“የቀለጣ ከተማ የወሰን ማስከበር ሥራ መጓተት ለወልደሃኔ – ዱርጊ የመንገድ ግንባታ እንቅፋት ሆኗል”-የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር

“የወሰን ማስከበር ሥራው በግንቦት ወር ይጠናቀቃል”  –የጠምባሮ ልዩ ወረዳ

አዲስ አበባ፦ የወልደሃኔ – ዱርጊ የመንገድ ግንባታ በፍጥነት እንዳይጠናቀቅ የቀለጣ ከተማ የወሰን ማስከበር ሥራ እንቅፋት እንደሆነበት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ። የጠምባሮ ልዩ ወረዳ በበኩሉ የወሰን ማስከበር ሥራውን ሙሉ ለሙሉ በግንቦት ወር እንደሚያጠናቅቅ ገልጿል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሶዶ አካባቢ የግንባታ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሰለሞን ሞላ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የወልደሃኔ – ዱርጊ የመንገድ ግንባታ ከሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ነው።

መንገዱ 41 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅ ደቡብ ምዕራብ ክልል- ዳውሮ ዞን እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል- ጠምባሮ ልዩ ወረዳን ያገናኛል ያሉት ኢንጂነር ሰለሞን፤ መንገዱ በፍጥነት እንዳይጠናቀቅ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ቀለጣ ከተማ አካባቢ ያለው የወሰን ማስከበር ሥራ መጓተት እንቅፋት ሆኗል ብለዋል።

ይህም በወሰን ማስከበር ሥራው የሌሉ ንብረቶች ጨምሮ የማስመዝገብ፣ ሕገ ወጥ የቤት ግንባታ እና የተለዩ ንብረቶችን አለማስነሳት የሚታዩ ችግሮች መሆኑን ጠቅሰው፤ የመንገዱን ግንባታ በቀሪው ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የወሰን ማስከበር ሥራ በፍጥነት ሊጠናቀቅ ይገባል ብለዋል።

ግንባታውን ኤምሲጂ ኮንስትራክሽን ከሜልኮን ኮንስትራክሽን ጋር በጥምረት እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ በላይነህ በበኩላቸው፤ በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ቀለጣ ከተማ አካባቢ ያለውን የወሰን ማስከበር ሥራ ሙሉ በሙሉ በመጪው በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም እንደሚጠናቅቅ ገልጸዋል።

በካሳ ሕጉ መሠረት ግንባታው ከመጀመሩ በፊት የካሳ ክፍያ እንዲከፈል ያስገድዳል። ነገር ግን ማህበረሰቡን በማሳመን ከካሳ ክፍያው በፊት የመንገድ ግንባታው እንዲጀመር ተደርጓል ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ የመንገዱ ዲዛይን ከተጠና በኋላ የተሰሩ ቤቶችን የማጣራት ሥራ እየተሠራ ነው። በዚህም ሕገ ወጥ ቤቶች ላይ ርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

የወልደሃኔ – ዱርጊ የመንገድ ግንባታ ሁለት ክልሎችን ያገናኛል። የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅም በሁለቱ ማህበረሰብ መካከል ያለውን የንግድና እርስ በእርስ ግንኙነት ያጠናክራል። ከዚህም ባለፈ ከመሠረተ ልማትና ከሥራ እድል ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።

የወልደሃኔ – ዱርጊ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠሪ መሀንዲስ ኢንጅነር ሳምሶን አለማየሁ በበኩላቸው፤ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ ከዲዛይን በኋላ የተሰሩ ሕገ-ወጥ ግንባታዎች፣ የወሰን ማስከበር ሥራዎች አለመጠናቀቅ በተለይ በቀለጣ ከተማ፣ የሲሚንቶና የብረት ዕጥረት በፕሮጀክቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ 41 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው ያሉት ኢንጂነር ሳምሶን፤ መንገዱ ሲጠናቀቅ ደቡብ ምዕራብ ክልል- ዳውሮ ዞን እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል- ጠምባሮ ልዩ ወረዳ ያገናኛል ብለዋል።

ሁለቱም ዞኖች ማለትም ከምባታ ጠምባሮ እና ዳውሮ ዞን ለማገናኘት ቀድሞ 250 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲጓጓዙ የነበረው መንገድ ፕሮጀክቱ ሲጠናቅቅ ወደ 49 ኪሎ ሜትር እንደሚቀንስም ተናግረዋል።

እንደ ኢንጂነር ሳምሶን ገለፃ፤ በከሰል ድንጋይ ምርት ምርታማ የሆነውን ዳውሮ ዞን የገበያ ትስስርን ያጎለብታል፡፡ የኢንቨስትመንት እድሎች በመፍጠር የገበያ ትስስርን ያጎለብታል፡፡

የመንገዱ ግንባታ የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሙም ከዕቅድም ከጊዜም አንፃር የተሻለ አፈፃፀም እያሳየ ሲሆን እስከ መጋቢት 2016 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ የፕሮጀክቱን 12 በመቶ ሥራ ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You