስ መተግበሪያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

ዳያስፖራዎች ሌሎች የባንክ አማራጮችንም በመጠቀም በቀጥታ ገንዘብ መላክ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዳያስፖራዎችን በሩቅ ምስራቅ፣ በአሜሪካ እንዲሁም በአፍሪካ የሚገኙትን በቀጣና በመከፋፈል ድጋፉን ለማሰባሰብ እንደሚሠራ ነው አቶ በላይነህ የገለጹት።

ከገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው ጋር በመሆን እንዳስፈላጊነቱ ዳያስፖራው ወደሚገኝበት ሀገራት ሄዶ በማወያየት የታቀደውን ገንዘብ ለማሰባሰብ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You