የሰው ልጆች ክብር በብዙ መንገድ ይገለጻል። ስለራሱ ታላቅ ቦታ የሚሰጥ ትውልድ ደግሞ ሌላውን ለማክበር አይገደውም። ሰዎች በተሻለ ቦታ በተገኙ ቁጥር አእምሯቸው ከመልካም ነገር ላይ ያርፋል። እንዲህ በሆነ ጊዜ ውስጠታቸው በጎውን እየተመኘ አካላቸው ከተሻለው ቦታ ይገኛል።
ሰሞኑን ‹‹ጽዱ ጎዳና፣ ኑሮ በጤና›› በሚል መርህ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ መካሄድ ጀምሯል። የዚህ ንቅናቄ ዋንኛ ዓላማ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት ክብርን ጠብቆ የመጸዳዳት ባህልን ለማዳበር ነው። ይህ ታላቅ ዓላማን ያነገበ እንቅስቃሴ የተለየ ትኩረት ተችሮታልና የብዙሃንን እጆችና ድጋፍ የሚሻ ሆኗል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት የቀረበው ይህ ሀገር አቀፍ ጥሪ መላውን ወገን የሚመለከት በመሆኑ ለሁሉም ‹‹ይድረስ፣ ይሰማ›› ተብሏል። ሀገራችን በተለይም አዲስ አበባ በአሁኗዊ አቋሟ ከፍተኛ በሚባል የከተማ መልሶ ግንባታ ላይ ትገኛለች። ከዚህ አኳያ ሊጀመር የታሰበው የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ግንባታ ፈጣኑን ለውጥ በመደገፍና ሂደቱን በማፋጠን ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል።
አዲስ አበባ ከተማችን የአፍሪካ ህብረት መዲና ብትሆንም እዚህ ለመድረሷ በርካታ ችግሮችን እየተሻገረች አልፋለች። የህብረቱ መቀመጫ ኢትዮጵያ ላይ መዝለቁን የማይሹ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ለተቃውሟቸው እንደምክንያት የሚጠቅሱት የከተማዋን ንጹህ ያለመሆን እውነታ ነው።
ከዚሁ የንጽህና ጉድለት ጋር ተያይዞ ሳይነሳ የማያልፈው የመጸዳጃ ቤቶች ችግርና በእኩል የሚስተዋለው በመንገድ ላይ የመጸዳዳት ልማድ ነው። ይህ እጅግ ነውር የሆነ፣ ነገር ግን እንደባህል ተዋርሶን የዘለቀ ድርጊት የሀገራችንን ገጽታ በክፉ የሚያስነሳ ሆኖ ዘመናትን አብሮን ተሻግሯል።
ሁሌም በመንገድ ላይ የመጸዳዳት ጉዳይ ከተነሳ ሀገራችን በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ትሆናለች። ችግሩ አስከፊና ተገቢነት የሌለው መሆኑ ቢታወቅም እስከዛሬ በቀላሉ ለመቅረፍና ከቆሻሻ የጸዳ አካባቢን ለመፍጠር ሳይቻል ቀርቷል።
ዓይንን በሚስቡ የከተማችን ማዕከላዊ ስፍራዎች ‹‹በዚህ ቦታ መጸዳዳት በሕግ ያስቀጣል›› የሚል ማሳሳቢያ በጉልህ ደምቆ መታየቱ ተለምዷል። በእንዲህ አይነት ቦታዎች ሆኖ መገኘት የግድ ይመስል ማሳሳቢያው በተቃራኒው ተተግብሮ ታያል። ይህን አስነዋሪ ድርጊት ለመከላከልም በሁኔታው ተሳትፈው የሚገኙ ቢኖሩ የተጠቀሰው የገንዘብ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም መጠቀሱ ብርቅ አይደለም።
ከህሊናና ከጥቂት ገንዘብ ቅጣት በላይ የሆነው ድርጊት ግን በሕግ የተፈቀደ ይመስል በየቦታው መስፋፋቱ አዲስ አይደለም። የቆሻሻ ገንዳ ባለበት ፣ የአጥር ከለላ በሚታይበት፣ የውሃ ቱቦና መፋሰሻ በሚገኝበት ስፍራ ሁሉ መጸዳዳት የተለመደ ሆኖ አብሮን ቆይቷል።
በአንድ ስፍራ ተጎራብተው የሚገኙ የቀበሌ ነዋሪዎች አንድ የመጸዳጃ ጉዳጓድን ለበርካታ አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው የማዋሉ እውነታ የተለመደ ነው። በነዚህ ሥፍራዎች ንጽህናው ያልተጠበቀና ቁጥሩ ተደራሽ ያልሆነ አገልግሎትን መጋራት የተለመደ ነው። ይህ እውነት የሕይወትን አስከፊ ገጽታ የሚያሳይና የሰዎችን ክብርና የመኖር መብት በእጅጉ የሚጋፋ አይነተኛ ምሳሌ መሆን ይችላል።
ይህ አይነቱን ችግር መፍትሄ ለመስጠት አንዳንድ የበጎ አድራጎት ተቋማት የተሻለ የመጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት ለግልጋሎት ሲያበቁ ይስተዋላል። ችግሩ ከቀድሞው በተሻለ እፎይታ ቢኖረውም በዘላቂነት መፍትሄ ላይ ለመድረስ ግን በቂ የሚባል አይደለም።
በከተማችን በተለያዩ ቦታዎች በነበሩ ጥረቶች ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ተሞክሯል። ተንቀሳቃሽ መጸዳጃ ሥፍራዎችን በማዘጋጀት፣ በመንገድ ላይ ዘላቂ ማረፊያዎችን በመሥራት እግረኞች በጥቂት የሳንቲም ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስተውለናል። ይህ እንቅስቃሴ በተለይ በከተማዋ መሀልና ዋና ዋና ስፍራዎች ቀላል የማይባል ድርሻን አበርክቷል።
እነዚህ ዘላቂ የመናፈሻ ሥፍራዎች ተጠቃሚዎች ሻይ ቡና ብለው በጥቂት ክፍያ አገልግሎቱን የሚያገኙበት በመሆኑ ለለበርካቶች ታላቅ መፍትሄን ይዞ ዘልቋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ወገኖች የአካባቢውን ንጽህና እየጠበቁ ተጨማሪ ገቢ እንዲኖራቸው ሚናው ከፍ ያለ ነው።
አንዳንዴ እነዚህ ሥፍራዎች ላይ የውሃ እጥረት ባጋጠመ ጊዜ የንጽህናው ጉዳይ ጎልቶ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ እግረኞች እንደዋዛ በየጥጋጥጉ መጸዳዳትን ባህል ያደረጉበትን አጋጣሚ በመሻር በኩል ታሪክን ቀይሯል። ከተወሰነ ጊዜያት ወዲህ ይህ አይነቱ መልካም ልማድ መበራከቱ በርካቶችን ለመጥቀም ምክንያት ሆኗል።
በአንዳንድ የከተማችን ቦታዎች የተለመደውን የመንገድ ላይ መጸዳዳት ለማስቀረት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። በተለይ በርካታ የሕዝብ እንቅሰቃሴ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች አገልግሎቱን በማስፋት ችግሩን መታደግ ተችሏል። አሁን በሥራ ላይ ባይሆኑም በመገናኛ አካባቢና ዙሪያው ተዘጋጅተው የነበሩ በርከት ያሉ ዘመናዊ መጸዳጃዎች የብዙሃኑን ክፍተት ሲሞሉ መቆየታቸውን ልብ ይሏል።
በቅርቡ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ዘመናዊነትን የተላበሰ ከመሆኑ ጋር ሥፍራውን የሚመጥን የመጸዳጃ አገልግሎት ሊኖረው እንደሚገባ ግልፅ ነው። ሃሳቡን ዕውን ለማድረግም ከሁሉም ወገን የተለየ ዝግጁነትና የበዛ ፍላጎት ይጠበቃል።
በርካቶች እንደሚሉት በከተማችን አንዳንድ ሥፍራዎች ለመጸዳጃ ሲባል የተዘጋጁ ቦታዎች ጠቀሜታቸው በእጅጉ የጎላ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች አገልግሎትን ሽተው የሚሄዱ ተጠቃሚዎችም ተገቢውን ክፍያ ማከናወናቸው የግድ ይላል። አሁን ላይ ግን በአንዳንድ ሥፍራዎች የተጋነነ ክፍያ መጠየቁ ችግሩ እንዲስፋፋ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአንዳንድ የመጸዳጃ አገልግሎቶች ለአንድ ጊዜ ብቻ እስከ አስራአምስት ብር ክፍያ ይጠየቅባቸዋል። ማንም ሊገምተው እንደሚችለው አንድ ሰው ይህን ያህል ክፍያ ከሚጠየቅ ዞር ብሎ የራሱን አማራጭ መውሰድ ፍላጎቱ ይሆናል። እንዲህ አይነት ክፍተቶች በተደጋገሙ ቁጥር ደግሞ ዓላማው በታቃራኒው ተጉዞ ችግሩን እንደሚያሰፋው ግልጽ ነው።
ከተማችን አዲስ አበባ ዘመናዊነትን ለመላበስ ስትዘጋጅ አስቀድማ አብሯት የቆየውን ክፉ ልማድ በማስወገድ ሊሆን ይገባል። ውብና ዓይን የሚስቡ ህንፃዎች፣ ጽዱና ዘመናዊ መንገዶች፣ ማራኪ ዛፎችና መዳረሻዎች ባሉበት በመንገድ ላይ መጸዳዳት ይሉት አስነዋሪ ልማድ ሊቀጥል እንደማይገባ ግልጽ ነው።
ይህ የሀገራችንን መልካም ስም ያቆሸሸ ፣ሁሌም በመረጃና በክፉ ማሳያ የምንጠቆምበት ባህል ከስሩ ተወግዶ ታሪክ ይቀየር ዘንድ የተጀመረው የእንቅስቃሴ ዘመቻ ሂደቱን ሊያፋጥን ርምጃውን ቀጥሏል። ሰዎች ሰው በመሆናቸው ተከብረው ሌሎችንም ያከብሩ ዘንድ መልካም የሚባለውን የመጸዳዳት ባህል ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል።
አሁን አዲስ አበባ በፈጣን የለውጥ ርምጃ ላይ ትገኛለች። እስከዛሬ በዓለም ላይ የጠለሸውን ገጽታዋን አጽድታ ስሟን ታድስ ትለውጥ ዘንድ የመጸዳጃ ቤቶች ታሪክ ሊቀየር የግድ ይላል። የሰው ልጅ በማንነቱ ክቡር ነው። ሌሎችን አክብሮ ራሱን የሚያከብር ትውልድ በበዛ ቁጥር ማንነት በተሻለ ሥፍራ ጎልቶ ይታያል።
ዛሬ ከትናንቱ ማንነት በተሻለ ተለውጠናል ስንል አፋችንን ሞልተን ለማውራት የሥልጣኔ መገለጫ የሆነው የንጽህና ጉዳይ ከእኛ ጋር ሊሆን ግድ ይላል። አሁን የታሪካችን ጥላሸት፣ የማንነታችን ክፉ ስም በመልካም ሊለወጥ ጊዜው ደርሷል።
የራስን ክብር ይዞ ለሌሎች መልካምነትን የማሳለፍ አንዱ መገለጫ ክብርን ጠብቆ የመጸዳዳት ባህልን ዕውን ማድረግ ነው። የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶችን ለመገንባት በሚኖረው ሂደትም የእያንንዱ ዜጋ ዐሻራ የሁሉም ወገን ተሳትፎ ሊተገበር የግድ ይላል። እንዲህ ሲሆን በጽዱ ጎዳና ኑሮና ሕይወትን በጤና ለመምራት ይቻላልና።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም